ብሄራዊ ምክክር ለሁለንተናዊ ተሃድሶ

ሀገራችን ሁለንተናዊ ተሀድሶ የሚያስፈልጋት ሰሞን ላይ ነን፡፡ በተለያዩ ትርክቶች የወየቡ ከሰላም ይልቅ ለጠብ፣ ከአንድነት ይልቅ ለመለያየት መንገድ በሚከፍቱ የጥላቻ መንፈስ ውስጥ ከወደቅን ሰነባብተናል፡፡ ሽንቁሮቻችን ከመጥበብ ይልቅ እየሰፉ ጣት ከመጠቋቆም ባለፈ የመፍትሄ አካል እንዳንሆን በራሳችን ላይ አስጨክነውናል። ኢትዮጵያዊነት የማይወክሉ እነዚህ የእኔነት ግሳንግሶች ከመካከላችን እንዲወጡ ሁሉን አቀፍ የተሃድሶ ንቅናቄ ለመተግበር የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ እንገኛለን፡፡

ብሄራዊ ምክክር ለሁለንተናዊ ተሃድሶ ስል መነሳቴ አንድም ወቅታዊ ችግሮቻችንን ለማቃለል ፤አንድም ዘላቂ ሰላምን ከማምጣት አኳያ ፋይዳው ላቅ ያለ መሆኑን በማመን ነው፡፡ ታላላቅ የሰው ልጅ ሥልጣኔዎች በልዩነት ውስጥ እንዴት ተከባብሮና ተቻችሎ መኖር እንደሚቻል በተረዳ ጭንቅላት የጥላቻ ድንበሮችን በማፈራረስ የመጣ ነው፡፡ እንደዚሁ ሁሉ መጨረሻ አልባ ኋላቀርነቶች ልዩነትን ለጸብ ከመጠቀምና የጥላቻ ድንበርን ከማፍረስ ይልቅ በማበጀት የሚመጣ ስለመሆኑ ለመረዳት ጠቢብ መሆን አይጠይቅም።

በዓለም የሥልጣኔ ታሪክ ውስጥ በደም የጠራ ፖለቲካ፣ በሞት የተመለሰ ጥያቄ አላውቅም። የሚኖርም አይመስለኝም፡፡ እንዲህ ዓይነት አስተሳሰቦች ሀገር ከማውደምና ትውልድን ከመመረዝ ባለፈ ይሄ ነው የሚባል በጎ ዐሻራ የላቸውም፡፡ አሸናፊነትን ከኃይል ጋር አቆራኝተን የፍቅርን ወደብ ላፈረስን ለእኛ ይሄ ጨዋታ ሊመስለን ይችላል፡፡

ሀገር ለመገንባት ግን ከዚህ የተሻለ አስተማማኝ አማራጭ የለንም፡፡ በብሄራዊ እርቅና ብሄራዊ መግባባትን ሳንፈጥር በያዝ ለቀቅ ከ60 የራቀ ዓመታትን አሳልፈናል፡፡ ዛሬም ከዛ የመግደልና የመሞት መንፈስ ሳንወጣ ትውልዱን በሌላ ስቃይ መጥተንበታል፡፡ ሀገር ለሁላችን እንድትበቃ ከሁላችን ለሁላችን የሆነ ሃሳብና ጨዋነት ያስፈልጋል፡፡ አድጋና በልጽጋ ሕዝብ የሚኮራባት፣ ትውልድ የሚታፈርባት እንድትሆን አብሮነትን ያገዘፈ የወንድማማችነት ባህል ያስፈልጋታል፡፡

አሁን ባለው ወቅታዊ ሁኔታ እንዲህ ነበርን ብለን ታሪክን የኋሊት መልሰን ከማውራት ባለፈ ምንም እያደረግን አይደለም፡፡ ያለፈው ትውልድ በደሙ ታሪክ ጽፎ ለምንጊዜም የምንኮራባትን ሀገር ሰጥቶናል፡፡ ያለፈው ትውልድ የእኔ የአንተ የሌለባትን በእኩል የምትጠራን ኢትዮጵያ በምንም ከማይላላ የብዙሃነት ውህደት ጋር አስረክቦናል፡፡ እኛ የዚህ ትውልድ ሰዎች ግን የተሰጠንን የአደራ ሀገርና ታሪክ ስንጠብቅ አንታይም፡፡ ትልቋን ኢትዮጵያ ትንሽ እያደረግናት ነው፡፡ የጋራ ታሪካችንን ወደምንምነት እየቀየርን ነው፡፡

ታሪክ ይጠበቃል እንጂ አይሸረፍም፡፡ ሙሉ ሀገር እንደተረከብን ሁሉ ሙሉ ሀገር የማስረከብ ግዴታ አለብን፡፡ የኮራነው፣ በዓለም አደባባይ ቀና ብለን የቆምንው በተረከብነው ያልተሸራረፈ ታሪክና እውነት ነው፡፡ መጪው ትውልድ እንዲኮራና ቀና ብሎ እንዲራመድ ያልተሸራረፈ ታሪክ ልናስረክበው ግዴታ አለብን፡፡ የተያያዙና የተጠላለፉ ብዙሃን እጆች የነደፉትን የታሪክ ገድል ሀገር ጠል በሆነ ፖለቲካና ግብረ ኑባሬ እየሸራረፍን የማንም እንዳይሆኑ ለማድረግ ዳር ዳር እያልን ነው፡፡

የታሪክ ሽርፈት የማንነት ሽርፈት ነው፡፡ ያልገባንና ያልተረዳነው አንድ ነገር ታሪኮቻችንን ስንሸርፍ ኢትዮጵያዊነታችንን እየሸረፍን መሆኑ ነው፡፡ እውነትን ስናዛናፍ አብሮነታችንን እያዛነፍን ነው፡፡ የዚህ መጨረሻው ደግሞ ጦርነትና ማህበራዊ ቀውስ ነው፡፡ ተነጋግሮ የማይግባባ ትውልድን ለመፍጠር መንገድ የሚከፍት ነው፡፡ ጦርነትና ጥላቻን፣ እልህንና ማንአለብኝነትን የፈጠሩብን ፖለቲካዊም ሆኑ ማህበራዊ ነውሮቻችን የታሪክ ሽርፈት የፈጠራቸው እንደሆኑ ቢገባን ስቃዮቻችንን በግማሽ ማስቀረት እንችል ነበር፡፡

ብሄራዊ ምክክር ስንል ብሄራዊ እርቅ ማለታችን ነው፡፡ እርቅ ስንል ሁሉን አቀፍ ሰላምና ተግባቦት፣ ይቅርታና ተሃድሶ ማለታችን ነው፡፡ ይህ የሚሆነው ደግሞ ለሰላም በተዘጋጁ አዕምሮና ልብ፣ ለይቅርታ በበረቱ አንደበቶች ነው፡፡ አንተም ተው አንተም ተው ብሎ ማስታረቅ የባህላችን ፊተኛ ሆኖ ከጥንት ወደዛሬ የመጣ ነው፡፡ ኢትዮጵያ እየተጎዳች ያለችው በጥቂት ራስወዳድ እና በብሄርና በጎሳ ሽፋን በተደበቁ ጽንፈኞች ነው፡፡ ብዙሃኑ ከድሮ ቀለሙ ጋር..አብሮነትን ሽቶ፣ ብዙሃነትን ናፍቆ የሚኖር ነው፡፡

ትግላችን አንድነታችን መመለስ፣ ኢትዮጵያዊነትን ማስቀጠል ከሆነ ቅደም ተከተላቸውን ስተው የተዘበራረቁብንን ስሜት ለበስ አካሄዶቻችንን ማስተካከል አለብን። ባልተስተካከለ ሃሳብ ውስጥ የተስተካከለች ሀገር የለችም፡፡ ባልተስተካከለ ፖለቲካ ውስጥ የሰመረ ትውልድ የለም፡፡ በየዘርፉ ያለው ሀገራዊ ሥርዓት የተሃድሶ ህክምና ያስፈልገዋል። ዋናውና ከስቃይ ሊታደገን የሚችለው ህክምና ደግሞ ምክክር ነው፡፡

ላለፉት 50 እና 60 ዓመታት ውስጥ ፖለቲካችንን ለማስተካከል፣ የልዩነት ቁርሾዎቻችንን ለማከም የሄድንባቸው የምክክር አቅጣጫዎች ዒላማቸውን ስተው ዛሬ ላይ ደርሰናል፡፡ አሁን ላይ ተግባራዊ ሊደረግ ከጫፍ የደረሰው የምክክር መድረክ ከብዙ ጊዜ በኋላ የተመለሰ ምናልባትም ለጀመርነው የሰላምና የአንድነት ትልም እንደመጨረሻ እድል ሊታይ የሚገባው እንደሆነ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡

ሀገርን ለመታደግ ምክክር ከሁሉም የተሻለው መንገድ መሆኑ የማይካድ ቢሆንም ላልተጠቀመበት እና እልኸኝነቱን ላልተወ ማህበረሰብ ግን ትርጉም አይኖረውም፡፡ ያለፉት ጊዜያቶች በምን ሁኔታ ይሄን እድል እንዳጡ ስንጠይቅና ስንመረምር የተለያዩ ምክንያቶችን እናገኛለን፡፡ የትኛውም ምክንያት ከሀገር መፍረስና ከማህበረሰብ መለያየት ስለማይበልጥ በየትኛውም ሁኔታ ላይም ሆነን ሀገራዊ ምክክር ማድረጉ ተመራጭ ነው ባይ ነኝ፡፡

ብሄራዊ ምክክር ለሁለንተናዊ ተሃድሶ ብዬ ስነሳ በምክንያት ነው፡፡ እንደሀገር ሰላም ለማምጣትም ሆነ ሰላምን ለማስቀጠል እንደብቸኛ አማራጭ ሊወሰድ የሚገባው ድርጊት ነው፡፡ ከኃይል ፖለቲካ ወደ አጽንኦት ፖለቲካ መውረድ በሰላም እጦት ለምትሰቃይ ሀገር ከፍታ እንጂ ዝቅታ አይደለም፡፡ ከክርክር ወደ ምክክር፣ ከፉክክር ወደ ንግግር መመለስ በጥላቻና በዘረኝነት እጣፈንታው ለሚያሰጋው ማህበረሰብ ክብር እንጂ ውርደት አይደለም። ተነጋግሮ ከመታረቅና ከመተቃቀፍ የላቀ ወደአንድነት የምንመለስበት ሁነኛ ጥበብ የለንም፡፡

‹ቤት በጥበብ ይሠራል በማስተዋልም ይጸናል› የሚል መጽሀፍ ቅዱሳዊ አስተምህሮ አውቃለው፡፡ በቅዱስ ቃሉ ላይ ቤት ትዳር ሆኖ የተገለጸ ቢሆንም እኔ ግን ቤት የሚለውን በሀገር መንዝሬ እንዲህ አልኩ፡፡ ቤት ሀገር ናት..ሀገር ትዳር፣ ማንነት፣ ህልም፣ ራዕይ ናት፡፡ ሀገር ክብር፣ ታሪክ፣ ስምና መታበያ ናት፡፡ እናም ሁሉንም የሆነች ይቺ ሀገራችን በጥላቻ እንዳትፈርስ በጥበብ ቆማ በማስተዋል እንድትጸና ያስፈልጋታል፡፡ ጥበብ ማረፊያዋ አስተውሎት ነው፡፡ አስተውሎት ደግሞ በመስከንና በመደማመጥ ውስጥ የሚንጸባረቅ የክብር ጸሀይ ነው፡፡ ሰክነንና ተደማምጠን የልዩነታችንን ምንጭ ካላደረቅን ሌላ መዳኛ የለንም፡፡

በከንቱ ያባከናቸው የምክክር እድሎቻችን ሰምረው ቢሆን ኖሮ ዛሬ ላይ ብዙ ጥያቄዎቻችን መልስ አግኝተው ድህነትን ካሸነፉ፣ ኋላቀርነትን ከረቱ ጥቂት ሀገራት ውስጥ እንሆን ነበር፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ እድሎቻችንን ሳንጠቀም ዛሬ ላይ ደርሰናል፡፡ ዋናውና ሊሰመርበት የሚገባው ጉዳይ እንዳለፈው ጊዜ እድሎቻችንን አባክነን የሚቆጭ ትውልድ እንዳንፈጠር ካለፈው በመማር ብዙ ማትረፍ ይኖርብናል። ይሄን በመሰለው ጉዳይ ላይ አያሌ ሀገራት ችግሮቻችውን በቁጥጥር ስር አውለዋል፡፡ እኛም በምክረ ሃሳብ ችግሮቻቸውን ከረቱ ሀገራት ውስጥ ሆነን ስማችን በአሸናፊነት እንዲጠቀስ ለምክክር ከመቀመጥ ባለፈ እድሎቻችንንም መጠቀም ትርፉ የላቀ ነው ፡፡

ብርቱዎች ሀገር ይሠራሉ እንጂ የተሠራ አያፈርሱም፡፡ ብልሆች ታሪክ ይጠግናሉ እንጂ ታሪክ አይሸራርፉም፡፡ ኢትዮጵያን እንወዳለን የምንል ሁሉ ከቃል ባለፈ የሀገር ፍቅር ስሜታችንን አንድም ታሪክ ባለማጣመም አንድም እውነትን አግዝፎ በመስበክ ፍቅራችንን ወንዝ ተሻጋሪ ማድረግ እንችላለን፡፡ ሠላምን በማምጣት ሂደት ውስጥ የማያቸው አንዳንድ ትዝብቶች አሉ፡፡ አንዳንዶቻችን ጠባቂዎች ነን፡፡ የተቀረነው ደግሞ ምንም ይሁን ግድ የማይሰጠን፡፡ ሀገር የጋራ ቅርስ ከሆነች ሰላምም የጋራ ውርስ መሆን አለበት፡፡ ይሄ ማለት በእርቀ መድረኩ ፊት ስለሰላም ሁላችንም አስተዋጽኦ አለን ማለት ነው፡፡

ከዛሬ ርቀን ነገን ባለማየታችን ብዙ ዋጋዎችን ከፍለናል፡፡ ከዛሬ አርቀን ነገን ማየት ብንችል ኖሮ አሁናዊ ስቃዮቻችን ማብቂያቸው በሆነ ነበር። ትናንት ላይ ዛሬን ባለማየታችን ለዛሬ ሀገራዊ ስቃይ ተዳርገናል፡፡ ዛሬ ላይ ሆነን ነገን በማየት መጪውን ትውልድ ከፈተና መታደግ እንችላለን። ለዚህ እንዲረዳን ደግሞ ሁለንተናዊ ተሀድሶን በሚያመጣ ሀገራዊ ምክክር ፊት ቆመናል፡፡

ታሪክ ጠባቂዎች እንሁን፡፡ ወንድማማች ሆነን በቅለን ወንድማማች ሆነን ካልገዘፍን መሳቂያ ነው የምንሆነው፡፡ እንደጣውንት የምንተያይባቸው የልዩነት አውዶች በፍቅር ሚዛን ፊት እዚህ ግቡ የሚባሉ አይደሉም፡፡ ግን ማክረርና ማባባስ ስለሚቀናን ለዓላማቸው የመስዋዕት በግ ሆነን ቀርበንላቸዋል። እስከመቼ? በትናንሽ እንከኖች ብዙ ዋጋ እየከፈልን ስለመሆኑ ከእኛ ወዲያ ምስክር የለም፡፡ ሁላችንም ተነጋግረን በመግባባት ሀገር እናድን፡፡

ትውልድ የፖለቲካ አስተሳሰብ ውጤት ነው፡፡ ከአጼው ሥርዓት ወዲህ ያሉ የፖለቲካ አስተሳሰቦች ትውልዱ ላይ የልዩነት ቀንበር ጭነውበታል ። አሁን ያለው ትውልድ የዛ ዘመን የፖለቲካ አስተሳሰብ ውጤት ነው፡፡ ይሄ ብሄር ተኮር እሳቤ እንዲጠራ ደግሞ ሰፊ ልብ፣ ከሰፊ ሃሳብና መድረክ ጋር አስፈልጓል፡፡ በእንዶድ እንደጠራ ሸማ ከልዩነትና ከጥላቻ ጠርተን ኢትዮጵያን የምንመስልበት ጊዜ ላይ ነን፡፡

የጸብ ከተማ የፍቅርን ታሪክ ያፈርሳል፡፡ ታሪክ የፈረሰባት ሀገር ደግሞ በምንም አትቆምም። ከአሉባልታ ርቀን ሕዝብ በሚያቀራርብ መፍትሄ ተኮር መድረክ ላይ መሳተፍ ለሀገር የምናዋጣው መዋጮ ነው፡፡ ወቅታዊ ችግሮቻችንን በአስታራቂና በአግባቡ በምክረ ሃሳቦች መቃኘት አለብን፡፡ ብሄራዊ ምክክር በሁለንተናዊ ተሃድሶ ኢትዮጵያን የሚታደግ ነውና አሻራችንን ለማሳረፍ እንረባረብ፡፡

በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)

አዲስ ዘመን   ኅዳር 17 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You