ከመሃል አዲስ አበባ በምስራቁ አቅጣጫ 520 ኪሎ ሜትሮችን እንደተጓዝን የበረሃ ንግስት በመባል የምትጠራዋን እና የተለያዩ ሕዝቦች በአንድነት የሚኖሩባትና ቀደምት ስልጣኔን ከተላበሱ የኢትዮጵያ ከተሞች መካከል አንዷ የሆነችውን ድሬዳዋ ከተማን እናገኛለን። ይህች ከተማ የውጭ ዜጎችን ጨምሮ በርካቶች ከተለያየ ቦታ በመምጣት ከትመው በፍቅር ተቻችለው የሚኖሩባት ከተማ ናት።
ታዲያ በስራ ጉዳይ ወደ ድሬዳዋ ከተማ በተጓዝኩበት ወቅት በከተማዋ የሚገኘውን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የድሬዳዋ ቁጥር አንድ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ለማየት ችዬ ነበር። በወቅቱ ከሄድኩበት የስራ ጉዳይ ባሻገር ሌላ ጉዳይ ቀልቤን ገዛኝ። ገና የጣቢያውን መግቢያ በር አልፈን ወደ ውስጥ ስንገባ ከፊት ለፊታችን የከተማዋን የበረሃ ሙቀት የሚያስረሳ ፈገግታ የተላበሱና እድሜያቸው 50ዎቹ መጨረሻ የሆኑ አንድ ግለሰብ እንኳን ደህና መጣችሁ በማለት ተቀበሉን። ፈገግታቸው ከልብ እንደሆነ ያስታውቃል።
ጣቢያውን እያዞሩ አስጎበኙን፤ አሁንም ትኩረቴ በእሳቸው ላይ ነው። ለአቀባበል ብቻ የመሰለኝ የፊታቸው ፈገግታ አሁንም እንዳለ ነው። እያንዳንዷን ነገር የሚያደርጉት ከልባቸው ነው። ለሚጠየቁት ጥያቄ ሁሉ ያለመሰልቸት በፈገግታ የታጀበ ምላሽ ይሰጣሉ። እኔ ከራሴ ጋር ንግግር ጀምሬያለው ከፈገግታቸው ጀርባ ያለው የሕይወታቸው ገፅ ቢገለጥ ምን አይነት ቁምነገር ይገኝበት ይሆን እያልኩ ለራሴ ጥያቄ እያቀረብኩ ነበር። በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ውስጥ ለ35 ዓመታት በትጋት መስራታቸውን ሳውቅ ደግሞ ስለእሳቸው የማወቅ ጉጉቴ ጨመረ።
እኚህ ሰው፤ በረጅም ቁመታቸው ላይ ቀጠን ያለ የሰውነት አቋም ያላቸው፤ ጥቁር የቆዳ ቀለም ተላብሰው ሙሉ ለሙሉ ነጥቶ ጥጥ የመሰለ ፀጉራቸውን በአጭሩ የተቆረጡ፤ ድሬዳዋ የሚለው ቃል በሳቸውም ሆነ ከሌላ ሰው ገና ከአንደበት ሲወጣ ፊታቸው የሚበራው፤ ቀልጣፋና ጨዋታ ወዳድ የሆኑት የድሬዳዋ ቁጥር አንድ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ስራ አስኪያጅ አቶ ሚካኤል አልይ ሙሳ ናቸው። የዛሬው የሕይወት ገፅታ ዓምድ እንግዳችን አቶ ሚካኤል አልይ ሲሆኑ የሕይወት ተሞክሯቸውን እንደሚከተለው አዘጋጅተን አቅርበናል።
የልጅነት ጊዜ
በምዕራብ ሐረርጌ መሰላ በምትባል ከተማ፤ ሳቃላፍቶ በምትባል የገጠር ቀበሌ ማሕበር በ1958 ዓ.ም ከአባታቸው ከአቶ አልይ ሙሳ እና ከእናታቸው ወይዘሮ ሀዋ አብዱላህ የተወለዱት አቶ ሚካኤል ለቤተሰባቸው ሶስተኛ ልጅ ሲሆኑ አባታቸው ከሶስት ሚስቶች 15 ልጆች የነበራቸው በግብርና ስራ የሚተዳደሩ ነበሩ።
በጊዜው ትምህርት የመማር እድል በጣም ትንሽ ነበር። ዘመኑ የንጉሳውያን አገዛዝ ዘመን የነበረበት በመሆኑ ሰፊ የትምህርት እድል የሚሰጠው ለባለርስት ልጆች ነበር። አቶ ሚካኤል በወቅቱ ይኖሩባት ከነበረችው መሰላ ከተማ የመማር እድል ያገኙት የጭሰኛ ልጆች ጥቂት እንደነበሩ ያስታውሳሉ። ከጥቂቶቹ መካከልም አቶ ሚካኤል አንዱ ነበሩ።
ለአቶ ሚካኤል ትምህርት ቤት ገብቶ ትምህርት መከታተል የአባታቸው ሚና ከፍተኛ ነበር። አባታቸው ልጆቻቸው ትምህርት እንዲማሩላቸው ከፍተኛ ጉጉት የነበራቸው ቢሆንም በወቅቱ ብዙ የጭሰኛ ልጆች የመማር እድልን ተነፍገው ነበር። ነገር ግን አባታቸው ልጃቸው አንዲማርላቸው ባላቸው ፍላጎት የመማር እድል ተመቻቸላቸው። ታዲያ አቶ ሚካኤል ያገኙት የመማር እድል እንዲሁ በቸርነት የተሰጣቸው አልነበረም። ከሰኞ እስከ ዓርብ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ በሳምንት ሁለት ቀን ወደ ባለርስቶቹ መኖሪያ በመሄድ የጉልበት ስራ የመስራት ግዴታ ነበረባቸው። ልጅ ስለነበሩ ጉልበት የሚያስፈልጋቸውን እንደመቆፈር እና መፍለጥ ያሉ ስራዎችን መስራት አይችሉምና በቡና ዛፎች ላይ በመውጣት ቡና ሲለቅሙ ይውሉ ነበር።
በተመቻቸላቸው የመማር እድል እዚያው መሰላ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ትምህርታቸውን መከታተል ጀመሩ። በወቅቱ ትምህርት ቤቱ ያስተምር የነበረው እስከ ስምንተኛ ክፍል ብቻ በመሆኑ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ለመከታተል ወደ አሰበ ተፈሪ በማቅናት ጨርጨር አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በመግባት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል። እስከ መሰናዶ ያለውን የትምህርት ጊዜ በዚሁ ትምህርት ቤት በመከታተል ሀገር አቀፍ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ወሰዱ።
የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከወሰዱ በኋላ በ1978 ዓ.ም ኮተቤ ወደነበረው እና በወቅቱ ኤሌክትሪካልና ኤሌክትሮኒክስ ኢንስቲትዩት በመባል ወደሚታወቀው የመብራት ኃይል ተቋም በመግባት ለሁለት ዓመት የዲፕሎማ ትምህርታቸው ተከታተሉ። ዲፕሎማቸውን የወሰዱት በኤሌክትሪካልና መካኒካል ቴክኖሎጂ የትምህርት ዘርፍ ሲሆን በወቅቱ ትምህርቱን የተከታተሉት 312 ምሩቃን ነበሩ።
የስራ ሕይወት
ትምህርት ጨርሰው ዲፕሎማቸውን እንደያዙ ቀጥታ ወደ ስራው ዓለም ተቀላቀሉ። በኛ ጊዜ እንዳሁኑ ትምህርት ጨርሶ ስራ ለመፈለግ መዞር የሚባል ነገር አልነበረም የሚሉት አቶ ሚካኤል፤ ትምህርት ጨርሰን ከተመረቅን በኋላ ለስራ ምድብ እጣ ይወጣ ነበር ይላሉ። ታዲያ አቶ ሚካኤል ትውልድና እድገታቸው በምስራቁ የኢትዮጵያ ክፍል በመሆኑ ወደዛው የመሄድ ከፍተኛ ፍላጎት ነበራቸው። ከምስራቁ የኢትዮጵያ ክፍልም ደግሞ ድሬዳዋ ከተማን እጅግ ይወዷት ስለነበር የስራ ምድባቸው ወደ ድሬዳዋ ከተማ እንዲሆን ፅኑ ፍላጎት ነበራቸው። በወቅቱ ኤርትራም አንዷ የኢትዮጵያ ክፍል ነበረች፤ ስለዚህ ምሩቃኑ ኤርትራን ጨምሮ በሁሉም የኢትዮጵያ ክፍል በእጣ መበተን ነበረባቸው።
አቶ ሚካኤልም ይህንን በልባቸው እያሰቡ ድሬዳዋ እንዲደርሳቸው እየተመኙ እጣው አወጡ። ያቺ ቀን ታዲያ ለአቶ ሚካኤል ትልቅ የደስታ እና ለአዲስ ሕይወት ጅማሮ መሰረት የሆነች እለት ሆነች። የልባቸው ፍላጎት ሰምሮ ያወጡት እጣ የናፈቋት ድሬዳዋ ከተማ ላይ አረፈ። ዛሬም ድረስ ስለዛች ቀን ሲያስታውሱ ፊታቸው የሚጋባ ደስታ ይነበብበታል።
መጀመሪያ ስራ ሲጀምሩ ደመወዛቸው 347 ብር የነበረው አቶ ሚካኤል በጊዜው በሁሉም የትምህርት ደረጃ ተለይቶ የተቀመጠ የደሞዝ እርከን እንደነበር ያስታውሳሉ። በደመወዝ እርከኑ መሰረት ለዲፕሎማ 347 ብር፣ ለዲግሪ 500 ብር፣ ለኢንጂነር 600 ብር፣ ለዶክትሬት 835 ብር ይከፈል ነበር።
ለስራ ወደ ድሬዳዋ ከተመለሱ በኋላ መጀመሪያ የስራ ገበታቸው ላይ የተገኙት በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ድሬዳዋ ቁጥር-1 የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ኤሌክትሮ ሜካኒክ በመሆን ነበር። ከጅምሩ የተመደቡት ግን በወቅቱ በሳቢያን አካባቢ በግንባታ ላይ በነበረው ድሬዳዋ ቁጥር-3 የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ነበር። የጣቢያው ግንባታ እስከሚጠናቀቅ በቁጥር-1 ኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ስራቸውን እንዲጀምሩ ተደርገው የስራ ሕይወታቸው በዚሁ ጣቢያ ቀጠሉ።
ከዓመታት በኋላ መጀመሪያ ወደተመደቡበት ድሬዳዋ ቁጥር-3 የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ በመዛወር ለአምስት ዓመታት በቴክኒሻንነት ካገለገሉ በኋላ ወደ ድሬዳዋ ቁጥር-2 የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ በመግባት ለአስር ዓመታት አገልግለዋል። ከዚያ ተመልሰው መጀመሪያ ስራ በጀመሩበት ድሬዳዋ ቁጥር-1 የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ለ20 ዓመታት ያገለገሉ ሲሆን አሁንም በዚሁ ጣቢያ ስራ አስኪጅ በመሆን ጣቢያውን በመምራት ላይ ይገኛሉ። አቶ ሚካኤል በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ውስጥ ከቴክኒሻንነት እስከ ስራ አስኪያጅነት ላለፉት 35 ዓመታት አገልግለዋል።
የትምህርት ዝግጅት ከዲፕሎማ በኋላ
አቶ ሚካኤል በዲፕሎማ ተመርቀው ያልሟት በነበረቸው ድሬዳዋ ከተማ ስራ ከጀመሩ በኋላ ወደ ሌላ ቦታ ሄዶ የመስራትን ሃሳብ ከአዕምሯቸው አውጥተው የተረጋጋ ሕይወት መስርተው መኖር ጀመሩ። ለድሬዳዋ ያላቸው ፍቅር የዲግሪ ትምህርታቸውን ላለመቀጠል እንዲወስኑ አደረጋቸው። ይህንን ውሳኔ ለምን እንደወሰኑ ሲያስረዱ “ትምህርት ብቀጥልና ዲግሪ ብይዝ የትምህርት ማስረጃዬን አስገብቼ ወደ ሌላ ቦታ እዛወራለሁ። እኔ ይህ እንዲሆን አልፈለኩም። መኖር በምፈልግበት ቦታ ቤት ሰርቼ ቤተሰብ መስርቼ ልጆች ስላፈራሁ ድሬን መልቀቅ ለኔ የሚታሰብ አልነበረም” ይላሉ።
የተወለዱት ደሬዳዋ ከተማ ባይሆንም በልጅነታቸው ብዙ ጊዜ ድሬዳዋ ይመላለሱ ስለነበር በርካታ ከድሬዳዋ ጋር የተያያዘ የልጅነት ትዝታ አላቸው። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በአሰበ ተፈሪ በሚከታተሉበት ወቅት ዓርብ ከሰዓት በኋላ ከልጅነት ጓደኛቸው ጋር በእቃ መጫኛ ባቡር ተሳፍረው ወደ ድሬዳዋ ከተማ በመምጣት ቅዳሜንም እዛው በመዋል ማታ በመጡበት አመጣጥ በእቃ ባቡር ተሳፍረው ሂሳብ ሳይከፍሉ ተደብቀው ወደ አሰበ ተፈሪ ይመለሱ ነበር። በልጅነት ትንሽ ልባቸው ውስጥ ትልቅ ቦታ የነበራት ድሬዳዋ ለኑሮም ሆነ ለስራ የሚመርጧት ከተማ ሆነች። ለዚህም ነው ገና ስሟን ሲጠሩትም ሆነ በሌሎች ስትጠራ ፊታቸው ፈገግታ የሚሞላው።
በወቅቱ ድሬዳዋ የሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝብ በፍቅር የሚኖርባትና አሁን ቀዝቀዝ ቢልም የንግድ ማዕከል የነበረች ከተማ መሆኗን የሚናገሩት አቶ ሚካኤል፤ ከዚህ ሁሉ በላይ ደግሞ የከተማዋ ሕዝብ አንዱ ከአንዱ ሳይለያይ ማን ምን በላ፣ ማን ምን ለበሰ ብሎ ልዩነት ሳይፈጥር በአብሮነት የሚኖርበት ሕዝብ ነው። በወቅቱ በቀኑ 12 የሚደርሱ የንግድ አውቶቢሶች ወደ ከተማዋ ይገቡ ነበር። ከፍተኛ የንግድ እንቅስቃሴ የነበረባት ከተማ በመሆኗ ደሬዳዋ ከሰባት ሰዓት በኋላ በ ሆቴሎች አልጋ ለማግኘት አዳጋች የሆነች ከተማ እንደነበረች ያስታውሳሉ።
ስለ ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል
የዛሬው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ያኔ የኢትዮጵያ መብራት እና ኃይል ባለስልጣን በመባል ይጠራ እንደነበር አቶ ሚካኤል ይናገራሉ። ከዚያም የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኮርፖሬሽን ወደሚለው ስያሜ ተለወጠ። ከጊዜ በኋላ ደግሞ ጥናቶች ተደርገው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት እና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ተብሎ በሁለት እንዲከፈል መደረጉንና አሁን ያለውም በዚሁ መሰረት መሆኑን ይስረዳሉ።
ዘርፉ በርካታ ስራዎች የሚሰሩበት በመሆኑ እና ሁሉንም ስራ በበቂ መልኩ ተደራሽ ለማድረግ በማለም መንግስት ተቋሙ በሁለት ተከፍሎ ሁለት የተለያዩ ግን ደግሞ ተመጋጋቢ የሆኑ ተቋማት እንዲሆኑ አደረገ። የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በመባል የተሰየመው ተቋም ከማመንጫዎች የሚመነጨውን የኤሌክትሪክ ኃይል ተቀብሎ በኤሌክትሪክ ማከፋፈያ ጣቢያዎች እንዲገባ ያደርጋል። የአትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በመባል የተሰየመው ተቋም ደግሞ፤ የማከፋፈያ ጣቢያዎች ለማሕበረሰቡ የመብራት ኃይል እንዲደርስ ካደረጉ በኋላ የቆጣሪ መትከል፣ ትራንስፎርመር መትከል፣ እና የመብራት አገልግሎት ክፍያ የመሰብሰብ ስራዎችን ይሰራሉ።
ከ35 ዓመታት በፊት አቶ ሚካኤል ስራ ሲጀምሩ በድሬዳዋ ቁጥር-1 የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ የኃይል ምንጭ በመሆን ያገለግል የነበረው በነዳጅ የሚሰራ የዲዝል ጀነሬተር ነበር። ኦጋዴን ድረስ ሙሉ ለሙሉ የሚሸፍን የኤሌክትሪክ ኃይል ይሰጥ የነበረውም በዚሁ የዲዝል ጀነሬተር ነበር። አሁን ግን ውሀን ጨምሮ የተለያዩ ታዳሽ ኃይሎችን በመጠቀም በቂ ኃይል ማመንጨት ስለተጀመረ ዲዝል ጀነሬተሮች ከአገልግሎት ውጪ እንዲሆኑ ተደርገዋል። ይህም ተቋሙ ያለፈበትን የለውጥ ሂደት የሚያሳይ መሆኑን ነው አቶ ሚካኤል የሚናገሩት።
ተቋሙ የነበረውን የሰው ኃይል እና አሁን ላይ ያለበትን ደረጃ አቶ ሚካኤል ሲያነጻጽሩ፤” ያኔ የነበረው የሰው ኃይል አነስተኛ በመሆኑና ስራ የሚከናወነው በጥቂት ሰራተኞች ብቻ ነበር፤ ጥገና የሚያስፈልጋቸው ብልሽቶች በሚያጋጥሙበት ወቅት የጥገና ባለሙያዎች ከአዲስ አበባ እስኪመጡ ይጠበቅ ነበር። አሁን ላይ ተቋሙ በቂ የሰው ኃይል ስላለው በድሬዳዋ ከተማ ያለውን ስራ በሙሉ ጥገናን ጨምሮ እዚሁ ባሉ ሰራተኞች ብቻ የሚከናውንበት አቅም ላይ ተደርሷል” ይላሉ።
በስራ ዓለም የሚያስታውሱተ ገጠመኝ
የሚሰሩት ስራ በቀጥታ ከኤሌክትሪክ ጋር የተያያዘ በመሆኑ በርካታ አሳዛኝ ገጠመኞችን አሳልፈለዋል። ስራው እጅግ በጣም ጥንቃቄን የሚጠይቅ በመሆኑ ከጥንቃቄ ጉድለትም ሆነ በስራ ላይ በሚያጋጥም አደጋ ሕይወትን እስከማጣት የሚያደርስ መስዋዕትነት ሊያስከፍል ይችላል። ታዲያ አቶ ሚካኤልም በሚሰሩበት ጣቢያ በአንድ ወቅት ያጋጠማቸውን ነገር መቼም እንደማይረሱትና ሁል ጊዜ ሲያስታውሱት የሚገረሙበት መሆኑን ይናገራሉ።
ነገሩ እንዲህ ነው። ከዕለታት ባንዱ ቀን እንደተለመደው አቶ ሚካኤል ዘወትር ከማይጠፉበት የስራ ገበታቸው ላይ ተገኝተው ስራቸውን እያቀላጠፉ በነረበት ሰዓት ከጣቢያው ለከተማው ነዋሪ የኤሌክትሪክ ኃይል የሚሰጥበት መስመር በድንገት ብልሽት ይገጥመዋል። በወቅቱ መስመሩ “አማ” በመባል የሚጠራ እንስሳ ገብቶበት ትራንስፎረመሩ ፍንዳታ ስለገጠመው በጣቢያው የነበሩ የጥገና ሰራተኞችን በማስተባበር ማለዳ የተጀመረ የጥገና ስራ ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ላይ ይጠናቀቃል።
በጊዜው ቴክኖሎጂም እንዳሁኑ አልተስፋፋም ነበርና መቆጣጠሪያ (ብሬከሩ) የሚዘጋውም የሚከፈተውም በእጅ የነበረ ሲሆን ብልሽቱ ባጋጠመበት ወቅት ግን መቆጣጠሪያ (ሪሞት ኮንትሮል) ተገጥሞ ገና ስራ ላይ መዋሉ ነበር። ስራውን ጨርሰው ጥገናው ውጤታማ መሆኑን ለማረጋገጥ ከርቀት ሆነን እንሞክረው የሚል ሃሳብ አቀረቡ። ሁሉም በሃሳቡ ተስማምተው ከትራንስፎርመሩ ራቅ ብለው በመቆም መስራቱን መሞከር ጀመሩ። ከደቂቃዎች በኋላ ትራንስፎርመሩ ከፍተኛ ፍንዳታ አሰማ። ሁሉም በድንጋጤ ከቆሙበት ለደቂቃዎች መንቀሳቀስ አቃታቸው።
አቶ ሚካኤል ሁኔታውን ሲያስታውሱ እንዲህ ይላሉ፤ “ከዚያ ቀደም እንደምናደርገው ትራንስፎርመሩን የምናበራውና የምናጠፋው በእጃችን ቢሆን በእለቱ ጥገናውን ስንጨርስ ትራንስፎርመሩ ላይ ወጥቼ የማበራው እኔ ስለነበርኩ ዛሬ በሕይወት አልኖርም ነበር።” ይህንና መሰል አጋጣሚዎች ኤሌክትሪክ ስራ ውስጥ በርካታ ቢሆኑም ስራው አስደሳች መሆኑን አቶ ሚካኤል ይናገራሉ።
የአመራርነት ጥበብ
አቶ ሚካኤል ለ35 ዓመታት ያገለገሉበትን ተቋም በስራ አስኪያጅነት በማስተዳደራቸው ደስታቸው ወደር የለውም። እሳቸው የመምራትና የማስተዳደር ስራ በተቋሙ የስራ ሂደት ውስጥ ብቻ የተገደበ አይደለም። በተቋሙ ተቀጥረው ለአምስት ዓመት ከሰሩ በኋላ በውስጣቸው የኖረ የማሕበራዊ ኑሮ ፍቅር ነበርና ገና በወጣትነታቸው በምስራቅ ሪጅን የድሬዳዋ የክበቦችና የሰራተኞች መረዳጃ እድር ሊቀመንበር ሆነው ተመርጠው ኃላፊነት ተቀበሉ።
ወቅቱ የእድሩ ኮሚቴዎች እድሩን በትነው ገንዘቡን ተከፋፍለው የጠፉበት ወቅት ነበርና ሰላምን የሚወዱት መክሰስም ሆነ መከሰስ የማይፈልጉት አቶ ሚካኤል በወጣትነት ጉልበታቸው እና ባደረባቸው ቁጭት ተነሳስተው ጉዳዩን ፍርድ ቤት ድረስ በመውሰድ ፍትህ አግኝተው የተዘረፈውን የእድር ብር ለማስመለስ ቻሉ። ሃቀኝነታቸውና ለእድሩ ያላቸው መቆርቆር በብዙዎች ዘንድ ተወዳጅ ያደረጋቸው አቶ ሚካኤል በየሁለት ዓመቱ ሊቀመንበር ይቀየራል የሚለውን የእድሩን መተዳደሪያ ሕግ በፍቅር አሸንፈው ለአስር ዓመታት እድሩን በሊቀመንበርነት መሩ። በእነዚህ አስር ዓመታት ውስጥ ስለመልካም መሪነታቸው በማለት የእድሩ አባላት ሁለት ጊዜ አራት አራት ግራም ወርቅ በስጦታ አበርክተውላቸዋል።
የአቶ ሚካኤል የመምራት አቅም በዚህ ብቻ የተገደበ አልነበረም። የእድር ሊቀመንበርነታቸውን ከለቀቁ በኋላ የምስራቅ ሪጅን የሰራተኛ ማሕበርን ለ15 ዓመታት በሊቀመንበርነት መርተዋል። ጣቢያውን በስራ አስኪያጅነት ከመምራት አልፈው የሰራተኞችን እድር እና የሰራተኛ ማህበርን በዚህ መልኩ በታማኝነት በመምራታቸው የሚሰማቸውን ደስታ ሲናገሩ በኩራት ነው።
አቶ ሚካኤል ከስራ ሕይወታቸው ባሻገር ባለትዳርና የሁለት ወንዶችና የአንድ ሴት ልጅ አባት ናቸው። በስራው ዘርፍ ብቻ ሳይሆን በቤታቸውም ልጆቻቸውን በቀና ጎዳና እንዲጓዙ ሌት ተቀን የሚተጉ አባት ሲሆኑ ለትምህርት ትልቅ ቦታ በመስጠታቸው ሶስቱንም ልጆቻቸውን አስተምረው በዲግሪ ፕሮግራም ለማስመረቅ በቅተዋል።
ስራን አጥብቀው የሚወዱትና ዘውትር ከስራ ቦታቸው የማይጠፉት ታታሪው አቶ ሚካኤል ከመደበኛው የስራ ገበታቸው በጡረታ ለመሰናበት የሁለት ዓመት እድሜ ብቻ ቀርቷቸዋል። ስለጡረታ ሲነሳ አቶ ሚካኤል ሁሌም የሚሉት ነገር አላቸው፤ “ስራን በአግባቡ ሰርቶ በሰላም ጡረታ መውጣትን የመሰለ ነገር የለም። ጡረታ ወጣው ማለት ከስራ ዓለም እርቆ ቤት መቀመጥ ማለት አይደለም። እኔ በበኩሌ በሰራሁበት የስራ መስክ ጥሩ እውቀት አለኝ፤ ከዚህ በኋላም ብዙ መስራት እችላለሁ” ባይ ናቸው።
በሃገራችን ስለጡረታ ያለው እሳቤ እንደሚያስገርማቸው የሚናገሩት አቶ ሚካኤል፤ በሌላው ዓለም እድሜ ከስራ አይገድብም፤ እድሜያቸው ገፍቶ በእርጅና ዘመናቸው ሀገር እስከመምራት የደረሱ በርካቶች ናቸው። ይህ በኛ ሀገር ሲተገበር አይስተዋልም፤ ከጡረታ በኋላ በብዙ መስክ ሀገር የሚጠቅም እቀውቀት ይዘው ቤት የተቀመጡ ብዙዎች አሉ ይላሉ። “ከጡረታ በኋላ ከዘራ የምንይዝበትን ስነልቦና ማስቀረት ይኖርብናል” ባይ ናቸው።
“ዩኒቨርሲቲዎቻችን ብቁ የሰው ኃይል እያመረቱ አይደለም፤ ይህንን በድፍረት መናገር እችላለሁ” ይላሉ አቶ ሚካኤል ስለዩኒቨርሲቲዎች የትምህርት ጥራት ሲናገሩ። ይህንን ለማለት ያበቃቸውም ተመራቂ ተማሪዎች ለተግባር ልምምድ እሳቸው ወደሚመሩት የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ በመምጣት ሲለማመዱ ከታዘቡት በመነሳት ነው። ለልምምድ ወደ ጣቢያው የሚመጡ ተማሪዎች ትምህርቱን በንድፈ ሃሳብ እንጂ በተግባር እንዴት እንደሚሰራ የሚያውቁት ነገር የለም፤ እኛ በተማርንበት ወቅት የነበረ ተማሪ በዲፕሎማ ደረጃ ስለሚማረው ትምህርት በተግባር የተሻለ ያውቃል ሲሉ በቁጭት ይናገራሉ።
እሳቸው በተማሩበት ጊዜ የነበረውን የትምህርት ስርዓት ሲያስታውሱ አሁን ካለው የትምህርት ስርዓት በብዙ መልኩ የተሻለ መሆኑንና በንድፈ ሀሳብ ከሚሰጠው ትምህርት ጎን ለጎን የተግባር ትምህርቱንም በትምህርት ተቋማት ውስጥ ጨርሰው ይወጡ እንደነበር ይናገራሉ። አሁን ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚመረቁ ተማሪዎች ኤሌክትሪካልና ሜካኒካል ኢንጂነር ከሚለው ስያሜ በስተቀር ይዘውት የሚወጡት የተግባር እውቀት ባለመኖሩ ወደ ስራ ዓለም ከተቀላቀሉ በኋላ ሲቸገሩ ሃዘን እንደሚሰማቸው ይገልፃሉ።
“አሁን ያለው ትውልድ በወረቀት ላይ ያለ እውቀት እንጂ በተግባር ሊተረጎም የሚችል እውቀት እየያዘ አይደለም። ይህ ሊታሰብበት የሚገባ ጉዳይ ነው፤ በዚህ ከቀጠልን ነገሩ እየከበደ ይሄዳል ” ይላሉ።
ስለኢትዮጵያ
አሁን ላይ ኢትዮጵያ ነዳጅ የላትም፤ ነዳጇ የኤሌክትሪክ ኃይሏ ነው። በዚህ ረገድ ደግሞ አቅሟን ለማሳደግ የአባይ ግድብን በመስራት ላይ ናት። ሕዝቦቿም በተለያየ መልኩ የግድቡን ግንባታ ሲደግፍ ቆይተዋል። ወደፊትም ይህ ተጠናክሮ ቀጥሎ በውሃም ሆነ በታዳሽ ኃይሎቿ በምታመነጨው የኤሌክትሪክ ኃይል ጎረቤት ሃገራት የምታዳርስና የገቢ ምንጯ ሆኖ የምትበለፅግበት ዘርፍ እንዲሆን እመኛለው ካሉን በኋላ ተሰነባብተን እኛም ወደ አዲስ አበባ ተመለስን።
በለጥሻቸው ልዑልሰገድ
አዲስ ዘመን ኅዳር 16 ቀን 2016 ዓ.ም