የሀገሪቱ የወጪና የገቢ ንግድ ሚዛን ከፍተኛ ልዩነት እንደሚታይበት ይታወቃል፡፡ ይህንንም ሀገሪቱ ለውጭ ገበያ ከምታቀርባቸው ምርቶች ከምታገኘው የውጭ ምንዛሬ ዝቅተኛነትና ለገቢ ምርት ከምታወጣው የውጭ ምንዛሬ ከፍተኛነት መረዳት ይቻላል፡፡
ሀገሪቱ ይህን ክፍተት ለማጥበብ በርካታ ተግባሮችን ታከናውናለች፤ ከእነዚህም መካከል የውጭ ምንዛሬ ለሚያስገኙና የውጭ ምንዛሬ ወጪን ለሚያስቀሩ ወይም ለሚቀንሱ ምርቶች ትኩረት ሰጥታ እየሠራች ያለችበት ሁኔታ ይጠቀሳል፡፡ ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ የግብርና፣ የኢንዱስትሪ እንዲሁም እንደ ወርቅ ያሉ የማዕድን ምርቶችን በስፋት በማምረት ለውጭ ገበያ ከማቅረብ በተጨማሪ፣ ከውጭ የሚገቡ የግብርና ምርቶችን እንዲሁም የኢንዱስትሪ ግብዓቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካትም በስፋት እየተሠራ ይገኛል፡፡
እንደሚታወቀው በሀገሪቱ በርካታ የኢንዱስትሪ ፓርኮች በመንግሥት ተገንብተው ወደ ሥራ ገብተዋል፤ የግሉም ዘርፍ እንዲሁ ኢንዱስትሪዎችን በስፋት እየገነባ ወደ ሥራ አስገብቷል፤ እያስገነባም ይገኛል፡፡ ኢንዱስትሪዎቹ ምርቶቻቸውን ለውጭና ለሀገር ውስጥ ገበያ እያቀረቡ ይገኛሉ፡፡
በግብርናውም ዘርፍ እንዲሁ ከውጭ የሚገቡ የግብርና ምርቶችን በሀገር ውስጥ በማምረት የሀገሪቱን የግብርና ምርቶች ፍላጎት ለመሸፈን በሚደረገው ጥረት በየዓመቱ ምርትና ምርታማነቱን መጨመር ተችሏል፡፡
ለእነዚህ ተኪ ምርቶች ትኩረት ተሰጥቶ መሠራቱን ተከትሎ አመርቂ ውጤቶች መታየት ጀምረዋል። ባለፈው በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት ሁለት ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ ተኪ ምርቶች መመረታቸውን ለእዚህ በአብነት መጥቀስ ይቻላል፡፡ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በቅርቡ እንዳስታወቀው፣ በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በ2016 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት በሦስት ወራት ውስጥ ብቻ የ350 ሚሊዮን ዶላር ተኪ ምርቶች በሀገር ውስጥ ተመርተዋል፡፡ 96 የሚደርሱ አዲስ ተኪ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ማምረት እንደሚቻል በጥናት ተለይቶም ወደሥራ ተገብቷል።
በግብርናው ዘርፍ በኩልም ተመሳሳይ ሥራዎች ተከናውነዋል፡፡ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ተመድቦለት ከውጭ የሚመጣውን ስንዴ በሀገር ውስጥ የስንዴ ምርት መተካት ተችሏል፡፡ በሀገሪቱ በመኸርም በበጋ መስኖ ስንዴ ልማትም እየተካሄደ የሚገኘው የስንዴ ልማት የሀገሪቱን የስንዴ ፍላጎት ብቻ ሳይሆን ማሟላት ያስቻለው ለጎረቤት ሀገሮች ስንዴ በመሸጥ የውጭ ምንዛሬ ማስገኘትም ችሏል፡፡ ለቢራ ብቅል የሚያስፈልገውን ገብስ ሙሉ ለሙሉ በሀገር ውስ ጥ ማምረት የተቻለበትን ሁ ኔታም ሌላው ማሳያ ሆኖ ሊ ቀርብ ይችላል፡፡
በማዕድን ዘርፉም እንዲሁ ከውጭ የሚመጣውን የድንጋይ ከሰል በሀገር ውስጥ ምርት መተካት የተቻለበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ ባለፈው በጀት ዓመት አንድ ነጥብ 186 ሚሊዮን ቶን የድንጋይ ከሰል በሀገሪቱ መመረቱን የማዕድን ሚኒስቴር ሰሞኑን አስታውቋል፡፡ ሀገራዊ ዓመታዊ የድንጋይ ከሰል ፍጆታው ከአንድ ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ቶን በላይ ስለመሆኑ ባለፈው ዓመት የተደረገ ጥናትን ዋቢ አድርጎ ሚኒስቴሩ ጠቁሟል፡፡ ይህም የድንጋይ ከሰል ፍላጎትን በሀገር ውስጥ መተካት ስለመቻሉ አንድ ማሳያ ነው፡፡
ይህ ሁሉ መንግሥት በተኪ ምርቶች ማምረት ላይ የያዘው አቅጣጫ ትክክል መሆኑን ያመለክታል፡፡ እስከ አሁን የተገኘው ውጤት በተኪ ምርቶች ላይ መሥራት ውጤታማ እንደሚያደርግ ያመላክታል፡፡ የሀገሪቱ የኢንዱስትሪ ዘርፍ የውጭ ምንዛሬ የሚያስገኙና የውጭ ምንዛሬን የሚያድኑ ሥራዎች ላይ በተለይ በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በተኪ ምርቶች ላይ በስፋት እየተከናወነ ያለውን ተግባር አጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል፡፡
በግብርናው ዘርፍም እንዲሁ ስንዴ በስፋት የማምረት ሥራው ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት መሆኑ እንዳለ ሆኖ ከውጭ የሚመጣውን የሩዝ ምርት በሀገር ውስጥ ለመተካት የተጀመሩ ሥራዎች መስፋፋት ይኖርባቸዋል።
በማዕድን ዘርፍም በድንጋይ ከሰል ላይ የታየው ውጤት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ማድረግ ላይ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ የድንጋይ ከሰል ምርቱ ሀገሪቱ ለድንጋይ ከሰል የምታወጣውን የውጭ ምንዛሬ ያስቀረ፣ የፋብሪካዎችን የግብዓቱን ጥያቄ በቅርቡ የመለሰ፣ ለበርካታ ዜጎች የሥራ እድል የፈጠረ፣ የዘርፉ ኩባንያዎች እንዲፈጠሩ ያስቻለ ትልቅ ስኬት ተደርጎ መወሰድ ይኖርበታል፡፡
ኢንዱስትሪዎች በድንጋይ ከሰል ላይ የሚያነሱትን የጥራት ችግር ጥራቱን የሚያስጠብቁ ፋብሪካዎች እየተገነቡ ያሉበት ሁኔታ ሊፈታው ይችላል፤ የኢንዱስትሪዎች የድንጋይ ከሰል ፍላጎት እየጨመረ ሊመጣ ስለሚችል ያንን ታሳቢ ያደረገ የድንጋይ ከሰል ምርት አቅርቦት እንዲኖር ከወዲሁ መሥራት ያስፈልጋል፡፡
መንግሥት በተኪ ምርቶች ላይ መሥራቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል በተደጋጋሚ አስታውቋል፡፡ ተኪ ምርት በማምረት የሀገር ውስጥ ፍላጎትን ማሟላት መቻል፣ በዚህም ሂደት የተገኘው ተሞክሮ በራሳቸው ተኪ ምርት ላይ አተኩሮ ለመሥራት ትልቅ አቅም በመሆን ያገለግላሉ፤ በሀገሪቱ የተኪ ምርቶች ፋይዳ በሚገባ ተለይቷል፤ በተጨባጭም ታይቷል፡፡
ተኪ ምርትን በስፋት ለማምረቱ ሥራ በትኩረት መሥራት የመንግሥት ተግባር ብቻ መሆን የለበትም። ውጤቱን ያጣጣሙት ወገኖችና የመላው ሕዝብና የሚመለከታቸው ባለድርሻዎች ሥራ ጭምር መሆን ይኖርበታል፡፡ ተሞክሮውን ማስፋት፣ አዳዲስ ተኪ ምርቶች ላይ አተኩሮ መሥራት፣ የሀገር ውስጥ የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶችን መጠቀም ላይ ያለውን የተሳሳተ አመለካከትም ማረቅ በስፋትና በትኩረት ሊሠራባቸው የሚገቡ ተግባራት ናቸው፡፡ ይህ ሲሆን ሀገርን በብዙ መልኩ እየታደጉ ያሉት ተኪ ምርቶች ተቀባይነት ይጨምራል፤ የማምረቱም ሥራ ይጠናከራል!
አዲስ ዘመን ኅዳር 17 ቀን 2016 ዓ.ም