የኢትዮጵያ አየርመንገድ – አንድ ለእናቱ…!!!

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ድምራቸው 67 የሚደርሱ አውሮፕላኖች ግዥ ለመፈጸም፤ የአውሮፕላኖቹ ምርት እንዲጀመር ከአሜሪካው አውሮፕላን አምራች ኩባንያ ቦይንግ ጋር የግዥ ትዕዛዝ ስምምነት ያደረገ ሲሆን ፤ ስምምነቱ የተፈጸመው ሁለቱም ድርጅቶች እየተሳተፉ በሚገኙበት በዱባይ የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ ዘርፍ ዓውደ ርዕይ ላይ ነው። አሥራ አንድ የ787 ድሪም ላይነር ሞዴሎች፣ ሃያ 737 ማክስ እንዲሁም 36 ዓይነታቸው በግልጽ ያልተለዩ ጀቶች ግዥ ይፈጸማል።

አውሮፕላኖቹ ተመርተው በሚቀጥሉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ አየር መንገዱ እንደሚረከብ ሰሞኑን የወጡ ዘገባዎች ያሳያሉ። ከአፍሪካ አየር መንገዶች እስከዛሬ ይኼን ያህል ቁጥር ያለው አውሮፕላን ግዥ በአንድ ጊዜ አለመፈጸሙንና የኢትዮጵያ አየር መንገድ የመጀመሪያ መሆኑን ቦይንግ ባወጣው መግለጫ ጠቅሷል። አዳዲሶቹ አውሮፕላኖች የተሻሻሉ ሞዴሎች መሆናቸውና በውጤታማ የነዳጅ አጠቃቀም 20 በመቶ፤ የበካይ ጋዝ ልቀትንና የድምጽ ብክለት 50 በመቶ እንደሚቀንሱ ተነግሯል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአሁኑ ሰዓት 147 አውሮፕላኖች ያሉት ሲሆን፣ ከቦይንግ የታዘዙት 67ቱ በጥቂት ዓመታት ሲደርሱ ቁጥሩ በግማሽ ያድጋል ተብሎ ይጠበቃል ሲሉ የመንግስትም የግልም ሚዲያዎች በስፋት እየዘገቡ ነው። ይህ የአየር መንገዱ ስኬት አንድ ማሳያ ነው። ለመሆኑ አየር መንገዱ እንዴት ለዚህ ስኬት ሊበቃ ቻለ ወይም ሚስጥሩ ምንድነው የሚለውን በስሱ እንመልከትና ወደ አመሠራረቱ እናዘግማለን።

የኢትዮጵያን አየር መንገድን ዛሬ ለደረሰበት ስኬት ያበቃው የመጀመሪያው መሪዎቹ ባለ ራዕይ መሆናቸው ነው። ርዕያቸውን እውን ለማድረግ ደግሞ ስትራቴጂካዊ ፕላን ቀርጸው፣ የረጅም ጊዜ ርዕይ አስቀምጠው እና አየር መንገዱ ምርጥ እንዲሆን በቁርጠኝነት ሌት ተቀን መስራታቸው አየር መንገዱን ስኬታማ አድርጎታል። ሁለተኛው ደግሞ አዳዲስ አውሮፕላኖችና ቴክኖሎጂ ላይ ያለስስት ኢንቨስት ማድረጉ ሲሆን፤ ሶስተኛው ከመሰሎቹ ጋር ስትራቴጂካዊ አጋርነት መመስረቱ ነው።

ሌላውና አራተኛው ለስልጠናና ለዕድገት ቁርጠኛ መሆኑ ሲሆን፤ አምስተኛ የገቢ አማራጮቹን ማስፋቱ፤ ስድስተኛው ከተለዋዋጩ ገበያ ጋር ራሱን ማላመዱ፤ ሰባተኛው ደግሞ በቡድን ስራ፣ በደንበኞች አገልግሎትና በምርጥ አሰራር የዳበረ የኮርፖሬት ባሕል ማጎልበት መቻሉ ነው ዛሬ ለደረሰበት እጅን በአፍ የሚያስጭን ስኬት ያበቃው።

ይሄን ማስጠበቅ፣ ማዝለቅና ማስፋት ይገባዋል። የሚነሱበትን ቅሬታዎች ከስር ከስር የመፍታት ባሕሉን ማጎልበትና ገለልተኝነቱን መከላከልና ማስከበርም ይጠበቅበታል። ስለስኬቱ ይሄን ያህል ሳወሳ እንደማንኛውም ኩባንያ ችግር እንዳለበት፣ ጉድለትና ውስንነትም እንደሚታይበት ዘንግቸው ፍጹም ሙሉ በኩልዬ እንዳልሆነ ጠፍቶኝ አይደለም። ስኬቱ በብዙ እጥፍ ስለሚበልጥ እንጂ።

ይልቅ የኢትዮጵያ አየር መንገድን ባሰብሁ ቁጥር ሁል ጊዜ ቁጭት የሚፈጥርብኝ አንድ ለእናቱ ሆኖ መቅረቱ ነው። እንደሱ የተዋጣላቸውና የተመሠከረላቸው አለማቀፍ አኅጉራዊና ሀገራዊ ድርጅቶች አለመፈጠራቸው ሁል ጊዜ ቁጭት ይፈጥርብኛል። የመልካም አስተዳደር፣ የግልጽነትና የተጠያቂነት ችግሮች ተደጋግመው የሚነሱባቸው የመንግስት የልማት ድርጅቶች እና ሲቪል ሰርቪሱ የአየር መንገዱን ዳና መከተል ለምን ተሳናቸው? ልዩነቱ ለምን የሰማይና የምድር ያህል ሆነ ስል እብሰከሰካለሁ።

ከአየር መንገዱ የአመራር ክህሎት መቅሰም ስንችል የመዋቅር ማሻሻያ፣ ቢፒአር፣ ቢኤስሲ፣ ካይዘን፣ ወዘተረፈ እያልን ዓለምን ብናካልልም ዛሬም ከዚህ አዙሪት ለምን መውጣት አልቻልንም ስል እጠይቃለሁ። የአየር መንገዱን ስኬት ማስፋት ወደ ሌሎች ተቋማት ማላማድ ለምን ተሳነን ስል አቤት እላለሁ። አየር መንገዱን ውጤታማ ያደረጉ አሰራሮችንና ኮርፖሬት ባሕሉን ቀምረን ወደ ሌሎች የማስፋት ነገር እንዴት የመንኮራኮር ሳይንስ ሆኖ ይቀርብናል።

እስኪ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት፤ የምርምርና የጥናት ድርጅቶች፤ ተመራማሪዎች እና የኢፌዴሪ ሲቪል ሰርቪስ ተወያዩበት እያልሁ፤ የሀገራችን ኩራት፣ የሰንደቅ ዓላማችን ሰንደቅ ስለሆነው አየር መንገድ አመሰራረትና ታሪካዊ ዳራ ላነሳሳ ወደድሁ። ብሩህ ዓለምነህ በአንድ ወቅት በአማርኛው ሪፖርተር “በታሪክ ሲቃ”የተወለደው የኢትዮጵያ አቪዬሽንና የአየር መንገዳችን በሚል ርዕስ ያጋሩትን መጣጥፍ መርጫለሁ።

‹‹በታሪክ ሲ በ1921 ዓ.ም. ነው፤ ርቀቱን አስሉት፤ ስሜቱን አስቡት! ክስተቱ እንግዳ ነው፤ ከዛሬ 87 ዓመት በፊት ክረምት ላይ። የአዲስ አበባ ሰው የክረምቱን ብርድ ለመቋቋም በተሰበሰበበት አጋጣሚ ሁሉ በከተማው ስለተናፈሰው እንግዳ ነገር ያወጋል። ቡና ሲጠጣ፣ ዕድር ላይ ሲታደም፣ ካቲካላ ቤት ሲሰባሰብ፣ እሳት ዳር ሆኖ ወግ ሲጠርቅ ሁሉ በከተማው ስለተናፈሰው ነገር ያወራል።

ስልክ ሲመጣ የሰይጣን ሥራ ነው ያለ ሕዝብ፣ መኪናን የሾርኒ ሲመለከት የነበረ ሕዝብ፣ ቴአትር ቤትን የሰይጣን ቤት ያለ ሕዝብ፣ ዛሬ ደግሞ እንኳን ለመቀበል፣ ጭራሽ ለማሰብ እንኳ ፈጽሞ የማይችለውን ነገር እንዲመለከት ቀን ተቆርጦለታል። ነሐሴ 12 ቀን 1921 ዓ.ም. የአዲስ አበባ ሕዝብ በሌሊት ተጠራርቶ፣ ኩታውንና ጋቢውን ደርቦ ወደ አንድ አቅጣጫ ይተማል። የክረምቱ ውርጭና አመዳይ፣ ጭቃና አረንቋ ሳይበግረው ሕዝቡ 15 ኪሎ ሜትር አቋርጦ በባዶ እግሩ ወደ ገፈርሳ ይተማል።

ንጉሡ ከነሚኒስትሮቻቸው፣ መኳንንቱና መሳፍንቱ፣ ዲፕሎማቶችና የሃይማኖት አባቶች ሳይቀሩ የታደሙበት ይኼ ክስተት በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ እጅግ እንግዳ የሆነውን ነገር ይዞ ሊመጣ ነው። ገፈርሳ ላይ በአበባ፣ በዘንባባና በሰንደቅ ዓላማ ያሸበረቁ ድንኳኖች ተዘጋጅተዋል፤ ገፈርሳ እጅግ ተሞሽራለች። ይህ ሁሉ ሽር ጉድ ‹‹በራሪውን የሰይጣን ክንፍ›› ለማየት ነበር። ሕዝቡ በርቀት በሚያያቸው አሞሮች ላይ ሁሉ እጁን እየቀሰረና ዓይኑንም እየሸነቆረ ‹‹በራሪውን ሰይጣን›› ቀድሞ ለማየት አብዝቶ ታገሰ።

ከብዙ ጥበቃና ትዕግሥት በኋላ ግን የሆነ ድምፅ ከርቀት ይሰማ ጀመር። ሕዝቡ በሁሉም አቅጣጫ ያለውን የሰማይ ጥግ ላይ ሁሉ በዓይኑ አማተረ። ወቅቱ ክረምት ነው፤ ሰማዩ ዳምኗል። ምንም የሚታይ ነገር ሳይኖር ድምፅ ብቻ ይመጣል፤ ድምፅ ብቻ ሕዝቡን ይዞራል። ድምፁም በጣም እየቀረበና ይበልጥ እየጮኸ ሲመጣ የሕዝቡ ጉጉት ወደ ድንጋጤና ፍርኃት ተቀየረ። ድንገት ግን ‹‹በራሪው የሰይጣን ክንፍ›› ድርብርቦሹን ደመና ቀዶ ወጣ። ሰይጣኑ አናቱ ላይ እንዳያርፍበት ሕዝቡ በየአቅጣጫው ይፈረጥጥ ጀመር። ድንጋጤና ግርምት፣ ፍርኃትና ጉጉት የናጠው የሕዝብ ትርምስ። ገፈርሳ ግራ ገባት።

‹‹በራሪው የሰይጣን ክንፍ›› ግን በሕዝብ ግርግር ሳይደናገጥ ሕዝቡን እንደ ታቦት ዞሮ ድንገት ድንኳኖቹ ፊት ለፊት ዠርገግ ብሎ አረፈ። ትርምሱ ቆመ፣ ድንጋጤው ወደ ፈንጠዝያ ተቀየረ። ገፈርሳን ዕልልታ፣ ፉጨትና ጩኸት ዋጣት! ሕዝቡ ካፒቴኑን ተሸክመው ተቀባበሉት፤ ገፈርሳ በፉከራና በሽለላ ተናጠች። እዚያ ቦታ ላይ ሆኖ ያንን ፈንጠዝያ፣ ያንን ጩኸት የማይጋራ ሊኖር አይችልም።

ንጉሥ ተፈሪም ዘለው ከድንኳናቸው ወጡ፤ እንባ እየተናነቃቸውም ተስፈንጥረው ካፒቴኑ ላይ ተጠመጠሙበት። ሕዝቡ ከንጉሣቸው ጋር በአንድ ላይ ሲቃ ውስጥ የገቡበት ክስተት ነው የመጀመሪያዋ ፓቴዝ አውሮፕላን ወደ አገራችን መምጣት። በመሆኑም የኢትዮጵያ የአቪዬሽን ታሪክ የሚጀምረው ሕዝቡንና መሪውን በአንድ የታሪክ ሲቃ ላይ በመግመድ ነው።

ይኼ የሕዝቡ ሲቃ ግን እንዲሁ እንግዳ በሆነ ክስተት ብቻ የተፈጠረ አይደለም። ይልቅስ ታሪክ ላይ የተመረኮዘ ገፊ ኃይል አለው እንጂ። የኢትዮጵያን ‹‹የቀድሞ ማዕረጓንና ኃይሏን›› የመመለስ እልህ። ንጉሥ ተፈሪም በዚያው ክስተት ላይ ያሰሙት ንግግርም ይኼንኑ የሚያረጋግጥ ነው። ‹‹ኢትዮጵያ…›› አሉ ንጉሡ፣ ‹‹ኢትዮጵያ በጥንት ሥልጣኔዋ ዘመን ከኢየሩሳሌምና ከዓረብ፣ ከሕንድም መንግሥታት ጋር በንግድና በፖለቲካ ትገናኝ ነበር።

አሁንም ያንን ማዕረጓንና ኃይሏን ለመመለስ፣ እንዲሁም የአገር ውስጥ ጉዳያችንን በፍጥነት ለመፈጸም እንዲረዳን ይኼንን የአየር ባቡር አስመጣን።›› ይኼንን የንጉሡን ንግግር ስናሳጥረው የአገራችን የአቪዬሽን ታሪክ ገና ከመነሾው ሁለት ተልዕኮዎችን አንግቦ የተነሳ ነው። ብሔራዊ ኩራትን መመለስና ኢኮኖሚያዊ ጥቅምን መቀዳጀት።

‹‹ኢኮኖሚያዊ ጥቅም›› የሚለውን ተልዕኮ የተቀበለው ከራሱ ከአቪዬሽን ኢንዱስትሪ ባህሪ ሲሆን፣ ‹‹ብሔራዊ ኩራትን መመለስ›› የሚለውን ተልዕኮ የተቀበለው ደግሞ ከሕዝቦቿ ‹‹ታሪካዊ ሲቃ›› ነው። በዚህ አገራዊ ርዕይ አማካይነት አቪዬሽን የትውልዱን ቁጭት ይዞ የአገሪቱ ታሪክና ርዕይ ተጋሪ ሆኗል። በዚህ ተልዕኮም የኢትዮጵያ አቪዬሽን ከአገራችን ታሪክ ጋር ብዙ ውጣ ውረዶችን አብሮ አሳልፏል።

በመሆኑም የኢትዮጵያን የአቪዬሽን ታሪክ ከአገሪቱ ታሪክ ነጥለን ልንመለከተው አንችልም። የመጀመሪያዋ አውሮፕላን ወደ ኢትዮጵያ የገባችበትን ዘመን በአገሪቱ የታሪክ ሒደት ውስጥ ከተን ስንመለከተው፣ ከዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ ጀምሮ ኢትዮጵያን የማዘመንና የቀድሞ ክብሯን ለመመለስ ሲደረጉ ከነበሩ ጥረቶች መካከል አንዱ ሆኖ እናገኘዋለን።

1921 እስከ 1928 .. የፋሽስት ወረራ ጊዜ ድረስ የነበሩት ሰባት ዓመታት የኢትዮጵያ የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ ጠንካራ መሠረት የተጣለበት ወቅት ነበር። አውሮፕላን ከማብረር እስከ አውሮፕላን መሥራት፣ ከበረራ ትምህርት ቤት እስከ አውሮፕላን መጠገኛ ጋራዥ (ሀንጋር) ከኢትዮጵያውያን አውሮፕላን ጠጋኞች እስከ ሴት አብራሪዎችን ማፍራት የተቻለበት ወቅት ነበር። የፋሽስት ወረራ ግን ሁሉን ነገር አወደመው፣ ሁሉን በዜሮ አባዛው።

የኢትዮጵያ የአቪዬሽን ታሪክ ከአገራችን ታሪክ ጋር ብዙ ውጣ ውረዶችን አብሮ አሳልፏል። በፋሽስቶች በተወረርንበት ወቅት እሱም አብሮ ተወሯል። በድል አድራጊነት በዓለም መድረክ ላይ ቀና ባልንበት ጊዜም፣ እሱም ከእኛ ጋር ቀና ብሏል። አገራችን ከፋሽስት ወረራ 1933 .. ነፃ በወጣች ማግሥት የአገራችን የነፃነት ብሥራት ሆኖ የተቋቋመው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ነው። አየር መንገዱ በዚህ ታሪካዊ ወቅት መቋቋሙ ከኋላ የአገሪቱን ቁጭት፣ ከፊት ደግሞ የሕዝቦቿን ራዕይ ተሸክሞ የሚበር አየር መንገድ እንዲሆን አድርጎታል።

ምሥጋና ለጸሐፊ ትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ ይሁንና በኢትዮጵያ መንግሥትና በአሜሪካው ትራንስ ወርልድ ኤርላይንስ (TWA) ኩባንያ መካከል በተደረሰ ስምምነት መስከረም 1 ቀን 1938 .. 2.5 ሚሊዮን ብር የኢትዮጵያ አየር መንገድ በቦርድ ተቋቋመ። የመጀመሪያ ዓለም አቀፍ በረራውንም መጋቢት 30 ቀን 1938 .. በአስመራ በኩል በማድረግ ወደ ካይሮ አደረገ።

ከዚህ በኋላ አየር መንገዱ አገሪቱ የምትገኝበትን ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታና የጥንታዊ ቅርስ ባለቤትነት ዕድሎችን እየተጠቀመ በፍጥነት ማደግ ጀመረ። ከተቋቋመ ገና በአራተኛ ዓመቱም ዓለም አቀፍ በረራዎቹን ከካይሮ በተጨማሪ ወደ ጅቡቲ፣ ኤደን፣ ጅዳ፣ ናይሮቢ፣ ፖርት ሱዳን፣ ካርቱም፣ ቦንቤና ካራቺ አስፍቷል።

በኢትዮጵያ የአቪዬሽን ታሪክ ውስጥ አጠቃላይ ኢንዱስትሪውን ሥር ነቀል ወደ ሆነ የላቀ ደረጃ የወሰዱ ሁለት አብዮቶች ተከስተዋል። ሁለቱም አብዮቶች ታዲያ የተከሰቱት በኢትዮጵያ አየር መንገድ የዕድገት ግፊት የተነሳ ነው። የመጀመሪያው አብዮት የመጣው የኢትዮጵያ አየር መንገድ 1952 .. የቦይንግ ጄት አውሮፕላኖችን ለመግዛት በመወሰኑ ነው።

ይህ ውሳኔ አብዮት ያስከተለበት ምክንያት ደግሞ በወቅቱ የነበረውና በጣሊያን የተሠራው የልደታው አየር ማረፊያ፣ አዲስ የሚገዙትን ጄት አውሮፕላኖች የማስተናገድ ብቃት የሌለው መሆኑ ነው። በመሆኑም ውሳኔው ሌላ አዲስ ዘመናዊ ኤርፖርት ቦሌ ላይ እንዲሠራ ከማድረጉም በተጨማሪ የቅኝት (Air Navigation) እና የአየር ትራፊክ መቆጣጠሪያ መሣሪያዎችም ከጊዜው ጋር እንዲዘምኑ ምክንያት ሆኗል።

ከአዲሱ ኤርፖርት ግንባታ ጎን ለጎንም አየር መንገዱን ኢትዮጵያዊ የማድረጉ ከፍተኛ ጥረትም የሚዘነጋ አይደለም። የአየር መንገዱን ቁልፍ የሥራ ሒደቶችን (የበረራ፣ የጥገና፣ የሽያጭና የአስተዳደር ሥራዎችን) ከአሜሪካውያን ተረክቦ በኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች የመተካቱ ጥረት እየተሳካ ሄዶ፣ 1963 .. ኮሎኔል ስምረት መድህኔን የመጀመሪያው የአየር መንገዱ ኢትዮጵያዊ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አድርጎ በመሾም ትልቅ ዕመርታ አስመዘገበ።

ሁለተኛው አብዮት ደግሞ ርዕይ 2025 (...) ነው። ይህ ርዕይ ልክ እንደ 1952 .. ውሳኔ ሁሉ በአዲስ አበባ ኤርፖርትና በአየር ትራፊክ ቁጥጥሩ ላይ ሥር ነቀል ለውጥ እንዲመጣ ያስገደደ ክስተት ብቻ ሳይሆን፣ የአየር መንገዱንም የውስጥ አደረጃጀት ከመሠረቱ እየቀየረ ያለ ውሳኔ ነው። .. 2010 የተቀረፀው ይህ 15 ዓመት የዕድገት መርሐ ግብር አየር መንገዱን ወደ ሰባት የተለያዩ የትርፍ ማዕከልነት በማዋቀር ወደ ግዙፍ የአቪዬሽን ግሩፕ ኮርፖሬትነት እያሳደገው ይገኛል።

በዚህም አየር መንገዱን ... 2025 112 አውሮፕላኖች 18 ሚሊዮን መንገደኞችንና 710,000 ቶን ጭነቶችን ወደ 92 ዓለም አቀፍ መዳረሻዎች በማጓጓዝ በዓመት አንድ ቢሊዮን ዶላር ትርፍ ላይ ለመድረስ አልሟል። በእርግጥ አየር መንገዱ በአሁኑ ወቅት የዓለም አቀፍ መዳረሻዎችን ብዛት 92 በማድረስ ከዕቅዱ አሥር ዓመት ቀድሞ ማሳካት ችሏል።

ይህ የአየር መንገዱ ርዕይ የአዲስ አበባ ዓለም አቀፍ ኤርፖርትን በሁለት ዙር፣ 2004 .. 1.1 ቢሊየን ብር እና በአሁኑ ወቅት ደግሞ በአምስት ቢሊዮን ብር፣ ግዙፍ የማስፋፊያ ፕሮጀክቶች ውስጥ እንዲገባ ከማድረጉም ባሻገር፣ የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት በአዲስ አበባ አቅራቢያ ሌላ ግዙፍ የኤርፖርት ከተማ የመገንባት ውሳኔ ላይ እንዲደርስ ምክንያት ሆኗል።

በአየር ትራፊክ ቁጥጥሩ ላይም ከፕሮሲጀራል ቁጥጥር እጅግ ዘመናዊ ወደሆነው የራዳር የአየር ትራፊክ ቁጥጥሩ እንዲቀየር ምክንያት ሆኗል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ እንደ ቦይንግ B787 እና ኤርባስ A350 ያሉ ዘመናዊ አውሮፕላኖች ባለቤት የመሆን ጥረቱም ሆነ፣ በሌሎች አየር መንገዶች ላይም እያደረገ ያለው ኢንቨስትመንትም የዚሁ ርዕይ 2025 አካል ነው።

ሻሎም ! አሜን።

በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)

Recommended For You