“ድሮ” ላይ መቸከል የፖለቲካ ቆሞ ቀርነት ነው

ግዜ አንድ ቦታ ቆሞ አይጠብቀንም። የእኛም እድሜ እንዲሁ። ቀን አልፎ ቀን ሲተካ፤ ወራት ወራትን እየቀየሩ ዓመታት ሲቆጠሩ የተወለደው ያድጋል፤ ጎረምሳውም ይጎለምሳል፤ ጎልማሳውም ወደ እርጅናው ተጠግቶ፣ ያረጀውም እንደየጥሪው ወደማይቀረው ዓለም ይሄዳል። ይህ የተፈጥሮ ጠባይ የሕይወት ኡደትና ጥሬ ሀቅ ነው። ይህንን የተፈጥሮ ግዴታ “አልቀበልም አሻፈረኝ!” ብሎ በቆመበት የሚቀርም የለም፤ ሊኖርም አይችልም። የሚሞክር ቢኖር እንኳን ተፈጥሮ እራሷ ሳይወድ በግድ እጅ እንዲሰጥ ታስገድደዋለች።

በዚህ ኡደት ውስጥ እድሜ መቁጠር አልያም በአካል መግዘፍ ብቻ በቂ አይደለም። በአስተሳሰብም ላቅ ማለት ያሻል። ከእለት እለት የተሻሉ ነገሮችን እየጨመሩና እራስን እያሻሻሉ መሄድ ይገባል። ዛሬ ልጅ የነበረው ነገ በጊዜ ሂደት በአካልም በአእምሮም ያድጋል። ክፉ ደጉን ለይቶ ለራሱ፣ ለቤተሰቡና ለአገሩ ጠቃሚ ዜጋ ይሆናል።

ግዜ ለሁላችንም እኩል የተሰጠ ከተጠ ቀምንበት እንደ አመጣጡ ካስተናገድነውም ብዙ የምናተርፍበት ነው። በጊዜ ውስጥ ሰው ብቻውን አይቀየርም። ዘመንም እንዲሁ የራሱ እሳቤና ስልጣኔን ይይዛል። የወል እሳቤ “ፋሽን” ይመጣል። በዚህ ግዜ “አይ እኔ ዘመኑን አልመስለም፤ አልከተ ልምም፤ የቀደመው ይሻለኛል” ካልን ለውጥን የምንቃወም የቀደመው እሳቤና የዘመን ላይ የተቸከልን ያደርገናል። ለዚህ ሁሉ አባባሌ መነሻ የሆነኝ ቁምነገር “እንደ አገርም ሆነ እንደ ማህበረሰብ አሁን ላይ ግዜ የደረሰበት ስፍራ ላይ ደርሰናል? ግዜ የሚጠብቅብን ንቃተ ህሊናስ አለን ?” የሚለው ጥያቄ በውስጤ ስለሚመላለስ ነው።

የ21ኛው ክፍለ ዘመን የቴክኖሎጂ የፈጠራ ብሎም ከፍ ያለ የስልጣኔ ዘመን ነው። ይህ ሁሉም ጤነኛ አእምሮ ያለው ሊስማማበት የሚችል የወል እውነት ነው። ዓለም ተቀይራለች። መቀየር ብቻ ሳይሆን በዘመናዊ አስተሳሰብና ስልጣኔ ተሻሽላለች። ግራ አጋቢው እውነታ ግን በዚህ ዘመን ላይ እየኖሩ ትናንት ላይ ተቸንክረው መንቀሳቀስ ያልቻሉ ሰዎች የመኖራቸው ጉዳይ ነው። ይበልጥ የሚያሳስበው ደግሞ በእድሜ ገፍተው፤ በአካል ገዝፈው “ተምረዋል ተመራምረዋል” የሚለውን ማእረግ ደርበው በዚህ እውነት ውስጥ የመገኘታቸው ጉዳይ ነው።

በተለይ በዚህ ዘመን ያሉ አብዛኞቹ ኢትዮጵያዊ ፖለቲከኞቻችን የቆሙበትን/የሚኖሩበትን ዘመን የሚዋጅ ማንነት አላቸው? ዓለም በስልጣኔ፣ በእውቀት፣ በቴክኖሎጂ፣ በኢኮኖሚ እንዲሁም በፖለቲካ የት እንደ ደረሰስ ያውቃሉ? ሚስጥሩንስ ተገንዝበዋል የሚለው ጥያቄ አብዝቶ በውስጤ ይመላለሳል።

ለአመክንዮው መሰረት የሆነኝ ዛሬም ድረስ የፖለቲካዊ ቅራኔያቸውን (ልዩነታቸውን) በሰላማዊ መንገድ በውይይት የመፍታት ፍላጎቱን በማጣታቸው ምክንያት ነው። ከዛ ይልቅ ፈጥነው ማኩረፍ፤ ወደ ግጭት የሚወስዱ መንገዶችን መምረጥ፣ አብዝቶ የሚታይባቸውና ዋነኝ የባህሪያቸው መገለጫ እንደሆነ በሙሉ ልብ መናገር እችላለሁ። በሁለተኛነት እነዚህ አካላት እንወክለዋለን ለሚሉት ሕዝብ ከልብ የመነጨ በጎ ሀሳብ ሳይሆን በስሙ መነገድ የሚፈልጉ መሆናቸው ከስሪታቸውና ባህሪያቸው መገንዘብ ይቻላል። ይህ ባህሪያቸው ዘመኑን የሚዋጅ ነው ብሎ ማሰብ የሚቻል አይመስለኝም።

የፖለቲካ ምሁራን “ፖለቲካ በስሜት ሳይሆን በስሌት የሚሰራ ነው” ይላሉ። እኔም በዚህ ሀሳብ እስማማለሁ። የሰው ሕይወት እያስያዙ ቁማር በመቆመር የሚገኝ ፖለቲካዊ ትርፍ የለም። በንጽሀን ተስፋና ደም ከመነገድ ባለፈ ትርጉም ያለው ፖለቲካዊ ትርጓሜ ሊሰጠው የሚችል አይደለም። መጨረሻውም የዜሮ ድምር ከመሆን አያልፍም።

ኢትዮጵያውያን እንደ አገር ብዙ ጦርነቶችና አለመረጋጋቶችን አሳልፈናል። ለዚህ ምክንያቱ እንደ ማሕበረሰብ ቁጭ ብለን በችግሮቻችን ዙሪዩ መወያያት አለመቻላችን ነው። ችግሩ ዛሬም ዘመንን ተሻግሮ ያለቀቀን ትልቁ በሽታችን ሆኖ ቀጥሏል። አሁንም በጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጠን፣ በችግሮቻችን ላይ ተወያይተን፣ ቆምንለት የምንለውን ሕዝብ ደህንነት ከማስጠበቅ ይልቅ ነፍጥ አንግበን አገርን ማወክን ምርጫችን አድርገናል።

በተለይም በአገራቸን ያሉ “ነጻ ያልወጡ ነጻ አውጪዎች” “ሰላም ይሻላል” ሲባሉ ጦርነት ምርጫቸው ያደረጉ ናቸው። እኔም እነዚህ አካላት እንዴት መኖር እንዳለባቸው ያልተገነዘቡ ከግዜው እሩቅ ወደኋላ የቀሩ ይመስሉኛል። ያለንበት ዘመን ይህንን የሚፈቅድ አይደለም። ግዜው ያመጣውን ዘመናዊ እድሎችን ሁሉ ተጠቅሞ ሰላምን ማስቀደም ከምንም በላይ ተጠቃሚ ያደርጋል።

የኢፌዴሪ መንግሥት ከአንድ ዓመት በፊት ከሕወሓት ጋር በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ባደረገው የሰላም ስምምነት ለሁለት ዓመት የዘለቀው ጦርነት እልባት ማግኘቱ የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው። ከጦርነት ማንም አያተርፍም። በውይይትና በመነጋገር ሰላምን ማስቀደም ስልጡንነት ነው። በዚህ ምክንያት መንግስትም ሰላም ወዳድ ሆኖ ያቀረበው የእንስማማ ጥያቄ ብዙ ነገሮችን ቀይሯል። ከጠፋው የበለጠ ውድመት እንዳይከሰት ብልህ ውሳኔ ወስኗል።

ዛሬም ግን በተለያዩ አካባቢዎች ድሮ ላይ ቆመው አስተሳሰባቸውን ወደዛሬው ነባራዊ ሁኔታ ማምጣት የተሳናቸው የጦር ሰባቂዎች አሉ። ከአንዴም ሁለት ጊዜ ለድርድር ተጠርተው ነበር። ለድርድር ጠረጴዛ ላይ ቁጭ እንዲሉ ረጅም መንገድ መጓዝ ቢቻልም፤ የሚያቀርቡት ሃሳብ ውሃ ቢወቅጡት አይነት ሆኖባቸው እነሆ ሳይሳካ ቀርቷል።

ይህ በእውነቱ በጣም የሚያሳዝን ከማሳዘንም አልፎ የሚያሳፍር ተግባር ነው። በባህላችን “ተበደልኩ” ባይና “በደልህን አስረዳ፤ የበደለህም ይካስህ” ሲባል በደሉን አስረድቶ የሚፈለገውን በግልጽ ተናግሮ በዚያኛው ወገን ያለውም አለኝ የሚለውን ሃሳብ አቅርቦ፣ አሸማጋይም መካከል ሆኖ “ከናንተ ይቅር” በማለት የሚበጀውን ሲወስን አልቀበልም ማለት ነውር ነው። ይህ እንደውም የሚያሳየው ከመጀመሪያውም ተበዳዩ ይዞት የቀረበውን ሃሳብ አያምንበትም አልያም ምናባዊ ነበር ማለት ነው።

ይህም ቢሆን ግን ዛሬም በዚህ አለመግባባት ተጎጂዎቹ እኛው ነን። ነጻ አውጪውን ጨምሮ፤ አገራችን አንድ እርምጃ ወደፊት ሁለት እርምጃ ወደኋላ እየተጎተተች ዜጎቿ ለእልቂት ለመፈናቀልና ለስደት እየተዳረጉ በአሳር በመከራ የሚገኘው ሀብት እየባከነ ሕዝብ ሁሌም በድህነት አረንቋ ውስጥ እንዲዘፈቅ እየሆነ ነው። በመሆኑም ሁሉም ነጻ አውጪ ኃይል የቆመበትን ዘመን ታሳቢ በማድረግ የኋሊት መንፏቀቅን በመተው ወደፊት በሚያራምዱ ሃሳቦች ዙሪያ ማተኮሩ ውጤታማ ያደርጋል።

ይህ ካልሆነ ግን ሁሌም ዘመን ይቀየራል ሌሎች አለማትም ጥለውን ይነጉዳሉ እኛ ግን በጦርነት አረር እየተጠበስን በረሃብ አለንጋ እየተገረፍን ለመቀጠል እንገደዳለን። ይህ ደግሞ ነጻ አውጪውንም ሆነ ሌላውን አካል የሚጠቅም አይደለም። እንደ ሀገርም ብሄራዊ ክብራችንን እየሸረሸረው የበለጠ አንገት የሚያስደፋ ችግር ውስጥ የሚከተን ነው።

በመንግሥት በኩል “ሕገ መንግሥቱንና የሀገሪቱን ሉዓላዊነት ለመቀበል ዝግጁ ከሆነ ከማንኛውም ኃይል ጋር በውይይት ችግሮችን ለመፍታት ያለማሰለስ ጥረት አደርጋለሁ” ባለው መሰረት ጥረቶችን አደርጎ እያሳየን ነው። ለምሳሌ ያህል በሆደ ሰፊነት በአገራችን በተገለጠ የሽብር ስራው ከሚታወቀው የሸኔ ሽብርተኛ ቡድን ጋር ያለውን አለመግባባት በሰላማዊ መንገድ በድርድር ለመፍታት ረጅም ርቀት ሄዷል።

ወገን እንዴት ነው ነገሩ! ከዛሬ 60 ዓመታት በፊት የነበረን የኦሮሞና የሌሎች የኢትዮጵያ ብሔረሰቦች ጥያቄዎችን ይዞ ዛሬ ላይ ጦር መማዘዝ ውጤታማ ያደርጋልን ? እኔ እንደሚገባኝ እነዚህ ጥያቄዎች ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ተመልሰዋል። ያልተመለሱም ካሉም የአንድ አገር ዜጎች ነንና “ቢዘገይም አይረፍድም” እንደሚባለው በሰላማዊ መንገድ እንዲመለሱ ማድረጉ የተሻለ አማራጭ ነው። በዚህ ዘመን አውዳሚ በሆነው ጦርነት ጥያቄ ለማስመለስ ጥረት ማድረግ ወደ አሮጌው ዘመን በፍቃደኝት ከመመለስ ተለይቶ የሚታይ አይሆንም።

ከዛሬ 60 ዓመት በፊት የነበረ ታሪክ ወይም ጥያቄ እያመዘዙ ሕዝብን ሰላም ከመንሳት፣ በሕዝቦቻችን መካከል አለመተማመን ከመፍጠር፣ ዘመኑን በሚዋጅ የፖለቲካ አስተሳሰብና ስልጡን መንገድ፤ ለሀገርና ለሕዝብ የሚበጅ፣ የቀጣዩን ትውልድ ነገዎች ብሩህ የሚያደርጉ ተሻጋሪ አስተሳሰቦችን ይዘው መንቀሳቀስ ያስፈልጋል። የሕዝባችንም ፍላጎት ከዚህ የተለየ አይደለም።

መንግስት አገር አማን ብሎ ከተሰደዳችሁበት ሰብስቦ አብረን እንስራ ማለቱ የሚያስመሰግነው ነው። አሁን ላይም ቢሆን “ችግራችሁ ምንድን ነው ኑ እንነጋገር” በገለልተኛ አካል እንሸማገል ማለቱ ኢትዮጵያዊ ጨዋነቱ ከመሆኑም በላይ ዘመንን ቀድሞ የተረዳ ዘመንን የዋጀ አካሄድ ነው። “ሰላም አያሻኝም ጥያቄዬን ሁሉ በጦር ታጅቤ ሕዝብ እያሰቃየሁ እፈጽማለሁ” ለሚሉ ወገኖች ትዕግስትም ልክ እንዳለው እንዲገነዘቡት ማድረግ ያስፈልጋል።

መንግስት በሀገሪቱ ሰላም ሰፍኖ ኢትዮጵያ ያላትን የተፈጥሮ ጸጋዎች ወደ ሀብትና አቅም ቀይራ ብልጽግናዋን ታረጋግጥ ዘንድ ካለው ጉጉት በመነጨ ከግማሽ መንገድ በላይ ተጉዞ ለጉዳዩ እልባት ለመስጠት ሞክሮ አልተሳካም። በመሆኑም “ምከረው ምከረው እምቢ ካለ መከራ ይምከረው” ነውና ብሂሉ አሁን እንደ ሕዝብ የመንግስትን ቆራጥ እርምጃ ማየት የሚያሻን ወቅት ላይ እንደምንገኝ አምናለሁ።

ከቁርጠኝነትም ባሻገር የዜጎችን ሰላምና ደህንነት የማስከበር ኃላፊነቱን ከምን ጊዜውም በላይ የሚወጣበት ወሳኝ ምዕራፍም ነው። በመሆኑም መንግስት ስለትዕግስቱና ስለሰጠው እድል ሁሉ እንደ ሕዝብ ክብር እየሰጠን በቀጣይ ግን “ሰላማችን ይረጋገጥ፤ ወጥቶ የመግባትና በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች ተንቀሳቅሶና ሰርቶ የመኖር መብታችን ይከበር ዘንድ ኃላፊነቱን ይወጣልን” ስንል ጥያቄያችንን እናቀርባለን። አበቃሁ!

 በእምነት

አዲስ ዘመን ህዳር 18/2016

Recommended For You