ጃፓን ጎብኚዎችን ለማበረታታት የአውሮፕላን ቲኬት በነፃ አቀረበች

ጃፓን ጎብኚዎችን ለማበረታታት የአውሮፕላን ቲኬት በነፃ አቀረበች፡፡ የሩቅ ምሥራቋ ጃፓን ሀገሯን ለሚጎበኙ ጎብኚዎች ነፃ የጉዞ ቲኬት እንደምትሰጥ ገልጻለች፡፡ የሀገሪቱ ቱሪዝም ቢሮ እንደገለጸው ጃፓንን ለሚጎበኙ ጎብኚዎች የሀገር ውስጥ በረራ ለማድረግ ነፃ የጉዞ ቲኬት ማዘጋጀቱን አስታውቋል፡፡

የነፃ ጉዞ ፕሮግራሙ የተዘጋጀው በጃፓን አየር መንገድ በኩል ለሚጓዙ መንገደኞች ሲሆን ዋና ዓላማውም የጎብኚዎችን ቁጥር ለመሳብ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ በተለይም በገጠራማ የሀገሪቱ አካባቢዎች ለሚጓዙ ጎብኚዎች የበለጠ እና የተሻለ የጉዞ ማበረታቻዎች ተሰጥተዋል፡፡ የአሁኑ የነፃ ጉዞ ቲኬት ዋጋ በጎብኚዎች ለሚጨናነቁ ቦታዎች እፎይታ ለመስጠት፣ ገጠራማውን የሀገሪቱ ቦታዎችን ለማስጎብኘት እና ከቱሪዝም የተሻለ ገቢ ለማግኘት ያለመ እንደሆነም ተገልጿል፡፡

ዩሮ ኒውስ እንደዘገበው ከሆነ ጎብኚዎች ይህንን ዕድል ለማግኘት መጀመሪያ በጃፓን አየር መንገድ መጓዝ እና የሀገር ውስጥ በረራዎች ቲኬት መግዛት ይጠበቅባቸዋል፡፡ አየር መንገዱ 24 ሰዓት እና ከዛ በላይ በጃፓን ለሚቆዩ መንገደኞች ለሀገር ውስጥ በረራ ያወጡትን ገንዘብ ተመላሽ ያደርጋል፡፡

እንዲሁም የዚህ ዕድል ተጠቃሚ ለመሆን የአሜሪካ፣ ካናዳ፣ ሜክሲኮ፣ ታይላንድ፣ ሲንጋፖር፣ አውስትራሊያ፣ ቻይና ሕንድ፣ ፊሊፒንስ እና ሌሎችም ሀገራት ዜግነት ሊኖራቸው ይገባል ተብሏል፡፡ በቀጣይም ጃፓን ለተጨማሪ ሀገራት ጎብኚዎች ይህን የነፃ ጉዞ ቲኬት ዕድል ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ማስታወቁን አል ዐይን ዘግቧል፡፡

አዲስ ዘመን መስከረም 15/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You