የጦርነት- የኢኮኖሚ ቀውስን እንደ ማሳያ

የሕዝብ እንደራሴዎች የጠቅላይ ሚኒስትሩን ማብራሪያ የሚያዳምጡበት ስድስተኛ መደበኛ ጉባኤ ለመከታተል ተሰይሜያለሁ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኢኮኖሚ፣ ሰላም፣ ግብርና፣ መሠረተ ልማት እና ሌሎችም ዘርፎች ላይ መንግሥታቸው እየሠራ ያለውንና ለመሥራት ያሰበውን ጉዳይ እንደተለመደው ያብራራሉ። እንደራሴዎቹም እኔም ጆሯችንን ስል አድርገን እናዳምጣቸዋለን።

የመንግሥታቸውን ጥረት፣ የሚያጋጥማቸውን እንቅፋት፣ የማኅበረሰቡን መረዳትና ትእግስት ማጣት፣ የተቃዋሚዎችን ጉድለት፣ ነፍጥ ያነገቡ ተቃዋሚዎች አመፅና በሰላም ለመፍታት የሚደረግ ጥረት፣ የኑሮውን ውድነት፣ የትርክታችን መዛባት፣ የቸገረንን፣ ያጣነውን፣ ያገኘነውን፣ የሆነልንን እያንዳንዱን ጉዳይ በዝርዝር ከመንግሥታቸው አቋም አንፃር እየተነተኑልን ነው። በዚህ መሀል ነው አንድ ንግግራቸው ትኩረቴን የወሰደው። ንግግሩ ከዚህ የሚከተለውን ይዘት ይይዛል።

«የካፒታል በጀታችንን ወይንም የልማት ፕሮጀክቶቻችንንም አጥፈን ቢሆን ኢትዮጵያን ለማዳን ዝግጁ ነን» የሚል ግርድፍ መልዕክት የያዘ ነው። ይህ ንግግር በጊዜው የእኔን ትኩረት ከመያዝ ባለፈ ዛሬም በስፋት በዚህ ገፅ ላይ ሃሳቤን እንድሰነዝር የገፋፋኝ ጉዳይ ሆነና ወደ እናንተ በድጋሜ ይዤው መጣሁ።

ጦርነት፣ ግጭት፣ ሥርዓት አልበኝነት ለኅብረተሰብ ሰላም መደፍረስ ምክንያት ናቸው። ከዚህ ባለፈ የሀገር ኢኮኖሚን በማድቀቅ፣ የትውልድን ሞራል በማላሸቅ፣ መሠረተ ልማትን በማውደምና ራዕይ አልባ ሀገር በማዋለድ ወደር አይገኝላቸውም። በዘመናት ሂደት የተገነባ ሥልጣኔ፣ ኢኮኖሚና አምራች ኃይል በአንድ ሳምንት ጦርነት ድራሹን ማጥፋት ይቻላል።

የጠፋውን ለመተካት፣ የወደመውን ለመመለስ ግን ዳግም ዘመናት የሚጠይቅ ነው። ለዚህ ነበር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለእንደራሴዎቻቸውና ለኢትዮጵያ ሕዝብ ደርግን እንደ ምሳሌ አንስተው በህልውና ጉዳይ «ፕሮጀክቶችንና የልማት አጀንዳዎቻችንን ለማጠፍ አናቅማማም» በማለት ሲናገሩ ንግግራቸው ሙሉ ለሙሉ ትኩረቴን የወሰደው። በዚህ ምክንያት ነበር በዛሬው ርዕሰ ነገሬ የጦርነትን አስከፊ የኢኮኖሚ ጫናና የውድቀት ገፅታ ለመመልከት የወደድኩት።

ጦርነት ውዱን የሰው ልጅ ሕይወት ከመቅጠፉ በላይ ኪስን አራቁቶ ከድህነት ወለል በታች እንደሚሰድድ ግልፅ ነው። የልማት አጀንዳዎቻችንን አጥፈን ወደ ጦርነት እንድንገባ የሚያስገድዱን ጉዳዮች ሲፈጠሩ ደግሞ የዛሬን ሳይሆን የመጪውን ትውልድ ተስፋ ጭምር የሚገድል ነው።

ይህንን ጉዳይ በዝርዝር ለመገንዘብ እንዲረዳን ጦርነት በኢኮኖሚ ላይ የሚያደርሰውን ጫና ከዚህ እንደሚከተለው ለመመልከት እንሞክር። ስለ ጉዳዩ ጥልቅና ግልፅ መረዳት እንድናገኝ ከራሳችን ጉዳዮችም ወጣ ብለን ዓለም አቀፍ አንድምታውን ጭምር ማየት ጠቃሚ ይመስለኛል።

ጦርነት የማይተካውን የሰው ሕይወት ከመቅጠፍ ያለፈ አጥፊ አቅም ያለው ነው። በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ጫና ከማሳደር አልፎ የዋጋ ግሽበት (inflation) ይፈጥራል። ለዚህ ጥሩ ማሳያው የዩናይትድ ስቴት (አሜሪካ) የእርስ በእርስ ግጭት ጥሩ ማሳያ ይሆናል። በእርግጥ እሩቅ ሄደን ምሳሌ ለማንሳት የሚያስገድድ የመረጃ እጥረት ያለብን ባይሆንም ግን እናንሳው።

አሜሪካ በወቅቱ (during civil war) የነበረውን ጦርነት ለመቋቋም በማያስችል የኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ ገብታ ነበር። ይህ ችግር ደግሞ ለተዋጊው ኃይል ደሞዝ ለመክፈል ጥሬ ዶላር እስከ ማተም ያደረሰ ጫና ፈጥሯል። በኢኮኖሚ ውስጥ የተረጨው ገንዘብ ደግሞ የዶላርን የመግዛት አቅም ያዳከመ መካከለኛ ገቢ ያለውን ዜጋ በፋይናንስ ተቋማት ውስጥ ያጠራቀመውን ገንዘብ ዋጋ ያሳጣ ሆኖ አልፏል።

ሂደቱ ዶላር ዋጋ እንዲያጣ፣ ገበያ ላይ ያለው ምርት ደግሞ በከፍተኛ ደረጃ እንዲቀንስ በማድረጉ ምክንያት ለቀውስ ርሃብና ትርምስ (cost-push infla­tion) የዳረገ ነበር። የጦርነት አስከፊነት ከታየባቸው ጊዜያት ውስጥ የእርስ በእርስ ግጭቱ በታሪክ መዝገብ ላይ እንዲሰፍር አድርጎታል።

ጥሪታችንን አሟጠን የልማት ሥራዎቻችንን አቋርጠን በጭፍን የምንገባበት ጦርነት አጥፊ ነው ስንል በምክንያት ነው። ጦርነት፣ ግጭትና ሥርዓት አልበኝነት እንኳን በድህነትና ለማደግ በሚደረግ መፍጨርጨር ውስጥ ያለ ሀገር ገብቶበት ይቅርና ከፍተኛ ኢኮኖሚ ያላቸውም ጭምር ለክፍለ ዘመናት የገነቡትን ሀገር በአንድ ምሽት የመናድ አቅም አለው።

እዚህ ጋር «እንኳን ዘንቦብሽ እንዲሁም ጤዛ ነሽ» የሚለውን ብሂል ማስታወስ ተገቢ ነው። የጠቅላይ ሚኒስትሩ «በዶላር ከምንገዳደል በሃሳብ እንገዳደር» በማለት ያስቀመጡትንም አማራጭ ማጤን ይበጃል (ይህ ምክረ ሃሳብ መንግሥትንም ነፍጥ ያነገቡትንም ኃይሎች ይመለከታል)።

«ጦርነት አውዳሚ ነው» ስንል በምክንያት ነው። በእርግጥ ከጦርነት የሚያተርፉ ሀገራት፣ ካምፓኒዎች መኖራቸው ሀቅ ነው። የጦርነት ቴክኖሎጂ ሸጠውና ግጭት ጠምቀው ረብጣ ገንዘብና ጠንካራ ኢኮኖሚ የሚገነቡ አሉ። እኛ ግን መረዳት ያለብን በሃሳብ ልዩነት የምንገባበት አውዳሚ አማራጭ ሕይወታችንን ከማስከፈል ተሻግሮ የመጪውን ትውልድ ተስፋ እንደሚያጨልም ነው።

በእርግጥ የአንድ ሀገር ኢኮኖሚ በልዩ ልዩ ምክንያት ጫና ውስጥ ሊገባ ይችላል። ግሽበትም ይጠበቃል። የኢኮኖሚ ባለሙያዎች እንደሚሉት ከግሽበት የሚያመልጥ አይኖርም። ይሁን እንጂ ፈቅደንና ግልፍተኛ ሆነን የምንጭረው ጦርነት የሚያስከትለው ጫና ከግሽበት የተሻገረ ቀውስ (hy­perinflation) ነው።

ለዚህ ጥሩ ማሳያ የሚሆነን ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ሀንጋሪና አውስትራሊያ ያስመዘገቡት ከቁጥጥር ውጪ የሆነ ግሽበት (hyperinflation) ነው። በሀንጋሪ ለ13 ወር የዘለቀው የገንዘብ የመግዛት አቅም መዳከምና የምርት እጥረት እንዲሁም በመንግሥት የፋይናንስ ተቋማት እምነት መጥፋት የተከሰተው በጦርነት ምክንያት ነበር። ታሪክም ይህንን ቀውስ በመዝገቡ አስፍሮት አልፏል።

በጦርነት ምክንያት ምርት ቢኖር እንኳን አቅርቦት ይስተጓጎላል። መንገዶች፣ የንግድ መስመሮች፣ ወደቦችና ሌሎች የግንኙነት ሰንሰለቶች ይበጠሳሉ። በዚህ ምክንያት ዋጋ ይንራል። የዓለማችን ከፍተኛ ስንዴ ላኪ ሀገራት የሆኑት ሩሲያና ዩክሬን ጦርነት ውስጥ በመሆናቸው ብቻ ያመረቱት እልፍ ስንዴ በመጋዘን ውስጥ የነቀዝ እራት እንዲሆን ተፈርዶበታል።

በዓለማችን ላይ ኮሽ ባለ ቁጥር ጣራ የሚነካው የድፍድፍ ነዳጅ ዋጋም የዚሁ ማሳያ ነው። ለጉዳያችን ጥሩ ምሳሌ የሚሆነው እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር 1990 የተከሰተው የገልፍ ጦርነት (gulf war) ነው። በጊዜው በዓለም ገበያ ላይ 21 ዶላር የነበረው አንድ በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ ከእጥፍ በላይ ጨምሮ 46 ዶላር ደርሶ ነበር።

ይህ እንግዲህ ከዛሬ 33 ዓመት በፊት የነበረ ማሳያ ነው። ዓመት የተሻገረው የሩሲያና ዩክሬን ጦርነትን ትተን እንኳን በመካከለኛው ምሥራቅ በሀማስና እሥራኤል መካከል የተቀሰቀሰውን ጦርነት በምሳሌነት ብናነሳ የነዳጅ ዓለም አቀፍ ገበያን በስድስት በመቶ እንዲጨምር እንዳደረገ እንገነዘባለን። ይህ ሁሉ የጦርነት፣ የግጭትና የቀውስ ዳፋ ነው።

ጦርነት የሚያመጣው ቀውስ በዚህ የሚያበቃ አይደለም። ከዚህም የከፋ በርካታ ፈተናዎችን ይደቅናል። ጦርነት ቀድሞ የነበረን የመንግሥት ዕዳ ከመክፈል ይልቅ እንዲባባስ ይዳርጋል። የበለጠ የመበደር ፍላጎት ያሳድራል። ትውልድ የበለፀገ ሳይሆን በዕዳ የታጨቀ ሀገር እንዲረከብ ያስገድዳል።

ኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከፍተኛ የዕዳ ጫና ካለባቸው ሀገራት አንዷ እንደሆነች መረጃዎች ያሳያሉ (እንደ መንግሥት በሀገር ውስጥ ከብሔራዊ ባንክ የሚበደረውን ሳይጨምር)። የልማት ሥራዎች ላይ ማተኮር ከተቻለ እና ዕዳን መክፈል ያን ያህል ላያስቸግር ይችላል።

ነገር ግን በጦርነት ውስጥ ሆኖ ዕዳን መክፈል የማይታሰብ ነው። እንዲያውም ለተደራራቢ የብድር ጫና ይዳርጋል። ለዚህ አሁንም ወደ ሁለተኛው ዓለም ጦርነት ተመልሰን ተጨባጭ የታሪክ እውነታዎችን እንመልከት።

በሁለተኛው ዓለም ጦርነት (World War II) ቀዳሚ ተሳታፊ የነበረችው ዩናይትድ ኪንግደም እዚህ ጋር ቆንጆ ምሳሌ ትሆናለች። የሀገሪቱ መንግሥት ብድር (national debt) የሁለተኛው ዓለም ጦርነት ማብቂያ ላይ በ150 በመቶ አድጎ ነበር። ይህ በ1950ዎቹ በከፍተኛ ሁኔታ አድጎ 240 በመቶ ደርሶ ነበር።

ዩናይትድ ኪንግደምም ከዩናይትድ ስቴት ብቻ ለጦርነት ፍጆታ የወሰደችውን ብድር ለመመለስ ከ20 ዓመት በላይ ፈጅቶባታል። ከዚህ በተፃራሪ አሜሪካ ለእንግሊዝ የጦር መሣሪያና ቴክኖሎጂ በመሸጥ አትራፊ ነበረች።

የጦርነት አስከፊነትን ደጋግሞ ማስመር ያስፈልጋል። ጦርነት በቁጥር ስሌት ውስጥ የማይገባውን ውዱን የሰው ልጅ ሕይወት ከማስገበሩም ባሻገር ብዙ ጥፋት ይዞ ይመጣል። ከዚህ ውስጥ ደግሞ ከፍተኛ ወጪን የሚጠይቅ የመልሶ ግንባታ ሥራ (መሠረተ ልማት) አንዱ ነው።

«የቸኮለች አፍሳ ለቀመች» እንደሚባለው ብሂል በጦርነት ውስጥም ውድመት ከደረሰ በኋላ የጠፋውን መልሶ ለመሥራት ከፍተኛ አቅም ይጠይቃል። ለሌሎች የልማት ሥራዎች እና ኢኮኖሚ ጫና ማቃለያዎች ይውል የነበረ ሀብት የግዴታ ለመልሶ ልማት እንዲውል ያስገድዳል። በቅርቡ በሀገራችን በሰሜኑ ክፍል የተነሳው ጦርነት ያደረሰውን ኢኮኖሚ ጫናና የጠየቀው የመልሶ ግንባታ ወጪ ልብ እንበል።

የእርስ በርስ ጦርነት በሀገሮች ኢኮኖሚ እድገት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደርሳል። ኢትዮጵያን ጨምሮ የእርስ በርስ ጦርነት የሚያጋጥማቸው ሀገሮች በቱሪዝም፣ በውጭ ኢንቨስትመንትና በሀገር ውስጥ ኢንቨስትመንት ውድቀት ያስከትልባቸዋል። የሀገር ውስጥ ምርት እድገት (GDP) እና የሕይወት ዘመን ቆይታ (Life expectancy) ዝቅተኛ እንዲሆን ምክንያት ነው።

ኦክስፋም ዩኒቨርሲቲ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2007 «የጠፉት የአፍሪካ ቢሊዮኖች» (Africa’s missing billions) በሚል በሠራው ጥናት በአፍሪካ ሀገራት በጦርነት ምክንያት የሚወድመው ሀብትና ንብረት ለእርዳታ በምዕራባውያንና በአደጉት ሀገራት በምፅዋትነት ከሚገባው እኩል እንደሆነ ይፋ አድርጎ ነበር።

ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በተፈጥሮ ሀብት የታደለች ሀብታም ሀገር ብትሆንም ያንን ግን በተደጋጋሚ በሚደረጉ ጦርነቶች ልትጠቀምበት አልቻለችም። የዜጎቿን ሕይወትም አልታደገችበትም። በከባድ ጦርነት ውስጥ አልፋለች። ጦርነቱ ወደ 4 ሚሊዮን ለሚጠጉ ሰዎች ሞት ምክንያት ከመሆኑም ባሻገር 9 ቢሊዮን ፓውንድ ወይም ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርቷ 29 በመቶው ወጪ እንድታደርግ አስገድዷታል።

ለዚህ ነው «ጦርነት» በየትኛውም መመዘኛ ቢታይ መጥፎ እንጂ ጥሩ ጎን የለውም የምንለው። ለዚህ ነው ወደ ግጭት ከማምራታችን በፊት (አፍስሰን ከመልቀማችን አስቀድመን) የሰላም አማራጮችን አሟጠን መጠቀም ይገባናል የምንለው። ለዚህ ነው ጠቅላይ ሚኒስትራችን ለእንደራሴዎቻቸው የሰላምን ጥቅም፣ የድርድርን አስፈላጊነትና በጠረጴዛ ዙሪያ ልዩነትን የመፍታት ምርጫን እንደ ተሻለ ሃሳብ ሲያቀርቡ ትኩረታችንን የወሰዱን። እርሳቸው እንዳሉት «በዶላር ከመገዳደል በሃሳብ መገዳደሩ» እንደሚበጅ የምናምነው። ሰላም!

ሰው መሆን

አዲስ ዘመን ህዳር 21/2016

Recommended For You