አዲስ አበባ፦ ገበያ መር የውጭ ምንዛሪ ተመን ሥርዓት ተግባራዊ በመደረጉ ሕገወጥ የቁም እንስሳት ንግድ እየተዳከመ መምጣቱን የኢትዮጵያ የቁም እንስሳት ላኪዎች ማኅበር አስታወቀ።
የማኅበሩ ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ዲና ገዛኸኝ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደተናገሩት፤ ባለፉት ዓመታት በርካታ የኢትዮጵያ የቁም እንስሳት በኮንትሮባንድ መንገድ ከሀገር ውጭ እንዲወጡ ይደረጋል። ይህም ሀገሪቱ ከዘርፉ ማግኘት ያለባት ጥቅም እንዳታገኝ አድርጓታል።
በተቃራኒው ደግሞ በኮንትሮባድ ሥራ ላይ ወይም ሕገወጥ የቁም እንስሳት ንግድ ላይ የሚሳተፉ አካላት ያልተገባ ጥቅም እንዲያገኙ አድርጓል ያሉት አቶ ዲና፤ በአሁኑ ጊዜ ከማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ጋር ተያይዞ ተግባራዊ የተደረገ ያለው ገበያ መር የውጭ ምንዛሪ ተመን ሥርዓት ኢትዮጵያ ከዘርፉ ተጠቃሚ እንድትሆን ያደርጋታል ብለዋል።
ገበያ መር የውጭ ምንዛሪ ተመን ሥርዓት ተግባራዊ በመደረጉ ሕገወጥ የቁም እንስሳት ንግድ እየተዳከመ መጥቷል ያሉት አቶ ዲና፤ ይህም ሕጋዊ የቁም እንስሳት ንግድ እንዲነቃቃ አድርጓል። ከዚህም ባለፈ በሕጋዊ መንገድ የሚሳተፉ ላኪዎችን አቅምና የሥራ ተነሳሽነት እያሳደገ መምጣቱን ገልጸዋል።
የቁም እንስሳት ንግድ በኮንትሮባንድ ተውጦ የቆየ በመሆኑ መንግሥት ለዘርፉ ትኩረት መስጠት አለበት ያሉት አቶ ዲና፤ ሕገወጥ የኮንትሮባንድ ንግዱ ከማኅበሩ አቅም በላይ በመሆኑ ማኅበሩ ውጤታማ እንዳይሆን አድርጎት ቆይቷል። ይህም የማኅበሩ አባላት በዘርፉ ተስፋ እንዲቆርጡ አድርጎት ነበር ነው ያሉት።
አሁን ላይ ገበያ መር የውጭ ምንዛሪ ተመን ሥርዓት ተግባራዊ በመደረጉ በጥቁር ገበያው እና በባንኮች መካከል ያለውን የውጭ ምንዛሪ ልዩነት አጥብቦታል ያሉት አቶ ዲና፤ ይህም የቁም እንስሳት በአነስተኛ የውጭ ምንዛሪ በኮንትሮባንድ መንገድ እንዳይሸጡ የሚያደርግ መሆኑን ተናግረዋል።
ሌላው በሕገወጥ መንገድ የቁም እንስሳትን በመሸጥ የሚገኘው የውጭ ምንዛሪ በጥቁር ገበያ ይመነዘር እንደነበር ያነሱት አቶ ዲና፤ ይህም በሀገር ውስጥ ገበያው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ሲያሳድር መቆየቱን ገልጸዋል። አሁን ግን መንግሥት ባደረገው የኢኮኖሚ ማሻሻያ ችግሩ እየቀነሰ መምጣቱን አስረድተዋል።
በአጠቃላይ አሁን ላይ የቁም እንስሳትን በጫካ ወስዶ ከመሸጥ ይልቅ በሕጋዊ መንገድ መሸጥ ተመራጩ መንገድ እየሆነ መምጣቱን ገልጸዋል።
ሳሙኤል ወንደሰን
አዲስ ዘመን መስከረም 15/2017 ዓ.ም