በጫኝና አውራጅ ላይ ተስፋ ሰጪ ርምጃ

ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ብዛት ያላቸው ዜጎች ሥራ ፍለጋ ወደ አዲስ አበባ ይመጣሉ፡፡ አጋጣሚና ዕድል በሰጣቸው የሥራ መስክም ተሰማርተው ዛሬን ለማሸነፍ ብሎም ነገን ብሩህና የተሻለ ለማድረግ ይተጋሉ።

ከዚህ ውጪም እዚሁ አዲስ አበባና ዙሪያዋ ያሉ ሥራ አጥ ወጣቶችን ወደ ሥራ በማስገባት፤ አምራች ኃይል ለማድረግ ባለፉት ዓመታት ብዙ ጥረቶች ተደርገዋል፡፡ በዚህም ስኬታማ መሆን የተቻሉባቸው የሥራ መስኮች እንዳሉ ሁሉ የከሸፉና ከዚህም ባለፈ የችግር ምንጭ የሆኑም አሉ።

ከእነዚህ ውስጥ የዕቃ ጫኝና አውራጆች ጉዳይ አንዱ ነው። የከተማዋ አስተዳደር ሥራ አጥ ወጣቶችን ሥራ ለመፍጠር ካደረጋቸው ጥረቶች አንዱ እነዚህን ወጣቶች በማኅበራት አደራጅቶ ወደ ሥራ እንዲገቡ ማድረግ ነበር።

የሥራ አጥ ወጣቶቹ በማኅበር የመደራጀት ጉዳይ ለሥራው እውቅና በመስጠት በሕግና ሥርዓት እንዲመራ ለማስቻል እንደሚሆን ለመገመት ብዙም የሚከብድ አይሆንም። ሃሳቡም ሆነ ጅምሩ የሚበረታታ እና እውቅና ሊሰጠው የተገባ ስለነበር በብዙዎች ተበረታትቷል፤ እውቅናም አግኝቷል።

ብዙም ሳይቆይ ግን ሁኔታው ከታሰበው ይልቅ ያልታሰቡ ችግሮችን ይዞ በመምጣቱ፤ ለከተማው ነዋሪ ነገሩ ‹‹በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ›› ሆኗል። ሀይ ባይ ያጡ የሰፈር ጌቶች የሚፈለፈሉበት፤ ከሕግና ከሥርዓት እራሳቸውን አግዝፈው የሚያዩ የጉልበተኞች ስብስብ ሆኗል።

ሰዎች በማኅበራዊና በኢኮኖሚያዊ ምክንያት ዕቃ ይገዛሉ፣ ይሸጣሉ፡፡ ቤት ይሸጣሉ ይለውጣሉ፡፡ ይከራያሉ፣ ያከራያሉ፡፡ ቤት ሲከራይ፣ ዕቃ ሲገዛና ሲሸጥ ደግሞ እንደ ክብደቱ መጠን መጫንና ማውረድ የግድ ነው፡፡ ገዥ የገዛውን ዕቃ በመኪና አስጭኖ ወደ መኖሪያ ቤቱ አልያም ወደ ንግድ ቤት ሊወስድ ይችላል፡፡ ሲደርስ ደግሞ በዕቃ አውራጆች ያስወርዳል፡፡

በቀድሞዎቹ የአዲስ አበባ የከተማ አካባቢዎች (እንደ መርካቶ ፒያሳ ..ወዘተ) በመሳሰሉ አካባቢዎች ዕቃ ገዝታችሁ ከፈለጋችሁ ራሳችሁ መጫን ማውረድ፤ አልያም ለፈለጋችሁት ሰው በፈለጋችሁት/ በተስማማችሁት ዋጋ ማስጫንም ሆነ ማስወረድ ትችላላችሁ፡፡ በጠቀስኳቸው ስፍራዎች ዕቃ ማውረድና መጫን የዕቃው ባለቤት ፍፁም ይሁንታ ያለበት ነው፡፡

ዕቃው ወይም ቁሱን የገዛው ሰውዬ /ሴትዮ መብት ነው፡፡ ጫኙና አውራጆቹ አሻፈረኝ ቢሉና የተጋነነ ዋጋ ቢጠይቁ ሥራውን ከማጣት ውጪ ሰሚ አይኖራቸውም፤ እናም ዕቃ ሲጭኑና ሲያወርዱ ሥራውን እንዳያጡ ዋጋ የሚጠሩት ተጠንቅቀው ነው፡፡

ይህ ለሕግና ለሥርዓት ተገዥነት ታዲያ በከተማዋ ዳርቻ ባሉ አካባቢዎች ማየት ‹‹ላም አለኝ በሰማይ ወተቷንም አላይ›› እንደሚሉት ተረት ነው፡፡ በአዲስ አበባ ዳርቻ አካባቢዎች እና በሸገር ዙሪያዎች ቤት ለቆ አልያም ተከራይቶ ዕቃውን በተሽከርካሪ የሚያስጭንና የሚያስወርድ ካለ በአካባቢው ካሉ ወጣቶች ጋራ አተካራ መግጠም፤ ክፈል አልከፍልም ጭቅጭቅ መግጠሙ የተለመደ ነው፡፡

በነዚህ አካባቢዎች ‹የጎበዝ አለቃ› የሆኑ ዕቃ ጫኛና አውራጆቹ፤ ዕቃዎችን ለማውረድ ሆነ ለመጫን በአስር ሺዎች ብር የሚጠይቁበት ሁኔታ ስለመኖሩም የአደባባይ ምስጢር ሆኗል፡፡ አንዳንዴ ከሚያወርዱት ዕቃ ዋጋ በላይም ሊጠይቁ ይችላሉ። ይሉኝታ የሚባል ነገር የለም።

ክስተቱ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ባሉባቸው አካባቢዎች የበዛ ነው፡፡ ቤት ለመከራየት አልያም ለመልቀቅ ዕቃ በሚያስጭኑና በሚያወርዱ ቤተሰቦች ላይ በብዛት ማየት የተለመደ ሲሆን፤ እነዚህ አካባቢዎች ጫኝና አውራጅ እንዳሻው የሚሆንበት፤ ፖሊስና የሚመለከታቸው አካላት ይህንን ሥርዓተ አልበኝነት ለመግታት ሲንቀሳቀሱ የማይታዩባቸው ናቸው።

 ይህ ችግር ባለባቸው አካባቢዎች ያሉ ወላጆችና ነባር ነዋሪዎች ከመዝረፍ ያልተለየውን ማን አለብኝነት ተው! ብለው ማስቆም የሚያስችል አቅም የላቸውም፡፡ በየአካባቢዎቹ የሚገኙ የሕግ አካላትና ተቋማት ለችግሩ ዘላቂ መፍትሄ ሲያፈላልጉ አይታይም።

በቅርቡ በኮዬ ፈጬ ከሚገኙ የጋራ መኖሪያ ቤቶች መካከል ቤት የደረሰው አንድ የትምህርት ሚኒስቴር ወዳጄ በአዲስ ከተማ ከተከራየው የግል ቤት ለቆ በቤቴ እየኖርኩ ቀስ በቀስ አድሳለሁ በሚል ወደ ተጠቀሰው ቦታ ዕቃውን ጭኖ ሄዶ ነበር፡፡ ዕቃውን ለማውረድ ግን 30 ሺህ ብር ካልከፈልክ አታወርድም ብለው አሻፈረኝ እንዳሉት አጫውቶኛል፡፡

በስንት ጭቅጭቅ ልመና 15 ሺህ ብር ለመክፈል ተገዶ ዕቃውን እንዳወረዱለት በቅሬታ ነግሮኛል፡፡ እኔ ይህን አልኩ እንጂ መሰል ክስተቶች በየጊዜው በየአካባቢው ይደመጣሉ፡፡ ይህ ከሁለት ዓመት በፊት የነበረው ከአምስትና 10ሺ ክፍያ አድጎ ተመንድጎ አሁን ከ30 ሺህ እስከ 50 ሺህ ብር ደርሷል፡፡

ይሁንና አሁን አሁን ሥርዓተ አልበኝነትና ማን ይነካኛል ዓይነት ጨዋታ ሊቀይር የሚያስችል ተስፋ ሰጪ ጅማሮ እየታየ ይመስላል፡፡ ለዚህም የአዲስ አበባ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ የማኅበረሰቡን መብት ሊያስጠብቅና ቀደም ሲል ሲታዩ የነበሩ የጫኝና አውራጅ አሠራር ችግሮችን ሊፈታ የሚችል አዲስ መመሪያ ማዘጋጀት እንደቻለ ኅዳር 1 ቀን 2016 ዓ.ም አስታውቋል። ነገሩ በጥቂቱም ቢሆን ለሕዝቡ እፎይታን ሊፈጥር እንደሚችል ይታመናል፡፡

ይህ መመሪያ፤ ማኅበረሰቡ ቅሬታ ሲያነሳበትና ሲማረርበት የነበረንና የኖረን ችግር ሥርዓት የሚያሲዝ፣ ነዋሪው በነፃነት ንብረቱን ለመጫንና ለማውረድ የሚያስችል እንደሚሆን ይታመናል። በየሰፈሩ ያሉ ከሕግና ሥርዓት በላይ የሆኑ ‹የጎበዝ አለቆችን› ከሕግ በላይ እንዳልሆኑ የሚያሳይ እንደሚሆን ይታሰባል፡፡

ኅብረተሰቡ (ነዋሪው) ለሚያገኘው አገልግሎት በአቅሙ መክፈል የሚያስችል፤ ሥራውን አክብሮ በሕግና ሥርዓት መሥራት የሚችል ኃይል መፍጠር የሚያስችል ሊሆን እንደሚችልም ይጠበቃል። መመሪያውን በጠንካራ ዲሲፕሊን ተግባራዊ ማድረግ ከተቻለ ሥርዓተ አልበኝነትን ለመቀነስና ለመቆጣጠር የሚረዳ በመሆኑ ይበል የሚያሰኝ ነው።

ኃይለማርያም ወንድሙ

አዲስ ዘመን ህዳር 21/2016

Recommended For You