ሀገራችን በማዕድን ሀብት ከበለጸጉ ሀገራት አንዷ ስለመሆኗ በስፋት ይነገራል። ይህንን ሀብት አውቆ ለመጠቀም በየወቅቱም የተለያየ ጥረቶች ቢደረጉም ፤ የሚጠበቀውን ያህል ከሀብቱ ተጠቃሚ መሆን አልተቻለም።
ከዚህ የተነሳም እንደ ሀገር ዕጣ ፈንታችንን በሚቀይር፤ ነገዎቻችንን ብሩህ ማድረግ በሚችል ሀብት ላይ ቆመን የድህነትና ኋላቀርነት መገለጫ ከሆኑ ሀገራት ተርታ ለመሰለፍ፤ ብሄራዊ ክብራችን በሚያሳንስ የታሪክ አዙሪት ውስጥ ለመገኘት ተገድደናል።
ይህንን የሀገራችንና እና የሕዝባችን ትናንቶች መቀየር የሚያስችል ሀብት አውቆ ለማልማት ከለውጡ ማግስት ጀምሮ በመንግስት ደረጃ የተለያዩ ጥረቶች እየተካሄዱ ነው። ከዚህ ውስጥም የማዕድን ዘርፉ በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫ መደረጉ ተጠቃሽ ነው።
በርግጥ እንደ ሀገር ድህነትን ታሪክ ለማድረግ ለጀመርነው የልማት ጉዞ የማዕድን ዘርፉ ሊኖረው የሚችለው አስተዋጽኦ የማይተካ ነው። በዘርፉ ኃላፊነት በሚሰማው መንገድ መንቀሳቀስ ከቻልን ደግሞ ሁኔታዎች ከምናስበው ባለፈም ሊሆን እንደሚችል መገመት አይከብድም።
የተሻለች ሀገር ለመጪው ትውልድ ለማስተላለፍ ከሁሉም በላይ ይህንን ሀብት በሚፈለገው ደረጃ ማወቅም፤ አልምቶ የኢኮኖሚው ዋልታ ማድረግም ተገቢ ነው። ለዚህ ደግሞ ከመንግስት ባሻገር የምርምር ተቋማትና የግል ባለሀብቱ ተሳትፎ የሚኖራቸው አስተዋፅኦ ከፍተኛ እንደመሆኑ፤ ይሄንኑ ሚናቸውን ማበርከት ይኖርባቸዋል።
በተለይም የምርምር ተቋማት ይህን ሀገራዊ ክፍተት በመሙላት ሂደት የሚኖራቸው አስተዋጽኦ፤ ለዘርፉ ትኩረት ከመስጠት ጀምሮ፤ ተመራማሪዎቻቸው በዘርፉ ዙሪያ ምርምሮችን እንዲያካሄዱ ማበረታታትን የሚያካትት ነው። ከዚህም ባለፈ ዘርፉን እያጋጠሙ ላሉ ችግሮች በጥናት ላይ የተመሰረቱ መፍትሄዎችን ማፈላለግ ይጠበቅባቸዋል።
ይህንን ሀገራዊ ሀብት ለማስተዋወቅም መንግሥት፣ ባለሀብቶች እና በዘርፉ የተሠማሩ የግል ሴክተሮች ድርሻቸው የጎላ ነው፤ ያሉንን አቅሞች አቀናጅተን ዘርፉን በሚፈለገው ደረጃ አልምተን ተጠቃሚ መሆን ካልቻልን የሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እድገት ጥያቄ ውስጥ መግባቱም የማይቀር ነው።
በርግጥ ሀገሪቱ የከበሩ ማዕድናት መገኛ ስለመሆኗ ከትናንት በስቲያ የተከፈተው የማዕድን ኤክስፖ ተጨባጭ ማሣያ ነው፤ ይህ እንደ ሀገር ሀብቱን አውቀን በማልማት ከድህነትና ኋላቀርነት የመውጣት እልህ ውስጥ እንድንገባ መነቃቃት ሊፈጥር የሚችል ነው። ይሄን ማዕከል በማድረግም ከሰሞኑ የማዕድን ኤክስፖ ተካሂዷል።
ይሄ ተማሪዎች፣ ተመራማሪዎች፣ ነጋዴዎች፣ ኢንቨስተሮችና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ደግሞ በዘርፉ ምን እንዳለና ምን እየተሠራ እንደሆነ በመማር ሀገራዊ ኢኮኖሚውን በአቅማቸው መጠን ማሳደግ የሚያስችላቸውን መነሳሳት ሊፈጥር የሚችል ነው።
ኤክስፖው ኢትዮጵያ ያላትን የማዕድን ክምችት የሚያሳይ፣ የማዕድን ሀብትን ወደውጭ ለመላክ ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር እና ለሚቀጥለው የብልጽግና ጉዟችን መሠረት የሚጥል ስለመሆኑም በብዙ መልኩ ለጥያቄ የሚቀርብ አይሆንም።
የምናስበው የዕድገት ደረጃ ላይ ለመድረስም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በኤክስፖው መክፈቻ ላይ እንዳሉት፤ በማዕድን ዘርፉ የተሰማሩ አልሚዎች በግል ማምረትና ኢንቨስት ማድረጋቸውን ማቆም ይጠበቅባቸዋል።
ከዚህ ይልቅ እንደ ሀገር በጋራ መሥራት የምንችልበትን፣ እውቀት የምናሰባስብበትንና የምንበለጽግበትን መንገድ መፍጠር ይገባል። ይህንን በአግባቡና ኃላፊነት በሚሰማው መንገድ ማድረግ ከቻልን የሀገሪቱ የብልጽግና ጉዞ መሠረት ይፋጠናል!
አዲስ ዘመን ኅዳር 16 ቀን 2016 ዓ.ም