መንግሥት ለአንድ ዓመት ከሚበጅተው በጀት ውስጥ 65 ከመቶ በላይ የሚሆነው ገንዘብ ለግዥ ይውላል። ይሁን እንጂ ይህን በጀት በአግባቡ ከመጠቀም አንጻር ውስንነት እንዳለ ይጠቀሳል። ከመንግሥት ግዥ አፈጻጸም ጋር በተያያዘ የሚስተዋለውን ከሕግ አግባብ ውጪ ግዥ መፈጸም እና ሌብነት፤ በተለይም በፌዴራል ተቋማት የሚስተዋለው በውስብስብ አሠራር የሚፈጸም ሌብነትና ብልሹ አሠራር መኖሩን ከዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት ሪፖርቶች መስማት የተለመደ ሆኗል።
ይህ ተግባር ደግሞ ምግባረ ብልሹ የሆኑ ግለሰቦችና ቡድኖች ባልተገባ መንገድ እንዲበለጽጉ፤ መንግሥት የሚበጅተው የሀገር ሀብት ለታለመለት ዓላማ እና ለሀገር ልማት እንዳይውል የሚያደርግ መሆኑ እሙን ነው። ይህንን ችግር ከመከላከል አኳያም በተለያዩ ጊዜያት የተለያዩ አሠራሮች የተሞከሩ ሲሆን፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ሥር የሰደደውን ችግር ለመቅረፍ ያስችላል የተባለለት የኤሌክትሮኒክስ የግዥ ሥርዓት ተግባራዊ መደረግ ጀምሯል።
ይህ እንደ ሀገር የተጀመረው የኤሌክትሮኒክስ የግዥ ሥርዓት ታዲያ በሁሉም የባለበጀት ተቋማት እንዲተገበር እየተሠራ መሆኑም ይታወቃል። እኛም በዛሬው የተጠየቅ ዓምድ ዕትማችን በዚህና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ በማተኮር፤ በተለይም አሠራሩ እየተስተዋለ ያለውን ስር የሰደደ ችግር በምን ያህል ደረጃ ያቃልለዋል? የሚለውን ነጥብ ማዕከል በማድረግ፤ የመንግሥት ግዥና ንብረት ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ከሆኑት አቶ ሐጂ ኢብሳ ጋር ቆይታ አድርገናል። መልካም ንባብ!
አዲስ ዘመን፡- እንደ ሀገር የመንግሥት የግዥ ሥርዓት ምን ደረጃ ላይ ይገኛል?
አቶ ሐጂ፡- የኤሌክትሮኒክስ የግዥ ሥርዓትን ለመተግበር ለሁለት ዓመታት ጥናት ተካሂዷል፤ የ14 ሀገራት ተሞክሮ ተቀምሯል። ይሄን መነሻ በማድረግም በ2014 ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ በዘጠኝ ተቋማት ላይ ተተግብሯል። በወቅቱ ከዘጠኙ ተቋማት ስድስቱ ግዥ ፈጽመውበታል። ቀሪዎቹ ያልተገበሩትም ወደ ሲስተሙ ያለመግባት በነበራቸው ፍላጎት ነበር። እናም በ2015 ዓ.ም ሥራውን በማጠናከር በ74 የፌዴራል ተቋማት እንዲተገበር ተደረገ። ሆኖም አራቱ ተቋማት አዳዲስ የተዋቀሩ ስለነበሩ መሠረተ ልማት ብዙም ስላልነበራቸው ግዥ ሳይፈጽሙ ሲቀሩ፤ 70ዎቹ ተቋማት ግን ግዢአቸውን በኤሌክትሮኒክስ ግዥ ሥርዓት አከናውነዋል። ይህ ጅማሮ እንደ ሀገር ለሚፈለገው ዘመናዊ የግዥ ሥርዓት ትልቅ መሠረት የጣለ፤ ሥራውም በጥሩ ደረጃ ላይ መሆኑን ያሳየ ነው።
አዲስ ዘመን፡- በ2015 በጀት ዓመት ለኤሌክትሮኒክስ ግዥ ሥርዓት ዋና ፈተና የነበረው ምንድን ነው?
አቶ ሐጂ፡- የ2015 በጀት ዓመት ዋና ተግዳሮት የነበረው ከ169 የፌዴራል ተቋማት 70ዎቹ በኤሌክትሮኒክስ ግዥ ሲፈጽሙ፤ 100 የሚጠጋ የፌዴራል ተቋም ደግሞ በማንዋል ግዥ ይፈጽሙ ነበር። በዚህም ነጋዴው ሁለት ቦታ ላይ የመቆም፤ ፌዴራል ተቋማትም አንዱን በኤሌክትሮኒክስ ግዥ እፈጽማለሁ ሌላው በማንዋል እንድገዛ ይፈቀድልን የማለት አጣብቂኝ ውስጥ ገብቶ ነበር። ይህም የሆነው ወጥ የሆነ የግዥ ሥርዓት ባለመኖሩ ነው።
ከዚህ በተጓዳኝ የንግዱ ማኅበረሰብም ሙሉ በሙሉ በኤሌክትሮኒክስ ግዥ ሥርዓት ውስጥ አለመግባት፤ እንዲሁም በኤሌክትሮኒክስ ግዥ እስኪለማመድ በማንዋል የመግዛትና የመሸጥ ፍላጎቶች ነበሩ። ስለዚህ ትልቁ ተግዳሮት የነበረው በኤሌክትሮኒክስ ግዥ የሚፈጽሙና በማንዋል ግዥ የሚፈጽሙ የፌዴራል ተቋማት መኖራቸው ሲሆን፤ ይሄም ለእኛ ከፍተኛ ማነቆ ነበር።
አዲስ ዘመን፡- ባለሥልጣኑ በቀጣይ በኤሌክትሮኒክስ ግዥ ሥርዓት ያለውን ችግር ለመቅረፍ ምን አስቧል?
አቶ ሐጂ፡- ዋናው እቅዳችን፣ በተያዘው 2016 በጀት ዓመት 169 የሚሆኑ የፌዴራል ተቋማትን ከተጠሪ ተቋማቱ ውጪ ሙሉ ለሙሉ በኤሌክትሮኒክስ ግዥ ሥርዓት እንዲገቡ ማድረግ ነው። ይህ በተገቢው ሁኔታ ተከናውኗል። በፌዴራል ደረጃ የቀሩት ተጠሪ ተቋማት ብቻ ናቸው። እስካሁን ያለው መረጃ በዕቅዳችን መሠረት 163 የሚሆኑት በግዥ ሥርዓቱ ውስጥ ገብተዋል።
አዲስ ዘመን፡- ቀሪዎቹ የትኞቹ ተቋማት ናቸው? ምን ደረጃ ላይ ይገኛሉ?
አቶ ሐጂ፡- የቀሩት ስድስት የሚሆኑ ተቋማት ሲሆኑ፤ እነዚህም ዩኒቨርሲቲዎች ናቸው። አራቱ የትግራይ ዩኒቨርሲቲዎች ናቸው። ይህም የሆነው በተፈጠረው ግጭት ምክንያት በዩኒቨርሲቲዎቹ ያሉ መሠረተ ልማቶች በደረሰባቸው ጉዳት የግዥ ሥርዓቱን ማስጀመር አልተቻለም። አሁን ላይ መሠረተ ልማቱ እየተሠራ ነው። ለባለሙያዎችም ሥልጠና እየተሰጠ ነው። ከሁለት ወር በኋላ ወደ ግዥ ሥርዓቱ የሚገቡበት ሁኔታ ይፈጠራል።
ቀሪዎቹ ዩኒቨርሲቲዎች ደግሞ በአማራ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሲሆን፤ እንጅባራና ደብረማርቆስ ዩኒቨርሲቲዎች ወደ ሲስተሙ ለመግባት ሥራ ላይ ናቸው። ስለዚህ አሁን ባለው መረጃ ከስድስቱ ተቋማት ውጪ ሁሉም የፌዴራል ተቋማት በኤሌክትሮኒክስ የግዥ ሥርዓት ገብተው ግዢአቸውን እየፈጸሙ ነው።
አዲስ ዘመን፡- በእርግጥ ሁሉም ተቋም ከማንዋል ወጥተው ሙሉ በሙሉ በኤሌክትሮኒክስ ግዥ እየፈጸሙ ነው? ከሆነስ ምን ያህል የንግዱ ማኅበረሰብስ በሥርዓቱ ተሳትፎ እያደረገ ነው?
አቶ ሐጂ፡- አዎ፤ እስሁን አንድም ተቋም በማንዋል ግዥ እንዲፈጽም ፈቃድ አልሰጠንም። የንግዱን ማኅበረሰብም በ2015 ሐምሌ ወር ላይ ሥራ ሲጀመር መቶ የሚሆኑ ንግድ ፈቃድ ያላቸው ሰዎች ነበር የተመዘገቡት። አሁን ላይ በትላልቅ ደረጃ ከሦስት እስከ 20 የተለያየ ንግድ ፈቃድ ያላቸው ከ15 ሺህ በላይ የሆኑ ነጋዴዎች ተመዝግበዋል።
በእያንዳንዱ ፈቃድ ሲታይ 38 ሺህ የሚሆን የንግዱ ማኅበረሰብ ተመዝግቧል። ሐምሌ 2015 መቶ ነበር፤ አሁን ላይ ግን ከ38 ሺ በላይ የንግዱ ማኅበረሰብ ተሳትፎ እያደረገ ነው። ስለዚህ በማንኛውም አገልግሎትና ሥራ ውስጥ በቂ ተወዳዳሪ አለ። በመሆኑም እስካሁን ባለው ሥራና ሂደት ውስጥ የገጠመን ምንም ችግር የለም።
አዲስ ዘመን፡- ምንም ችግር አልገጠመንም ሲሉ፤ ሁሉም ሥራዎች እንከን አልባ በሆነ መንገድ እየተሠሩ ነው ማለት ነው?
አቶ ሐጂ፡- ይህ ሲባል ጥቃቅን ችግሮች የሉም ማለትም አይደለም። ለምሳሌ፣ የኤ.ቲ.ኤም አገልግሎት ከተጀመረ ቆይቷል። ነገር ግን ኤሌክትሮኒክስ ቢሆን በኔትወርክ የሚሠራ በመሆኑ አልፎ አልፎ ‹‹ስታክ›› ወይም ከአገልግሎት ውጪ ሲሆን ይታያል። ሞባይልም ቢሆን እንዲሁ ነው። ስለዚህ ከጥቃቅን ችግሮች ውጪ በሚፈለገው ሁኔታ ወደ ሥራ ተገብቷል።
አዲስ ዘመን፡- የ2016 በጀት ዓመት ሩብ ዓመት ላይ እንደመገኘታችን መጠን፤ በዚህ ጊዜ ውስጥ የግዥ ሥርዓቱ ምን ያህል ውጤታማ ሆኗል?
አቶ ሐጂ፡- በሩብ ዓመቱ የተገኘው የአሠራር ለውጥ ባለፈው በጀት አመት ከነበረው የበለጠ ነው። ባለፈው አመት ሙሉ 70 ተቋማት ብቻ ነበሩ፤ አሁን ላይ 163 ተቋማት በሩብ ዓመቱ በኤሌክትሮኒክስ ግዥ ሥርዓት ውስጥ ገብተዋል። በዚህም በሩብ ዓመቱ ብቻ ከ728 በላይ የሚሆኑ ጨረታዎች አየር ላይ አሉ። በ2015 ዓመቱን በሙሉ 20 የሚሆኑ ጨረታዎች ናቸው አየር ላይ ውለው የነበሩት።
በግዥ ሂደት የመጀመሪያው ሩብ ዓመት የዝግጅት፤ ሁለተኛና ሦስተኛው ሩብ ዓመት የግዥ ነው። አራተኛ ሩብ ዓመት ደግሞ በጣም ጥቃቅን ግዥዎች ካልሆኑ በስተቀር ከግንቦት በኋላ ሙሉ በሙሉ ይዘጋል። ስለሆነም ያለው ሂደት ሲገመገም መልካም ውጤት ላይ ነው ያለው።
አንዱ የዚህ የኤሌክትሮኒክስ ግዥ ሥርዓት ጠቀሜታ ሰኔ ላይ ያለውን የግዥ ሩጫ ሙሉ በሙሉ ዝግ ያደርጋል። ለምሳሌ፣ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በዚህ ሩብ ዓመት ብቻ የበጀት ዓመቱን ግዥ 92 በመቶ ደርሷል። ይህም ተቋሙ ማቀዱን፤ በበጀት ዓመቱ ምን እንደሚገዛ ማወቁን የሚገልጽ አፈጻጸም ነው። ስለዚህ ሦስተኛና አራተኛ ሩብ ዓመት ላይ ምንም ግዥ ላይኖረው ይችላል።
አዲስ ዘመን፡- የኤሌክትሮኒክስ የግዥ ሥርዓት አቅዶ ከመግዛት አንጻር ምን ፋይዳ ይኖራል?
አቶ ሐጂ፡- ድሮ የተቋማት ውድቀት ለገዥ ዕቅድ አለማቀድ ነው። የሰኔና የግንቦት የግዥ ሩጫ የሚያሳየውም ግዥ ያለ ዕቅድ የሚሠራ በመሆኑ ነው። እንዲሁ በዘፈቀደ የመንግሥትን በጀት ላለመመለስ ትዝ ሲል ሶፋ መግዛት፤ ቢሮ ይታደስ፤ አጥር አጥራለሁና መሰል ያለ ዕቅድ የሚሠሩ ሥራዎች ብዙ ነበሩ። የኤሌክትሮኒክስ ግዥ የሚመልሰው ያለ ዕቅድ የሚገዛ የተቋም ንብረት እንዳይኖር ማድረግ ነው።
ማንኛውም ተቋም ወደደም ጠላም ግዥ ፈላጊ ከሆነ ዕቅድ ማቀድ ግዴታው ነው። አንድ ተቋም ውሃ እገዛለሁ ቢል ከመጀመሪያው ዕቅዱ ውስጥ ካልተካተተ ሲስተሙ እቅድህ አይደለም ብሎ ይዘጋል። ዕቅድ ውስጥ ሳይገባ ግዥ አይፈጽምም። በመሆኑም 163ቱም የፌዴራል ተቋም የግዥ ዕቅድ አላቸው። ቀሪዎቹ ተቋማትም በማንዋል ዕቅዱ ስላላቸው ኔትወርኩ ሲስተካከል ወደ ሲስተም ይለወጣል። አቀዱ ማለት መቼ ነው የሚገዛው፤ ምንድን ነው የሚገዛው፤ ከየት ነው የሚገዛው፤ የዕቅዱ ዝርዝር በለቀማ፣ በውስን ጨረታ፣ በሀገር አቀፍ ጨረታ ነው፤ ወይም በዓለም አቀፍ ጨረታ ነው የሚለው አብሮ የሚታይ ነው።
በፊት አንድ ሊትር ነዳጅ 80 ብር እየተገዛ መቶና ሁለት መቶ መኪና በየሱቁና በየሆቴሉ እየዞረ የሚያባክንበት ሁኔታ ነበር። ፕሮፎርማ ለመሰብሰብ ሁለት ቀን ሲዞር ይውላል፤ በሦስተኛ ቀን ሂዶ ይለቅማል። አሁን ላይ በፌዴራል ተቋማት ደረጃ አንድም መኪና ፕሮፎርማ ለመሰብሰብ በየሱቁ አይዞርም። በኤሌክትሮኒክስ ግዥ ሥርዓት ግን ሁሉም በኦንላይን በመሆኑ የሚባክን ነዳጅ፤ ጉልበትና ጊዜ የለም። በዚህም አሠራሩ መንግሥትና ሕዝብን አቀራረበ ለማለት ያስችላል።
አዲስ ዘመን፡- ተቋማት በዚህ መልኩ ዕቅድ የሚያቅዱት ኃላፊነት ስላለባቸው፣ ወይንስ በእናንተና በአሠራሩ ጫና ምክንያት ነው?
አቶ ሐጂ፡- በተቋማቱ ዕቅድ እንዲታቀድ ማድረግ የየተቋማቱ ኃላፊዎች ሥራ ነው። የመጀመሪያ ፍርድ ቤት ለአብነት እንዲነሳ ያደረገውም የተቋሙ ኃላፊዎች ተግባራዊ ስላደረጉና ለሥራው ቁርጠኛ ስለሆኑ ነው። የመጀመሪያ ፍርድ ቤት 12 የሚሆኑ ቅርንጫፎቹን ጨምሮ ወደ ሲስተሙ ገብተዋል።
መንግሥት ከሕዝቡ ሰብስቦ ነው በጀት የሚበጅተው። ስለዚህ እያንዳንዱ ተቋም አመራር ዕቅድ ማቀድ አለበት። አንድ የመንግሥት ሠራተኛ በደሞዙ ያቅዳል። ስለዚህ እንደ አቅም ለመኖር ዕቅድ አስፈላጊ ነው። ይህም ያለዕቅድ የሚባክነውን በጀት ለማስቀረት ከፍተኛ ሚና አለው።
አሁን ላይ እንደ ሀገር ለመጀመሪያ ጊዜ በሚባል ደረጃ ሁሉም የፌዴራል ተቋም የግዥ ዕቅድ አላቸው። ሁሉም ፌዴራል ተቋም በሚባል ደረጃ በኤሌክትሮኒክስ ግዥ እየገዙ ነው። በዚህም የመጨረሻ ሩብ ዓመት ግዥ እንደማይፈጸም እቅዳቸው ላይ ማስቀመጥ አለባቸው። ባለሥልጣኑም ከሚያዝያ 30 በኋላ ግዥ የሚባል ሙሉ በሙሉ ያቆማል። ይህ ማለት ግን ጥቃቅን ግዥዎች ይቆማሉ ማለት አይደለም።
አዲስ ዘመን፡- ጥቃቅን ግዥዎች ሲባል ምን ማለት ነው?
አቶ ሐጂ፡- ጥቃቅን ግዥ ማለት ለምሳሌ፣ አንድ ኃላፊ መንገድ እየሄደ ጎማው ቢፈነዳበት ሰኔ ላይ አይገዛም ተብሎ አይመለስም። እስከ ሰኔ 28 ሊገዛ የሚችልበት
አግባብ ይኖራል። ነገር ግን መሠረታዊ ግዥ የሚባሉት በሙሉ በዕቅድ ብቻ መገዛት አለባቸው። የፕሮጀክትም ቢሆን ሰኔ ላይ አይደለም እገዛለሁ የሚባለው፤ የአዲስ በጀት መጀመሪያ ወሩ ሐምሌ ላይ ሊታቀድ ይገባል። በዚህ ዓመት ከፌዴራል ውጪ ባሉ ተቋማት ላይ አዲስ አበባ ተጀምሯል።
አዲስ ዘመን፡- ለፌዴራል ተቋማት ተጠሪ የሆኑ ተቋማት ቁጥር ከፍተኛ ነው፤ በዚህ ደግሞ በማንዋል ግዥ የሚባክነው በጀት ቀላል አይደለም፤ እነዚህን ወደ ግዥ ሥርዓቱ ማስገባት ያልተቻለበት ምክንያት ምንድን ነው?
አቶ ሐጂ፡- ይህ የሆነበት ዋናው ምክንያት የባለሥልጣኑ አቅም ውስንነት ነው። ለሁሉም ፌዴራል ተቋማት ባለሙያ ተመድቦ ሥራ እያገዘ ነው። ለሁሉም በአንድ ጊዜ መድረስ አይቻልም። ምክንያቱም ያለው የሰው ኃይል ውስንነት ነው። በ163 ተቋማት ለአንድ ወር የሚሆን ሥልጠና ተሰጥቷል። ከእቅድ ጀምሮ እስከ ውል አስተዳደር ድረስ ለአንድ ወር ሰልጥኖ ወደ ሥራ ተገብቷል።
በመሆኑም ተጠሪ ተቋማትን ጨምሮ ለማስገባት ከሰው ኃይል አንጻር አይቻልም። ሳይደገፉ ወደሥራ ቢገቡ ደግሞ የሚጎድሉ ነገሮች አሉ። ለምሳሌ፣ ገቢዎች ሚኒስቴር ከአምስት በላይ ቅርንጫፍ አለው። ማዕከላዊ ስታስቲክስ ከ27 በላይ ቅርንጫፍ አለው። ስለዚህ የሁሉንም ተቋማት ተጠሪ ይግቡ ከተባለ ከአቅም በላይ ይሆናል። ሆኖም በሂደት አቅም እየተፈጠረ እስከ ቀበሌ ድረስ ያለው የግዥ ሥርዓት ተግባራዊ ሲሆን አለአግባብ የሚባክን የመንግሥት በጀት ማዳን ያስችላል።
አዲስ ዘመን፡- ዓለም አቀፍ ጨረታዎች ላይ መጓተቶች ይታያሉ፤ ይህም በፕሮጀክቶች አፈጻጸም ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እየፈጠረ መሆኑ ይነገራል፤ በዚህ ላይ እርሶ ምን ይላሉ? ለዚህ ችግር መቃለልስ የኤሌክትሮኒክስ ግዥ ምን ያግዛል?
አቶ ሐጂ፡– የኤሌክትሮኒክስ የግዥ ሥርዓት ዓለም ላይ ባመጣው ለውጥ ምክንያት ነው ኢትዮጵያም እንደ ሀገር የገባችበት። ይህም ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ እንዳይጠናቀቁ አንዱ ማነቆ የሚሆነው የግዥ ሥርዓቱ አለመዘመኑ ነው። ስለዚህ ይህ ሥርዓት የግዥ ጊዜን የሚያሳጥር ነው፤ ሌብነትን በከፍተኛ ሁኔታ ይከላከላል።
ለምሳሌ፣ በቀደመው ግዥ ‹‹ፕሮፎርማ›› የሚባል የግዥ አሠራር አለ፤ ከሦስት ሱቅ ፕሮፎርማ ማምጣትና እንዴት እንደተመረጠም ሳይታወቅ በተጭበረበረ መንገድና በጥቅም ትስስር ግዥ የሚፈጸምበት ሂደት ነበር። ይህም በጥቅም ኔትወርክ የተመሠረተ ነበር። ሦስቱም ሱቅ በተለያየ ማለትም በእናት በአባት በልጅ የተለያየ ማህተም አላቸው። የሚሰጠው ፕሮፎርማ ግን ከአንድ ሱቅ ነው። አሁን ላይ ይህ አሠራር እየተቀየረ ነው።
በዚህ ዓመት ድል የተነሳና በልበ ሙሉነት መናገር የሚቻለው ይህን ዓይነት መሰል ስርቆት መቅረፍ መቻሉ ነው። በፊት ዓለም አቀፍ ጨረታ ከሦስት እስከ አራት ወር ነበር። አሁን ላይ ከሁለት ወር በታች ባለ ጊዜ ግዥ ይፈጸማል።
አዲስ ዘመን፡- ባለው ተጨባጭ ሁኔታ በዓለም አቀፍ ጨረታዎች ላይ የሚታይ ውስንንት የለም ማለት ይቻላል?
አቶ ሐጂ፡- ውስንነት የለም ማለት ሳይሆን፤ ደላላ ከመሃል ይጠፋል። ዓለም አቀፍ ጨረታ ቢወጣ በቀድሞ አሠራር ደላላ ይገዛና ለቻይና፤ ለአሜሪካ፤ ለቱርክና መሰል ሀገሮች ላይ ሆነው ለሚጫረቱ ድርጅቶች ይልካል። ከአራት ወር በላይ የሚቆየው በማንዋል ከዚህ ተገዝቶ በፖስታ ቱርክ ላይ ለሚወዳደረው ዓለም አቀፍ ተጫራች አድርሶ ሞልቶ እስኪመለስ ያለው ጊዜ ነው። አሁን ላይ ግን በአንድ ጊዜ ዓለም ላይ ላለ የንግዱ ማኅበረሰብ ጨረታው በእጅ ስልኩ ስለሚደርሰው ወዲውኑ ሞልቶ መጫረት የሚችልበት አውድ ተፈጥሯል። ለዚህም ጊዜው አጭር እንዲሆን አደርጓል።
ስለዚህ እንደ ድሮው በር ተዘጋብኝ የሚባል ነገር የለም፤ ሰነዱን የሚሸጠው አካል ዛሬ አልገባም፤ ለሥራ ወጥቷል አይባልም፤ ሰነድ ለመግዛት ከክፍለ ሀገር አዲስ አበባ መምጣት አይጠበቅም። በኤሌክትሮኒክስ የግዥ ሥርዓት አድሎ፤ ማጭበርበር የሚባል ነገር የለም፤ ለተጫራቾች እኩል ዕድል የሚሰጥ ነው። ለማንም ነጋዴ አያዳላም።
ለአብነት፣ በኮንስትራክሽን ዘርፍ አራት ሺህ 18 ተወዳዳሪዎች አሉ። ድሮ መርጦ ለሦስቱ አሊያም ለሁለቱ የሚሰጥበት ዕድል ነበር። አሁን ግን፣ ለሁሉም ጨረታው ስለሚደርስ በሥርዓቱ ተወዳደረ አልተወዳደረ የእያንዳንዱ ተጫራች መብት ነው። ምክንያቱም አሁን ላይ ፕሮፎርማ ጨረታና ውስን ጨረታ ከሌብነት ወጥቷል። ስለዚህ ዓለም አቀፍ ጨረታው ላይ ምንም ውስንነት የለም።
የሜጋ ፕሮጀክቶች ግዥ የሚፈጸምው በዓለም አቀፍ ጨረታ ነው። ዓለም አቀፍ ጨረታ የሚወጣው ሁልጊዜም ለግዙፍ ፕሮጀክቶች ግንባታ ነው። ስለዚህ የሀገር ውስጥ ተጫራችም አቅሙ ያለው ሁሉ በመስፈርቱ ይወዳደራል። ውድድሩ ጠንካራ ነው። ኤሌክትሮኒክስ ግዥ ፉክክር ካለ ወደ ትክክለኛው ዋጋ የመጠጋት ዕድል አለ። የውሸት ዋጋዎችን ማስወገድ ያስችላል።
አዲስ ዘመን፡- አልፎ አልፎ በጨበጣ ውስጥ ገብተው በዓለም አቀፍ ጨረታ የሚሳተፉ ተቋማት እንዳሉ ይነገራል፤ ለጨረታው ያላቸው አቅም በምን ይገመገማል?
አቶ ሐጂ፡- ምን አልባት ንግድ ሚኒስቴር ካልተሳሳተ ጨበጣም ሆነ ቆረጣ የሚባል የለም። ለምሳሌ፣ አበበ የሚል ስም የተመዘገበ የግብር መክፈያ ቁጥር ‹‹ቲን ነምበር›› ሲገባ ከንግድ ሚኒስቴር ጋር ይገናኛል። ስለዚህ አበበ ንግድ ፈቃድ አለው ወይ ይልና ያለው የችርቻሮ ከሆነ ኮንስትራክሽን ጨረታ ከተመዘገበ እሱ የችርቻሮ ነው፤ ኮንስትራክስን ላይ ገብቶ መወዳደር አይችልም ብሎ ሲስተሙ ይጥለዋል። ስለዚህ በትክክለኛ ፈቃዱ ብቻ ነጋዴው ይወዳደራል።
የኮምፒዩተር ፈቃድ ያለው ሰው በራሱ ብቻ እንጂ የመኪና ጨረታ ላይ ሊወዳደር አይችልም። ስለዚህ ንግድ ሚኒስቴር ፈቃድ ሲሰጥ በትክክለኛ መንገድ ካልሰጠና በጨበጣ መዝግቦ አልፎ ካልሆነ በስተቀር ባለሥልጣኑ የሚወስደው መረጃ ከንግድ ሚኒስቴር ነው። ድሮ የሚያስቸግረው አንዱ መጥቶ ክስ ያቀርባል። አሁን ላይ ግን አስር ፈቃድ ካለው አንድ ሰው አስሩንም ይዘረዝራል። ድሮ የዓመቱን ግብር ሳይከፍል የሚወዳደር ነበር። አሁን ላይ ግን ግብር መገበሩን አለመገበሩን የግብር መክፈያ መለያ ቁጥር ሲገባ ይለየዋል። ካልገበረ ከውድድር ውጪ ይሆናል።
ስለዚህ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በከፍተኛ ሁኔታ ይቀንሳል። በተጨማሪም ገንዘብ መኖሩንና አለመኖሩን ከባንኮች ጋር ያገናኛል። ፡ የመንግሥት ከሆነ ከኢፍ ሚስ ጋር ያገናኘዋል። ስለዚህ ቀድሞ የነበረውን የሰነድ ማጭበርበር ቀንሷል። ይህም የኦዲት ሥራን አቅሏል። አሁን ላይ እያንዳንዱ ኦዲተር በኦንላይ የሚለቀቀውን ጨረታ የመከታተል ዕድል ተፈጥሮለታል።
አዲስ ዘመን፡- የኤሌክትሮኒክስ የግዥ ሥርዓት ንብረት ባግባቡ ሳይቆጠር ባለው ንብረት ላይ አላስፈላጊ ግዥን በማስቀረት ረገድ አስተዋጽኦው ምን ያህል ነው?
አቶ ሐጂ፡- ውሸት መናገር ጥሩ አይደለም። ንብረት ላይ አሁንም ብዙ ችግር አለ፤ ምክንያቱም ብዙ ነው። በእርግጥ አሁን ላይ እየተገዙ ያሉ ዕቃዎች ወደ ኮምፒዩተር ስለሚሰፍሩ ግዥ ከማውጣት በፊት የተመዘገቡት ንብረቶች የማየት ዕድል ተፈጥሯል። ነገር ግን የቆዩ ንብረቶችም አሉ። ለምሳሌ፣ በኃይለሥላሴ፤ በደርግ የተገዙ ንብረቶች አሉ። መቼ እንኳን እንደተገዙ መለየት አቅቶን መከራ የምናይባቸው መኪናዎች አሉ። የመኪናዎቹ ታሪከ ባለመመዝገቡ የዛሬ 30 አመት የተገዛ መኪና እንሽጥ ሲባል እንዲሁ ተነስቶ የሚሸጥ አይደለም።
መቼ እንደተገዛ፤ በመንግሥት ገንዘብ ነው የተገዛው ወይስ በእርዳታ መልክ የሚለውን መለየት አይቻልም። ዕዳ እንዳለበት፤ በመኪናው ወንጀል መሠራቱን አለመሠራቱን ተጣርቶ ነው የሚሸጠው። ነገር ግን አሁን ላይ የመኪናው ታሪካዊ ዳራ ተመዝግቦ ባለመኖሩ በርካታ ተሽከርካሪዎች መሸጥ ተስኖናል። ነገር ግን እንደ አንደ መፍትሔ ታሪክ የሌላቸውን ተሽከርካሪዎች በአንድ ተሰብስቦ ለመንግሥት ቀርቧል። ከተፈቀደ ይሸጣል። ከዚያ ውጪ ግን ለቆዩ ዕቃዎች ለመሸጥም ለማስወገድም መነሻ የሚሆን ሰነድ የለም።
እንደ ኬሚካል ያሉትን በሀገር ደረጃ ማስወገድ የማንችላቸው የተቀመጡ አሉ። እነዚህን የማስወገጃ መፍትሔ እየተጠና ነው። ወደፊት አንድ ኬሚካል ከመጣ በኋላ እንዴት ይወገዳል? መቼ ይወገዳል? የሚለው የሚረጋገጠው ኬሚካል ካስገቡ በኋላ አይደለም። ሲገባ ለስንት ዓመት እንደሚያገለግል ማረጋገጥ ያስፈልጋል።
ለምሳሌ፣ ከአንድ ዓመት በኋላ የአገልግሎት ጊዜው የሚያልፍ ኬሚካል በእርዳታ መልኩ ወደ ሀገር ውስጥ ይገባል። ዕቃው ከገባ በኋላ ጥቅም ላይ ሳይውል የአገልግሎት ጊዜው ያልፋል። ከዚያ በኋላ ለማስወገድ ከገባበት ዋጋ በላይ ይጠይቃል። ስለዚህ እያንዳንዱ ተቋም ኬሚካል ከማስገባቱ በፊት የዕቃውን ዕድሜ የአካባቢ ብክለት ተፅዕኖ አለመኖሩን አረጋግጠው ማስገባት አለባቸው። ማንኛውም ኬሚካል ወደ ሀገር ውስጥ ሲገባ የረጅም ጊዜ አገልግሎት ሊሰጥ የሚችል መሆኑን ማረጋገጥ ያስፈልጋል። ካልሆነ ግን ወደ ሀገር ውስጥ ሳይገባ ወደ መጣበት ሀገር መመለስ፤ እና እያጣሩ ማስገባት እንደሚገባ በአዋጅ ላይ ተቀምጧል።
አዲስ ዘመን፡- የአገልግሎት ጊዜያቸው ያለፈባቸው ንብረቶችን ተቋማት በአግባቡ ማስወገድ ሳይችሉ ሲቀሩ ባለሥልጣኑ የሚወስደው እርምጃ አለ?
አቶ ሐጂ፡- አይ፣ አንወስድም፤ ወስደንም አናውቅም። ከዚህ በፊት የነበረው አዋጅ ይህን ሥልጣን አልሰጠንም። በንብረት ላይ ተጠያቂነት የሚባል ጉዳይ የለም። በዚህ ምክንያት ሰው ንብረትን መንካት ይፈራል። አመራር በአንድ ተቋም ሲሾም በርካታ መኪኖች ቆመው ቢያገኝ ሳይነካ ይነሳል። በአዲሱ አዋጅ ላይ ግን ተጠያቂነት እንዲኖር ተደርጓል። ኃላፊ ተሹሞ በገባበት ተቋም ውስጥ ንብረትን በእንክብካቤ የመያዝ፤ መወገድ ያለበትን በወቅቱ ማስወገድ፤ መሸጥ ያለበትንም በወቅቱ መሸጥ እንደሚገባው ተቀምጠዋል። ይህን ባለማድረግ ተጠያቂነት እንዳለበት በአዋጅ ተቀምጧል። እስካሁን ንብረትን በማባከን የተጠየቀ አካል የለም አልጠየቅንም። ወደፊት ግን ተጠያቂነት ይኖራል።
አዲስ ዘመን፡- በ2015 በጀት አመት የነበረው አፈጻጸምን እንዴት ይገልጹታል?
አቶ ሐጂ፡- ባለፈው ዓመት እስከ ዓመቱ መጨረሻ 27 የሚሆኑ የፌዴራል ተቋማት ዕቅድ የላቸውም ነበር። ነገር ግን ግዥ ይፈጽማሉ። በዚህም የባለሥልጣኑ ኃላፊነት የነበረው ለገንዘብ ሚኒስቴር ሪፖርት ማድረግና ለፓርላማ ማሳወቅ ነው። የእኛ ሥራ የግዥ አፈጻጸምን ከእነ ጉድለቱ ዝርዝር ባለመልኩ ለገንዘብ ሚኒስቴር ማሳወቅ ሲሆን፤ እርጃ የመውሰድ ሥልጣን የገንዘብ ሚኒስቴር ነው። በዋናነት እንደ ሀገር ለመጀመሪያ ጊዜ ሁሉም የፌዴራል ተቋም የግዥ ዕቅድ እንዲኖራቸው ተሠርቷል።
ስለዚህ የ2015 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸሙ የፌዴራል ተቋማት በኤሌክትሮኒክስ ግዥ ሥርዓት እንዲገቡ ማድረግ ነው። ለምሳሌ ኢፍ ሚስ ከጀመረ 15 ዓመቱ ሲሆን ያለው አንድ መቶ (15 ተቋም) ብቻ ነው። የኤሌክትሮኒክስ ግዥ ሥርዓት ግን በሦስት ዓመት ውስጥ 169 ተቋማት እንዲገቡ ተደርጓል። የግዥ ሥርዓቱ ሙሉ በሙሉ እንደ ሀገር ተግባራዊ ሲደረግ ፋይናንሻል ኦዲተርን ይተካል። ማጭበርበር፤ መደራደር አይቻልም። ምን ያክል በጀት ከብክነት መታደግ እንደተቻለ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እያጠና ነው። ከግለሰብ እስከ መንግሥት ምን ያህል ገንዘብ ማዳን እንደተቻለ ጥናቱ ሲጠናቀቅ ይፋ ይደረጋል።
አዲስ ዘመን፡- በ2016 በጀት አመት እንደ ግብ ምን ተይዟል? ምንስ ለማሳካት ታስቧል?
አቶ ሐጂ፡- የዚህ ዓመት እቅዳችን፣ በ2016 በጀት አመት መጨረሻ ሁሉም የፌዴራል ተቋም ከእነ ተጠሪዎቻቸው በግዥ ሥርዓቱ ውስጥ እንዲገቡ ማድረግ ነው። ይህ ሲሆን ሌብነትንና ማጭበርበርን በብዙ መልኩ እንደተዋጋን እንቆጥረዋል። ይህ ሲሆን የጥቅም ኔትወርክ እና አድሎ ጠፍቶ መልካም አስተዳደርና ፍትሐዊነት ይሰፍናል። አሁን እንኳን የንግዱ ማኅበረሰብ እንኳን እኩል መወዳደር የሚችልበት ሁኔታ ተፈጠረ የሚል ምላሽ እየሰጡ ነው። ለዚህ ሥራ እንዲያግዘንም ከደረጃዎች ኤጀንሲ ጋር በመነጋገር 328 ዕቃዎች ላይ ደረጃ ወጥቷል።
አዲስ ዘመን፡- ስለነበረን ቆይታ እናመሰግናለን።
አቶ ሐጂ፡- እኔም አመሰግናለሁ።
ሞገስ ተስፋ
አዲስ ዘመን ኅዳር 19 ቀን 2016 ዓ.ም