«በከተማዋ በአቅርቦቱና በፍላጎት መካከል ሰፊ ክፍተት መኖሩ የትራንስፖርት እጥረት ፈጥሯል»አቶ ምትኩ አስማረ የአዲስ አበባ ከተማ ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ

 የኢኮኖሚያዊ እንዲሁም ማህበራዊ አልፎ ተርፎም ፖለቲካዊ መረጋጋትን ከሚያሰፍኑ ነገሮች መካከል የተሳለጠ የትራንስፖርት አገልግሎት አንዱና ዋነኛው ነው፡፡ በአንድ ሀገር ላይ የተሳለጠ ትራንስፖርት በኖረ መጠን የህብረተሰብ ከቦታ ቦታ የመዘዋወር ነጻነት ከማግኘቱም ባሻገር በዚህም ምክንያት ኢኮኖሚያዊ እድገቶች መመዝገባቸው እውን ነው፡፡

በተቃራኒው የትራንስፖርት ሁኔታ በተለያዩ ምክንያቶች ከታወከ የህብረተሰብ እንቅስቃሴ ይገታል፤ ይህ ሆነ ማለት ደግሞ ኢኮኖሚያዊ ዝውውር ስለማይኖር እድገት ይሉት ነገር የሚታሰብ አይሆንም፡፡

በተለይም በመዲናችን አዲስ አበባ ከህዝቡ ቁጥር ከፍተኛነት አንጻር የትራንስፖርት ጉዳይ ዋናና መሠረታዊ ነው፡፡ ይህንን መሠረታዊ የሆነ ነገር በተቻለ መጠን የህብረተሰቡን ፍላጎት ለማርካት እንደ ከተማ አስተዳደር በርካታ ጥረቶች ይደረጋሉ፡፡ ያም ቢሆን ግን በየእለቱ እየጨመረ ከሚመጣው የሕዝብ ቁጥር አንጻር አሁንም ድረስ የትራንስፖርት ጉዳይ የተመለሰ ጥያቄ ሊሆን አልቻለም፡፡

በሥራ መግቢያና መውጪያ ሰዓት ያለው የትራንስፖርት እጥረት ህብረተሰቡ ሳይወድ በግድ ረጃጅም ሰልፎችን ይዞ ጊዜውን በጎዳናዎች ላይ እንዲያጠፋ እያስገደደው ነው፡፡ እኛም በከተማ ደረጃ ያለውን የትራንስፖርት ሁኔታ አስመልክተን ከቢሮው ሃላፊ ከአቶ ምትኩ አስማረ ጋር ቆይታን አድርገናል፡፡

 አዲስ ዘመን፦ የአዲስ አበባ ከተማ ትራንስፖርት ቢሮ ሥልጣንና ሃላፊነትን በማንሳት እንጀምር፤የተሰጠው ሥልጣንና ሃላፊነት እስከ ምን ድረስ ነው ?

አቶ ምትኩ ፦ ትራንስፖርት ቢሮው በአዋጅ 1074 /2014 መነሻነት አጠቃላይ የከተማዋን ትራንስፖርት እንዲመራ እና እንዲያስተባብር የተቋቋመ ሲሆን በስሩም የትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ ፣ የአሽከርካሪና ተሽከርካሪ ቁጥጥር ባለሥልጣን፣ የቀላል ባቡር አገልግሎት ድርጅትና የከተማ አውቶቡስ ድርጅት ይገኛሉ፡፡

እነዚህን ቀላቅሎ የሚገኝና በከተማ አስተዳደሩም ከፍተኛ የሆነ በጀት የተበጀተለት እና 12ሺ አካባቢ ሠራተኞችን የሚያስተዳድር ነው፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ ትራንስፖርት ቢሮ የከተማዋን አጠቃላይ የትራንስፖርት ዘርፍ ስምሪትና ቁጥጥር ይሠራል፤ በዚህም 11 ቅርንጫፎች በየክፍለ ከተሞቹ አሉት ፤ የትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲም በከተማዋ ያለውን የትራፊክ ፍሰትና ደህንነት በ 11 ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶቹ አማካይነት ይቆጣጠራል፡፡ የአሽከርካሪና ተሽከርካሪ ፍቃድና ቁጥጥጥር ባለሥልጣንም አጠቃላይ የመንጃ ፍቃድ አሰጣጥ ሥርዓቱን የተሽከርካሪ ምዝገባና ቁጥጥሩን እንዲሁም ደህንነቱን በ12 ቅርንጫፎቹ በመቆጣጠር ላይ ይገኛል፡፡ ቢሮው እነዚህን አቀናጅቶ በመያዝ ነው የከተማዋን የትራንስፖርት ዘርፍ እየመራ ያለው፡፡

አዲስ ዘመን፦ በዚህ ልክ በትራንስፖርት ዘርፉ ላይ እየተሠራ ካለው ሥራ አንጻር ከስፋቱም የተነሳ የሚታዩ ችግሮች ምንድን ናቸው?

አቶ ምትኩ፦ እንደ ከተማ የትራንስፖርት ፍላጎቱ እለት በእለት እየጨመረ ባለበት ሁኔታ እንዲሁም ከተማዋ ከእለት እለት እየሰፋች ከመምጣቷ ጋር ተያይዞ የትራንስፖርት ፍላጎቱም በጣም ሰፊ መሆኑ ለማንም የሚደበቅ አይደለም፡፡ ከዚህ አንጻር ቢሮው ዘርፉን በአግባቡ ለመምራት ከፍ ያለ ጥረትን የሚያደርግ ቢሆንም የአቅርቦትና ፍላጎት መጠኑ የተስተካከለ አለመሆኑ ከፍተኛ ተግዳሮት ነው፡፡

ለምሳሌ በዚህ ዓመት 3 ነጥብ 2 ሚሊዮን ጎዞዎችን በቀን እንፈጥራለን ብለን አቅደን ነበር።ይህንንም እቅድ እንግዲህ ባሉን ባሶች ታክሲዎች ሀይገርና በተለምዶ ቅጥቅጥ የሚባሉትን እንዲሁም ባቡርን ተጠቅመን ነው፡፡ በዚህም ግቡን ያሳካን ቢሆንም የሚፈለገው ግን ከ 4 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ጉዞዎች በቀን ማድረግ ነው፡፡

ይህንን ስል ምን ለማለት ፈልጌ መሰለሽ እንደ ከተማዋ ነዋሪነቴ ሕዝቡ በእግር መሄድን ሳይቀር የትራንስፖርት አማራጭ አድርጎ እየተጠቀመ ነውና ይህ ሲጨመር በጣም ሰፊ ይሆናል፡፡ ግን ደግሞ እኛ እንደ ቢሮ የምናቀርበው የትራንስፖርት አማራጭና የሕዝቡ ፍላጎት ሲነጻጸር ሰፊ ርቀቶች አሉ፡፡ በመሆኑም ለከተማዋ ትራንስፖርት ትልቁ አስቸጋሪ ሁኔታ የፍላጎትና አቅርቦት የተመጣጠነ አለመሆን ነው፡፡ በዚህ ምክንያት በከተማዋ በተለይም በሥራ መግቢያና መውጪያ ሰዓት ላይ ረጃጅም ሰልፎችን መመልከት የተለመደ ሆኗል፡፡

አዲስ ዘመን ፦ እዚህ ላይ ግን የአቅርቦትና ፍላጎት አለመመጣጠን ከባድ ችግር እንደሆነ ተስማምተናል፤ ነገር ግን ያሉንንስ የትራስፖርት አማራጮች በትክክ ለኛው ወይም ችግሩን በሚያቃልል መልኩ አሰማርተን እየተጠቀምንበት ነው ማለት ይቻላል?

አቶ ምትኩ፦ ያሉንን የትራንስፖርት አማራጮች ከማስተካከል በአግባቡ ከመጠቀም አንጻር ሁለት ነገሮች ተግዳሮቶት ናቸው፡፡ አንደኛው የምልልሱ ሁኔታ ሲሆን አንድ የትራንስፖርት አማራጭ አንድ ቦታ ደርሶ ለመመለስ የሚወስድበት ጊዜ መንገዶች ስለሚዘጋጉ ይዘገያል ፤ ይህ ደግሞ ምልልሱ ላይ ከፍ ያለ ጫናን ያሳድራል፡፡ በመሆኑም የቁጥጥሩ ማነስ እንደተጠበቀ ሆኖ በመንገድ መዘጋጋት ምክንያት ቶሎ ቶሎ ተመላልሰው ሰውን አለማንሳታቸው ችግሩን ያሰፋዋል።ሌላው ያሉንን ትራንስፖርት አማራጮች በአግባቡ ከማስተዳደር አኳያ የቴክኖሎጂ ሥርዓቶችን በአግባቡና በስፋት እየተጠቀምን ካለመሆኑ ጋር እስከ አሁንም ሥራዎች ሰዎች ስለሚሠሩ ችግሮች ይስተዋላሉ፡፡ ከመሠረተ ልማት ጋር የተያያዘው ችግርም ሌላው ነው። ትራንስፖርት ስንል ብቻውን የሚሄድ ነገር አይደለም፤ የተሻሉ አውቶቡሶች እንዲወጡ ብዙ ዴፖዎች ያስፈልጉናል፤ ህብረተሰቡም ተረጋግቶ ትራንስፖርት ሊጠብቅባቸው የሚችል ተርሚናሎች ያስፈልጋሉ፡፡ ከዚህም ባለፈ ራሳቸውን የለዩ መንገዶች ያስፈልጋሉ፡፡ የመቆሚያ ቦታዎችም ያስፈልጋሉ፤ እንግዲህ እነዚህ ሁሉ እጥረቶች ናቸው ችግሮቹን እያባባሱ ያሉት፡፡

በሌላ በኩል አንድ ቦታ መንገድ መዘጋጋት ካለ መኪኖች በየቦታው ይቆማሉ፤ ይህ ደግሞ የሚያወጡት የተቃጠለ ጭስ አየሩን ለብክለት ይዳርገዋል፡፡ በመሆኑ ዘርፉ ለአየር ብክለትም የራሱ ድርሻ እያበረከተ ነው ማለት ይቻላል፡፡ እንደ ከተማ አብዛኛው ተሽከርካሪዎቻችን 20 እና ከዚያ በላይ ዓመታትን ያስቆጠሩ በመሆናቸው እንደ ልብ ተንቀሳቅሰው እንዳይሠሩ አብዛኛውን ጊዜያቸውን በጋራዦች አካባቢ እንዲያሳልፉም ያደርጋል፡፡

አዲስ ዘመን፦ ችግሮቹን ለመፍታትስ ከተማ አስተዳደሩ ምን ዓይነት ርምጃዎችን እየወሰደ ነው?

አቶ ምትኩ፦ ችግሮቹን ለመፍታት እንደ መንግሥትም ሆነ እንደ ከተማ አስተዳደር በርካታ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው፡፡ ባለፈው በጀት ዓመት ብቻ ወደ 310 አውቶቡሶች ተገዝተዋል፡፡ በነገራችን ላይ ለእኛ አንድ አውቶቡስ በቀን እስከ 1 ሺ ሰዎችን ነው የሚያጓጉዘው ፤ 310 አውቶቡሶች ተገዙ ሰንል 310 ሺ አዳዲስ ሰዎች ይጓዛሉ ማለት ነው።በመሆኑም ይህ አካሄዳችን አቅርቦትን ለማሳደግ ነው፡፡

በተጨማሪም በዚህ በጀት ዓመት 67 አውቶቡሶች አስገተብተናል፡፡ አሁን ላይም የሚያስፈልጋቸውን ህጋዊ ሂደት እየጨረሱ በመሆኑ በቅርቡ ወደአገልግሎት ይገባሉ፡፡ አቅርቦትን ከማሳደግ አንጻርም የሚኖረው ፋይዳ በቀላሉ የሚታይ አይሆንም፡፡

በሌላ በኩልም የጥገና አቅማችንን በከፍተኛ ሁኔታ ማሻሻል ሲሆን የከተማ አውቶቡስ አገልግሎት የተለያዩ ዲፖዎች ያሉት ቢሆንም የተሻለ ሥራን መሥራት እንዲችሉ የጥገና አቅማቸው ተጠናክሮ አንድም ባስ እንዳይቆም የማድረግ ሥራው ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ በአሁኑ ወቅት በአማካይ 138 ገደማ ባሶች በቀን ወጥተው አገልግሎት የሚሰጡ ሲሆን ከእነዚህ ምክንያት ደግሞ 1 ሚሊዮን የሚጠጋ ተጓዥ አገልግሎቱን እያገኘ ነው፡፡

አቅርቦትና ፍላጎት ሊጣጣምበት ከሚችለው መንገድ ሌላው የቁጥጥር አቅምን ማሳደግ በመሆኑ እንደ ቢሮ ከ አራት መቶ በላይ የሚሆኑ ተቆጣጣሪዎች አሉን፤ እነሱን በሁለት ፈረቃ በማሰማራት በተለይም መነሻና መድረሻ ቦታዎች ላይ በተቻለ መጠን ቁጥጥር እንዲያደርጉ የታክሲውን አገልግሎት አሰጣጥ ለማሳለጥ ይሠራል፡፡

እንደ ከተማ ይህ ሥራ ያስፈለገውን ባለን መረጃ መሠረት የከተማዋ የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ከ 69 በመቶ በላይ በታክሲዎች የሚሸፈን በመሆኑ ሲሆን እነዚህ ታክሲዎች ህብረተሰቡን በአግባቡ እንዲያገለግሉ ከማስቻል አንጻር የቁጥጥር ሥራው ይደረጋል፡፡ ያሉንንን አውቶቡሶችም በተገቢው ሁኔታ ተመላልሰው አገልግሎት እየሰጡ ነው፡፡ በዚህም ወደ ስድስት የሚሆኑ የተለዩ መስመሮችን በማዘጋጀት መስመሮቹ ባሶች ብቻ ቅድሚያ አግኝተው የሚመላለሱባቸው እንዲሆኑ የማድረግ ሥራ እየተሠራ ነው፡፡

ከዚህ ባለፈ ግን ችግሩን ለመቅረፍ መሠረተ ልማትን ማስፋፋት አይነተኛ መንገድ በመሆኑ የከተማ ባሶቹ የሚገለገሉበት የሸጎሌና የቃሊቲ ዴፖዎች እንዳሉ ሆነው ሌላ ተጨማሪ መካኒሳ ላይ ትልቅ ዴፖ ለማስገንባት ሥራዎች እየተሠሩ ነው። ምክንያቱም የተሻሉና ደህንነታቸው የተጠበቁ አውቶቡሶች ከሌሉን ህብረተሰቡን በአግባቡ ማስተናገድ አንችልም፤ ከዛም ባለፈ ደግሞ የትራፊክ ፍሰቱን ሰላማዊ ከማድረግ አንጻር ሥራዎች እየተሠሩ ነው፡፡

አዲስ ዘመን፦ እናንተ ተቆጣጣሪዎችን አሰማርታችሁ ከምትሠሩት ሥራ ባሻገር ግን ከዘመኑ ቴክኖሎጂ ጋር የተራመዱ ሥራዎችን በመሥራት በኩል ያለው ነገር ምን ይመስላል?

አቶ ምትኩ፦ የትራፊክ ፍሰቱን ሰላማዊና የተረጋጋ ለማድረግ የቁጥጥር ሥራም ለመሥራት መገናኛ ላይ ትልቅ የትራፊክ ማኔጅመንት ሴንተር በማስገንባት ላይ ነን። ከጥቂት ጊዜያት በኋላም ቢሮ ቁጭ ብለን አጠቃላይ የትራንስፖርት ሥርዓቱን ማየት የምንችልበት ሁኔታ ይፈጠራል።

አዲስ ዘመን ፦ በካሜራ ማለት ነው?

 አቶ ምትኩ፦ ያው የመቆጣጠሪያ ማዕከል ነው። ከመንገድ ላይ ከካሜራዎች እንዲሁም ከሌሎች አማራጮች መረጃዎችን ይወስዳል። በሌላ በኩል ደግሞ አብዛኛውን ጊዜ የትራፊክ ፍሰቶች የሚታወኩት መጋጠሚያ መንገዶች ላይ ከመሆኑ አንጻር ቅድሚያ ማግኘት ያለበትን እያየን የምንሠራው ሥራ አለ፡፡ አሁን ላይ የቤቱ ግንባታ በመጠናቀቅ ላይ ሲሆን ወደታች አራት ወለል አለው ሰፊ በጀትም ነው የወጣበት፤ በመሆኑም በቀጣይ ፍሰቱን ከማስተካከል አንጻር ውጤታማ ያደርገናል ብለን እናስባለን፡፡

ይህ አይነቱ አሠራር ደግሞ በሌሎች ሀገሮች የተለመደ ከመሆኑም በላይ እኛም የአንዳንድ ሀገሮችን ተሞክሮ አይተናል በመሆኑም አሁን ላይ ያለንበትን ችግር ከማቃለል አንጻርም ሚናው በቀላሉ የሚታይ አይሆንም፡፡ በመጀመሪያው ዙር ወደ 99 መገናኛዎች ይሠሩና በቀጣይ ደግሞ መንገድ ላይ መቆምን የሚከታተል ቅድሚያ ለባሶች የሚሰጥ የሚቆጣጠር እና አደጋዎች ሲደርሱም በቶሎ ምላሽ እንዲያገኙ የሚያደርግ ይሆናል፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ ህብረተሰቡ ከቤቱ ከመውጣቱ በፊት በየትኛው መንገድ ቢሄድ ይሻለኛል የሚለውን መረጃ የሚሰጥ ነው፡፡

ሌላው ቢሮው ትልቅ ሃላፊነት ያለበትና በርካታ ሥራ የሚሠራበት ከመሆኑ ጋር በተያያዘ ለዋና መሥሪያ ቤትነት የሚሆን 20 ወለል ያለው ህንጻ በመገንባት ላይ ነው፡፡ ይህ ሲጠናቀቅ ደግሞ ተበታትነው ያሉ ቢሮዎችን በአንድ አሰባስቦ የተወሰኑ ክፍለ ከተሞችም አብረውት የሚሆኑበትን ሁኔታ ስለሚፈጥር ምቹ የሥራ አካባቢን ይፈጥራል፡፡ ህብረተሰቡም በአንድ ቦታ ሁሉንም አገልግሎቶች ማግኘት የሚችልበት አጋጣሚ ይሰፋል፡፡ ይህ የሚያሳየው ደግሞ ከተማ መስተዳድሩ ለትራንስፖርቱ ዘርፉ የሰጠውን ልዩ ትኩረት ነው።

ይህ የቴክኖሎጂ ሁኔታ ደግሞ በማጠናከር ከዓለም ባንክ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ የከተማ አውቶቡስ አገልግሎትን ማዘመን ላይ ትኩረት ያደርጋል፡፡ ይህም ሲባል የአውቶቡሶቻችንን አጠቃላይ እንቅስቃሴ መቆጣጠር የሚያስችል ነው፡፡ አሁን በሙከራ ላይ ባለበት ሁኔታ እንኳን ባሶቹ የትና በምን ሁኔታ ላይ ነው የሚውሉት የሚቆሙት የሚለውን በጫናቸው ሁለት መቶ ገደማ ካሜራዎች ለማየት ችለናል። በቀጣይም ወደካርድ ሥርዓት ለመግባትም እየሠራን ነው፡፡ እነዚህ ሥራዎች ሲጠናቀቁ ደግሞ የቁጥጥር ሥራችን ውጤታማ ከመሆኑም በላይ የስምሪት ሥርዓታችንም የተሻለ ስለሚሆን እነዚህ ሥራዎችን አጠናክረን እንቀጥላለን።

አዲስ ዘመን ፦ አዎ በተለይም ስምሪት ላይ ከፍ ያለ ችግር ያለ ይመስላል ፤ ይህንን ያልኩበት ዋና ምክንያቴ ደግሞ አንዳንድ መስመሮች ተሳፋሪ የለም ግን ደግሞ ትራንስፖርት አማራጩ ብዙ ነው ሌሎች ላይ ሰው ይበዛል ግን ደግሞ ትራንስፖርት የለምና ቴክኖሎጂው እነዚህንም ያስታርቃል የሚል እምነት ያለ ይመስለኛል እርስዎ ያሉት ከገባኝ?

አቶ ምትኩ፦ አዎ አሁን አውቶቡሶቻችን ላይ በጀመርነው ክትትል ምሳ ሰዓት ሻይ ምናምን ብለው ይደበቃሉ እሱን ሁሉ ማየት ችለናል ፤ሌላው ተጓዡ የት አካባቢ ይበዛል ? የሚለውንም እያየን ነው። አሁን ላይ አሠራራችን በሰው ስለሆነ ምደባ ላይ ከፍተኛ ክፍተቶች አሉ፡፡ ይህንን ለማመጣጠን ደግሞ ቴክኖሎጂው አቅም ይሆነናል፡፡ ሌላውና ዋናው ግን ለህብረተሰቡ መረጃ መስጠት ነው፡፡ አሁን ላይ እንኳን ሶስት ቦታዎች ላይ ለህብረተሰቡ በተለይም የአውቶቡሶችን መዳረሻ ሰዓት የማሳወቅ ሥራ ተጀምሯል፡፡ በመሆኑም ለህብረተሰቡ የሚፈልገው ባስ በዚህ ሰዓት በዚህ ደቂቃ እዚህ ትደርሳለች የሚል መረጃ መስጠት እየሠራን ነው፡፡

በመሠረቱ ሥራው ቀላል አይደለም ግን ደግሞ ወደዘመናዊነቱም መሄድ ስላለብን እየሠራን ነው፡፡ እነዚህን ከሠራን ደግሞ ችግሮቹን መፍታት እንችላለን የሚል እምነት አለን፡፡ መንግሥት ዘርፉን ለማሳደግ አቅሙ የፈቀደውን ሁሉ እያደረገ ቢሆንም በተለይም የግል ባለሀብቶች በትራንስፖርት ዘርፍ መሠማራት መቻል አለበት፡፡ የእነሱ መግባት ደግሞ ዘርፉን ውጤታማ ያደርገዋል፡፡

በሌላ በኩል እስከ ዛሬ ስንጠቀምበት የነበረውን የትራንስፖርት አጠቃቀም ልምምድ ማሻሻል ይገባል። በተለይም ለአጭር ኪሎ ሜትሮች መሰለፍን በማቆም ትንሽ መንገድ በእግር በመጓዝ ብስክሌትና ሌሎች አማራጮችን በመጠቀም ሁኔታውን ማመቻቸት ይገባል፡፡

አዲስ ዘመን፦ የከተማዋን ትራንስፖርት ከሚያውኩ ነገሮች መካከል የመኪና ማቆሚ ያዎች (ፓርኪንጎች) ናቸውና እንደው እነሱን ዘላቂ መፍትሔን የሚያገኙበትን መንገድ ከመፍጠር አንጻር የተሠራው ሥራ ምን ይመስላል?

አቶ ምትኩ፦ አዎ መሠረተ ልማት ለትራንስፖርት መሳለጥ አይነተኛ ሚና ያለው ነው። ይህንንም በመረዳት የካ ላይ እየተገነባ ያለ ትልቅ የመኪና ማቆሚያ አለ። ወደላይ ሶስት ወደታች ሁለት አምስት ወለል ያለው ነው፡፡ በዚህም 910 ተሽከርካሪዎችን በቀላሉ የሚይዝ ነው፡፡ ይህም መንገድ ላይ ከመቆም ጋር ተያይዞ ያሉትን ችግሮች በመቅረፍ በኩል አይነተኛ ሚና ይኖረዋል። ሌሎችም በዚህ አይነት መልኩ የሚሠሩ ሥራዎች ይኖራሉ፡፡

አዲስ ዘመን፦ ሰዎች የሚፈልጉትን ትራንስ ፖርት በችግርና ከብዙ ጥበቃ በኋላ አግኝተው እንኳን መንገድ ስለሚዘጋጋ ጊዜያቸውን መንገድ ላይ ለማጥፋት ይገደዳሉ ከዚህ አንጻር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ያለው ቅንጅታዊ አሠራር ምን መልክ አለው?

አቶ ምትኩ፦ ብዙ መንገዶች የሉንም ማለት አይቻልም ፤ መንገዶች አሉን፤ ከዚህ ይልቅ እንደውም የውስጥ ለውስጥ መንገዶቻችን ብዙ አይደሉም፤ አብዛኛው ሰውም የሚሄደው በዋና መንገድ ላይ ብቻ ነው፤ የምንወጣባቸውም ሰዓቶች ተመሳሳይ ናቸው። ይህ አጠቃቀማችን ደግሞ በመንገዱ ላይ ጫና ይፈጥራል ፤ መጨናነቁም ይመጣል፡፡ በመሆኑም የሚችል ሰው ቀደም ብሎ ቢወጣ አንደኛ ለመንገዱ ሰላማዊነት ሁለተኛ ለራሱም ያሰበበት በሰዓቱ ከመድረስ አንጻር ሚናው ከፍተኛ ነው፡፡

በቅንጅት ከመሥራት አንጻር በተለይም ወሳኝ ሰዓት በሚባሉት ጠዋትና ማታ ላይ ከተፈቀደላቸው የጭነት ተሽከርካሪዎች ውጪ እንዳይንቀሳቀሱ የማገድ ሥራ ተሠርቷል፡፡ ሌላው ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ በቢሮው ስር የሚገኝ ተቋም ነው ከእርሱም ጋር በአግባቡና በቅንጅት እየሠራን ነው፡፡ ከመንገዶች ባለሥልጣን ጋርም ጥሩ የሥራ ግንኙነት ፈጥረን ተናበን እየሠራን ነው፡፡

አዲስ ዘመን፦ የትራንስፖርት ችግርን ይፈታል ተብሎ እምነት ከተጣለበት አንዱ ቀላል ባቡር ነውና እንደው አሁን ባለው ሁኔታ ለትራንስፖርት ችግሩ መፍትሄ ሆኗል ማለት ይቻላል?

አቶ ምትኩ፦ ከቀላል ባቡር ወደከተማ አስተ ዳደሩ ከገባ አንድ ዓመት ሆኖታል ፤ ባቡሩ ወደሥራ ሲገባ 41 አካባቢ ፉርጎዎች ነበሩት ፤ በእነዚህ ፉርጎዎች ደግሞ በቀን እስከ 120 ሺ ሰዎች ያጓጉዟል ተብሎ ነው የተጀመረው፡፡ እስከ ቅርብ ጊዜም ጥሩ ግልጋሎትን ሰጥቷል ፡፡

ባቡር ሰፊ ጥቅም ያለው ነው በተለይም ምንም አይነት የትራፊክ መጨናነቅ የማያግደው ከመሆኑ አንጻር ብዙ የህብረተሰብ ክፍሎችን በአንዴ የሚያነሳ ረጃጅም ርቀቶችን የሚጓዝ በመሆኑ ጥቅሙ ብዙ ነው፡፡ ነገር ግን ከጥገና ከመለዋወጫ ጋር የተያያዙ ችግሮች አሉበት። የጥገና አቅምም ሌላው ችግሩ በመሆኑ በተለይም ከተማ አስተዳደሩ ውስጥ ከገባ በኋላ ባቡሩ በሙሉ አቅሙ እንዲሠራ ለማድረግ ብዙ ሥራዎች እየተሠሩ ሲሆን የቻይናንም ድጋፍ አግኝተናል፤ መለዋወጫዎችም እየመጡ ነው። ከሁሉም በላይ ደግሞ ሰባት አዳዲስ ባቡሮች ወደሀገር እንዲገቡ የማድረግ ሥራውም እየተሠራ ነው፡፡ እንደ ከተማ አስተዳደር ደግሞ አጠቃላይ ጥገናውን የተሻለ ቀጣይና ዘላቂ እንዲሆን ለማድረግ ሰፊ ሥራዎች በመሠራቱ በቀጣይ በሙሉ አቅሙ ወደሥራ የሚገባበት ሁኔታ ይፈጠራል።

በጠቅላላው የባቡር ትራንስፖርት ለሀገር ኢኮኖሚ ሰፊ ድጋፍ ያለው ከመሆኑ አንጻር የተሻለም ትኩረት ቢያገኝ ረጅም ርቀት ከመሄዱ የምንመድበውን የትራንስፖርት አገልግሎት ወደሌሎች መስመሮች ለማዞር ስለሚጠቅምን በመኪና የሚመጣውም ሰው ባቡርን ተጠቅሞ የመንገድን መጨናነቅ እንዲቀንስ በማስቻሉ በኩል ሚናው የጎላ ስለመሆኑ መታወቅ ይኖርበታል፡፡

አዲስ ዘመን፦ እንደ ከተማ የትራንስፖርቱን ፍሰት የሚያሳልጡ ተርሚናሎች ግንባታ ብዙ ትኩረት አልተሰጠውም፤ ለምንድ ነው?

አቶ ምትኩ፦ እንደ ከተማ ብዙና ሰፋፊ ተርሚናሎች ያስፈልጉናል፤ አሁን ባለው ሁኔታ ጥሩ ተርሚናል ያለን መርካቶ ላይ ነው፡፡ ይህ ተርሚናል በቀን 5 ሺ ያህል ሰዎች ያስተናግዳል ሰዎች ቁጭ ብለው ነው አገልግሎት የሚያገኙት ንጽህናው የተጠበቀ ነው። ልክ እንደዚህ ሁሉ ሌሎችንም መገንባት ያስፈልጋል፡፡

አሁን ባለው ሁኔታ ግን ተርሚናሎች ብለን የምንላቸው የታክሲ መጫኛና ማውረጃ ቦታዎችን ነው። ህብረተሰቡ ይንገላታል ልክ ነው ግን ደግሞ ከአንዱ ተርሚናል ወደሌላው ለመሄድ ቢያንስ አምስት መቶ ሜትር ቢሆን ነው፡፡ ይህንን ጉዞ በቀን ውስጥ ማድረግ ደግሞ ይመከራል፡፡ ግን ደግሞ ችግሮቹን ለመፍታት የተርሚናል ግንባታዎች ያስፈልጉናል ለምሳሌ መገናኛ ተርሚናልን ለመገንባት እቅድ አለ ፤ በቀጣይም ሌሎችን እየገነባን ችግሮቹን ለማስተካከል እንሞክራለን።

ለጊዜው ግን መዳረሻ ቦታዎችን ተቀራራቢ በማድረግ ሰዎች እንዳይንገላቱ ማድረግ ጊዜያዊ መፍትሔዎችን የመስጠት ሥራ እንሠራለን፡፡

አዲስ ዘመን ፦አሁን በቅርብ ጊዜ ውስጥ ቢሯችሁ የመጓጓዣ በተለይም ለታክሲዎች የታሪፍ ማሻሻያ አድርጓል፡፡ አንዳንድ አስተ ያየት ሰጪዎች የተደረገው ማሻሻያ በጣም የበዛ ነው ይላሉና በዚህስ ላይ ያልዎት አስተያየት ምንድን ነው?

አቶ ምትኩ፦ በቢሮው የሚሠሩ ሥራዎች ታሪፍን ጨምሮ በጥናት የተደገፉ ናቸው ፤ የህብረተሰቡንም የኑሮ ሁኔታም ከግምት ውስጥ ያስገባ ነው፡፡ ነገር ግን አሁን ልንነጋገር የሚገባው ታሪፉ ላይ ሳይሆን ታሪፉን በአግባቡ የማስፈጸም የቁጥጥጥር ሥራው ላይ ነው። በቅርቡ የጨመርነው ታሪፍ የከተማ አውቶቡስንና ባቡርን የሚመለከት አይደለም፡፡ በመሆኑም አማራጭ እየፈጠርን ነው ማለት ነው፡፡

አሁን እኛ ጋር በተደጋጋሚ እየመጣ ያለው ታክሲዎች በተጨመረላቸው ታሪፍ መሠረት እየሠሩ አይደለም የሚል ነው፡፡ ቢሮው እንግዲህ ከላይም እንዳነሳሁልሽ የቁጥጥር ሥራውን በሰዎች አማካይነት በሁለት ፈረቃ እየሠራን ነው፡፡ ነገር ግን ህብረተሰቡም በራሱ ግዴታውን ተወጥቶ መብቱን መጠየቅ ይገባዋል ይህ ሲሆን ደግሞ የጋራ አቋም መያዝ ቢቻል ብዙ ለውጦች ይመጣሉ፡፡

እኛ ደግሞ ህብረተሰቡን ብቻህን ተጋፈጥ ሳይሆን ያልነው በልዩ ሁኔታ ታሪፉ በታክሲው ውስጥ እንዲለጠፍ መለጠፍ ብቻም ሳይሆን ታርጋ ቁጥሩም አብሮ እንዲካተት የማድረግ ሥራ እየሠራን ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም እንደዚህ አይነት ችግር ያጋጠመው ሰው ወደ 9417 ላይ በነጻ ስልክ በመደወል መረጃ መስጠት ይችላል፡፡

ከሁሉም በላይ ግን በተለይም የታክሲ አሽከርካሪዎች ሥራቸውን ሲያከናውኑ ፍጹም ሥነ ምግባር የተላበሱ ሊሆን ይገባል። በአንጻሩ ተገልጋዩም ገንዘብ ከፍያለሁ በሚል ብቻ ከሥነ ምግባር ውጪ የሆኑ ተግባራትንም ሊፈጽም አይገባም፡፡

ቢሮው በያዝነው በጀት ዓመት ብቻ 21ሺ ገደማ ቅጣቶችን ቀጥቷል፡፡ ያለን ታክሲ 14 ሺ አይደርስም ቅጣቱ ግን ደብል ነው፡፡ ይህም አሠራር አስተማሪ ስላይደለ ቢሮው ቅጣቱን ጠንካራ ከማድረግ ጎን ለጎን የማስተማርና ልዩ ፍቃድን ለመስጠት በዝግጅት ላይ ነው፡፡

ለምሳሌ አንድ ሰው በትራንስፖርት ዘርፉ ላይ ለመሠማራት ከፈለገ ግዴታ የኦፕሬተርነት ፍቃድ ያስፈልገዋል እያልን ነው፡፡ መንጃ ፈቃድ ስለያዘ ብቻ ታክሲ አይነዳም፡፡ ይህንን ሳብራራልሽ ኦፕሬተርነት ሲባል ቢሮው አሠልጥኖ የሚሰጠውን ልዩ ፍቃድ መያዝ የግድ ይሆናል ማለት ነው፡፡

ከዚህ ሁሉ በላይ ግን ሰውም ለተጋነነ የትራንስፖርት ወጪ እንዳይዳረግ የብዙሃን ትራንስፖርትን ማሳደግ ትልቅ መፍትሔ ነው፡፡ ምክንያቱም አንበሳ አውቶቡስ ላይ ከታሪፍ በላይ ተጠየኩ ብሎ ቅሬታ የሚያሰማ ሰው የለም፡፡ በመሆኑም ይህንን ማሳደግ ይገባል ፤ እኛም የተባሉትን ችሮች ሁሉ ለማቃለል እየሠራን ነው፡፡

አዲስ ዘመን፦ ለነበረን ቆይታ በጣም አመሰግናለሁ።

አቶ ምትኩ ፦ እኔም አመሰግናለሁ፡፡

 እፀገነት አክሊሉ

አዲስ ዘመን   ኅዳር 17 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You