ከእኛ አልፈን ለልጆቻችን ተስፋ የምትሆን ሀገር እንስራ !

በኢትዮጵያ የሀገረ መንግሥት ግንባታ ጉዞ ብዙ ታሪካዊ ሁነቶች ተስተናግደዋል። እነዚህ ታሪካዊ ሁነቶች በክፉም በደጉም ሊነሱ የሚችሉ ናቸው። ይህ ደግሞ ትናንት የተገነቡባቸው ሁነቶች/ታሪኮች ባህሪ ነው። ይህንን እውነታ በበቂ ሁኔታ ለትውልዶች ማስገንዘብ ባለመቻላችን በብዙ ፈተናዎች እየተፈተንን ነው።

በእርግጥም የሀገራችን አብዛኛው የታሪክ ትርክት በጦርነት ላይ የተመሠረተ ነው። ይህም በመሆኑ ለከፋ ድህነትና ኋላ ቀርነት ተዳርገናል። እንኳን ከእኩዮቻችን ከታናናሾቿም አንሳ ዘመናት አስቆጥረናል። በየዘመኑም ከዚህ የችግር አዙሪት የምንወጣባቸውን የተለያዩ ዕድል እና መልካም አጋጣሚዎችን መጠቀም ሳንችል ቀርተን አሳልፈናል።

ከ1953 ዓ.ም መፈንቅለ መንግሥት ጀምሮ የ1966ቱ አብዮት፣ የ1983ቱ የኢህአዴግ ድል፣ የ1997ቱ ምርጫ፣ የ2010 ለውጥ እንደመልካም አጋጣሚ ሊቆጠሩ የሚችሉ ናቸው። እስከ 1997 ድረስ ያሉትን ላንመልሳቸው ያባከንናቸው መልካም አጋጣሚዎች ነበሩ፤ የአሁንም ቢሆን በብዙ ፈተናዎች እየተናጠ ነው።

የ1966 ሶሻሊዝም፣ የ1983 የብሔር ፌዴራሊዝም ሕዝብ ሳይመክርበትና ሳያስብበት በጊዜው በነበሩ መንግሥታት የተጫኑ ርዕዮቶች ናቸው። ሀገርና ሕዝብን ያልተገቡ ብዙ ዋጋዎችን ከማስከፈል ባለፈ፤ ዘላቂ ሀገራዊ ሰላምና ልማትን በማስቀጠል ሕዝባችንን ከሚፈልገው የብልጽግና ጎዳና ሊወስዱት አልቻሉም።

በአንድ ወቅት ዮሴፍ ወርቁ ደግፌ የተባለ ጸሐፊ «ቤት በጥበብ ይሠራል በማስተዋልም ይጸናል» በሚል ርዕስ በፃፈው መጣጥፍ፤ «ኢትዮጵያውያን በትንሹም ይሁን በትልቁ በማንኛውም ሀገራዊ ጉዳዮቻችን ላይ ዘወትር በከፋ የአለመግባባት ልዩነት (ቅራኔ) ውስጥ ስለምንገባ፤ በኅብረት (በአንድነት) ለመሥራት ፈፅሞ አለመቻላችን ከመጥፎ ሰብእና (ባህርይ ችግር) ወደ መጥፎ ፖለቲካ ባህልነት እየተቀየረ መጥቷል» ይላል።

«የኢትዮጵያ ሕዝብ ለሺህ አመታት የዘለቁ ታላላቅ ቀደምት ሃይማኖቶች ተከታይ እንደመሆኑ፤ ከእኛ በላይ በጥሩ ሥነ ምግባር የታነጸና ደግሞም ባለታሪክ ሕዝብ በዓለም ላይ የሚገኝ አይመስለንም።

«ነገር ግን እንደታሪካችን ጥንታዊነትና የቆየ ሃይማኖተኛነታችን ሳይሆን፤ ትናንት ነፃነታቸውን ካገኙ ሀገሮች ጋር ስንወዳደር እንኳን ያለማደጋችን ምስጢር የእኛን የባህርይ ችግር የሚያጋልጥ ነው።

«ነፃነታቸውን ካገኙ ሃምሳ አመት ያልሞላቸው ሀገሮች ከሞላ ጎደል በአጭር ጊዜያት ውስጥ ሠርተው ለውጥ ሲያመጡ፣ እኛ ሺ አመታት ቀደምት ብንሆንም ተስማምተን በጋራ ለመሥራት ባለመቻላችን ብቻ፣ በሚጠበቅብን ደረጃ ማደግ እንዳልቻልን» አትቷል።

በርግጥ በቀደምት ሀገራዊ ትርክቶች ላይ አለመግባባቶች የመኖራችን ያህል እንደ ሀገር ለሺ አመታት አብረን እንድንዘልቅ ያደረጉን፤ የጋራ ፖለቲካዊ ፤ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እሴቶች እንዳሉን መካድ የሚቻል አይደለም። ባህላዊና መንፈሳዊ እሴቶች እንደምንጋራም አፍን ሞልቶ ለመናገር የሚከብድ አይደለም።

በአብዛኛውን የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት አሁን አሁን እየተፈጠሩ ያሉ አለመግባባቶች፤ ሥራዬ ተብለው በሚከወኑ የተዛቡ ትርክቶች የመዋጣቸው እውነታ እንደ ሀገር ለሀገረ መንግሥቱ ሆነ ለብሔራዊ አንድነታችን ስጋት እየሆነ ከመጣ ውሎ አድሯል። ይህ በአብዛኛው በፖለቲካ ኢሌቱ፤ በአክቲቪስቱና በምሁሩ እየተቀነቀነ ያለው ልዩነቶችን አጉልቶ መስበክ፤ የጋራ በምንላቸው በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ባገኙ ብሔራዊ ማንነቶቻችን ዙሪያ ሳይቀር ልዩነቶች እንዲሰፉ የሚያስችል ክፍተት እየፈጠረ ነው።

ይህን ዓይነት ችግር የብሔራዊ አንድነት እና የሀገረ መንግሥት ስጋት በሚሆንበት ወቅት፣ ችግሩን ቁጭ ብሎ በሰላማዊ መንገድ በውይይት መፍታት ዘላቂ መፍትሔ እንደሚሆን ይታመናል። ለዚህም እንደ ሀገር ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን አቋቁመን ወደ ሥራ መግባታችን በብዙ መልኩ የሚበረታታ እና እውቅና ሊሰጠው የሚገባ ነው።

ምክክርና ውይይት በቦሲንያ ተፈጥሮ ለነበረው የእርስ በርስ ግጭት ዘላቂ መፍትሔ ለማስገኘት፣ በካምቦዲያና በቱኒዝያም ፤ ከሁሉም የከፋ የዘር ፍጅት ባስተናገደችው በሩዋንዳ ስኬታማ ውጤት አስገኝቷል። ‹‹እኔ ርዋንዳ ነኝ›› የሚለው ሕዝባዊ መፈክር ከርዋንዳ ጭፍጨፋ በኋላ የተፈጠረ ቢሆንም፣ መፈክሩ ዛሬም በርዋንዳውያን ልብ ውስጥ ፀንቶ ይገኛል።

ሀገራችን የዛሬዎቹን ሆነ ያደሩ ችግሯቿ ዘላቂ መፍትሔ ለማበጀት ያቋቋመችው ኮሚሽን አሁን ላይ የልዩነት አጀንዳዎችን ወደ ምክክር በማምጣት የጋራ ሀገራዊ እሴቶችን መፍጠር ዋነኛ ግቡ አድርጎ እየተንቀሳቀሰ ነው። ለግጭትና አለመረጋጋት ምክንያት በመሆን የፖለቲካ ሥርዓት ለውጦች ማምጣት ያስቻሉ ቅራኔዎችን በሠለጠነው የሃሳብ ውይይት ብቻ እንዲፈቱ እየሠራ ይገኛል።

ሀገራዊ የምክክር መድረኩ ችግሮቻችንን ለዘለቄታው ለመፍታት ትልቅ አቅም እና ዕድል ነው። በከፍተኛ ሁኔታ ሕዝብን በማሳተፍ ቀዳሚ ሊሆን የሚችል እንደሆነም እየተነገረ ነው። ከ16 በላይ ተቋማት በንቃት የሚሳተፉበት ከመሆኑ አንፃር ሁሉንም ኢትዮጵያዊ በአንድም በሌላም የማሳተፍ ዕድሉ ከፍተኛ ነው።

በተለይ አሁን ላይ በኃይል ሃሳብን በሌላው ላይ መጫን እንደ ሀገር ያለንን አቅም ከማዳከም ውጪ የሚያተርፈው ነገር አይኖርም። ከዚህ ይልቅ ልዩነቶችን በውይይት፣ በንግግር መፍታት እንደሀገር ሕዝባችን የሚሻውን ልማት እውን ለማድረግ ያለን አንድ አማራጭ እንደሆነ ከመቼውም ጊዜ ይልቅ መረዳት የቻልንበት ነው ።

የኢትዮጵያ ሀገር ምስረታ ከሌሎች የአፍሪካ ሀገሮች የተለየ ነው። ሌሎች ሀገራት አሁን ያላቸው ይዘትና ቅርፅ የያዙት በቀኝ ገዢዎች ነው። የእኛ የሀገረ መንግሥት ምስረታ ታሪክ ረጅም ዘመን ያስቆጠረና የየዘመኑን ዐሻራ የተሸከመ ነው። በዚህ የረጅም ዘመን ሀገረ መንግሥት ታሪክ ውስጥ በእውቀትም ያለ እውቀትም ሊነሱ የሚችሉ ጥያቄዎች ይኖራሉ። ጥሩም መጥፎም ሊባሉ የሚችሉ የታሪክ ክስተቶች ይኖራሉ።

እነዚህን ታሪካዊ እውነታዎች አስታርቆ መሄድ ዛሬዎቻችንን ብቻ ሳይሆን ነገዎቻችንን ብሩህ ለማድረግ ወሳኝ እንደሚሆን ይታመናል፣ የኮሚሽኑ አስፈላጊነት ሆነ ተልዕኮ የሚመነጨው ከዚህ ተጨባጭ እውነታ ነው። ትናንቶቻችንን ጎራ ለይተን ለማውገዝና ለመመረቅ ሳይሆን አውቀናቸው ከነሱ ለመማር ነው ።

የቀደሙት ታሪኮቻችን፤ «ብርሃማ ሆኑ ጨለማማ» ገፆቻችን ፤ የምንጋጭባቸው፣ የምንጣላባቸው፣ ዛሬዎቻችንን የምናባክንባቸው ሳይሆኑ፤ የምንማርባቸው ፣ የመማሪያ መጻሕፍቶቻችን ሊሆኑ ይገባል።

እዚህ ላይ /በብሔራዊ ውይይቶቻችን ወቅት / ትኩረት ልንሰጣቸው የሚገቡ መሠረታዊ ጉዳዮች አሉ። የመጀመሪያው ብሔራዊ የምክክር ኮሚሽኑ በአዋጅ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት ሁሉም ጥያቄዎች ወደ የውይይት መድረኩ እንዲመጡ ዕድል መስጠት አለበት። ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል አለኝ የሚለውን ጥያቄ ይዞ እንዲቀርብ ማስቻል ይተበቅበታል። በዚህ ሂደት አይነኬ የሚባል ጥያቄ ሊኖር አይገባም።

የሌሎች ሀገራት ተሞክሮ ለዚህ እውነታ ትኩረት የሰጠ ነው። የምክክር ሂደቶቹ ከፍተኛ እልቂት ለፈጠሩ አለመግባባቶች ሳይቀር መፍትሔ ማበጀት አስችሏል። በዚህም የታሪክ ሆነ የታሪክ ትርክት ለውጥ መፍጠር ችለዋል። የደቡብ አፍሪካን ተሞክሮ ማንሳት ይቻላል፤ ለብሔራዊ እርቅ የምክክርና የእርቅ ኮሚሽን አቋቁመው ሀገራቸውን ከፍ ካለ ጥፋት መታደግ ችለዋል። በትናንቱ ላይ ተወያይተው ነገዎቻቸውን ብሩህ በሚያደርጉ ዕድሎች ላይ ተወያይተው ወደፊት መራመድ ችለዋል።

በሀገራችንም በሥራ ላይ የሚገኘው ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ትውልዱን በመንታ መንገድ ላይ ያቆሙ፤ እስከ ዛሬም በሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ በተጨባጭ ዘላቂ መፍትሔ ማፈላለግ የሚያስችል አስቻይ ሁኔታ ይፈጥራል ተብሎ ይጠበቃል። የኮሚሽኑን ተልዕኮ በውጤት ለመደምደም ማኅበረሰቡ ተነጋግሮ ለመግባባት የተከፈተ አእምሮና ለይቅርታ የተከፈተ ልብ ያስፈልጋል።

የምክክር ኮሚሽኑ ሥራ እንዲሳካ የተለያዩ አካላት ኃላፊነት አለባቸው። ከእነዚህ አካላት መካከል በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሰው የመገናኛ ብዙሃን ናቸው። የመገናኛ ብዙሃን የመገንባትም ሆነ የማፍረስ ኃይላቸው ከፍ ያለ ነው። በተለይ አሁን ባለንበት 21ኛው መቶ ክፍለዘመን የኢንፎርሜሽን (የመረጃ ዘመን) በመሆኑ፤ ሕዝቡን ከተሳሳቱና ከተዛቡ መረጃዎች መታደግ ይጠበቅባቸዋል።

የምክከር ኮሚሽኑ ዓላማና ተልዕኮ ለሕዝብ ከማስረዳት ባለፈ፤ የምክክር ምንነትን አስፈላጊነትን በማስረዳት፣ ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት ያለውን ሁለንተናዊ ፋይዳ በማስገንዘብ ሙያዊ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ሊወጡ ይገባል።

መገናኛ ብዙሃኑ የማኅበረሰብ መሪዎች፣ የሃይማኖት አባቶችን፣ ምሁራንን በማነጋገር፣ የተለያዩ የኅብረተሰብ አካላትን በማሳተፍ፣ ጉዳዩ በማኅበረሰቡ ውስጥ ትኩረት እንዲያገኝ ማድረግ፤ ሀገሪቱ ያላት ተስፋ ተነጋግራ ችግሮችን መፍታት እንጂ ጦርነት ግጭት አለመሆኑን ማስተማር ይኖርባቸዋል ።

ሀገራዊ ምክክር የአዲስ ባህል ግንባታ አካል ተደርጎ የሚወሰድ፤ እንደሀገር መቀጠል ከፈለግን መነጋገርን፤ መመካከርን ባህል ማድረግ እንዳለብን የሚያመላክት ተጨባጭ ተሞክሮ ሊሆን የሚችል ነው። የምሁራን እና የምርምር ተቋማት ተሳጥፎም ወሳኝ ነው።

የሃይማኖት አባቶችም ለሀገር ብቻ ሳይሆን ለግለሰብ ሰላም ለመንፈሳዊ ሕይወቱ ካለው ሁለንተናዊ ፋይዳ አንጻር፤ የሰላምን አስፈላጊነት አበክረው ሊሰብኩ፤ ለዚህ ደግሞ ችግሮችን በንግግር በውይይት መፍታት ዋነኛ አቅም ስለመሆኑ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ሊያስተምሩ ያስፈልጋል፤ ይህ የሃይማኖታዊ ኃላፊነታቸው አካል ስለመሆንም በአግባቡ ተገንዝበው ሊንቀሳቀሱ ይገባል። አስፈላጊ ከሆነም አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ሃይማኖተኛ ከመሆኑ አንጻር በሀገራዊ አለመግባባቶች ዙሪያ ፀሎት እና ምልጃዎችን ማካሄድ፤ባለጉዳዮችን መምከርና መገሰፅ ይጠበቅባቸዋል።

በአጠቃላይ ለምክክር ኮሚሽኑ ስኬት ሁላችንም (ዜጎች) በጋራ ልንታገል ይገባል። በንቃት በመሳተፍ ዓላማውንም በመደገፍ ቁርሾአችንን በይቅርታ፤ ልዩነታችንን በሰጥቶ መቀበል መርህ ልንፈታ ታሪክም፣ ሕግም፣ ህልውናም ግድ የሚሉን ዘመን ላይ እንገኛለን። ይህንን ዕድል ካልተጠቀምን እንደሀገርም እንደሕዝብም የምንከፍለው መስዋዕትነት ከባድና ምናልባትም ከህልውናችን ጋር የተያያዘ ሊሆን ይችላል።

ሀገራችን ያለችበትን የፖለቲካ ትኩሳት በመረዳት፣ ካለፉት የጎደፈ ፖለቲካ ታሪካችን በመማር፣ የዓለም አቀፍ ተጨባጭ ሁኔታን ታሳቢ በማድረግ፣ የልዩነት ትርክቶችቻንን በማጥበብ፤ አሰባሳቢ ትርክቶች ላይ ትኩረት በማድረግ እንደ ትውልድ ተሻጋሪ ታሪክ ለመሥራት ራሳችንን ልናዘጋጅ ይገባል፤ ልዩነቶቻችንን ወደ ጠረጴዛ በማምጣት ተወያይተን ሀገራዊ እድገትን በጋራ የሚያራምድ የጋራ ብሔራዊ አጀንዳ ለመቅረፅ እንዘጋጅ።

የኮሚሽኑ ተልዕኮ ጥንታዊቷ ስመ ገናና ሀገራችንን ከጥፋት ከመታደግ ባለፈ፤ ወደ ቀደመ የታሪክ ከፍታዋ የመመለስ ተልዕኮ አካል በመሆኑ በሙሉ አቅማችን ተነጋግረን እና ተስማምተን ልንንቀሳቀስ ያስፈልጋል። በዚህም ከእኛ አልፈን ለልጆቻችን ተስፋ የምትሆን ሀገር እንስራ ።

ታሪኩ ዘለቀ

አዲስ ዘመን   ኅዳር 19 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You