በዓባይ ወንዝ ላይ፣ ሕልም በሃሳብ ተደግፎ፤ ምኞትን በትልም ተነድፎ፤ ትልም በተግባር ተቀይሮ፤ ድሮ ሕልም የነበረው ዛሬ በብርሃኑ ወጋገን ማራመድ ሲጀምር፤ የትውልድ ባለታሪክነት፣ የመሪነትም ልዕልና ተገልጧል፡፡ ምክንያቱም ቀደምቶቻችን አስበውና አልመው በንድፍ ያኖሩት ዓባይ፤ ዛሬ በእኛ ዘመን ንድፉን ተመልክተን፣ ሕልምና ምኞታቸውን ተላብሰን ዓባይን ለኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫነት እንዲውል ገድበን የታለመው ብርሃን እውን እንዲሆን አድርገናል፡፡
ይሄን ስናደርግ ቀደምቶቻችን የተፈተኑበትን ችግር በመገንዘብ፤ በልመና ሳይሆን በራስ አቅም ለመገንባት የፋይናንስ ምንጭ ራሳችን እንድንሆን ተልመን ነው፡፡ የቀደሙትን ሕልምና ትልም ወደ ተግባር መለወጥ የቻለው የዛሬው ትልውድ ታዲያ፤ በራሱ ተልሞ ሊተገብር ያሰበውን ከመፈጸም የሚያግደው የለምና በራሱ የፋይናንስ አቅም ጀምሮ እነሆ በብርሃን ታጅቦ ወደ ፍጻሜው ጫፍ ደርሷል፡፡
በዚህ መልኩ መንግስት እና ሕዝብ ተባብረው ለመገንባት የወጠኑት የዓባይ ግድብ፤ መንግስት ለግንባታው ካዋለው ወጪ ውስጥ ከ18 ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ብር በላዩ ኢትዮጵያውያን ከሕጻን እስከ አዛውንት፣ ከጉልት ቸርቻሪ እስከ ባለሃብት፣ በሀገር ውስጥም ከሀገር ውጪም ያሉ ኢትዮጵያውያን ተባብረው ለዚህ ግድብ እንዲውል ያዋጡት ገንዘብ ነው፡፡
ኅብረተሰቡ በልገሳ፣ በቦንድ ግዢ፣ በቶምቦላ፣ በአጭር የጽሑፍ መልዕክት (8100 A)፣ በሕዳሴው ዋንጫ እና በሌሎችም መንገዶች ግንባታው እውን ከሆነበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን ድረስ ድጋፋቸውን እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ ተማሪው ከወላጆቹ የምትሰጠውን የኪስ ሳንቲም ቆጥቦ፤ የመንግስት ሰራተኛው ከወር ደመወዙ አርሷደሩ ከምርቱ ቀንሶ፤ አርብቶ አደሩ ከእንስሳቱ ቆጥሮ፤ ነጋዴው ከትርፉ አውጥቶ፤ ዳያስፖራውም ባለበት አቅሙ የፈቀደውን ተሳትፎ አድርጎ ሁሉም አለኝታነቱን አረጋግጧል፡፡
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ነሐሴ 17 ቀን 2014 ዓ.ም የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ሀብት ማሰባሰብ የሕዝብ ድጋፍን አጠናክሮ የማስቀጠል እንቅስቃሴን በተመለከተ ባወጣው መግለጫ እንዳመለከተው፤ ባንኩ ለግድቡ ግንባታ እና ለኃይል ማስተላለፊያ ግንባታ ፕሮጀክት የሚውል ከ149 ነጥብ 82 ቢሊዮን ብር በላይ ብድር በማቅረብ የግድቡን ፍጻሜ እውን እያደረገ ይገኛል።
ከዚህ ባሻገርም ዜጎች ለግድቡ የሚያደርጉትን ድጋፍ የማሳለጥ ተግባርን እየከወነ ሲሆን፤ በዚህም እ.ኤ.አ እስከ ሰኔ 30/2022 ድረስ በብር እና በውጭ ሀገር ገንዘብ ለሕዳሴው ግድብ የተደረገው ሃብት ማሰባሰብ ተግባር ጉልህ ነው፡፡ በዚህም በባንኩ በኩል ከስምንት ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ብር በላይ የቦንድ ሽያጭ ተከናውኗል፡፡ ከ208 ሚሊዮን ብር በላይም ለግድቡ ግንባታ የሚውል ገንዘብ ከዜጎች በልገሳ ተገኝቷል፡፡
በተመሳሳይ መልኩ፣ ከውጪ ሀገር ቦንድ ሽያጭ በውጪ ምንዛሬ 37 ሚሊዮን ዶላር፣ ሦስት ነጥብ ሦስት ሚሊዮን ዩሮ፣ እና አንድ ነጥብ አንድ ሚሊዮን ፓውንድ ገቢ ተደርጓል፡፡
በሌላ መረጃ ደግሞ፣ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የግድቡ ግንባታ አፈፃፀምና የመሰረት ድንጋይ የተቀመጠበትን 12ኛ ዓመት በዓል አከባበር በተመለከተ በ2015 ዓ.ም ማገባደጃ ላይ ምክክር ባደረገበት ወቅት እንደተገለጸው፤ የግድቡ የመሰረት ድንጋይ ከተቀመጠበት ጊዜ ጀምሮ 18 ቢሊዮን ብር በተለያዩ መንገዶች ለግድቡ ግንባታ ከኅብረተሰቡ መሰብሰብ ተችሏል፡፡
ይሄ ደግሞ ሕዝቡ ለግድቡ ከፍጻሜ መድረስ እያደረገ ያለው ተግባር በእጅጉ ከፍ ያለ መሆኑን የሚጠቁም ሲሆን፤ ይሄው የሕዝብ ተሳትፎ (በገንዘብም፣ በጉልበትም) እንደ እስካሁኑ ሁሉ በዚህ በጀት ዓመትም ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ የዚህ ማሳያው ደግሞ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት በ2016 በጀት ዓመት ለመሰብሰብ ካቀደው ከአንድ ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ብር ውስጥ፤ በበጀት ዓመቱ ሁለት ወራት ብቻ በተለያየ መንገድ ከ297 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰብ መቻሉ ነው፡፡ እስካሁንም ከ18 ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ብር በላይ በተለያየ አግባብ መሰብሰብ ተችሏል፡፡
በዚህ መልኩ ሁሉም ዜጎች፣ ሁሉም የከተማ አስተዳደሮች፣ ሁሉም ክልሎች የየራሳቸውን ዐሻራ እያሳረፉ ይገኛል፡፡ ከሰሞኑም የኦሮሚያ ክልል እንዳስታወቀው ደግሞ፣ በዚህ ዓመት እንደ ክልል አንድ ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ብር ለዓባይ ግድብ ግንባታ የሚውል ሃብት ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሰራ ይገኛል፡፡ ለዚህም “ቃላችንን እናድሳለን” በሚል መሪ ሃሳብ በክልል ደ ረጃ ለግድቡ ግንባታ የሀብት ማሰ ባሰቢያ ንቅናቄ ተ ጀምሯል፡፡
በ2015 ዓ.ም በክልሉ ከአንድ ነጥብ ስምንት ቢሊዮን ብር በላይ በመሰብሰብ ከፍ ያለ የሕዝብ ተሳትፎ የታየ መሆኑን የገለጸው የኦሮሚያ ክልልም፤ የዚህ ዓመት እቅዱም እንደ ሀገር ካለው ተሳትፎ ጋር ሲዳመር ለግድቡ ከፍጻሜ መድረስ አበርክቶው ከፍ ያለ መሆኑም ነው የተጠቆመው፡፡ በመሆኑም እንደ ሀገርም፣ በየክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች በዚህ መልኩ የሚደረገው ድጋፍና ተሳትፎ እንደ ቀደመው ሁሉ ዛሬም የቀጠለ ሲሆን፤ ይሄም ግድቡን ለማጠናቀቅ የሚጠይቀውን ሃብት ለማሳካት የሚያግዝ እንደመሆኑ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል!
አዲስ ዘመን ኅዳር 18 ቀን 2016 ዓ.ም