አቶ ሌንጮ ለታ በኢትዮጵያ የተቃዋሚው የፖለቲካ ትግል ውስጥ በተለይም ከኦሮሞ ነጻ አውጭ ግንባር ጋር በተያያዘ ስማቸው ከሚነሳና ድምጻቸው ጎልቶ ከሚሰማ ሰዎች አንዱ ናቸው፡፡ ረጅሙን እድሜያቸውን ያሳለፉት ለኦሮሞ ህዝብ ነጻነት በመታገል ነው፡፡
በአሜሪካን ሀገር በኬሚካል ኢንጂነሪንግ የተመረቁት አቶ ሌንጮ፤ ኢሕአዴግ ወደ ስልጣን ሲመጣ የሽግግር መንግስቱ አካል ሆነው ተሳትፈዋል፡፡
በወቅቱ ኢሕአዴግ ጸረ ዴሞክራሲያዊ አካሄድ መከተሉን ስንረዳ ለቀን ወጥተናል ይላሉ፡፡ ኦነግ በራሱ በድርጅቱ ውስጥ ያለውን ችግር እንዲፈታና እንዲያስተካክል ለ20 ዓመታት ውስጠ ድርጅት ትግል ማድረጋቸውን ያወሳሉ፡፡ ለውጥ ሊመጣ ባለመቻሉ ከድርጅቱ ተሰናብተው በእራሳቸው የሚመራውን የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኦዴግ) መስርተው ሲንቀሳቀሱ ቆይተዋል፡፡ በቅርቡም መንግስት በውጭ የሚገኙ የፖለቲካ ሃይሎች በአገራቸው ሰላማዊ ትግል እንዲያደርጉ በጋበዘው መሰረት ወደ ኢትዮጵያ ገብተዋል፡፡ ባለፈው ሳምንትም ፓርቲያቸው ከኦዴፓ ጋር ውሕደት ለመፈጸም የሚያስችለውን ስምምነት ፈጽሟል፡፡ ከአንጋፋው የፖለቲካ ሰው ጋር ያደረግነውን ቃለ ምልልስ ይከታተሉት፡፡
አዲስ ዘመን፡- አቶ ሌንጮ ለታ ዋቀዮ ማን ናቸው ?
አቶ ሌንጮ፡- የተወለድኩት ደምቢዶሎ የሚባል ቦታ ምእራብ ኦሮሚያ ነው፡፡ በልጅነቴ እዛው ነው የተማርኩት፡፡ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን አዳማ በሚገኝ አንድ የሚሲዮን ትምህርት ቤት የተማርኩ ሲሆን፤ በኋላም ዩኒቨርሲቲ ገብቼ ተምሬ የጨረስኩት አሜሪካን ሀገር ነው ፡፡
አዲስ ዘመን፡- አሜሪካን የት ዩኒቨርሲቲ ነው የተማሩት ?
አቶ ሌንጮ፡- ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ራችስተር ይባላል፡፡ የተመረቅኩት በኬሚካል ኢንጂነሪንግ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ኦነግ ከተመሰረተበት ወቅት ጀምሮ በትግሉ ውስጥ ነበሩ፡፡ በዚህ ረጅም ዓመት የነበረው እንቅስቃሴ እንዴት ይገለጻል?
አቶ ሌንጮ ለታ፡- ይሄ ረጅም ነው፤ የሃምሳ ዓመት እንቅስቃሴ፡፡
አዲስ ዘመን፡- በስንት ዓመተ ምሕረት ተመሰረተ?
አቶ ሌንጮ፡- እ አ አ በ1974፤ በእኛ አቆጣጠር በ1966 ዓ.ም ማለትም በአብዮቱ ወቅት ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ኦነግ ከሽግግሩ መንግስት የወጣበት ምክንያት ምንድነው?
አቶ ሌንጮ፡- ዴሞክራሲን ለመመስረት ነበር ተስማምተን የመጣነው፡፡ የኢሕአዴግ አያያዝ ግን ወደ ዴሞክራሲ እንደማያመራ ተገነዘብን፡፡ ጊዜያችንን ከማጥፋት ብለን ለቀን ወጣን፡፡
አዲስ ዘመን፡- በሽግግር መንግስቱ ወቅት ለፕሬዚዳንትነት እንዲወዳደሩ በእጩነት ቀርበው አልፈልግም ብለው ነበር ይባላል፤ እውነት ነው ?
አቶ ሌንጮ፡- አይደለም፡፡ በወቅቱ የተወካዮች ምክር ቤት ሊቀመንበር እንድሆን አቶ መለስ ፈልጎ ነበር፡፡ እኔ ግን አልተስማማሁም፡፡ እርሱ የፈለገው ጠንካራ ነጥብ ከሆነ የምንወያይበት እራሱ ሊመጣ፤ ሌላውን የቀረውን ስራ እኔ እንድሰራለት ነበር፡፡ እኔ ደግሞ አልተስማማኝም፡፡
አዲስ ዘመን፡- ከኦነግ በመለየት ኦዴግን የመሰረታችሁበት መሰረታዊ ምከንያት ምንድነው?
አቶ ሌንጮ ፡- 20 አመት ለሚጠጋ ጊዜ ኦነግ ስትራቴጂውን እንዲያሻሽል በውስጥ ሆነን ታግለናል፡፡ ብዙም ግፊት እየፈጠርን ነበር፡፡ ያ አልተሳካም፡፡ እኔን አሰናበቱኝ፡፡ እ … ዝም ብሎ ቁጭ ከማለት ብዬ ከሌሎች መሰሎቼ ጋር አዲስ ድርጅት አቋቋምን፡፡
አዲስ ዘመን፡- ኦዴግ የመገንጠል አላማን ይደግፋል ?
አቶ ሌንጮ ፡- አይደግፍም፡፡
አዲስ ዘመን፡-አላማው ምንድነው ?
አቶ ሌንጮ፡- አላማው ያለውን የብሔሮች ፌዴሬሽን ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን መታገል ነው፡፡ ፌዴሬሽኑ የእኛ ሀሳብ ስለሆነ መደገፍ አለብን፡፡ የኢሕአዴግ አያያዝ ኢ ዴሞክራሲያዊ ስለነበረ፤ ይህም በሀገሪቷ ላይ ብዙ አደጋ ሊያመጣ እንደሚችል ስለተገነዘብን በሰላማዊ መንገድ ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን ማድረግ ነው አላማችን፡፡
አዲስ ዘመን፡- ኦነግ በሽግግሩ መንግስት በአንዳንድ ቦታዎች ግድያ ፈጽሟል ተብሎ ይወቀሳል፡፡ ኦዴግን የመሰረታችሁት ኦነግ ይወቀስበት የነበረውን ጉድለት በማረም ከተወቃሽነት ለመውጣት ነው የሚል አስተያየት ይሰነዘራል፡፡ በዚህ ላይ ምን አስተያየት አለዎት?
አቶ ሌንጮ፡- ይህ ጥያቄ በጣም ብዙ ጊዜ ይነሳል፡፡ ይመስለኛል ወደ መቶ ጊዜ መልሼዋለሁ፡፡ መልሴንም ሳትሰማ አልቀረህም፡፡ በደኖና አርባ ጉጉ ለፕሮፓጋንዳ ፍጆታ ኢሕአዴግ ያቀናጀው ትረካ ነው እንጂ፤ እሬሳ ከገደል ሲወጣ የሚታየው ኦነግ የፈጸመው ግድያ አይደለም፡፡
አዲስ ዘመን፡- ኦነግ ለረጅም ዘመን ታግሎ ስኬታማ መሆን አልቻለም፡፡ ከዚህ አንጻር ክፍተቶች ስለተፈጠሩ ሕዝቡን ይቅርታ መጠየቅ አለበት የሚሉ ክፍሎች አሉ፡፡ እርስዎ እንዴት ያዩታል?
አቶ ሌንጮ፡- ይህን ኦነግን ጠይቀው፡፡ እኔ አሁን ኦነግ አይደለሁም፡፡
አዲስ ዘመን፡- 1986 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ መጥተዋል፡፡ ምክንያቱ ምን ነበር ? ምን አጋጠመዎት፤ታስረው ነበር ?
አቶ ሌንጮ፡- ያኔ ሁሉን አቀፍ ስብሰባ እዚህ ከተማ እንዲዘጋጅ ነበር ሃሳቡ፡፡ በእዚያ ስብሰባ ለመሳተፍ የመጣ የእኛ አባል ታሰረ፡፡ ኦነግም ውስጥ ይሄን ያህል ከፍተኛ ሚና አልነበረውም፡፡ በእሱ ፋንታ እኔን እሰሩኝ ለማለት ነው የመጣሁት፡፡ ለ10 ቀን ያህል ታስሬአለሁ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ከእስር እንዴት ተፈቱ ?
አቶ ሌንጮ፡- ከአቶ መለስ ጋ ተገናኝተን ያው ተስማምተን ነው የለቀቀኝ፡፡
አዲስ ዘመን፡- በወቅቱ በምን ነበር ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ጋ የተስማማችሁት ?
አቶ ሌንጮ፡- እርሱም ይል የነበረውን እኔም የማምንበት ነበር፡፡ እዚሁ ሀገር ቤት ሆነን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓቱን የመገንባቱ ጉዳይ ላይ ከእነርሱ ጋ መታገል ይሻላል የሚል እምነት ስላለኝ፡፡ እርሱም ያንን ስለተቀበለ ነው የተለቀቅነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ወዲያው ተመልሰው ወደ አሜሪካን ገቡ ?
አቶ ሌንጮ፡- አዎ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ከኦዴፓ ጋር ያደረጋችሁት ውሕደት መነሻ ምክንያቱ ምንድን ነው ?
አቶ ሌንጮ፡- ስምምነት ያደረግነው በብዙ ምክንያት ነው፡፡ አንደኛ የኦሮሞ ሕዝብ የኦሮሞ ድርጅቶች አንድ ላይ እንዲሰባሰቡ ከፍተኛ ግፊት እያደረገ ነው፡፡ እኔ አንድ ጊዜ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጠሩት የፓርቲዎች ስብሰባ ላይ ተሳትፌ ወደ 14 የኦሮሞ ድርጅቶች ነበሩ የሚል ገለጻ ተደርጎ ነበር፡፡ ይሄ ለኦሮሞም ለኢትዮጵያም አይበጅም፡፡
አዲስ ዘመን፡- ከውሕደቱ ጋር በተያያዘ አንዳንድ አስተያየቶች ይሰነዘራሉ፡፡ የተቃውሞ ጎራውን አዳክሞ በኢሕአዴግ እንዲዋጡ ያደርጋል የሚሉ አሉ፡፡ ኢሕአዴግ አቅጣጫውን እንዲቀይር ተጽእኖ ይፈጥራል የሚሉም ይደመጣሉ፡፡ ጉዳዩን እንዴት ያዩታል?
አቶ ሌንጮ፡- አንደኛ ነገር ውሕደት ላይ ለመስራት ነው የተስማማነው እንጂ ውሕደቱ አልተፈጸመም፡፡ ብዙ ነገሮች ገና በውይይት ይፈታሉ፡፡ የፖለቲካ አቋምና ርእዮተ ዓለም የመሳሰሉት፡፡
አዲስ ዘመን፡- አብዮታዊ ዴሞክራሲስ ?
አቶ ሌንጮ፡- ገና የሚጠናና በውይይት የሚፈታ ነው፡፡ ሁለተኛ እኛ ከኦዴፓ ጋር የተስማማነው ሌላ ድርጅት ለማጥቃት ወይንም ለማዳከም ሳይሆን አብረን ችሎታችንን አንድ ላይ ደምረን ለዴሞክራሲያዊ ግንባታ ለመታገል ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ኦዴፓ አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ርእዮት ሲከተል ቆይቷል፤ የእናንተ ርእዮት ምንድን ነው ?
አቶ ሌንጮ፡- ይሄን መግለጽ አስቸጋሪ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ከኦዴፓ ጋር ስምምነታችሁ እስከምን ድረስ ነው፤በቀጣዩ ምርጫ የምትወዳደሩት እንደ አንድ ፓርቲ ነው ወይንስ ለየብቻ ?
አቶ ሌንጮ፡- ኦዴፓ የኢሕዴግ አባል ነው፡፡ ስንዋሀድም በዛው የሚቀጥል ይመስለኛል፡፡ ውሕደታችን እየተካሄደ ያለውን የለውጥ ሁኔታ ለማጎልበት ነው፡፡ እስከዛ ድረስ እንታገላለን፡፡
አዲስ ዘመን፡- በኢትዮጵያ አንድነት ላይ ያላችሁ አቋም ምንድነው ?
አቶ ሌንጮ፡- ኢትዮጵያ አንድ ሀገር ሆና እንድትቀጥል እንፈልጋለን፡፡ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ ለኦሮሞም ይጠቅማል ብለን እናምናለን፡፡ ኦሮሞነትን የሚያቅፍ አይነት መሆን አለበት፡፡ ቀደም ብዬ በሽግግሩ መንግስት ዘመን ያልኩት ኢትዮጵያዊነትን ለመቀበል ለመደራደር እንፈልጋለን ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነትንም ኦሮሞነትንም ደርበን አንድ ላይ ለመያዝ ከቻልን ኢትዮጵያ ትልቅ ሀገር ስለሆነች አብዛኛውም ኦሮሞ ስለሆነ ትክክለኛ አቋም ነው፡፡ ከዚህ በፊት እኛን ያሳመጸን ኦሮሞነትን ካልተውክ ኢትዮጵያዊነትን መጎናጸፍ አትችልም የሚለው ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ለምን፤ እንደዚህ የሚል ውሳኔ ነበር ?
አቶ ሌንጮ፡- ነበር አዎ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ንጉሱ ራሳቸው በኋላም ፕሬዚዳንት መንግስቱ የኦሮሞ ደም እንደነበራቸው ይነገራል፤ የዚህ አይነት አቋም ነበራቸው ?
አቶ ሌንጮ፡- ጉዳዩ የደም አይደለም፡፡ የአስተሳሰብ ነው፡፡ አጼ ኃይለስላሴ የኦሮሞ ደም እንዳለባቸው የሚወራው ከሞቱ በኋላ ነው፡፡ መንግስቱም ኦሮሞ መሆኑ የተገለጸው ከስልጣን ከተወገደ በኋላ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- በዚያን ጊዜ ስለኢትዮጵያዊነት እንጂ ስለዘር ይነሳ ነበር?
አቶ ሌንጮ፡- ይሄ የዘር ጉዳይ አይደለም፤ የብሔር ጉዳይ ነው፡፡ ‹‹ኔሽን ቢዩልዲንግ›› ተብሎ የተወሰደው አንድ ቋንቋ፤ አንድ ባሕል፤ አንድ ታሪክ የሚለውን አካሄድ ሁለቱም ይከተሉ ነበር- የአጼ ኃይለስላሴም የመንግስቱም አስተዳደር፡፡ ያ ነው ያሳመጸን፡፡ አሁን ኦሮሞም ሆነህ ኢትዮጵያዊ መሆን ትችላለህ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ኦሮሞነትና ኢትዮጵያዊነት ምን ይለየዋል?
አቶ ሌንጮ፡- እንዳልኩህ ነው፡፡ የአጼ ኃይለስላሴም የመንግስቱም አስተዳደር የኦሮሞ ባሕልና ቋንቋ እንዲሰረዝ እንዲጠፋ እንዲደመሰስ በግልጽ ይሰሩ ነበር፡፡ ወንጌል እንኳን መስበክ በሕግ ክልክል ነበር፤ በኦሮምኛ ቋንቋ፡፡
አዲስ ዘመን፡- በዚያ ዘመንም ቢሆን ብዙዎቹ የኢትዮጵያ ሹማምንት፣ ሚኒስትሮችና ጄኔራሎች ኦሮሞዎች ነበሩ፤ ይሄ እንዴት ነው የሚታየው?
አቶ ሌንጮ፡- ጉዳዩ ይሄ አይደለም፡፡ ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ግን ኦሮሞን ወክለው አይደለም፡፡ ለኦሮሞ ቆመዋል ወይ ቢባል አልነበረም ነው መልሱ፡፡ እንዲያውም አንድ መስሪያ ቤት በኦሮሞ የሚመራ ከሆነ በእዚያ ጊዜ ሁለተኛ ኦሮሞ ለመቅጠር በጣም አዳጋች ነበር፡፡
አዲስ ዘመን፡- ይሄ በጃንሆይ ጊዜ ነበር?
አቶ ሌንጮ፡- በመንግስቱም ጊዜ ያው ነበር፡፡ ለምን ዘመዶቹን ሰብስቦ ቀጠረ ተብሎ ሊከሰስ ስለሚችል ነው፡፡ ኦሮሞ ባለስልጣን ከሆንክ እዚያ መስሪያ ቤት ሌላ ኦሮሞ እንዲቀጠር አታደርግም፡፡
አዲስ ዘመን፡- በቀደመው ዘመን በኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት እነ ጄኔራል መርእድ ንጉሴ፤እነ ጄኔራል ደምሴ ቡልቶ፤እነ ጄኔራል መርዳሳ ሌሊሳ፤እነ ጄኔራል ካሳዬ ጨመዳና ሌሎችም ባለስልጣናት የኦሮሞ ተወላጆች ነበሩ፡፡ በብዛት በተለያዩ የኃላፊነት ቦታ ሲመሯት የነበሩት እኮ ኦሮሞዎች አልነበሩም?
አቶ ሌንጮ፡- ልንገርህ የሴኔጋሉ ሴዳር ሴንጎር፤ የኮትዲቯሩ ሁፌት ቡዋኜ የፈረንሳይ ምክር ቤት አባሎች እኮ ነበሩ፡፡ ያ ግን የፈረንሳይ ጭቆና በሴኔጋል ላይ አልነበረም ማለት አይደለም፡፡
አዲስ ዘመን፡- የነበረውን የሕዝብ መብት አላስጠበቁም እንጂ ሌላ ነገር የለውም ለማለት ነው?
አቶ ሌንጮ፡- የሕዝቡን መብት አላስጠበቁም፡፡ ሌላ የለውም፡፡
አዲስ ዘመን፡- በሀገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች በሚነሱ ግጭቶች በኦሮሞ ስም የተደራጁ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ስም ይነሳል፤ በዚህ ላይ ምን አስተያየት ይሰጣሉ ?
አቶ ሌንጮ፡- እኛ የለንበትም፡፡ ይሄ ግጭት በታጠቁ ኃይሎች የሚፈጸም ነው፡፡ እኛ የታጠቀ አንድም አባል የለንም፡፡ በትጥቅ ትግልም አናምንም፡፡
አዲስ ዘመን፡- ኦዴግ ምን ያህል አባላት አሉት?
አቶ ሌንጮ፡- ውጭ ሀገር ነው አብዛኛዎቹ አባላት ያሉት፡፡ በሀገራችን ውስጥ ገና መመልመል ጀምረናል፡፡ ቢሮ እስካሁን እዚሁ አዲስ አበባ ነው የከፈትነው፡፡ በክልል ቀስ በቀስ ሁኔታውን እየተረዳን ነው የሚሆነው፡፡ እኛ ከዚህ ሀገር ከወጣን ወዲህ ኢትዮጵያ በጣም ተቀይራለች፡፡ ስለዚህ በችኮላ የሚደረግ ነገር ብዙ ስህተት ሊያስከትል ይችላል፡፡ በእርጋታ እየታየ ነው መሆን ያለበት፡፡
አዲስ ዘመን፡- በሀገሪቱ የመጣውን ለውጥ ለማስቀጠል ምን መደረግ አለበት ይላሉ ?
አቶ ሌንጮ፡-ከምርጫ በፊት መፈጸም ያለባቸው ጉዳዮች አሉ፡፡ የተቋማት መጠናከር አንዳንዴም መፈጠር ፤ተቋማት ከገዥው ፓርቲ ነጻ አቋም እንዲይዙ ፤የፖለቲካ ባሕላችንም እንዲሻሻል ፤በዚህ ላይ መስራት ጀምረናል፡፡ ወደፊትም እንሰራለን ብለን እናምናለን፡፡
አዲስ ዘመን፡- እንዴት ነው ከፖለቲካ ወገንተኝነት ነጻ የሆኑ ተቋማት መፍጠር የሚቻለው ?
አቶ ሌንጮ፡- ይቻላል፡፡ የፖሊስና የሰራዊት ኃይሉ እንዲሁም የምርጫ ቦርዱ፤ የፍትህ ሥርዓቱ እነዚህ ሁሉ ከማንኛውም ፓርቲ ነጻ መሆን አለባቸው፡፡ እስከ አሁን ግን ከኢሕአዴግ ጋር ተመሳጥረው ነው የተዋቀሩት፡፡
አዲስ ዘመን፡- ቀጣዩ ምርጫ በምን አግባብ መሆን አለበት ብለው ያምናሉ ?
አቶ ሌንጮ፡- ይሄ በድርድር በውይይት የሚወሰን ነው፡፡ ፓርቲዎች ስብሰባ ጀምረዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቅርቡ በሩን ከፍተውታል፡፡ በፓርቲዎች መካከል ዴሞክራሲያዊ ባህል ስለመገንባት መስማማት ላይ መድረስ አለብን፡፡
አዲስ ዘመን፡-ከአዲስ አበባ የባለቤትነት ጥያቄ አንጻር የእናንተ አቋም ምንድን ነው ?
አቶ ሌንጮ፡- አዲስ አበባ የኦሮሚያ አካል ነች፡፡ ይህ ጥያቄ ለምን እንደሚነሳም አይገባኝም፡፡ ለምሳሌ የመቀሌ የባለቤትነት ጥያቄ ተብሎ አይጠየቅም፡፡ መቀሌ ደሴት አይደለችም፤ በትግራይ ውስጥ ነው ያለችው፡፡ የትግራይ አካል ነች፡፡ ባሕር ዳርም ደሴት አይደለም፡፡ የአማራ ክልል አካል ነው፡፡ አዲስ አበባ እንዴት ሆኖ ነው ደሴት የሚሆነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ጥያቄው የሚነሳው አዲስ አበባ የኢትዮጵያ መዲናና ሁሉም ብሄር ብሄረሰቦች የሚኖሩባት ነች ከሚል ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ምን አስተያየት አለዎት ?
አቶ ሌንጮ፡- አንደኛ ነገር አንድ ከተማ ድርብ ስራ ሊሰራ ይችላል፡፡ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ ሊሆን ይችላል፡፡ የኦሮሞም ዋና ከተማ ሊሆን ይችላል፡፡ ከዚህ አንጻር ነው እያወራን ያለነው፡፡ ኦሮሞ አያገባውም ከተባለ ችግር ነው የሚፈጠረው፡፡ አዲስ አበባ በኦሮሚያ ላይ ትጠለላለች እንጂ ኦሮሚያ በአዲስ አበባ ላይ አትጠለልም፡፡ ይሄን መገንዘብ ለአዲስ አበቤው ለከተሜው ሕብረተሰብ አስፈላጊ ነው፡፡ ይሄንን የጋራ መስተጋብር ሁሉም ተረድቶ ይሄ ከተማ የኦሮሞ ዋና ከተማ የፌዴሬሽኑም ዋና ከተማ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ በዚህ ላይ ባንነታረክ ይሻላል፡፡ ዋጋ የለውም፡፡
አዲስ ዘመን፡- በሕገመንግስቱ አዲስ አበባ ኦሮሚያ ክልል ውስጥ የምትገኝ ከተማ በመሆኗ ክልሉ ልዩ ጥቅም ማግኘት እንዳለበት ተደንግጓል፡፡ ይሄ ስራ ላይ አልዋለም፡፡ ይሄንንስ እንዴት ያዩታል ? ምን መደረግስ አለበት ?
አቶ ሌንጮ፡- ሕጉ መውጣት ነበረበት፡፡ እስከዛሬ አልወጣም፡፡ እኛ ሕጉ እንዲወጣ ግፊት እናደርጋለን፡፡ ድንጋጌው የሚያስቀም ጠው አዲስ አበባን እንደ ኦሮሚያ ዋና ከተማ ነው፡፡ አንዳንድ መሻሻሎች መደረግ አለባቸው፡፡ የኦሮሞ አካል መሆኑን የሚያንጸባርቁ ድርጊቶችና ድርጅቶች መኖር አለባቸው ብለን እናምናለን፡፡
አዲስ ዘመን፡-እናመሰግናለን!
አቶ ሌንጮ፡- አመሰግናለሁ!
ወንድወሰን መኮንን