የሀገር ፍቅርን በስራቸው የገለጹት የቴሌኮሙ ሰው

በዓለማችን ላይ በአሁን ሰዓት የምናስተውላቸውን ለውጦች አዲስ የፈጠራ ሀሳብ ባመጡ የፈጠራ ባለቤቶች ብቻ ሳይሆን እነዚህን የፈጠራ ውጤቶች ደፍረው ለመጀመሪያ ጊዜ የሞከሯቸውና እውቅና የሰጧቸው ሰዎች ለዓለም መቀየር ትልቁን ድርሻ ይወስዳሉ። ነገር ግን የለውጥ ሂደት መነሻው ሀሳብ በመሆኑ ከተለመደው አስተሳሰብና አኗኗር ለየት ብለው ለምን ብለው የጠየቁ ሰዎችን መርሳት አይገባም ።

መጋቢት ሁለት 1928 ዓ.ም በጥንታዊቷ አንኮበር ከተማ አፈርባይኔ በተባለች መንደር ተወለዱ። የተወለዱበት ወቅት ጣልያን ኢትዮጵያን የወረረበትና ወደ አንኮበር የተጠጋበት ጊዜ ነበር። የሚኒልክ ቤተመንግስት የሚገኘው ደግሞ በዚሁ በአንኮበር ሲሆን በዚያ የነበሩ አርበኞችም ቤተመንግስቱን እየጠበቁ ይዋጉ ነበር። የጣልያን ጦር ወደ ከተማዋ ተጠግቶ የመሳሪያ ድምፅ ሲሰማ የአጼ ሚኒልክን ቤተመንግስት እንዳልነበር ሲያደርገው በስፍራው የነበሩ ጎጆ ቤቶችም ሲቃጠሉ በአካባቢው የነበሩ ነዋሪዎችም ራሳቸውን ለማዳን ከቦታው መሸሽ ጀመሩ። ወይዘሮ አስካለ ማርያም የአራስ ቤት ልጃቸውን ይዘው ከቦታው ሸሹ። በማግስቱ ነገሩ ሲረጋጋ የተረፈውም ሰው ወደቀዬው ሲመለስ ሕጻኑና ወይዘሮ አስካለ የደረሱበት አልታወቀም። ሞተዋል ተብሎ ለቅሶ ይጀመራል። ባለቤታቸው እምሩ ራስወርቅም ወዲያና ወዲህ እያሉ ፈልጉልኝ በማለት ተጨንቀዋል። ሰዓቱ ረፈድፈድ ሲል ሁሉም ወደ ነበረበት ተመልሶ ሁካታው ጋብ ሲል እናት አራስ ልጃቸውን በጉያቸው አቅፈው ወደመንደራቸው ተመለሱ። በሕይወት በመገኘታቸውም እልልታ ሆነ። መምህር ራስወርቅም ልጄ ተረፈልኝ ብለው እግዚአብሔርን አመስግነው የልጃቸውን ስም ተረፈ ብለው ሰየሙት።

የተረፈ አባት በሙያቸው የተለያዩ መጽሀፍትን ይጽፉ የነበረ፣ በቤተክህነት ውስጥ የሚያገለግሉ ሰው ነበሩ። ከዚህም ሌላ አባታቸው ራስወርቅ የተለያዩ መጽሀፎችን የማሸግ ስራ የሚሰሩ ሲሆን ከጣልያን ወረራ በኋላ ትንሳኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤትን አቋቁመዋል። በተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤትም የመጀመሪያው መምህር ነበሩ።

ጣልያን በኢትዮጵያ ላይ ያደረገው ወረራ ተረፈን ገና ከልጅነት ጊዜያቸው ጀምሮ ሲፈትናቸው፤ አባታቸውም ሆኑ ወንድሞቻቸውም ለሀገራቸውም ትልቅ መስዋዕትነትን የከፈሉ ናቸው። ጣልያን በኢትዮጵያ ለአምስት ዓመት ሲቆይ የተረፈ አባት ሚናቸው ሁለት ነበር። አንድም የቤተክርስትያን አገልጋይ አንድም ደግሞ በአንኮበር የነበሩ አርበኞችን በድብቅ ማገዝ። በዚህ ስራቸው ያግዟቸው የነበሩት የተረፈ ታላቅ ወንድም ጥሩነህ ራስወርቅ ናቸው። እሳቸው በተፈሪ መኮንን ት/ቤት ሳሉ የፈረንሳይኛ ቋንቋን ለምደው ነበርና ወደ አንኮበር ተጉዘው በዚያ ሰፍሮ የነበረውን ከፍተኛ ቁጥር ያለው የጣልያን ጦር በመጠጋት የታቀደውን እና የተደረገውን ለአባታቸው በመናገር እንደ ውስጥ አርበኛ ሆነው አገልግለዋል።

ሌላኛው ወንድማቸው ሜጄር ዮሀንስ ራስወርቅ ሲሆኑ በጊዜው ጣልያን ኢትዮጵያ ላይ የምታደርሰውን ግፍ ለመቃወም ንጉሰነገስቱ ወደ ጄኔቭ ሲያመሩ ዮሀንስና አጋሮቻቸው በሀገር ውስጥ ትልቅ ተጋድሎ ፈጽመዋል። በአንድ አጋጣሚም ሜጄር ዮሃንስ ከሌሎች አለቆች ጋር ጦራቸውን ለማጠናከር ሲሰባሰቡ በድንገት በጣልያን ጦር ከበባ ስር ወደቁ። ወደ አዲስ አበባ አምጥተዋቸውም እንዲተባበሯቸው ጠየቋቸው የቁም እስረኛ አድርገውም አስቀመጧቸው። በዚያን ወቅትም በየካቲት 12 1934 ዓ.ም ግራዚያኒ ላይ በተደረገው የግድያ ሙከራ በኢትዮጵያውያን ላይ በደረሰው ግፍ ውስጥ እጃቸው አለበት በሚል ሜጀር ዮሀንስ ላይ ሞት ፈረዱባቸው።

ኢንጂኒየር ተረፈ ከካህንና መምህር አባት እንደመገኘታቸው በልጅነታቸው ከአባታቸው እግር ስር ፊደልን ቆጥረዋል። በ1933 ዓ.ም ቤተሰቦቻቸው ወደ አዲስ አበባ ሲመጡ በቄስ ትምህርት ቤት ገብቶ ዳዊትን ደግመዋል። በዳግማዊ ሚኒልክ ትምህርት ቤት ቀጥሎም ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት በመግባት ትምህርታቸውን ቀጥለዋል። ተፈሪ መኮንን በዘመኑ በሀገሪቱ ትልቅ ከሚባሉት ትምህርት ቤቶች ውስጥ አንዱ ነበር። ከአንድ ሺህ በላይ ተማሪዎች የሚማሩበት ሲሆን የንጉሠ ነገሥቱ ቤተ መንግሥት ቅርብ ስለነበር ጃንሆይ በየጊዜው ትምህርትቤቱን ይጎበኙ ነበር። ይህም ዘወትራዊ ጉብኝት ተማሪዎቹንና መምህራኑን ያስደስታቸውና ያበረታታቸው ነበር።

በሕይወት ዘመናቸው ለነበራቸው በጎ ስብዕናና የቀናነት መንፈስ በትምህርትቤታቸው ውስጥ የነበረው የስካውት ቡድን መርህ በእጅጉ እንደረዳቸውና ሕይወታቸውን ሙሉ ሲከተሉት እንደነበር በነበራቸው ቃለመጠይቅ ተናግረዋል። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ከጨረሱ በኋላ በቀዳማዊ ኃይለስላሴ ዩኒቨርሲቲ ለመግባት ቻሉ። በመጀመሪያው የትምህርት ዓመትም የነበራቸው ውጤት በብዙዎች ዘንድ መነጋገሪያ ሲሆን ለወጣቱ ተረፈ ደግሞ በእችላለሁ መንፈስ በላቀ ውጤት እንዲቀጥሉ አድርጓቸዋል። ከትምህርት ባሻገርም በዩኒቨርሲቲ ውስጥ በርካታ ስራዎች ላይ መሳተፋቸውን ቀጠሉ። በተሳትፏቸውም ከንጉሰነገስቱ ሙገሳን አግኝተዋል።

በ1950 ዓ.ም ለተሻለ ትምህርት ከተመረጡ ሌሎች ተማሪዎች ጋር ወደ ኒውዮርክ አሜሪካ አቀኑ። ኢንጂኒየር ተረፈ የመረጡት የትምህርት ክፍል የኤሌክትሪክ ምህንድስና ነበር። በሚማሩበት ትምህርትቤት ውስጥ ጥቂት ጥቁሮች ብቻ ሲኖሩ በመረጡት ትምህርት ክፍል ውስጥ ከጓደኛቸው ማህዲ መሀመድ በቀር ሌላ ጥቁር አልነበረም። ተረፈና ጓደኛው በክፍሉ ውስጥ በጊዜ ተገኝተው ሲቀመጡ ከነሱ በኋላ የሚመጡት ነጭ ተማሪዎች በፍፁም በአጠገባቸው አይቀመጡም ነበር። ሁለቱ ተማሪዎች ለዚህ መፍትሄ ያደረጉት ተማሪዎች ገብተው ካለቁ በኋላ መሄድን ነበር። ይህ ከትምህርቱ በላይ በጣም ከባድ ነበር። የኢንጂኒየሩ ጓደኛ ማህዲ ወደ ጂኦሎጂ የትምህርት ክፍል ሲቀይር ኢንጂኒየር ተረፈ ብቻቸውን ሆኑ። መምህሩ በክፍሉ ውስጥ የሚሰጡትን የቡድን ስራ አብሯቸው ለመስራት የሚፈልግ ነጭ አልነበረም። ሌሎች በቀኝ ግዛት ተይዘው የነበሩ ሀገራት በእንደዚህ አይነት ጫና ውስጥ ሲወድቁ አንገታቸውን ይደፋሉ። ወጣቱ ግን ይህ ታሪክ በዘመናቸው አልነበረምና ለመቀበል ፍቃደኛ አልነበሩም። ታሪካቸውን ማንነታቸውን ማወቃቸውም የመንፈስ ጥንካሬ አሳድሮባቸዋል። በመሆኑም በገፏቸው ቁጥር ጠንክረው በመማር በትምህርታቸው ውጤታማ ለመሆን ችለዋል።

ኢንጂኒየር ተረፈ ትምህርታቸውን እንደጨረሱ በተማሩበት ሀገር በትልልቅ ኩባንያዎች ውስጥ የመስራት እድል ጠቀም ካለ ክፍያ ጋር ቀርቦላቸው ነበር። ነገር ግን ኢንጂኒየሩ ፍቃደኛ አልነበሩም ምክንያታቸው ደግሞ ለውጭ ሀገር የትምህርት እድል ተመርጠው የስንብት ፕሮግራም ሲደረግላቸው ጃንሆይ ያሏቸው በልባቸው ቀርቶ ነበር። ‹‹ የተማረ የሰው ኃይል ያስፈልገናል እናንተ ውጪ ሀገር የምትሄዱት ትምህርት ቀስማችሁ ሀገራችሁን እንድታገለግሉ ነው። ሀገራችሁ ትጠብቃችኋለች እንደጨረሳችሁ ተመልሳችሁ ኑ ›› የሚል ንግግር ነበር። በዚያ የወጣትነት እድሜ ላይ ከንጉሰ ነገስቱ አንደበት ለሀገር ትጠቅማላችሁ መባል ትልቅ ነገር በመሆኑ በጊዜው ወደ ውጭ ሀገር የሄዱ ተማሪዎችም ትምህርታቸውን እንደጨረሱ ወደ ሀገራቸው መመለስን ነበር የሚያስቡት።

ትምህርታቸውን ጨርሰው ወደ ሀገራቸው ሲመለሱ ስራቸውን የጀመሩት በቴሌኮሙኒኬሽን ቦርድ ውስጥ ነበር። ለመጀመሪያ ጊዜ የተመደቡበት የትራንስሚሽንና የረጅም ርቀት ስርጭት ክፍል ነበር። በጊዜው ገና የ25 ዓመት ወጣት ቢሆኑም የእድሜ ማነስ ሳይገድባቸው ስራቸውን በጥልቅ ማስተዋል ሰርተዋል።

በወቅቱ የፋክስ ግንኙነት ባለመኖሩ የመልዕክት ልውውጥ የሚደረገው በቴሌግራፍ ነበር። ይህ የቴሌግራፍ የመልዕክት ልውውጥ የሚደረገው በላቲን ፊደላት ነበር። በዓለም ላይ የራሳቸው ፊደላት ያላቸው ሀገራት ውስን ሲሆኑ ከአፍሪካ ደግሞ ኢትዮጵያ የራሷ ፊደል ያላት ብቸኛዋ ሀገር ናት። ነገር ግን ለመልዕክት ልውውጥ የምትጠቀመው የላቲን ፊደልን ነበር። ይህ ለሀገር ወዳዱ ኢንጂኒየር በቀላሉ የሚታለፍ አልሆነም የራሳችንን ፊደል ለምን አንጠቀምም ሲሉ ጠየቁ የተሰጣቸውን ምክንያትም በቂ ሆኖ አላገኙትም። የመከራከሪያ ነጥቡ የነበረው የኢትዮጵያ ፊደላት ቁጥር ከላቲን ፊደላት ቁጥር መብለጡ ቴሌፕሪንተሮቹ የተፈጠሩት ለላቲን ፊደላት ነው የሚል ነበር። ኢንጂኒየሩም የኢትዮጵያ ፊደላትን እንዴት ቴሌፕሪንተር ውስጥ ማስገባት እንደሚቻል በሆሄያቱ ላይ ልዩ ጥናት አደረጉ።

ጥናታቸውን ሲጨርሱም በወረቀት የሰፈረው ንድፈ ሀሳብ ሲመንስ ለተባለ የጀርመን ኩባንያ ተላከ። ኢንጂኒየር ተረፈም ወደ ጀርመን ሄደው በቴሌፕሪንተሩ ላይ የፊደላቱን አቀማመጥ ልክ መሆኑን ካረጋገጡ በኋላ በኢትዮጵያዊው ወጣት የተሰራ የመጀመሪያው ቴሌፕሪንተር ይፋ ሆነ። ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴም ቴሌፕሪንተሩን መርቀው በከፈቱበት እለት አንዱ ቴሌፕሪንተር በአሥመራ ቤተ-መንግስት አንደኛው አዲስ አበባ ተቀመጠ። በወቅቱ የኤርትራው ገዢ የነበሩት ራስ አስራተ ካሳ በአዲሱ ቴሌፕሪንተር መልዕክታቸውን በአማርኛ ፊደላት ሲልኩ ግርማዊነታቸው መልዕክቱን አይተው የደስታ ስሜታቸውን መደበቅ አልተቻላቸውም ነበር።

ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ኢንጂኒየሩ ለሰሩት ስራ በጊዜው የነበሩትን ስራ አስኪያጅ ምን አድርጋችሁለታል ሲሉ ቢጠይቁም ‹‹ አስፈላጊው ተደርጎለታል ›› ሲሉ መለሱ፤ ነገር ግን ወጣቱ ኢንጂኒየር ተረፈ ራስወርቅ ምንም ጥቅም አላገኙም ነበር። ኢንጂኒየሩም ስለዚህ ጉዳይ አንስተው ለመጠየቅ ፍላጎት አልነበራቸውም። ነገር ግን በአእምሮኣዊ ንብረት የባለቤትነት መብታቸው እንዲጠበቅ አድርገዋል። ኢንጂኒየር ተረፈ ራስወርቅ ይህንን የኢትዮጵያ ፊደል የያዘ ቴሌፕሪንተር ለመስራት ባደረጉት ጥናት ሀሁ በቀላሉ የሚል ፊደላትን በቀላሉ ለመማር የሚያስችል መማሪያ መጽሀፍም አዘጋጅተዋል።

የዓለም አቀፍ የቴሌኮምኒኬሽን አንድነት በ1865 ዓ.ም ተቋቁሞ መቀመጫውን ጄኔቭ ያደረገ ትልቅ ድርጅት ነው። ይህን ድርጅት ኢንጂኒየሩ በተቀላቀሉበት ዘመን ሕብረቱ የአፍሪካ ክፍልን የሚመራ ባለሙያ በመፈለግ ለአባል ሀገራቱ ክፍት ቦታ መኖሩን አሳወቀ። ኢንጂኒየር ተረፈም ከተወዳዳሪዎቹ አንዱ ሆነው የትምህርት ሁኔታቸውና የሰሩት ስራ ሁሉ በሚገባ ታይቶ የሕብረቱ ባልደረባ ለመሆን ቻሉ። ከዚያም በዓለም አቀፍ የቴሌኮምኒኬሽን ሕብረት የአፍሪካ ጉዳይ ክፍል ውስጥ ስራቸውን ጀመሩ። የተመደቡበት ክፍል ስራ አፍሪካ በቴሌኮም ዘርፍ እድገት እንድታመጣ ማስቻል ነው። በሕብረቱ ውስጥ የአፍሪካ ጉዳዮች ኃላፊ ሆነው በሰሩባቸው ዓመታት የአፍሪካን የቴሌኮም ዕድገት እውን ለማድረግ ልክ እንደሁልግዜው መስራት ጀመሩ። የመጀመሪያው የሕብረቱ ቀዳሚ ተግባር የቴሌኮምኒኬሽን ማሰልጠኛዎችን በየሀገሩ መመስረት ነበር።

ኢንጂኒየር ተረፈ ራስወርቅ አንዳንድ የአፍሪካ አገራት ነፃነታቸውን ካገኙ በኋላም የስልክ መገናኛ መስመራቸው ከድሮ ቀኝ ገዢ ሀገራት ጋር ስለነበረ መስመሩን የሚያስተላልፉት በብራስልስ፣ በፓሪስ፣ በለንደንና በሮም በኩል በመሆኑ ቀኝ ገዢዎቹ መረጃውንም ይጠቀሙበት ነበር። የኢንጂኒየር ተረፈ ራስወርቅ ትልቁ ስኬት የነበረው የቀኝ ግዛት መስመርን መስበር መቻላቸው ነበር።

በመስሪያቤቱ በነበራቸው ቆይታ የበርካታ ሀገራትን የቴሌኮም የእድገት ደረጃ ለመለየት ችለዋል። በእርሳቸው የስራ ዘመን የቻይና ቴሌኮምኒኬሽን ከኢትዮጵያም ያነሰ በመሆኑ ቻይና እና ጃፓን አሁን ላሉበት የቴሌኮሙኒኬሽን ኢንደስትሪ ትልቅ አስተዋፅኦ ካደረጉ የሕብረቱ ሰዎች ውስጥ ይጠቀሳሉ። በኢትዮጵያ ውስጥ በቴሌው ዘርፍ ብዙ መሠራቱን ያምኑበታል። በዓለም አቀፍ የቴሌኮም ዘርፍ ባለሙያዎች ዘንድ ትልቅ ከበሬታን አግኝተዋል። ኑሯቸውንም ስራቸውንም በጄኔቭ አንድ ብለው የጀመሩት የስራ ዘመንም ለ40 ዓመታት ያህል ዘልቋል።

ኢንጂኒየር ተረፈ ራስወርቅ ትዳር የመሰረቱት በ1954 ዓ.ም ሲሆን ከወይዘሮ ብርሀኔ አስፋው ጋር ከ50 ዓመታት በዘለቀ ትዳራቸው መተሳሰብ መደጋገፍና ፍቅር የሚታይበት ነበር። በትዳራቸው ሶስት ልጆችን አፍርተዋል። ኢንጂኒየር ተረፈ ራስወርቅ አብዛኛውን የስራ ሕይወታቸውን ከሀገራቸው ውጪ ስላሳለፉ ልጆቻቸውም የተወለዱት ከሀገር ርቀው ነበር። በዚህም ስለ ሀገራቸው ያላቸው ቦታ እና እይታ እንዳይቀንስ ኃላፊነት የሚሰማቸው ሀገራቸውንና ማንነታቸውን እንዲያውቁ አድርገው አሳድገዋቸዋል። ልጆቻቸውም በተሰማሩበት የስራ ዘርፍ ሀገራቸውን በበጎ ለማገልገል እየሰሩ ሲሆን በስማቸው የተሰየመ ፋውንዴሽንና የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሽልማትን መስርተው ሳይንስና ቴክኖሎጂ ነክ ፈጠራዎች በኢትዮጵያ እንዲበረታቱ ያደርጋሉ። በተጨማሪም የኢንጂኒየር ተረፈ ፈጠራ የሆነውን የመጀመሪያውን ቴሌፕሪንተር የሀገር ሀብት ነው በማለት ለኢትዮጵያ ቅርስና ጥበቃ ባለስልጣን አበርክተዋል። በርክክቡ ወቅትም ቴሌፕሪንተሩ በሙዚዬም ውስጥ ከሚገኙ ውስን የኢትዮጵያን የቴክኖሊጂ ጉዞ የሚያሳይ ቅርስ መሆኑ ተጠቅሷል።

ኢንጂኒየር ተረፈ ራስወርቅ የስራ ጊዜያቸውን ጨርሰው ጡረታ በወጡበት ጊዜም ልረፍ ብለው ሳይቀመጡ ወደ ተወለዱባት አንኮበር ከተማ ተመልሰው ታሪካዊነቱን በሚመጥን መልኩ ከእህታቸው ልጅ ኃይለ ገብርኤል ዳኜ (ዶ/ር) ጋር በመሆን አምባ ኤኮቱሪዝም ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር በማቋቋም ፋሺሽት ጣሊያን ኢትዮጵያን በ1928 ዓ.ም. በወረረ ጊዜ በጦር አውሮፕላን ያወደመውን የአፄ ምኒልክ ሕንፃ በባሕላዊ መንገድ እንደገና ከማሠራታቸውም ባሻገር በዙሪያው የነበሩትን የሹማምንቱን መኖሪያ ቤቶችን በጥንቱ አሠራር እንደገና በመገንባት የእንግዶች መኝታ ቤቶች በተለየ መልኩ ሎጅ በመስራት አንኮበር በድጋሚ ለቱሪስቶች ምቹ እንድትሆን አድርገዋል። የስራ ጉዟቸውን ሕይወታቸውን የሚዳስስ ‹‹የአንኮበሩ ሰው በጄኔቫ›› የሚል መጽሀፍም አሳትመዋል።

ላመኑበት ጉዳይ እስከመጨረሻው ቆመው ያሰቡትን የሚያሳኩ፤ ለሀገራቸው የነበራቸውን ፍቅር በሕይወት ዘመናቸው በስራዎቻቸው ውስጥ የገለጡት እኚህ የሀገር ባለውለታ በተወለዱ በ86 ዓመታቸው ሚያዝያ 30 ቀን 2014 ዓ.ም አጥተናቸዋል። ስማቸውም በሰሩት ስራ ሁል ጊዜ ሲወሳ ይኖራል።

ሰሚራ በርሀ

አዲስ ዘመን   ኅዳር 19 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You