
አዲስ አበባ፡- በኢትዮጵያ እና ቻይና ባለሃብቶች ትብብር በስድስት ቢሊዮን ብር ወጪ የብረታብረት ማምረቻ ኢንዱስትሪ በትግራይ ክልል ሊገነባ መሆኑ ተገለጸ። በአስር ወራት ውስጥ የሚገነባው ይህ ኢንዱስትሪ የሥራ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ትናንት ይፋ ተደርጓል።
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት ጌታቸው ረዳ በመርሐ ግብሩ ላይ እንዳሉት የሌጀንድ ብረታብረት ኢንዱስትሪ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ለበርካታ ወጣቶች የሥራ ዕድል የሚፈጥር በመሆኑ አስፈላጊው ድጋፍ ይደረግለታል።
ሌሎች በግልና በማኅበር የተደራጁ ባለሃብቶችም የዚህን የልማት ፕሮጀክት አርዓያ ተከትለው በማልማት ራሳቸውንና ሀገራቸውን እንዲጠቅሙ መልዕክት አስተላልፈዋል። የብረታብረት ማምረቻው 75 በመቶ በኢትዮጵያዊው ባለሃብት ኢንጅነር ያሬድ ተስፋይ የተሸፈነ ሲሆን ቀሪው 25 በመቶ ደግሞ በቻይናዊው ባለሃብት ሚስተር ሊ ዮን መሸፈኑን የፕሮጀክቱ አስተባባሪ አቶ ሳምሶም ገብረመድህን ገልጸዋል።
የሌጀንድ ብረታ ብረት ማምረቻ ኢንዱስትሪ 6ሺህ ለሚሆኑ ወገኖች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥርም ተናግረዋል። እንደ ኢዜአ ዘገባ የመቀሌ ከተማ ከንቲባ ይትባረክ አመሐ በበኩላቸው ከተማ አስተዳደሩ ለሌጀንድ ብረታብረት ኢንዱስትሪ አሁን ከተሰጠው የግንባታ ቦታ ባለፈም ቀጣይነት ያለው ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ህዳር 18/2016