ዛሬ ላይ ፈተና የሆኑ ያደሩ ዕዳዎችን ለመክፈል

 የበለጸጉ ሀገራት ዛሬ የደረሱበት የዕድገት እና የብልጽግና ማማ ላይ የደረሱት አባት አያቶቻቸው ባቆዩላቸው ወረትና ባሰፈኑላቸው ሰላም፤ ፍቅርና አንድነትነ ነው። ትናንት የተሠሩት በጎ ሥራዎች ለዛሬ ብልጽግናቸው እርሾ ናቸው። በተቃራኒው ደግሞ ከትናንት ያደሩ ቁርሾዎች ለዛሬ ዕድገት እንቅፋቶች ናቸው።

የዛሬዪቱ ኢትዮጵያ የትንናት እና የትናንት በስቲያ ቀጣይ እንጂ ዛሬ እንደጅብ ጥላ በቅላ ያደረች አይደለችም። የዛሬዪቱ ኢትዮጵያ የትናንት ደስታዎች፤ መከራና ችግሮች ወራሽ ነች። መጥፎና በጎ ትርክቶች ባለቤት ነች። ከዚህ ውጪ የሚያደርጋት የሀገረ መንግሥት ሆነ የማኅበረሰብ ታሪክ የለም።

በየትኛውም የዓለም ክፍል ያለ ትውልድ በታሪክ በአንደኛው ምዕራፍ፤ የወረሰው ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ዕዳ አለው። ለዚያ ዕዳ ዋጋ ከፍሏል፤ ተመሳሳይ ዕዳ ውስጥ እንዳይገባም ካለፈው ተምሮ ዛሬዎቹን ሆነ ነገዎቹን የተሻሉ ለማድረግ ተንቀሳቅሷል፤ በዚህ ሂደት የተሳካለትም ያልተሳካለትም ማኅበረሰብ/ሀገር አለ።

ይህ እውነታ በእኛም ሀገር የተለየ አይደለም። እንደ ሀገር በተለያዩ ዘመናት ከገባንባቸው እና ብዙ ዋጋ ከሚያስከፍሉን ዕዳዎቻችን መውጣት አለመቻላችን ዛሬዎቻችንን እንድናጣ እየተገደድን ነው። በዚህም ስለነገዎቻችን ተስፈኞች እንዳንሆን ከመሆን ባለፈ፤ የሀገረ መንግሥት ግንባታችን ተግዳሮት ውስጥ እንዲወድቅ እየሆነ ነው።

እንደ ሀገር ከትናንት ተምረን መሻገር ካልቻልናቸው ዕዳዎቻችን / ችግሮቻችን መካከል የትናንት የፖለቲካ ዕዳ አንዱ ነው። ታሪካችንን ላገላበጠ፤ በአግባቡ ለመረመረ አብዛኞቹ ችግሮቻችን ከትናንት ከወረስናቸው የፖለቲካ ዕዳዎች የሚመነጩ ናቸው። ይህ ትውልድ ሆነ የፖለቲካ ሥርዓቱ የሚከሰሱበት አይደለም።

ኢትዮጵያውያን የአኩሪ ማኅበራዊ ባህላዊና መንፈሳዊ ዕሴቶች ባለቤት ናቸው። መከባበር፤ መደማመጥ፤ መቻቻልና መተዛዘን ከእነዚህ ዕሴቶች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው። እነዚህ እሴቶች ለሀገረ መንግሥት ግንባታ ከፍ ያለ አቅም እንደሆኑ ይታመናል።

ይህም ሆኖ ግን፤ የትናንት የፖለቲካ ዕዳዎቻችንን እንዴት አድርግን እንክፈልና ዛሬዎቻችንን ከትናንት ጥላ እናውጣ ከማለት ይልቅ፤ ትናንት ላይ ቆመው በሚያላዝኑ፤ ቆሞ ቀር ፖለቲከኞች ምክንያት እንደ ሀገር ብዙ ትውልዶች ያልተገቡ ዋጋዎችን ለመክፈል ተገድደዋል።

የትናንት ባለዕዳ የሆነውን ትውልድና መንግሥት መውቀስን ዋነኛ የፖለቲካ አጀንዳ ያደረጉት እነዚህ ቆሞቀር ፖለቲከኞች፤ ትናንትን በትናንት መነፅር፤ የየዘመኑንም ትውልድ በራሱ ዘመን የአስተሳሰብ እሴቶች/ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እሴቶች/ከመገምገም ይልቅ በአሁነኛ ጥራዝ ነጠቅ እሳቤ በመክሰስና በመኮነን ለሀገራዊ ሰላም ሆነ ለሀገረ መንግሥቱ ፈተና ሆነዋል።

የትናንት ችግሮች እንዴት እንደሚቀረፉና ሕዝብም ለዘመናት ይዞ የተጓዛቸው መልካም ዕሴቶችን እንዴት ማስቀጠል እንደሚገባው ከመምከር ይልቅ መልካም ዕሴቶች ቀሰበቀስ እንዲናዱ በማድረግ ወንድም በወንድሙ ላይ መታመን እንዲያጣ፤ ልዩነቶችን ጌጦቹ አድርጎ ሳያፍር ለዘመናት አብሮ በኖረ ሕዝብ መካከል ጥላቻ እንዲፈጠር፣ የዘመኑን ትውልድ ባልኖረበት ዘመን ትርክት በመወንጀል ለማሸማቀቅ፤ በዚህም የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት ረጅም ርቅት እየሄዱ ነው። ንጹሃን ባልዋሉበት ሜዳ እንዲፈረጁ፤ እንዲሰደዱ፤ እንዲፈናቀሉና እንዲገደሉ አድርገዋል።

ከሁሉም የሚያሳፍረውና የሚያሳዝነው ደግሞ፤ በ1960ዎቹ በነበረው አሳዳጅና ተሳዳጅ፤ ገዳይና አስገዳይ ፖለቲካ ጭምር ተዋናይ የሆኑ አካላት ዓይናቸውን በጨው አጥበው ትናንት ለተፈጸመው ችግር የዛሬውን ትውልድ በአደባባይ ሲወቅሱ የመታየታቸው እውነታ ነው ።

እነዚህ ሰዎች ያደፈ ታሪካቸውን ይዘው ተሸፋፍነው መተኛት ሲገባቸው፤ እኔ ያላቦካሁት አይጋገርም በሚል ፈሊጥ በየቦታው ያዙኝ ልቀቁኝ ሲሉ ይደመጣሉ። ኅብረተሰቡ ተረጋግቶ እንዳይኖር የተለያዩ ሰሞነኛ አጀንዳዎችን በመፍጠር ውዥንብር መፍጠር ሥራቸው ሆኗል። እነዚህ የደም ፖለቲከኞች ዛሬም ለመጡበት በደም የተጨማለቀ መንገዳቸው ወጣቱን ለማማለል ሲጥሩ ይታያሉ።

ቆሞ ቀር በሆነው የፖለቲካ አስተሳሰብ ላይ የተቸነከሩት እነዚሁ ፖለቲከኞች ኢትዮጵያን የምታክል ታላቅ ሀገር ወደ ጎጥና መንደር አውርደው አንሰው ሊያሳንሷት ይሞክራሉ። ከ13 የአፍሪካ ሀገራት በላይ በአርማነት የወሰዱትን ሰንደቅ ዓላማ በመጸየፍ ጭምር የቅኝ ገዢዎችን ሃሳብ ሲደግሙ ይስተዋላሉ።

ለእነዚህ ወገኖች ዕሴት፣ ታሪክ፣ ባህል፣ ወግ የሚሏቸው ኢትዮጵያዊ ዕሴቶች ይጎረብጣቸዋል። እኩልነት የሚሉት ነገር ደግሞ ያማቸዋል። እነዚህ ቆሞ ቀር ፖለቲከኞች መገኛቸው ብዙ ነው። እዚህም እዚም አሉ። በየትኛውም ብሔር፤ በየትኛውም ሃይማኖት ውስጥ አሉ። ሆኖም ለብሔራቸውም ሆነ ለሃይማኖታቸው የማይቆረቆሩና ይልቁንም በብሔርና በሃይማኖት ጭምብል ውስጥ የራሳቸውን ጥቅም የሚያሳድዱ ነጋዴዎች ናቸው።

ጥቅማቸውን ለማጋበስ ሲሉም የተፋቀረን ያጣላሉ፤ አብሮ የኖረን ያቃቅራሉ፤ ወንድማማቾችን ያለያያሉ። ወሬያቸው በሙሉ ክፋትና ጥላቻ ብቻ ነው። በእነዚህ ሰዎች መዝገበ ቃላት ውስጥ ፍቅር፣ሰላም፣አብሮ መኖር የሚሉት ቃላት ታስሰው አይገኙም።

በኋላቀሩ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ባህል ውስጥ የሃሳብ ልዩነት ክብር የለውም፣ ዕውቅናም አይሰጠውም። በሃሳብ የተለየን እንደ ደመኛ ጠላት ማሳደድ፣ ማሰር፣ መግደል ወይም ማሰናከል የተለመደ ድርጊት ነው። ከአብሮነት ይልቅ ነጠላ ሆኖ በመቆም በአሸናፊነትና ተሸናፊነት መንፈስ ሀገርን ለመምራት መዳዳት ያረጀው የኢትዮጵያ ፖለቲካ አካሄድ ነው።

የዛሬው ትውልድ ለዘመናት የታኘከን ማስቲካ ለማላመጥ ፍቃደኛ አይደለም። የመጠፋፋትና የመገፋፋት ፖለቲካ ሰልችቶታል። ከልዩነት ይልቅ አንድነትን፤ ከመለያየት ይልቅ አብሮነትን፤ ከጥላቻ ይልቅ ፍቅርን፤ ከመበታተን ይልቅ አብሮ መኖርን፤ ይሻል። ይህንን እውነታ መረዳት ሆነ ለእውነታው ታምኖ መኖር ለነዚህ ፖለቲከኞች የሚዋጥ አይደለም።

በ1960ዎቹ ያላዋጣው የመጠፋፋትና የመገፋፋት ፖለቲካ ዛሬ ሕይወት አይኖረውም። ትናንት የመከነ ዘር ዛሬ ፍሬ ሊያፈራ አይችልም፤ ዘመን ያለፈበት ፖቲካችሁን በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ሆነ በዚህ ትውልድ ስፍራ አይኖረውም። ለእናንተም ቢሆን መቼም ሊያተርፋችሁ የሚችል የፖለቲካ ስትራቴጂ አይደለም፤ ዘመኑን የሚዋጅ አቅም የለውም።

ዛሬ «የአክሱም ሐውልት ለወላይታው ምኑ ነው» የሚለው ከፋፋይና አግላይ አመለካከት ተቀይሮ ‹‹ሁሉም የኢትዮጵያ፤ ኢትዮጵያ የሁሉም›› በሚለው ተቀይሯል። ኢትዮጵያን ወደ ቁልቁለት ይዟት ሲንደረደር የነበረው የከፋፋይነትና የአግላይነት ማርሽ ተቀይሮ ወንድማማችነት፤ እህትማማችነት፤ አንድነት፤ አብሮነት፤ በሚሉ ምርጥ ማርሾች ተቀይሯል።

ዛሬ ሥልጣን ለመያዝ ብረት ማንሳት ሳይሆን ቁጭ ብሎ በጠረጴዛ ዙሪያ መወያየት ብቻ በቂ ነው። በጠረጴዛ ዙሪያ በሚደረጉ ውይይቶች ችግሮችን የመፍታት ባህል ባለማዳበራችን ምክንያት ችግሮቻችን ከአንድ ትውልድ ወደ ሌላው እየተሻገሩ ለሴራ ፖለቲካ አቅም ሆነው ቆይተዋል።

መነጋገር፣ መደማመጥ በሌለበት መተማመን ስለማይኖር ችግሮች የመፍትሔ ያለህ እያሉ ዓመታት ማስቆጠራቸው የማይቀር ነው። በዚህም፣ የችግሮቹ ባለቤት የሚጠበቅ ሆነ የማይጠበቅ ዋጋ ከመክፈል ሊታደግ የሚችል አይኖርም። ልክ በ1960ዎቹ እንደነበረው ከ50 አመትም በኋላ አሀዳዊና ፌዴራሊስት እየተባባሉ መካሰስ የዛሬም ትውልድ ዕዳ ከመሆን የሚያልፍ አይሆንም።

በቀደሙት ዘመናት ከመጣንበት ኋላቀር የፖለቲካ አስተሳሰብ አንጻር፣ ፖለቲካችንን በዕውቀት እና ሞግቶ ከማሸነፍ ላይ ከመመስረት ይልቅ ዛሬም ደምና አጥንትን እየቆጠሩ ሥልጣን ለመቆናጠጥ በሚደረጉ ሙከራዎች ጥላ ውስጥ ስለመኖሩ ያለፉት ሦስት አመታት ተጨባጭ ማሳያ ናቸው ።

ይህ ትውልድ እንደ ትውልድ /ሀገርም እንደሀገር ካለፈው ትውልዶች የወረሰቻቸው ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ዕዳዎችን ብቻ ሳይሆን የፖለቲካ ዕዳም ጭምር ነው። ይህን ዕዳ መክፈል በዚህ ትውልድ ጫንቃ ላይ ወድቋል።

የአስተዳደር ወሰን ጥያቄ፣ የማንነት ጥያቄ፣ የብሔር ጥያቄ፣ የቋንቋ ጥያቄ፣ የሃይማኖት ጥያቄ ወዘተ እየተባለ ለሚቀርቡ ትናንት ላልተመለሱ ስፍር ቁጥር ለሌላቸው ጥያቄዎች ተገቢውን ምላሽ መስጠት የዚህ ትውልድ የቤት ሥራ ሆኗል።

እነዚህ ያደሩ የቤት ሥራዎች ደግሞ በአንድ ጀንበር ተመልሰው የሚያልቁ አይደሉም። ጊዜ ያስፈልጋቸዋል። በኢትዮጵያ ውስጥ የብሔር ጥያቄ በይፋ ለውይይት ከቀረበ ከሃምሳ ዓመታት በኋላ፣ ጥያቄው በአግባቡ መልስ ባለማግኘቱ ዛሬም ድረስ የብሔር ነፃ አውጪዎች ነፍጥ አንስተው ጫካ መግባት ፋሽን ከመሆን አላለፈም።

ከሁሉ የከፋው ደግሞ የብሔር ጥያቄና የነፃ አውጪነት መንፈስ ዛሬ የተፈጠረ በማስመሰል በዛሬው ትውልድ ላይ ክስ የሚያሰሙ ፖለቲከኞችና አክቲቪስቶች መብዛታቸው ነገሩን የበለጠ አስገራሚ ያደርገዋል።

ቢያንስ የዛሬው ትውልድ የወረሰውን ዕዳ እንዲከፍል ጊዜ መስጠትና መደገፍ አንድ ነገር ሲሆን፣ ካልተቻለም ተበዳዩን በዳይ ከሚያደርግ ፍረጃ መውጣት ኅሊና ካለው አንድ ዜጋ የሚጠበቅ ተግባር መሆን አለበት።

አዲስ ዘመን   ኅዳር 19 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You