ሽልማቱን እንደማነቃቂያ

 መምህር ያደታ ኢማና በመድኃኒዓለም ሁለተኛ ደረጃ መሰናዶ ትምህርት ቤት መምህር ናቸው፡፡ ለ35 ዓመታት በመምህርነት ሙያ አገልግለዋል። መምህሩ ለሦስት ዓመታት ብቻ ነበር ጉዳት ሳይደርስባቸው ተማሪዎች ያስተማሩት። በጊዜ ሂደት ግን የአጥንት ካንሰር በሽታ አጋጠማቸው። በጠና ታመው ለሁለት ወራት ያህል በሆስፒታል አሳለፉ። ሕክምናቸውን ጨርሰው ከወጡ በኋላ ለስድስት ወራት ያህል በክራንች መሄድ ግድ ሆነባቸው፡፡ እግራቸው ቢያስነክሳቸውም ያለ ክራንች ድጋፍ በመንቀሳቀስ ዛሬም ትውልድን በመቅረጽ የመምህርነቱን ሙያ ገፍተውበታል፡፡

በኢትዮጵያ በብዙ ዘርፎች የተለያዩ ሽልማቶች ሲሰጡ የተመለከተው የካቲም አካል ጉዳተኝነት ግንዛቤ እና ድጋፍ ድርጅት መሥራች እና ሥራ አስኪያጅ ወጣት አማኑኤል ሰለሞን እንደሚለው፣ አካል ጉዳተኞች ላይ ያለው ጫና የበረታ ነው። ጫናዎችን ተቋቁመው ውጤታማ የሆኑ ተማሪዎች ተምረው ቢመረቁ ሥራ አንይዝም የሚል አመለካከት ስላላቸው እንዲህ አይነቱን ሽልማት በመስጠት ለማበረታት ያለመ ነው። ይህንን እነርሱ ይጀምሩት እንጂ የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮም ሆነ የትምህርት ሚኒስቴር ሥራውን በባለቤትነት እንዲቀጥሉት ይፈልጋሉ፡፡

እንዲሁም አካል ጉዳተኛ መምህራን በማይመች ሁኔታ ውስጥ ሆነው ምቹ እና ለሀገር ጠቃሚ የሆኑ እንዲሁም ሀገር የምትኮራባቸው ተማሪዎችን ያፈሩ ብዙ መምህራን አሉ፡፡ እነዚህ መምህራን ታዲያ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ መሆናቸውን በመረዳት፤ መምህራኑን ለማመስገን እንዲሁም ክብር በመስጠት ተስፋ እንዳይቆርጡ ለማበረታታት ያለመ የእውቅና እና የሽልማት መርሐ ግብር ኅዳር 17 ቀን 2016 ዓ.ም በብሔራዊ ቴአትር ተካሂዷል፡፡

ሽልማት ካገኙት መካከል አብዛኞቹ ከ28 ዓመት በላይ በመምህርነት ያገለገሉ ሲሆን፤ እነርሱን ማበረታታት ክብር መስጠት እና መሸለም ‹‹ለካ የሚመለከተን አካል አለ›› ብለው ተስፋ ሳይቆርጡ እንዲሠሩ ከማድረግ በሻገር ምርታማ የሆኑ ተማሪዎችን ለማፍራት ስንቅ ይሆናቸዋል፡፡

አቢጊያ ውብአለ ደግሞ የእድገት ጮራ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ናት፡፡ በከፊል የእይታ ችግር አለባት፡፡ እርሷም ሽልማቱን ከተቀዳጁት 12 ተማሪዎች መካከል አንዷ ናት፡፡ የ10ኛ ክፍል ተማሪ ስትሆን፤ በ2015 ዓ.ም ከክፍሏ አንደኛ በመውጣት ለሽልማት በቅታለች፡፡

‹‹ሴትነቴን በጣም እወደዋለሁ፡፡ ለወደፊት የተገደበች ሴት መሆን አልፈልግም፡፡ እግዚአብሔር ከረዳኝ በቀጣይ ተፅዕኖ ፈጣሪ ሴት ለመሆን እፈልጋለሁ፡፡ በተጨማሪም ሕግ እና ሕክምና ባጠና ደስ ይለኛል፡፡›› በማለት የወደፊት ሕልሟን ገልጻለች፡፡ አካል ጉዳተኛ መምህራን እና ተማሪዎች እንዲህ መሸለማቸው ደስ የሚል እና የሚበረታታ እንደሆነ የምትገልፀው ተማሪ አቢጊያ፤ እርሷም ለወደፊት አካል ጉዳተኞችን የሚያበረታቱ እና የሚያግዙ ሥራዎችን ለመሥራት ፍላጎት እንዳላት ታስረዳለች፡፡

ከ28 ዓመታት በላይ በመምህርነት አገልግለው ሽልማት ከተሰጣቸው መምህራን መካከል ተጠቃሽ የሆኑት የእንግሊዝኛ ቋንቋ መምህር ያደታ ሽልማቱ የሚያበረታታ መሆኑን ይናገራሉ። እንዲህ ዓይነቱ ሽልማት ቀጣይነት ያለው መሆን ይኖርበታልም ባይ ናቸው፡፡ ሌሎች አካል ጉዳተኞችን ለማነቃቃት ይጠቅማልና፡፡

የካቲም አምባሳደር የሆኑት አምባሳደር ሙሉ ሰለሞን በበኩላቸው፤ ‹‹አካል ጉዳተኝነት ሲባል ብዙዎቻችን የተገደበ ነገር ነው ብለን ነው የምናስበው፡፡ ነገር ግን አካል ጉዳተኝነት ገደብን ማንሳት ነው፡፡›› ሲሉ ጀግናና ምሳሌ ሆነው ለሽልማት ለበቁት መምህራን እንዲሁም ተማሪዎች ያላቸውን ድጋፍ ገልጸዋል፡፡

ወጣት አማኑኤል እንደሚናገረው የአካል ጉዳተኝነት ተግዳሮቶቹ ብዙ ናቸው፡፡ ‹‹የዚህን ዓመት ጥርሳችንን ነክሰን ነው ያዘጋጀነው፣ የሚያግዘን አካል የለም፡፡›› ይላል ስለሽልማቱም ሲያስረዳ፡፡ ‹‹እንችላለን›› የሚለው በየዓመቱ የሚዘጋጀው መርሐ ግብር እንዲቀጥልም ይፈልጋል። ትኩረት አድርገው የሚሠሩት ኪነጥበብ ላይ ነው። ለኅብረተሰቡ አካል ጉዳተኞች መሥራት እንደሚችሉ በማሳየት መንግሥት እንዲቀጥልበት ከማድረግ በሻገር መገናኛ ብዙኃንም ትኩረት ተሰጥተው መሥራት አለባቸውም ይላል ፡፡

እንደ መሥራቹ ወጣት አማኑኤል ገለፃ ዝግጅቱ በተጠበቀው ልክ አይደለም፡፡ መገናኛ ብዙኃን እንዲህ አይነቱ ዝግጅት ላይ ተሳትፏቸው አናሳ ነው፡፡ ዛሬም ቢሆን በየቤታቸው የተደበቁ ብዙ አካል ጉዳተኞች አሉ። አካል ጉዳተኛ ወላጆች ያሏቸው ብዙ ልጆች አሉ፡፡ አካል ጉዳተኛ ልጅን በሰንሰለት አስሮ ማስቀመጥ፤ እንግዳ ሲመጣ ልጁን የሚያሸሹ ብሎም የሚደብቁ ብዙ ሰዎች ናቸው። ስለዚህም ሰዎች ግንዛቤ እንዲያገኙ መገናኛ ብዙኃን ትኩረት ሰጥተው መሥራት ይጠበቅባቸዋል፡፡

የአካቶ ትምህርት ወይም ድጋፍ የሚያሻቸው ተማሪዎች በቂውን ትኩረት እያገኙ አይደለም የሚሉት መምህር ያደታ፤ የማየት ፣ የመስማት፣ ግልፅ ያልሆነ እና ሌሎች ችግር ያለባቸውን ተማሪዎች መኖራቸውን ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ሀገሪቱ አካል ጉዳተኞችን ብትደግፍ ከዚህ የበለጠ እድገት ልታስመዘግብ ትችላለች፡፡ ትኩረት ማድረግ የሚገባው አካል ጉዳቱ ላይ ሳይሆን ችሎታው ላይ መሆን አለበት፡፡

ወጣት አማኑኤል እንደሚናገረው፣ አሁን ላይ በኢትዮጵያ ከ20 ሚሊዮን በላይ አካል ጉዳተኞች አሉ። ቁጥሩ ከፍተኛ ነው፡፡ ስለዚህም ይህንን ከፍተኛ ቁጥር ዘንግቶ ምንም ለውጥ ማምጣት አይቻልም፡፡ ብዙ ውጤታማ መሆን የሚችሉ ተማሪዎች ጓዳ ቢቀመጡ ወይም ወደ ሱስ ቢሄዱ ሀገሪቷ ትጎዳለች፡፡ ምርታማ ዜጋ ለማፍራትም አዳጋች ይሆንባታል። ይህን ከፍተኛ ቁጥር ወደ ምርታማነት ቢቀየር ሀገር በሚገባ ትቀየራለች፡፡

ቴአትር ቤቶች አካል ጉዳተኛ ሲቀጥሩ አይታይም። ለአካል ጉዳተኛ ተብሎ የተመረጠ ሥራ አለ፡፡ የኪነጥበብ ዘርፍ የተተወው ለሌላ ይመስላል፡፡ በትምህርት ቤቶች አካል ጉዳተኞች እንቅስቃሴ የተገደበ ነው፡፡ ቡድኑ ይህንን ችግር ለመፍታት በአሁን ወቅት በስምንት ትምህርት ቤቶች ለዓይነ ስውራን፣ መስማት ለተሳናቸው እና የአእምሮ እድገት ውስንነት ላለባቸው ተማሪዎች የአካል ብቃት እንቀስቃሴ እየሰጠ ይገኛል፡፡ በቀጣይ ይህንን ሥራ አጠናክሮ ለመሥራት ታስቧል፡፡

አሁን ላይ በርካታ ፈተናዎች አሉ፡፡ አካል ጉዳተኝነት እንደ ጥላ የሚከተል በተጨማሪም ማንም ሰው ነገ ላይ ጉዳተኛ ላለመሆኑ ዋስትና የለውም፡፡ በመሆኑም መንግሥትም ይሁን ሌሎች ደጋፊ አካላት የአካል ጉዳተኛውን ሕይወት ሊቀይር የሚችል ሥራዎች ማበረታታት ይገባል፡፡ የአካል ጉዳተኞች ቀን ብሎ ከመዘከር ባለፈ ተግባራዊ ሥራ መሥራት ያስፈልጋል፡፡

እየሩስ ተስፋዬ

አዲስ ዘመን   ኅዳር 20 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You