የልማታችንና የሰላማችን ጠንቅ የሆነውን ሙስና በጋራ እንከላከል!

 ሙስና እና ብልሹ አሠራር የሀገራችንን ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ እድገት የሚገታ ተግባር መሆኑን በመገንዘብ የሕግ ሥርዓት መዘርጋት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ በኢትዮጵያ የሥነምግባርና ፀረሙስና ኮሚሽን በአዋጅ ተቋቁሞ ላለፉት ሃያ ዓመታት በሥራ ላይ ይገኛል። በዚህም ተቋሙ ከግንዛቤ ማስጨበጥ ጀምሮ የሙስናን ችግሮች መፍታትና መግታት የሚያስችሉ ተግባራትን ሲያከናውን ቆይቷል።

ይሁን እንጂ በተለያዩ ምክንያቶች የሙስና ችግር ከዕለት ዕለት ስር እየሰደደ እና ለሀገር ማኅበራዊ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እንዲሁም የሰላምና ደህንነት ስጋት እስከመሆን መድረሱ ተደጋግሞ ተነግሯል። የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶክተር) በአንድ ወቅት በፓርላማ ንግግራቸውም ለሙስና የተሰመረው ቀይ መስመር ቀይ ምንጣፍ ሆኗቸው የሚመላለሱበት ሙሰኞች ስለመኖራቸው እና ችግሩም ትልቅ ሀገራዊ በሽታ ስለመሆኑ ገልጸው ነበር።

ይሄን ችግር ከግምት ባስገባ መልኩም በተለይም ሀገራችን የተጀመረውን የልማት፣ የሰላም እና የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ቀጣይነት ያለው እንዲሆን፤ ሙስና እና ብልሹ አሠራርን መከላከል በመልካም ሥነ-ምግባር የተገነባ፣ ሙስናን የሚፀየፍ በፅናት የሚታገል ኅብረተሰብ መፍጠር በማስፈለጉ የፌዴራል የሥነ-ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅን አዋጅ ቁጥር 1236/2013 እንደገና እንዲሻሻል ተደረገ።

ከዚህ በኋላም ተቋሙ የተሰጠውን ተልዕኮ ለመወጣት በርካታ ተግባራትን ያከናወነ ሲሆን፤ ከሰሞኑ ይፋ ባደረገው መረጃ መሠረትም፤ ባለፉት 20 ዓመታት ጉዞው ከ20 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ግንዛቤ እንዲያገኙ አድርጓል። ከዚህ ባለፈም ሕግን ለማስከበር ባደረገው እንቅስቃሴ 11 ሺህ 350 የሙስና ወንጀል የክስ መዝገቦች ላይ ውሳኔ በማሰጠት ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ ማስመለስ ችሏል።

በዚህ ረገድ ባለፉት ሦስትና አራት ዓመታት የተሻለ ሥራን ማከናወን እንደቻለ ያስታወቀው ኮሚሽኑ ታዲያ፤ በተለይም ባለፉት አራት ዓመታት በኢትዮጵያ ሙስናን ለመከላከል በተሠራ የቅድመ መከላከል ሥራ ከዘጠኝ ቢሊዮን ብር በላይ፤ እንዲሁም ከአራት ሚሊዮን ካሬ ሜትር በላይ መሬት ከምዝበራ ማዳን ችሏል። ከ829 ሚሊዮን ብር በላይ በሙስና የተገኘ ገንዘብም ተመላሽ እንዲሆን አድርጓል።

ከዚህ በተጓዳኝ ባለፉት ሦስት ዓመታት የፍርድ ውሳኔ ያረፈባቸው ንብረቶች ወደ መንግሥት እንዲገቡ አድርጓል። ከእነዚህ ውስጥም 12 ቀላል ተሽከርካሪዎች፣ 179 ከባድ ተሽከርካሪዎች እና 17 ኮንቴይነሮች እንዲሁም 10 ቤቶች ወደ መንግሥት ገቢ ከሆኑት መካከል ይገኙበታል። በተመሳሳይ አንድ ነጥብ 09 ኪሎ ግራም ወርቅ ወደ መንግሥት ካዝና እንዲገባ ተደርጓል።

ይሄን እና መሰል ጅምር ውጤቶች ሊገኙ የቻሉት ደግሞ፣ በአንድ በኩል መንግሥት ግልፅነትና ተጠያቂነት የሰፈነበት አሠራርን ለመፍጠር የፖለቲካ ቁርጠኝነት የታየባቸው ርምጃዎችን በመውሰዱ ሲሆን፤ በሌላ በኩል የፀረ ሙስና ትግሉን ተቋማዊ እና ሀገራዊ በሆነ አደረጃጀት እንዲመራ በመደረጉ ነው።

ይሁን እንጂ በጅምር ደረጃ ሊታይ የሚችለው ይሄን መሰል ተግባርና እርምጃ፣ ከችግሩ ግዝፈትና ስፋት አንጻር ገና ብዙ መስራት የሚገባን፤ ሥራውም በጥብቅ ዲስፕሊን ሊመራ እና በጠንካራ መናበብ በታገዘ ትብብርና ቅንጅት ሊከወን የሚገባው ነው። ምክንያቱም ሙስና የሀገር ኢኮኖሚን የሚያናጋ፤ የማኅበራዊ እሴትና መሠረትን ሸርሽሮ የሚንድ፤ የፖለቲካ ስብራትን የሚፈጥር፤ እንዲሁም ከፍ ያለ ሀገራዊ ሰላምና ደህንነት ላይ አደጋን የሚጋርጥ ክፉ ደዌ ነውና።

ይሄንን ደዌ በወቅቱ የችግሩን ምክንያት መለየት፤ ችግር የተከሰተበትን ቦታ ማከም፤ በሽታው ላይድን የተጠናወተውን ቦታም ቆርጦ መጣልና በተሻለ አካል በመተካት ሕመሙን ማስታገስ፤ በሂደትም መፈወስ ይገባል። ይሄ የሚሆነው ደግሞ የችግሩን ግዝፈት በመረዳት፤ ሥራውም የአንድ አካል ብቻ አለመሆኑን አውቆ ሁሉም ከልብ በመነጨ ኃላፊነትና ትጋት የበኩሉን ማበርከት ሲችል ነው!

አዲስ ዘመን   ኅዳር 19 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You