አሜሪካ ከቻይና እና ከሩሲያ የሚገቡ የመኪና ቴክኖሎጂዎችን ልታግድ ነው

አሜሪካ በደኅንነት ስጋት ምክንያት ለመኪና መሥሪያ የሚውሉ ከሩሲያ እና ከቻይና የሚገቡ የሶፍትዌር እንዲሁም የሃርድዌር ቴክኖሎጂዎችን ወደ ሀገሯ በሕግ እንዳይገቡ ልታግድ ነው። አሜሪካ ከዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰችው ከሁለቱ ሀገራት የሚመጡ የቴክኖሎጂ መሣሪያዎች “ለብሔራዊ ደኅንነቴ” ያሰጉኛል በማለቷ ነው።

ባለሥልጣናት እንደሚሉት ቴክኖሎጂዎችን መከልከል ያስፈለገው በተለይም አሽከርካሪ አልባ ዘመናዊ መኪናዎችን ለማምረት የሚገቡ መሣሪያዎች ምናልባት ወደፊት በአሜሪካ ጎዳናዎች የሚሽከረከሩ መኪናዎች ከሁለቱ ሀገራት በርቀት ቁጥጥር ሊደረግባቸው እና ላልተፈለገ ዓላማ ሊውሉ ይችላሉ የሚል ስጋት በመኖሩ ነው።

ገደብ የሚጣልባቸው ቴክኖሎጂዎቹ ‘ሾፌር አልባ መኪናዎችን’ ለማምረት የሚያገለግሉ እና ተሽከርካሪዎች እርስ በእርስ እንዲግባቡ የሚያደርጉ የመኪና የትስስር መረብን (ኔትዎርክ) ለመፍጠር የሚያስችሉ ሶፍትዌሮች ናቸው። በአሁን ጊዜ በአሜሪካ የቻይና እና የሩሲያ ሶፍትዌር የተጫነባቸው ብዙ ተሽከርካሪዎች የሉም።

ይሁንና የአሜሪካ የንግድ ሚኒስትር ጂና ሪማንዶ “እቅዱ በተወሰኑ ሶፍትዌሮች ላይ የሚደረግ እና የአሜሪካንን ጥቅም የሚያስጠብቅ ይሆናል’’ ብለዋል። “መኪኖች ዛሬ ዛሬ ካሜራ፣ ማይክሮፎን፣ ጂፒኤስ እና ሌሎች ቴክኖሎጂዎች አሏቸው። ከኢንተርኔት ጋር ተሳስረዋል። ጠላት እነዚህን መረጃዎች ካገኘ ከርቀት ላልተገባ ተግባር ሊያውላቸው እንደሚችል ለማሰብ ብዙ ጥረት አይጠይቅም። ለብሔራዊ ደኅንነታችንም የአሜሪካውያንን የግል መረጃ ለመጠበቅም ስንል እገዳውን እንጥላለን” ብለዋል።

ቻይና በበኩሏ “አሜሪካ የቻይና ድርጅቶችን ለመጉዳት ስትል ብሔራዊ ደኅንነት የሚለውን ጽንሰ ሐሳብ እየለጠጠችው ነው” ስትል ወቅሳለች። የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ሊን ጂያን “አሜሪካ የንግድ ሕጎችን እንድታከብር እንሻለን። ፍትሐዊነት፣ ግልጽነት እና አንዱን ያላገለለ የንግድ ዓውድ እንዲኖር እንጠይቃለን” ብለዋል።

አሁን ውይይት ይደረግበታል የተባለው ይህ ረቂቅ በተለይ ቻይና በአሜሪካ የተሽከርካሪ ምርት ኢንዱስትሪ ውስጥ ባለው ሠንሠለት አንዳችም ቦታ እንዳይኖራት የሚያደርግ ነው። ከዚህ ቀደም አሜሪካ ከቻይና በሚገቡ የኤሌክትሪክ መኪናዎች፣ ለኤሌክትሪክ መኪና የሚሆኑ ባትሪዎች እና በሌሎችም ከቻይና በሚገቡ ቁሳቁሶች የታሪፍ ጭማሪ ማድረጓ አይዘነጋም።

አሁን በሶፍትዌር ቴክኖሎጂ ምርት ላይ የሚጣለው ገደብ ከፈረንጆቹ 2027 በኋላ በሚመረቱ የመኪና ሞዴሎች ላይ ተግባራዊ የሚደረግ ነው። በሃርድዌር ላይ የሚጣለው ገደብ ደግሞ ሕጉ ከወጣ ከሦስት ዓመት በኋላ ተግባራዊ የሚሆን ነው። ይህም በአሜሪካ የተሽከርካሪ ኢንዱስትሪው ሌላ አማራጭ እንዲያገኝ ጊዜ ለመስጠት የታሰበ ነው ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።

አዲስ ዘመን መስከረም 15/2017 ዓ.ም

 

 

Recommended For You