ሀገራዊ ምክክር ለጋራ ሰላም

በኢትዮጵያ የተለያዩ ዓላማዎችን አንግበው በፖለቲካው መድረክ ላይ የሚገኙ ኃይሎችና ልሂቃን የሃሳብ ልዩነቶች እየሰፉ መሄዳቸው ሀገርን ለብዙ ውጥንቅጥ ዳርጓል፡፡ ልዩነት ተፈጥሯዊ ነው፣ ነገር ግን እነዚህን ልዩነቶች በሠለጠነ መንገድ ማስተናገድ ባለመቻሉ በየአካባቢው ግጭቶች እንዲበራከቱ ሆኗል፡፡

ግጭት ያስነሱትንም ሆነ ያላስነሱትን ልዩነቶች እና ጥያቄዎች መሠረት በማድረግ ተቀራርቦ በውይይት ችግሮች እንዲፈቱ በማድረግ ሀገራዊ አንድነትን የመገንባት አስፈላጊነት አያጠያይቅም። ለዚህ ደግሞ ሀገራዊ ምክክር አወንታዊ ሚና ይኖረዋል ተብሎ ይታመናል።

በኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች መካከል መሠረታዊ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የተፈጠሩ ልዩነቶችን ለማርገብ ይቻል ዘንድ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በአዋጅ እንዲቋቋም ተደርጓል፡፡ ኮሚሽኑ ለሥራው ይረዳው ዘንድም በክልሎች ተዘዋውሮ ከተለያዩ ህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ውይይት አድርጓል፡፡

ከህብረተሰቡም አጀንዳዎችን ተቀብሏል። በተጨማሪም ለመገናኛ ብዙኋን የተለያዩ ሥልጠናዎችን ሰጥቷል፡፡ የኮሚሽኑ መቋቋም በተለይ ሰላም ወዳድ ለሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ትልቅ ተስፋን የጫረ ጉዳይ ነው፡፡ በየጊዜው አዳዲስ የብጥብጥ አጀንዳ እየቀረጹ ሀገሪቱን ሰላም ለማሳጣት የሚጥሩ ኃይሎች በበዙበት በዚህ ወቅት ችግሮችን ሊፈታ የሚችል አካል መፈጠሩ የብዙዎችን ተስፋ ያለመለመ ነው። ህብረተሰቡም ኮሚሽኑን ለመርዳት በቻለው መጠን እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል፡፡

ኮሚሽኑ በአዋጅ ከተሰጡት ሥራዎች መካከል ከዚህ በፊት በመንግሥታዊም ሆነ መንግሥታዊ ባልሆኑ ተቋማት የተደረጉ ሀገራዊ የምክክር ሂደቶችን እና የተገኙ ውጤቶችን ያጠናል፣ በቀጣይ በሚያካሂዳቸው ሀገራዊ ውይይቶች በግብዓትነት የሚጠቀማቸው መሆኑንም ይጠቀሳል፡፡

ቀደም ብሎ ሀገራዊ መግባባት ለማምጣት ይረዳሉ የተባሉ ውይይቶች የተደረጉ ቢሆንም በሊህቃን መካከል መግባባት ስላልነበረባቸው ውጤት አላመጡም፡፡ በተለይ በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት በሚደረጉ ክርክሮች ላይ የሚነሱት የተሳሳቱ ትርክቶች በአንድ ጉዳይ የተለያየ እውነታ እንዲፈጠር አድርገዋል፡፡

እነዚህ የተሳሳቱ ትርክቶች እንዲታረሙ የምክክር ኮሚሽኑ ዋነኛ ሥራ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ከዚህም ባለፈ ፤ በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ያለውን የተራራቀ የአመለካከት ልዩነት በአግባቡ እንዲያስተናግዱ ማድረግ የሚያስችል አስቻይ ሁኔታ ለመፍጠርም መልካም አጋጣሚ የሚፈጥር ነው፡፡

ይህ ሲባል በሀገራችን ክልል አቀፍና ሀገር አቀፍ ፓርቲዎች የሚያራምዱት የፖለቲካ ርዕዮተዓለም ኢትዮጵያ ከሚለው ሀገራዊ መንፈስና ስሜት የሚቀዳ በማድረግ ሀገራዊ አንድነትን በጠንካራ መሠረት ላይ ለማዋቀር የተሻለ እድል የሚፍጠር ነው፡፡

በአጠቃላይ ኮሚሽኑ በልሂቃኖች መካከል ሀገራዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ያሉትን ልዩነቶች በጥናት፣ በሕዝባዊ ውይይቶች ወይም ሌሎች አግባብነት ያላቸውን መንገዶችን በመጠቀም የመለየት ሥራ ካከናወነ በኋላ ትኩረት የሚደረግባቸው ነጥቦችን በመለየት ሀገራዊ መግባባት እንዲፈጠርባቸው ያደርጋል፡፡

በዚህም ቁጭ ብሎ የመነጋገር ልምድ ይዳብራል፤ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትም ይሰፍናል። ከዚህ በዘለለ በሚደረጉ ህዝባዊ ውይይቶች በሚነሱ ሃሳቦች ላይ በመመርኮዝ ወደፊት የተሻለ ሀገር ለመፍጠር የሚያግዙ ውሳኔዎች ሊተላለፉ እንደሚችሉ ይጠበቃል፡፡

በርግጥ ኮሚሽኑ በዋነኛነት በተለያዩ አካባቢዎች የሚታዩትን ግጭቶች እንዲቆሙ ለማድረግ ቅድሚያ ተቀራርቦ መወያየት ላይ ማተኮር እንዳለበት በተለያዩ ጊዜያት በሰጠው መግለጫ አሳውቋል፡፡ ለዚህ ደግሞ ኃላፊነቱን ወስዶ አቀራርቦ ለማወያየት በትጋት እየሠራ ነው።

ይህ ቢያንስ ሰላም ለመፍጠር ብዙ አማራጮች እንዳሉ ያመላከተ ነው። ሁሉን ያሳተፈ ሀገራዊ መግባባት መፍጠር ጊዜ የሚሰጠው ጉዳይ አለመሆኑ ታውቆ በተቃራኒ ወገን የቆሙ አካላት ወደ ውይይት መምጣት ይጠበቅባቸዋል፡፡

ለኮሚሽኑ መጠናከር የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለምክክር የሚሆኑ አጀንዳዎችን መምረጥ፣ ከኮሚቴዎችም ሆነ ከሕዝብ የሚገኙ ምክረ ሃሳቦችን ለመንግሥት ማቅረብ፣ ለኮሚሽኑ እንቅስቃሴ የሚያስፈለጉ የውስጥ ደንብ እና መመሪያዎችን ማውጣትን ጨምሮ መሠረታዊ የአስተዳደራዊ ተግባራትን በበላይነት እንደሚመራ በአዋጅ ተደንግጓል።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውስጥ የሚገኙ አባላት ከተለያየ የሕዝብ ክፍል እንደመምጣታቸው ከመጡበት አካባቢ የሚነሱ ሃሳቦችን ማንፀባረቅ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑም ያልተገደበ ድጋፍ ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡

ኮሚሽኑ አጀንዳዎችን ለይቶና ለምክክር የሚሆኑ ግብዓቶችን ካሟላ በኋላ ምክክሮች ብቃት ባለው ገለልተኛ በሆነ አካል የሚመሩ፤ ያለመግባባት መንስኤዎችን በትክክል የሚዳስስ አጀንዳ ላይ የሚያተኩሩ ይሆናሉ፡፡ ግልጽ ብሎም ለማስፈጸም የሚያስችሉ ውጤታማ ሀገራዊ ውይይትን የሚያስተናግድ ሥርዓትን የመዘርጋት ሥልጣኑን ተጠቅሞ ውጤት የሚያመጣ ሥራ እንደሚሠራ ይጠበቃል።

ልዩነቶች በነበሩባቸው ሃሳቦች ላይ ሰፊ ውይይት ተደርጎ ሀገራዊ አንድነት የሰፈነባት ኢትዮጵያ እንደምትፈጠር የሁሉም ዜጋ እምነት ነው፡፡ ይህ ሲባል ግን ጉዳዩ ለኮሚሽኑ ብቻ የሚተው መሆን የለበትም፡፡ ኮሚሽኑ ሂደቱን የሚያስፈጽም ተቋም ነው፤ ለዚህ ጉዳይ መሳካት ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ኃላፊነቱን መወጣት አለበት፡፡

በየመድረኮች የምንሰማው፣ በመገናኛ ብዙኃን የምናየውና የምንሰማው ሰላም ለማምጣት ሁሉም መረባረብ እንዳለበት የሚመክር ነው። ለዚህ ግን ሁሉም ኃላፊነት ወስዶ የሚሳተፍ መሆን አለበት፡፡ ተፈጥሯዊ የሆነውን ልዩነት ዋጋ እያሳጣነው ነው፡፡ ልዩነት ወደ ግጭት የሚወስድ አስመስለነዋል፡፡

ሙዚቃ አለመውደድ መብት ነው፡፡ ሙዚቃ መውደድም መብት ነው፡፡ ሙዚቃ የሚወድ ሰው የማይወዱትን ከጠላ፣ ሙዚቃ የማይወድም የሚወዱትን ከጠላ ችግሩ ያኔ ነው፡፡ ፖለቲካው ላይ የምናየው ልዩነት ልክ እንደዚህ አይነት ነው፡፡ መሠልጠን ማለት የሰዎችን ልዩነት ማክበር ነው፡፡

የሠለጠኑ ሀገራትን የሥልጣኔ ምጥቀት መዘርዘር ወደ ሥልጣኔ አይወስድም፡፡ ወደ ሥልጣኔ የሚወስደው እነርሱን መሆን ነው፡፡ ከየት ተነስተው ዛሬ የት ላይ እንደደረሱ ማየት ነው፡፡ የራሳችንን የቁርሾ ታሪኮች እየጠቀስን ለዛሬ መጨቃጨቂያ ከማድረግ በሥልጣኔ የበለጡን ሀገራት ከየት ተነስተው ምን አድርገው ነው ኮሽ የማይልበት ሀገር የፈጠሩት የሚለውን ብናስተውል ነው ለምንቆረቆርለት ሕዝብ የሚጠቅመው፡፡

በአጠቃላይ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ተመካክረን መፍትሔ የምናመጣበትና የሠለጠነች ሀገር የምናስረክብበት ትልቅ እድል ነው ፤ ይህንን እድል በአግባቡ ተጠቅሞ ፤ የኮሚሽኑን ዓላማ ለስኬት ማብቃት የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት ነው !።

ብርሀን ፈይሳ

አዲስ ዘመን   ኅዳር 17 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You