በማስተዋል ያልተደገፈው የዋጋ ጭማሪ

ሁሉም ነገር ደርዝ አለው። ሁሉም ነገር ልክ አለው። ደርዝ የሌለው፤ ልክ የሌለው፤ በማስተዋል ያልተደገፈ ነገር ሁሉ፣ ይዋል ይደር እንጂ ለማንም አይበጅም።

አሁን አሁን እየታየ ያለው ነገር ሁሉ ይኸው ነው፤ ደርዝ የለውም፤ ልክ የለውም፤ በማስተዋል የተደገፈ፣ በግንዛቤ የተቃኘ፣ ኢትዮጵያዊ ባሕልንም ሆነ ማንነትን (የኢኮኖሚንም ይሁን ሌላ) ያገናዘበ አይደለም።

ይሉኝታ የለውም፤ ወገናዊነት አይታይበትም። “እኔ ከሞትኩ ∙ ∙ ∙” እንዳለችው እንስሳ ሊሆን የቀረው ምንም ነገር የለም። ጉዳዩን በአንድ ነገር ላይ ብቻ አተኩረን እንመልከተው።

ይህ ጸሐፊ ስራውም ውሎውም 4 ኪሎ ነው። የድሮውን እንተወውና የአሁኑን ዘመን አራት ኪሎ በሚገባ ያውቀዋል። ያሉት ነገሮች በቤት ቁጥር፣ በንግድ መደብር ደረጃ ይታወቃሉ።

በመሆኑም፣ ምን ስንት ነበር፤ አሁን ስንት ገባ? ስንት ጭማሪ አሳየ፣ ምክንያቱስ? የሚሉትን ሁሉ (ያው የኪስ ጉዳይ ነውና) ይታወቃሉ። በመሆኑም፣ ጤነኛውን ከበሽተኛው መለየት ላይ ችግር የለም ማለት ነው። የጀበና ቡናን ወስደን እንመልከት።

የጊዜ፣ የዘመን ጉዳይ ሆነና ገበያውን የተቆጣጠረው የጀበና ቡና ነው። እኛ መጀመሪያ የጀመሩት ሴትዮ ምስጋና ይግባቸውና ዛሬ የጀበና ቡና ከትላልቅ ቢዝነሶች ተርታ እየተሰለፈ ነው። በተለይ ከታክሲና መሰሎቹ ነፃ መሆኑ ባለቤቱን ፈርጠም ለማድረግ ጊዜ አይፈጅበትም።

ይህ ባልከፋ። ሰርቶ ማግኘት የሚጠበቅ ነውና ያስደስታል። ነገር ግን ይህ “ሰርቶ ማግኘት”፤ “ነግዶ ማትረፍ” የሚሉት ነገር እያወዛገበ የመሆኑ ጉዳይ ነው። የዚህ ምክንያቱ ደግሞ ገበያው ከስነምግባር ማፈንገጡ ብቻ ሳይሆን፣ በዘርፉ የሚታዩ ተግባራት በማስተዋል የሚከናወኑ ሲሆኑ አለመታየታቸው ነው።

እዚህ 4 ኪሎ የጀበና ቡና፣ የአንዱ ስኒ ዋጋ ግራ በሚያጋባ ደረጃ በየቀኑ ለማለት ቅር እስከማይል ድረስ ዋጋው እየተቆለለ፤ ለጠጪው ሳይሆን ለራሱ፣ ለሻጩ ሳይቀር እየገረመው ይገኛል።

ከወር በፊት 15 ብር የነበረ የአንድ ስኒ የጀበና ቡና ዋጋ፣ ምንም ሳይታሰብ 20 ላይ ጉብ ብሎ ተገኘ። ይህ አይደለም የሚገርመው፤ የሚገርመው በ20 ከሳምንት በላይ ሊዘልቅ ሳይችል ቀርቶ እነሆ 25 ብር ላይ ተገማሽሮ ተቀምጧል። “ምክንያት?” ሲባል፣ ምንም፤ ዝም፣ ጭጭ።

በመሰረቱ፣ ፎቆች ኮሪደሮቻቸው ለሕንፃው ተጠቃሚዎች መንቀሳቀሻ ይሆኑ ዘንድ ታስበው ነበር የተገነቡት፤ መሆን ያለበትም ያ ነበር። እሱ ቀረና እያንዳንዷ ካሬ ተሸንሽና (የየመፀዳጃ ክፍሎቹ ፊት ለፊት ሳይቀር) ለጀበና ቡናና ኮስሞቲክስ “መደብር” ተከራየች። ያ ሌላ ታሪክ ነውና ወደ ቡናችን እንመለስ።

አንዳንድ የጀበና ቡና ነጋዴዎች ለዋጋ መጨመር ምክንያታቸውን ሲያስቀምጡ “ኪራይ ጨመሩብን” የሚል ነው። እንደዚህ ፀሀፊ ከሆነ ይህ በፍፁም አያሳምንም። ወይም፣ እንደዛ የሚያደርግ ባለ ፎቅ ካለ፤ በየ15 ቀኑ ኪራይ የሚቆልል ባለሀብት ከሆነ እሱ በቀጥታ ወደ አማኑኤል ማቅናት ይገባዋል።

ምክንያቱም፣ መቸም አይደለም የሕንፃ ኮሪደር፣ የሕንፃው ቢሮ እንኳን ቢሆን ቢያንስ ከሁለት ዓመት በታች ውል የለምና ነው። በመሆኑም የባለ ጀበናዎቹን ዋጋ መጨመር ከኪራይ መጨመር ጋር ማያያዝ ውሀ የሚቋጥር አይሆንም።

አንድ ባለ መደብር አዛውንት በዚሁ ጉዳይ ላይ ስናወራ የተናገሩት ነገር ለቁም ነገር የሚበቃ ነው። “አዛውንቱ የዛሬ ነጋዴዎች አንድ ነገር ይይዛሉ፤ ከእሱው ላይ ስንጥቅ በማትረፍ መክበር ይፈልጋሉ። ንግድ እንደሱ አይደለም። በንግድ ዓለም ትርፍ የሚገኘው ከብዛት ነው። የሸቀጥ፣ እቃዎችን አይነት ማብዛት፤ ከእነዛ ላይ መጠነኛ ትርፍን ማግኘት። ያ ተሰባስቦ ነው ትርፉን ጥሩ የሚያደርገው” ነበር ያሉት።

እውነታቸውን ነው። ከዛ በኋላ ልብ ብለን ስንመለከት ያየነው ነገር ቢኖር እሳቸው ያሉትን ነው። አብዛኛው ነጋዴ ሸቀጦችን በብዛት የያዘ ነው። ሱቆች ተቆጥሮ የማያልቅ ሸቀጦች አሏቸው። ቡና ቤቶች፣ የልብስ መደብሮች ወዘተ በርካታ አይነቶችን ነው ይዘው የሚቀርቡት።

ወደ ጀበና ቡና ነጋዴዎች ስንመጣ ግን አብዛኞቹ ቡና ብቻ እንጂ፣ ሻይ እንኳን የላቸውም። ብስኩት፣ ሳንቡሳ፣ የፕላስቲክ ውሀ ∙ ∙ ∙ አያቀርቡም። ማስቲካ፣ የሞባይል ካርድ ወዘተ የላቸውም። ሙሉ ለሙሉ ማትረፍ የሚፈልጉት ከአንድ ነገር ብቻ ነው፤ ከቡናው።

እድሜ ለባለ ጀበና ቡና ባለቤቶች፣ ዛሬ ዛሬ የቡና አገር ሰው ሆኖ ቡና የማይጠጣው ሰው ቁጥሩ እየበዛ እየሄደ፤ የሚጠጣው ሰው እየቀነሰ ነው። አንድ ስኒ ቡና 25 ብር ከሆነ፤ እንዴት ሆኖ ነው ሁሉም ሰው፣ በተለይም የቡና ሱስ ያለበት ሁሉ በ25 ብር አንድ ስኒ ቡና የሚጠጣው? በቀን አራት ጊዜ እንጠጣ ብንል እኮ 100ዋን ቁጭ አደረግን ማለት ነው። ይህ ለብዙሀኑ የሚቻል ነው?

እዚህ ላይ አንድ በጣም የሚገርም ጉዳይ አለ። አብዛኞቹ የጀበና ቡና ነጋዴዎች በአንድ ሰው የሚስተናገዱ ናቸው። “የሰራተኛ ደሞዝ” ይሉ ጣጣ የለባቸውም። አጨማመራቸው ግን 5 ብርን በአንድ ብር ቦታ በማስቀመጥ ነው ዋጋ የሚቆርጡት።

ገና ለገና አዲስ አበባ የሰው ጫካ ሆናለችና ከዚህ ሁሉ ውስጥ ለኔ የሚሆን አላጣም ከሚል የተሳሳተ መነሻ ሁሉ ይመስላል ነግቶ ሲመሽ ዋጋ መቆለል ነው፤ 4 ኪሎ እየሆነ ያለው ይሄ ነው።

ዛሬ እኮ ትንሹ የጀበና ቡና ዋጋ (በስኒ) 15 ብር ነው – የሚረባውም፣ የማይረባውም፤ በመንግስት ቤት የሚነግደውም፣ በሰው መሄጃ መንገዶች ላይ ላስቲኩን ወጥሮ ቁጭ ያለውም፤ ቀበሌውም። ሁሉም ከማን አንሼ ነው መሰለኝ ስራቸው ገበያ ማረጋጋት ሳይሆን ገበያውን ማጦዝና አብዛኛውን የማሕበረሰብ ክፍል ከገበያ ማስወጣት ነው።

የድሮዋ እናት 4 ኪሎ ዛሬ ይሄንን ነው የምትመስለው። መጨመር፣ መጨመር፣ የት ጋ ስምምነት ላይ እንደሚደርሱ ባይታወቅም በተመሳሳይ ሰዓትና ቀናት ሁሉም ተመሳሳይ የዋጋ ጭማሪ ላይ ይገኛሉ። እፍረት የለም፤ በ4 ኪሎ ሰሞኑን እየታየ ያለው ይሄ ነው።

አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ አንድ ስኒ የጀበና ቡናን ከ15 ብር አንስቶ 25 ላይ ማድረስ ምን ይባላል፤ የጤና ነው? በዚህ ከቀጠለስ ምን አይነት ኢኮኖሚያዊ እድገት ይመልሰዋል?

እዚህ ላይ አንድ ነገር ልብ ማለት ያስፈልጋል፤ ሻጭም በተመሳሳይ ሁኔታ ሸማች መሆኑን። ግሽበት አገርን ነውና የሚጎዳው እሱ በጆንያ ሰበሰብኩ ሲል መልሶ በጆንያ ወስዶ ያስረክበዋል። በቃ፣ ይኸው ነው።

ከሁሉም በፊት፣ ሁላችንም ከመጎዳታችን በፊት፤ አብዛኛውን የሕብረተሰብ ክፍል ከገበያው ከማስወጣታችን በፊት ∙ ∙ ∙ በፊት ∙ ∙ ∙በፊት፤ ቆም ብለን ልናስብ፣ ውሳኔዎቻችንንም በማስተዋል ልናደርግ ይገባል። ባጭሩ፣ የአቦይን ትዝብታዊ አነጋገር እንዋስና በ“እየተስተዋለ” ትዝብታችንን እናጠቃልል።

ግርማ መንግሥቴ

አዲስ ዘመን   ኅዳር 18 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You