ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በአዲሱ ዓመት የመጀመሪያ ወር መስከረም ከሚያደርጓቸው ውድድሮች መካከል የበርሊን ማራቶን ተጠባቂው ነው። በርካታ የዓለም የማራቶን ኮከቦች በሚፋለሙበት በዚህ ውድድር ከሁለት ሳምንት በኋላ ሲካሄድ ኢትዮጵያውያንና ኬንያውያን አትሌቶች በሁለቱም ፆታ የሚያደርጉት ፉክክር እንደወትሮው በጉጉት ይጠበቃል።
በተደጋጋሚ የርቀቱ የዓለም ክብረወሰን በሚሰበርበት የበርሊን ማራቶን ከ2014 በኋላ የርቀቱ ፈርጦች ቀነኒሳ በቀለና ኢሉድ ኪፕቾጌ በዘንድሮው ውድድር አይሳተፉም። ይህም የአሸናፊነቱ ቅድመ ግምትና የዓለም ክብረወሰን የማሻሻል ተስፋው በአዳዲስ የርቀቱ ከዋክብት ትከሻ ላይ ወድቋል።
በወንዶች መካከል በሚደረገው ፉክክር 42 ኪሎ ሜትሩን ከ2:05 በታች ማጠናቀቅ የቻሉ ስድስት አትሌቶች ይሳተፋሉ። በሴቶች መካከል ደግሞ ከ2:20 በታች ያጠናቀቁ አራት አትሌቶች እንዲሁም ከ2:22 በታች የፈፀሙ አስር አትሌቶች ተሳታፊ ናቸው። ከነዚህ መካከል ከ2፡16 በታች ማጠናቀቅ የቻሉ ሁለት አትሌቶች ይገኙበታል።ባለፈው ዱባይ ማራቶን በርቀቱ ለመጀመሪያ ጊዜ በተሳተፈች አትሌት በተመዘገበ ፈጣን ሰዓት 2:16:07 ያሸነፈችው ትዕግስት ከተማ አንዷ ስትሆን በቶኪዮ ማራቶን ሁለተኛ ሆና ያጠናቀቀችው ኬንያዊቷ ሮስማሪ ዋንጂሩ ሌላኛዋ አትሌት ነች።
በርሊን ላይ የመጀመሪያ ውድድሯን የምታደርገው ትዕግስት ባለፈው ዓመት በዚሁ ውድድር የዓለም ክብረወሰን የሰበረችውና የኦሊምፒክ የብር ሜዳሊያ ያጠለቀችው ኢትዮጵያዊት አትሌት ትዕግስት አሰፋ የልምምድ አጋር ስትሆን ወደ በርሊን የምታቀናው ቀዳሚውን ፈጣን ሰ ዓት ይዛ ነው።
ሁለተኛውን ፈጣን ሰዓት ይዛ በውድድሩ የምትሳተፈው ዋንጂሩ ከሁለት ዓመት በፊት የመጀመሪያ የማራቶን ውድድሯን በርሊን ላይ አድርጋ ሁለተኛ ሆና ስታጠናቅቅ 2:18:00 በማስመዝገብ ነበር። ይህን ሰዓት ባለፈው ቶኪዮ ማራቶን ሁለተኛ ሆና ስታጠናቅቅ ወደ 2:16:14 አሻሽላለች። ይህ ያሳየችው እድገትም ዘንድሮ ቶኪዮ ላይ ትኩረት እንዲሰጣት አድርጓል።
የቀድሞዋ የ1500 ሜትር ባለክብረወሰን ገንዘቤ ዲባባ ከመካከለኛ ርቀት ወደ ማራቶን ፊቷን ካዞረች ወዲህ አጀማመሯ ጥሩ ቢሆንም ብዙ ርቀት አልተጓዘችም። ዘንድሮ ግን በርሊን ላይ የማራቶን ታሪክን በፈጣን ሰዓት ለማድመቅ ትሮጣለች። ገንዘቤ ከሁለት ዓመት በፊት የመጀመሪያ የማራቶን ውድድሯን አምስተርዳም ላይ አድርጋ 2:18:05 ማጠናቀቅ እንደቻለች ይታወሳል። ይህንን ሰዓትን ግን ባለፉት ሁለት ዓመታት ማሻሻል አልቻለችም። ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት የብርጓል መለሰ በ2:19:36 ርቀቱን ከ2፡20 በታች ማጠናቀቅ ከቻሉ አራት አትሌቶች አንዷ ስትሆን ዘንድሮ በርሊን ላይ ጠንካራ ተፎካካሪ ከሚሆኑ ኮከቦች መካከል ስሟ ይገኛል። መስታወት ፍቅር (2:20:45)፣ አዝመራ ገብሩ (2:20:48)፣ ሲሳይ ጎላ (2:20:50)፣ አባብል የሻነህ (2፡20፡ 51)በውድድሩ የሚሳተፉ ኢትዮጵያውያን ናቸው።
በወንዶች መካከል በሚደረገው ፉክክርም ቀዳሚውን ፈጣን ሰዓት የያዘው ኢትዮጵያዊው አትሌት ታደሰ ታከለ ነው።2:03:24 ምርጥ ሰዓቱ ሲሆን ሁለተኛና ሦስተኛውን ፈጣን ሰዓት ይዘው ከሚወዳደሩት ኬንያውያን አትሌቶች ሮናልድ ኮሪር (2:04:22)፣ ሳይብሪያን ኮኩት (2:04:34) ጋር የሚያደርገው ፉክክር ተጠባቂ ነው። ታደሰና ኮሪር ባለፈው በርሊን ማራቶን ሦስተኛና አራተኛ ደረጃን ይዘው ያጠናቀቁ አትሌቶች መሆናቸው ይታወሳል። ኃይለማርያም ኪሮስ (2:04:41)፣ ባዘዘው አስማረ (2:04:57)፣ሚልኬሳ መንገሻ(2:05:29)፣ ሃይማኖት አለው (2:05:30) በውድድሩ የሚሳተፉ ኢትዮጵያውያን ናቸው።
እኤአ ከ1974 ጀምሮ እየተካሄደ የሚገኘው የበርሊን ማራቶን ከዓለም አምስቱ ታላላቅ የማራቶን ውድድሮች አንዱ ሲሆን፣ ዘንድሮ ሃምሳኛ ዓመቱን ያከብራል። በውድድሩ የግማሽ ክፍለ ዘመን ጉዞ አስራ ሦስት ያህል የዓለም የማራቶን ክብረወሰኖች የተሰበሩበት ሲሆን ይህም ከሌሎች የማራቶን ውድድሮች የተለየና አትሌቶች ፈጣን ሰዓት ለማስመዝገብ እንዲመርጡት አድርጎታል። ከሁለት ሳምንት በኋላ ሃምሳኛ ዓመቱን ሲያከብርም ከአትሌቶች በተጨማሪ ለመጀመሪያ ጊዜ ከሃምሳ ሺ በላይ ሕዝብ እንደሚሳተፍ ይጠበቃል፡፡
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን መስከረም 15/2017 ዓ.ም