ሀዲስ ዓለማየሁ፣ አቤ ጉበኛ፣ ዳኛቸው ወርቁ፣ ታደሰ ሊበን…. የመሳሰሉት የኢትዮጵያ ደራሲዎች ይኖሩበት የነበረውን ዘመን ቀድመው የሄዱ፣ እንኳን የኖሩበትን ዘመን ከ100 ዓመት በኋላ የሚኖረውን ትውልድ ቀድመው የነቁ እና የሠለጠኑ ናቸው። መጽሐፎቻቸው ከተጻፉ እነሆ ከ60 ዓመታት በኋላ እንኳን እነርሱ የሳሏቸውን ገጸ ባሕሪያት ያህል አልሠለጠንም!
ሰሞኑን ፍቅር እስከ መቃብር አጀንዳ ነውና ከፍቅር እስከ መቃብር እንጀምር። በፍቅር እስከ መቃብር ውስጥ ያለው ጉዱ ካሣ ንጥር አድርጎ የሚያሳየን የሀዲስ ዓለማየሁን አርቆ አሳቢነት ነው።በዚያ ዘመን ውስጥ ሆኖ ዛሬን የኖረ ሰው ነው፤ ዛሬ ራሱ የጉዱ ካሣን ያህል የነቃ የለም ለማለት ያስችላል። ለመብት የሚታገል፣ ኋላቀር ልማድን የሚቃወም፣ ጌታና ሎሌ የሚባል ነገር ፀረ እኩልነት መሆኑን የሚያውጅ ነበር።በዚያን ዘመን አሜሪካና አውሮፓውያን ራሱ በጉዱ ካሣ ልክ የመብትና ነፃነት ተሟጋች አልነበሩም።
አቤ ጉበኛ ‹‹አልወለድም›› ሲል ያንን አስፈሪ ንጉሣዊ ሥርዓት ይሞግታል። አቤ ጉበኛም ሆነ ሀዲስ ዓለማየሁ እንደ መንግሥት ብቻ ሳይሆን እንደ መለኮታዊ ስጦታ ይታይ የነበረውን ንጉሣዊ ሥርዓት በዚያ ልክ ይታገሉት ነበር።በዚያን ዘመን ንጉሣዊ ሥርዓቱን መድፈር መንግሥትን እንደ መተቸት ሳይሆን ፈጣሪን እንደ መዳፈር ሁሉ ይታይ ነበር። ‹‹በእንዲህ አይነት ሥርዓት ውስጥ አልወለድም›› ነው ያለው አቤ ጉበኛ። በዚያ ቀና ብሎ ማየት በማይቻልበት ዘመን ውስጥ ነው ሀዲስ ዓለማየሁ እነ አበጀ በለውን ፈጥረው ‹‹በቃ!›› ሊል የሚገባ ትውልድ መፈጠር እንዳለበት ያሳዩት።
ዳኛቸው ወርቁ ‹‹አደፍርስ›› በሚባለው ገጸ ባሕሪ (የመጽሐፉም ስም አደፍርስ ነው) ልማዳዊ የሆነውን የማኅበረሰብ አመለካከት ይሟገት ነበር።አደፍርስ የተባለበት ምክንያትም የአካባቢውን ነባር ልማድ ስለሚያደፈርስ ነው። ልክ እንደ ጉዱ ካሣ ማለት ነው።ጉዱ ካሣ ትክክለኛ ስሙ (ገጸ ባሕሪ መሆኑን ልብ እንበልና!) ካሣ ዳምጤ ነው። የአካባቢው ማኅበረሰብ ግን ሰውየው እብድ ስለመሰላቸው ‹‹ጉዱ ካሣ›› አሉት።አደፍርስንም ስሙን ያወጣለት የአካባቢው ሰው ነው። እነርሱ የለመዱትን ነገር ስለሚያደፈርስባቸው ማለት ነው። ዳኛቸው ወርቁ ቀድሞ የነቃ ስለሆነ እነዚያ ልማዳዊ ነገሮች እንዲቀየሩና የሰው ልጅ ነፃ መብት እንዲኖረው ይታገል ነበር ማለት ነው።
‹‹መስከረም›› በሚለው የታደሰ ሊበን የአጫጭር ልቦለዶች ስብስብ መጽሐፍ ላይ ‹‹ጅብ ነች›› የሚል አንድ አጭር ልቦለድ አለ።በነገራችን ላይ ይህ አጭር ልቦለድ በአማርኛ ቋንቋ መማሪያ መጻሕፍት ምንባብ ላይ እንደነበር አስታውሳለሁ።እንደየክልሎች ሥርዓተ ትምህርት የማይኖርበትም ሊኖር ይችላል።
‹‹ጅብ ነች›› በሚለው አጭር ልቦለድ ውስጥ አሰፋ የሚባል ገጸ ባሕሪ አለ። አሰፋ ተማሪ ሲሆን አንዲት የአካባቢያቸውን ልጅ ያፈቅራል። ያፈቀራትን ልጅ ነው እናቱ ‹‹ጅብ ነች›› የሚሉት። ምክንያቱም በዘመኑ ‹‹ቡዳ›› በሚባል ልማድ ይታመን ነበር። ቡዳ የሚባሉት ደግሞ ጅብ ይሆናሉ ተብሎ ይታመናል። ይህ ልማድ ዛሬም የሚኖርባቸው አካባቢዎች ይኖራሉ። ታደሰ ሊበን ግን ‹‹አሰፋ›› በሚባለው ገጸ ባሕሪ ይህን ልማድ የተሟገቱት ከዛሬ 80 ምናምን ዓመታት በፊት ነው። መጽሐፉ የታተመው በ1940ዎቹ ውስጥ ሲሆን ሳይታተም የቆየበትን ደግሞ አናውቅም። ያም ሆነ ይህ ከዛሬ 70 እና 80 ዓመታት በፊት ይህን መሞገት ቀድሞ መንቃት እና መሠልጠን ነው። ምክንያቱም እነዚህ ልማዶች ‹‹የተማረ›› በሚባለው ዜጋ ሳይቀር ዛሬም አሉ።
እነዚህን አራት ደራሲዎች እንደ ማሳያ የጠቀስኩት ቀደም ያሉ ስለሆኑ እንጂ አገዛዝን የተቃወሙ ብዙ አሉ።አገዛዝን ብቻ ሳይሆን ግን ማኅበረሰባዊ ኋላቀር ልማድንም መሞገት ያስፈልጋል። ‹‹ሚንጊ ነኝ›› የሚባለውን አይነት ጎጂ ልማድ የሚሞግቱ ብዙ መጻሕፍት አሉን። እነዚህ መጻሕፍት ተደራሽነታቸው ሊሰፋ ይገባል።
ኢትዮጵያ እንዲህ አይነት ከዘመን ቀድመው የነቁ ደራሲዎች እያሏት፤ ዳሩ ግን እንደነ ዶስቶየቭስኪ እና ችኑዋ አቼቤ ዓለም አቀፍ ዝነኛ አልሆኑም። ሥራዎቻቸው በብዙ ቋንቋዎች አልተተረጎሙም። ምክንያቱ ቀላል ይመስለኛል።ራሳችን እኛ ኢትዮጵያውያን በዓለም አቀፍ ቋንቋዎች ስላልጻፍናቸው ነው። በተለይም እንደ አሁኑ ዓለም የረቀቀ ቴክኖሎጂ ላይ ከመድረሱ በፊት መጻሕፍት ይነበቡ ስለነበር በዓለም አቀፍ ቋንቋዎች ተጽፈው ቢሆን ኖሮ ዓለም ያውቃቸው ነበር።በዚያው በተጻፉበት ዘመን በውጭ ቋንቋዎች ቢጻፉ ኖሮ ለዓለም የፖለቲካና የባሕል አብዮት ማሳያ ይሆኑ ነበር።ፍቅር እስከ መቃብር በእንግሊዘኛ የተተረጎመ ቢሆንም በተፈለገው ልክ አይደለም፤ አንዳንድ ቅሬታዎችም ሲነሱበት ነበር።
የችኑዋ አቼቤ ‹‹Things Fall Apart›› ኢትዮጵያ ውስጥ እጅግ በተደጋጋሚ ስሙ ይነሳል። በተለይም ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ያሉ መምህራን ስለነጭ ተፅዕኖ ሲያወሩ ምሳሌ የሚያደርጉት ችኑዋ አቼቤን ነው። በአጭሩ፤ የችኑዋ አቼቤ ሙግት ነጮች በአፍሪካውያን ላይ የጫኑትን ቀንበር መሟገት ነው። ራሳቸው አፍሪካውያን ደግሞ የራሳቸውን ጥለው በውጭው ዓለም የተቃኙ፣ ከውጭውም ከራሳቸውም ሳይሆኑ የአዕምሮ መደበላለቅ የሚያጋጥማቸውና የዋዠቁ መሆናቸውን የሚያሳይ ነው።
ይህ የችኑዋ አቼቤ መጽሐፍ የተወራለትን ያህል ግን የሀዲስ ዓለማየሁ ‹‹የልምዣት›› መጽሐፍ አልተወራለትም። የልምዣት የባዕድ የባሕል ወረራን ይሞግታል። አንደኛው ገጸ ባሕሪ (ባሻህ ዘለሌ ማለት ነው) የጣሊያን ወረራን የተዋጋ አርበኛ ነው። ያም ሆኖ ግን ለነፃነት ትግልም ሆነ፣ ለባሕል ወረራ ትግል በብዛት ምሳሌ የሚደረገው ከዚህ ገጸ ባሕሪ ይልቅ የውጮችን ነው።
ዋናው ነገር ለምን የእነርሱ የበለጠ ተፅዕኖ ፈጠረ የሚለው አይደለም። የእኛዎቹን እንዴት ተፅዕኖ ፈጣሪ እናድርጋቸው? የሚለው ነው።ፍቅር እስከ መቃብር በፊልም መምጣቱ እንደገና እንደ አዲስ አጀንዳ እንዲሆን አድርጎታል። መነቃቃት ፈጥሯል። ወደ ፊልም የለወጡትን ሰዎች ከልብ ልናመሰግን ይገባል፡፡
በዚያው ልክ ግን ደራሲዎቻችንን ዓለም አቀፍ የማድረግ ሥራ አልተሠራም።ባለፉት ሳምንታት ባየናቸው ሁለት ትዝብቶች እንደገለጽነው ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የብዙዎች ምኞት የውጭ አገር ቋንቋ መቻልና ውጭ ሀገር መኖር ነው። በዚያው ልክ ግን የሀገራቸውን ታሪክ፣ ባሕልና ወግ በዓለም አቀፍ ቋንቋዎች ቢያስተዋውቁ ጥሩ ነበር። እንዲህ አይነት መጽሐፎችን መጻፍ ባይችሉ እንኳን ቢያንስ ቢተረጉሙ ጥሩ ነበር።
ችግሩ ግን የትውልድ ክፍተት እየተፈጠረ ነው።ነባር ማንነትን ሳይለቁ ዘመኑ የደረሰበት ሥልጣኔ ላይ በመድረስ ትናንትን ማስታወስ ጥሩ ነበር።ችግሩ ግን እነ ችኑዋ አቼቤ እንዳሉት ከዚያም ከዚህም ሳንሆን የዋዠቀ ማንነት ውስጥ ገብተናል። አሁን ላይ ያሉት ዛሬን ቀድመው ነገን መጻፍ ነበረባቸው። ምክንያቱም አሁንም ኋላቀር ልማዶች አሉብን። አሁንም ፖለቲካዊ አስተዳደራችን አልሠለጠንም። አርቆ ማስተዋልን ካለፉት ደራሲዎቻችን እንማር፡፡
የኢትዮጵያ ደራሲዎች እንደ ሌሎቹ ዓለም አቀፍ ደራሲዎች ዓለም አቀፍ ዝና ያላገኙት ሀሳባቸው ከሌሎች አንሶ ሳይሆን በራሳቸው ቋንቋ ብቻ ስለተጻፈ ይመስላል።
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን መስከረም 15/2017 ዓ.ም