ሰው ሰራሽ አስተውሎት፤

የሰው ሰራሽ አስተውሎት/Artificial Intelligence /AI/ጉዳይ ከሳይንስ አልፎ የማሕበራዊ፣ የኢኮኖሚ፣ የደህንነት፣ የሳይበር ጦርነት፣ የወታደራዊ ዝማኔ፣ የሉዓላዊነትና የልዕለ ኃያልነት እርካብ መቆናጠጫ ከመሆን አልፎ የጂኦፖለቲካ ሚዛን መለካኪያ ከሆነ ውሎ አደረ። በሚቀጥሉት ጥቂት ዓመታት በAI የበላይ የሆነ ዓለምን በመዳፍ ለመጨበጥ ተጨማሪ አቅም ያገኛል። አሜሪካና ቻይና በዚህ ዘርፍ ጉሮሮ ለጉሮሮ እየተናነቁ ያሉት ለዚህ ነው።

ማን አሸናፊ ሆኖ እንደሚመጣ በቅርብ እናያለን። የAIን ጉዳይ በቁንጽል ሳይሆን በማዕቀፍ ማየት ያስፈልጋል። እንደ ሀገር የሚሰጠው ትኩረትም ይሄን ታሳቢ ያደረገ ሊሆን ይገባል። የምዕራባውያን የስለላ፣ የደህንነትና የአለማቀፍ ግንኙነት ልሳን የሆነውና ተነባቢው የ”Foreign Affairs”መጽሔት ሰሞነኛ ዕትም በአንድ ጊዜ ከአንድም ሁለት ጥልቅ መጣጥፎችንና ትንተናዎቹን በAI ላይ ማድረጉ ምን ያህል ገዥ አጀንዳ እየሆነ እንደመጣ ያረጋግጣል።

ጀምስ ማኒካና ማይክል ስፔንስ በገራ፤ “The Coming AI Economic Revolution”በሚል ርዕስ ባስነበቡን መጣጥፍ፤ የAI አንድ ዘርፍ የሆነው አዲሱ ሰውሰራሽ አስተውሎት ወይም ጄነሬቲቭ አርቲፊሻል ኢንተሊጀንስ ብቻ ለዓለም ኢኮኖሚ በዓመት 4 ትሪሊየን ዶላር ያበረክታል። በዓለማችን በግዙፍነቱ 4ኛ እንደሆነ የሚነገርለት የጀርመን ጥቅል ኢኮኖሚ 4 ትሪሊየን ዶላር መሆኑን እዚህ ላይ ልብ ይሏል።

እንግዲህ ይህ ሌሎች እንደ አውቶሜሽን ያሉ የAI ዘርፎች ለኢኮኖሚው ከሚያመነጩት 11 ትሪሊየን ዶላር በተጨማሪ መሆኑ ነው። በAI ባቡር መነሻንና መዳረሻን ጠንቅቆ አውቆ በጊዜ መሳፈር ወሳኝ ስለሆነ ነው ትኩረት ተሰጥቶ የምናየው። ኢትዮጵያ አበክራ ከሶስት ዓመታት በፊት የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት አቋቁማ የሰው ሰራሽ አስተውሎትን በተለያዩ ተቋማት ስራ ላይ ለማዋል እየጣረች ያለችው ለዚህ ነው።

ሰው ሰራሽ አስተውሎትን በሀገር በቀል ተቋም ገርቶ በማሰልጠን ለሀገር ጥቅምና ልማት ማዋል ይገባል ሲሉ የቴክኖሎጂ ጉዳዮች አማካሪና በebs የቴሌቪዥን መርሀ ግብር አዘጋጅ ሰለሞን ካሳ፤ በኢትዮጵያ የሰው ሰራሽ አስተውሎት የሚገኝበት ደረጃና መሰል ጉዳዮች ዙሪያ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ፤ የሰው ሰራሽ አስተውሎት በእርሻ፣ በአስተዳደር፣ በትምህርትና በሌሎች በርካታ አገልግሎቶች ላይ እንደሚተገበር፤ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ለኢትዮጵያ ክፍተትን በመሙላት፣ ወደኋላ ያስቀረን እና ያልተቀላጠፈ ስርዓታችንን ለማዘመን ያግዛል ሲሉም ተናግረዋል።

በተጨማሪም ኢትዮጵያውያን በዚህ ሂደት አልፈው ከሀገራቸው አልፈው ለዓለም ብዙ ማበርከት እንደሚችሉ፤ የሰው ሰራሽ አስተውሎት በዓለም ላይ እያደገ መምጣቱን ተከትሎ ብዙ ዘርፎች እንዲወለዱ ምክንያት መሆኑን፤ ዘርፉን እንደ ኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ባለ ሀገር በቀል ተቋም ገርቶ በራስ ልክ ማሰልጠንና ለበጎ ተግባር ማለትም ለሀገር ጥቅምና ልማት ማዋል ግድ እንደሚልም አሳስበዋል።

የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ከእድሜ አንጻር ገና ቢሆንም እየተንቀሳቀሰ ያለው ግን ከዚያ በላይ እንደሆነ፤ ኢትዮጵያን በአፍሪካ በሰው ሰራሽ አስተውሎት ግንባር ቀደም የሚያደርጋትን ተቋም እውን ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ደግሞ የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ወርቁ ጋቸና (ኢ/ር) አክለው መግለጻቸው በመግቢያዬ ላጋራኋችሁም ሆነ በማስከተል ለማካፍላችሁ ታሪካዊ ዳራ መነሻ ሆኖኛል፡፡

በነገራችን ላይ መጭው ዘመን የ”AI”ነው። ባጠረ ጊዜ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ የእያንዳንዳችን የሕይወት ቅንጣት የሚነካ ስለሆነ ስለ AI ግንዛቤ መያዝም ስላለበት ወይም AI Literacy መጎልበት ስለሚገባው ብዙኃን መገናኛዎች ብዙ ስራ ይጠብቃቸዋል።

የኢንዱስትሪ አብዮት በ18ኛው መቶ ክፍለ ዘመን  መጨረሻ ተጀምሮ በ19ኛው መክዘ ተጠናክሮ የቀጠለ ወሳኝ የቴክኖሎጂና የኢኮኖሚ እምርታ ነው ። አዳዲስ ፋብሪካዎች የተፈጠሩበት፣ የእንፋሎት ኃይል በስፋት ጥቅም ላይ የዋለበት፣ ማሽኖች ወደ ስራ የገቡበት፣ ምርትና ምርታመነት የጨመረበት እና ከተሞች የተስፋፉበትና ዛሬ የምንገኝበት ዓለም የተበየነበት ታላቅ ክስተት ነው። በሰው ልጆች ታሪክ ሶስት የኢንዱስትሪ አብዮቶች የተካሄዱ ሲሆን አራተኛውን ደግሞ ተያይዘነዋል።

ሁሉም የየራሳቸውን አዳዲስ የፈጠራና ኢኮኖሚያዊ ማዕበል አስነስተዋል። የመጀመሪያው የኢንዱስትሪ አብዮት ችቦ በእንግሊዝ ተለኩሶ ወደ አውሮፓና ሰሜን አሜሪካ የተቀጣጠለ ሲሆን የዘመነ ፋብሪካና የእንፋሎት ኃይል መለያው ናቸው። ሁለተኛው የኢንዱስትሪ አብዮት በ19ኛው መክዘ መገባደጃ ተጀምሮ እስከ 20ኛው መክዘ መጀመሪያ የቀጠለ ሲሆን እንደ መኪናና አውሮፕላን ያሉ መጓጓዣዎች፤ የኤሌክትሪክ ኃይልና የኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂዎች በስፋት ጥቅም ላይ የዋሉበት ነው።

ሶስተኛው የኢንዱስትሪ አብዮት ከ20ኛው መክዘ አጋማሽ ዛሬ ድረስ የቀጠለው ሲሆን የዲጂታል ቴክኖሎጂ፣ በይነ መረብ ወይም ኢንተርኔት፣ አውቶሜሽን፣ ሮቦቲክስና ሌሎች ቴክኖሎጂዎች የተስፋፉበትና በስፋት ጥቅም ላይ  የዋሉበት ነው። ብዙ ሊቃውንት አሁን የምንገኝበትን ጊዜ የአራተኛው የኢንዱስትሪ አብዮት የተጀመረበት፤ የዲጂታል ቴክኖሎጂ የተቀናጀበት፣ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ወደ ስራ የገባበት፣ በይነ መረብ እያንዳንዱን የሕይወት ቅንጣትና የኢኮኖሚ ዘርፍ ማዳረስ የጀመረበት ከመሆኑ ባሻገር በአኗኗራችንና በግንኙነታችን ላይ የዝሆን ዳናውን እየተው ያለ ምዕራፍ ነው። እጃችን የገባን ቴክኖሎጂ ተለማምደነውና ተዋውቀነው ሳናበቃ እጃችን ላይ የሚያረጅበትና በፍጥነት የሚለዋወጥበት ዘመን ነው።

ለብዙዎቻችን የሰው ሰራሽ አስተውሎት አዲስ ግኝትና ቴክኖሎጂያዊ እመርታ የቅርብ ጊዜ ክስተት ቢመስለንም የዘርፉ ልሒቃን ግን ጥንስሱ ጥንታዊ ነው ሲሉ ሀተታ ተፈጥሮንና ስነ ቃልን በዋቢነት ያወሳሉ። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ተስፋም ስጋትም ይዞ ወደፊት እየመጣ ያለው ሰው ሰራሽ አስተውሎት ግን የተጀመረው በ20ኛው መክዘ አጋማሽ ሲሆን የኮምፒውተር ሊቃውንት ስልተ ቀመር ወይም አልጎሪዝምና አስበው የሚሰሩ ማሽኖች ወደ ስራ እየገቡበት ያለ ጊዜ ነው።

በ1943 ዓ.ም ዋረን ማክኩሎችና ዋልተር ፒትስ በጋራ በነርቭ አውታረ መረብ የሚታገዝ ሒሳባዊ ሞዴል ወይም mathematical model of neural መፍጠራቸው ለዛሬው ሰው ሰራሽ አስተውሎት እርሾ ሆኖ አገልግሏል። በ1950 ዓ.ም አለን ተርኒግ እንደ ሰው ማሰብ የሚችል ማሽን ፈልስፎ ሙከራ አደረገ። በ1950ዎቹና 60ዎቹ General Problem Solver (GPS) እና ሎጂክ ቴዎሪስትን ጨምሮ በርከት ያሉ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ፕሮግራሞች በለጸጉ።

በ1956 ዓም የዳርትማውዝ ጉባኤ”ሰውሰራሽ አስተውሎት”ራሱን ችሎ እንዲጠና ከመወሰኑ ባሻገር ዛሬ የምንጠቀምበትን ይሄን መጠሪያውን አገኘ ። በዚሁ ጉባኤ የተሳተፉ የዘርፉ ሊቃውንት AI ውስብስብ ችግሮችን የመፍታት አቅም እንዳለው ለመጀመሪያ ጊዜ ይፋ አደረጉ። በ1970ዎቹና 80ዎቹ በAI (Artificial Intel­ligence) ዘርፍ የሰውን ልጅ የመወሰን አቅም የሚተካከል የኮምፒውተር ፕሮግራምለማበልጸግ ርብርብ ይደረግ ነበር።

ዳሩ ግን በ1990ዎቹ የሚፈለገውን ያህል ውጤታማ ባለመሆኑ ምርምሮቹ መቀዛቀዝ ጀምረው ነበር ። በ21ኛው መክዘ ደግሞ እንደገና ማንሰራራት ጀመረ። ከዚህ በኋላ ነጮች እንደሚሉት የተቀረው ታሪክ ነው ። ሰውን ተክተው የሚሰሩ፣ ስልተ ቀመርን algorithm የሚረዱ ማሽኖች ስራ ላይ መዋል ጀመሩ። በርካታ መረጃዎችን አብላልተው የሚሰሩ ከፍተኛ አቅም ያላቸው ኮምፒውተሮች ወደ ስራ መግባታቸው ዘርፉን ያጎለብተው ጀመር።

አሁን አሁን AI የማይገባበት የሕይወት ቅንጣት የለም። በጤናችን፣ በማሕበራዊ ሚዲያ አጠቃቀማችን፣ በመረጃ አፈላለጋችን፣ በፖለቲካችን፣ በትምህርታችን፣ በኢኮኖሚያችን፣ በምርምራችን፣ በግብርናችን፣ በማዕድን ፍለጋና ልማታችን፣ በአገልግሎት አሰጣጣችን፣ ወዘተረፈ እሱ በዚያ አለ። ለሰው ልጅ በርካታ ትሩፋት ይዞ የመጣ ቢሆንም ስጋት መደቀኑ አልቀረም።

የሰው ሰራሽ ክሕሎት በዚህ ከቀጠለና ያለ ሰዎች ጣልቃ ገብነትና ተሳትፎ ራሱን ችሎ መንቀሳቀስ ከጀመረ የሰውን ልጅ ከምድረ ገጽ ሊያጠፋ ይችላል የሚል ስጋት እየፈጠረ ነው። የArtficial Intelligence AI ጉዳይ ብርቱ ጥንቃቄ ይጠይቃል ይሉናል በጎግል የሰው ሰራሽ ክሕሎት ቤተ ሙከራ የዲፕማይንድ ዋና ስራ አስፈጻሚ ዴሚስ ሀሳቢስ። ብዙዎቹ በAI ላይ ሙከራ እያደረጉ ያሉ ተመራማሪዎች እጃቸው ውስጥ የገባው ቴክኖሎጂ እጅግ አደገኛ መሆኑን በቅጡ የተገነዘቡ አይመስሉም ይላሉ ዋና ስራ አስፈጻሚው። በዘረ አዳም ሕልውና ላይ አደጋ ስለደቀነው የሰው ሰራሽ አስተውሎት ከተለያዩ ምንጮች ያጠናቀርሁትን መረጃ እንዲህ ላጋራችሁ ወደድሁ።

Artficial Intelligence ወይም AI ግስጋሴ በሰው ልጆች ሕልውና ላይ የደቀነው አደጋ፤ ክፉኛ ያሳሰባቸውና ያስጨነቃቸው ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ለ6 ወር እንዲቆም በግልጽ ደብዳቤ መጠየቃቸው የዚያ ሰሞን መነጋገሪ ነበር። ኤለን መስክን ጨምሮ የAI አባቶች በመባል የሚታወቁ ከ1100 በላይ የዘርፉ ጉምቱ ሊቃውንት በፉክክርና በውድድር፤ እየተለቀቁ ያሉ የAI ግኝቶች በዚሁ ከቀጠሉ በሰብአዊ ፍጡር ላይ አደጋ ሊደቅኑ ስለሚችሉ እንዲቆሙ መንግስትንም ኩባንዎችንም ተማጽነዋል።

ተማጽኖው የመጣው ጉግልና ማይክሮሶፍት ራሱን ችሎ የሚሰራ ሰው ሰራሽ አስተውሎት ከለቀቁ በኋላ ነው ይለናል የእንግሊዙ ዜና አገልግሎት ሮይተርስ። በግልጽ ደብዳቤ እንዲቆም ከጠየቁት መካከል የStability AI ዋና ስራ አስፈጻሚ ኤማድ ሞስታ፤ ዮሹዋ ቤንጊዎ፣ ስቱዋርት ሩሶ፣ የአፕል መስራች ስቲቭ ወዚናክ ሌሎች ኢንዱስትሪው ላይ የሚሰሩ ጉምቱዎች፤ ሰው ሰራሽ አስተውሎት ፈጣሪዎቹን ጨምሮ ማንም ሊቆጣጠረው፣ ሊረዳውና ሊተነብየው የማይችል አደጋ በሰው ዘር ላይ ስለደቀነ እንዲቆም ተማጽነዋል። ሲቆም ደግሞ የዘርፉን ተዋናዮችን ያሳተፈ፣ ለሕዝብ ግልጽ የሚሆንና ክትትል የሚደረግበት ሊሆን ይገባል ሲሉ ያስጠነቅቃሉ።

ፈጠራ ሰዋዊ ነው። የሰው ልጅ ላለፉት 300,000 ዓመታት ከሌሎች ፍጥረታት በተለየ ኪነ ጥበባዊ ስራዎችን፣ የምግብ አሰራር ዘዴዎችን፣ የፖለቲካ ማኒፌስቶዎችን፣ ማሕበረሰቦችን፤ ባጠቃላይ ያልነበሩ አዳዲስ ነገሮችን ፈጥሯል ይሉናል አንድሪው ቾውና ቢሊ ፔሪጎ በጋራ በTIME መጽሔት ባስነበቡን መጣጥፍ። በዚህ ቅጽበት እንኳ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ወይም Artificial Intelligence/AI/፤ ሰዓሊውን ተክቶ ረቂቅና ውብ ስዕሎችን እየሳለ፣ ሰዎችን ሆኖ በኢሜል መልስ እየሰጠ፣ ሙዚቀኛውን ሆኖ ሙዚቃን እየቀረጸ ነው።

ወይም ዋና ስራ አስፈጻሚውን ተክቶ ስለ ኩባንያው የዕቅድ አፈጻጸም ለታዳሚው ገለጻ እያደረገ፤ አልያም በኮምፒውተር ኮድ የተፈጠረ ስህተትን ለይቶ መፍትሔ እየሰጠ፤ የሕንጻ ግንባታ ንድፍ እያዘጋጀ፤ ተማሪውን ተክቶ እየተፈተነ፤ ጋዜጠኛውን ተክቶ መጣጥፍ እየጻፈ፤ ለሕመምተኛው የጤና ምክር እየሰጠ፤ ተከሳሹን ተክቶ ጥብቅና ቆሞ ሊሆን ይችላል።

ምን አደከማችሁ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ያልገባበት የሕይወት ቅንጣት የለም ማለት ይቻላል። የመድሀኒትንና የቤት ዋጋን ከማውጣት አንስቶ እስከ መኪና መገጣጠምና በማሕበራዊ ሚዲያ የምንመለከተውን ማስታወቂያ እስከ መወሰን ደርሷል። በዚህ ተገርመን ሳናበቃ አዲስ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ወይም Generative AI ወደ ስራ እየገባ ነው ይሉናል እነ አንድሪው በጹሑፋቸው።

ይሄኛው አስተውሎት ጥራትና ጥልቀት ያለው አዲስ ጹሑፍ፣ ምስልና ድምጽ መፍጠር የሚችል ነው። አዲሱ የሰው ሰራሽ ክህሎት ወይም Gener­ative AI ማሕበራዊ ሚዲያ ጥቅም ላይ ከዋለበት ጊዜ አንስቶ አስገራሚው ቴክኖሎጂያዊ ግኝት ወይም እምርታ ነው። የዚህ ግኝት አካል የሆነው ChatGPT የተሰኘው የደረ ገጽ ማፈላለጊያ ወይም ሰርች ኤንጅን ለምንጠይቀው ነገር ሁሉ ምላሽ መስጠት የሚችል ሰው ሰራሽ አስተውሎት ነው።

ሌላው አዲሱ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ወይም Dall-E የምናልመውንና የምንመኘውን ስዕል መሳል የሚችል ነው። በተለይ ChatGPT ባለፈው ጥር ስራ ላይ ከመዋሉ ከ100 ሚሊየን በላይ ተጠቃሚዎችን በማፍራት፤ ኢንስታግራምና ቲክቶክ ይዘውት የነበረውን ክብረ ወሰን ሰብሯል። በየቀኑ 13 ሚሊየን ደንበኞች እየተጠቀሙበት ይገኛል። በመቶዎች የሚቆጠሩ አዳዲስ እንደ ChatGPT ያሉ የሰው ሰራሽ አስተውሎቶች ወደ ገበያው ለመግባትና ተጠቃሚዎችን ለማፍራት የሞት ሽረት ፉክክር ላይ ተጠምደዋል። ከMidjourney እስከ Stable Diffusion እና GitHub’s Copilot ውድድር ላይ ናቸው ይሉናል የመጽሔቱ ጸሐፊዎች።

ሻሎም ! አሜን።

በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)

አዲስ ዘመን   ኅዳር 20 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You