ሀገራችን ኢኮኖሚያቸው በግብርና ላይ ከተመሠረቱ የዓለም ሀገራት አንዷ ተደርጋ የምትጠቀስ ነች። ለዘርፉ የሚስማማ የተፈጥሮ አካባቢ፤ ሰፊ የውሀ እና የሰው ሀብት ባለቤትም ናት። እነዚህን አቅሞች ስትራቴጂክ በሆነ መንገድ አቀናጅታ መንቀሳቀስ ከቻለች ነገዎቿ ብሩህ ስለመሆናቸው ብዙዎች ይስማማሉ ።
መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ በሀገራችን የከርሰ ምድር ውኃን ሳይጨምር 123 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር የሚጠጋ የውኃ ሀብትና ከ36 ሚሊዮን ሔክታር በላይ ሊለማ የሚችል መሬት አለ፤ ከዚህ ውስጥ እስካሁን እየለማ ያለውም 16 ሚሊዮን ሔክታር ያህሉ ብቻ ነው፡፡
ከዚህ ውስጥ ከ5 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሄክታር በላይ በመስኖ የሚለማ ሲሆን፤ ከዚህ ውስጥም እስካሁን የለማው ከ1.1 ሚሊዮን ሄክታር የበለጠ አይደለም፤ ይህም ሀገሪቱ በዘርፉ ምን ያህል የቤት ሥራ እንደሚጠብቃት በተጨባጭ አመላካች ነው።
እንደ ሀገር በግብርናው ዘርፍ /በእርሻ/ ያለንን ይህንን ሰፊ አቅም ወደሚጨበጥ አቅም በመለወጥ፤ ሀገርን ከምግብ እህል ተመጽዋችነት ለመታደግ መንግሥት ባለፉት አራት ዓመታት ሰፋፊ ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል።
በተለይም ሀገሪቱ ለስንዴ ምርታማነት ያላትን አመቺና ሰፊ የተፈጥሮ አካባቢ/መሬት/ እና የውሀ ሀብት በማቀናጀት እያካሄደ ያለው የበጋ መስኖ ልማት በዓለም አቀፍ ደረጃ ሰፊ እውቅናን በማትረፍ፤ ለተሞክሮነት ተመራጭ እየሆነ ይገኛል።
ሀገራችን ከሰሃራ በታች ካሉ የአፍሪካ አገሮች ስንዴን ለማምረት የሚበቃ የተሻለ በቂ መሬት፣ ውኃ፣ አምራች ኃይል ባለቤት እንዳላት፤ ከሰሐራ በታች ካሉ የአፍሪካ ሀገራትም በስንዴ ምርት ቀዳሚ ስለመሆኗ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
የተለያዩ ጥናቶች እንደሚጠቁሙት ደግሞ በሀገሪቱ ከአሥር ሚሊዮን በላይ አርሶ አደሮች ስንዴ በማምረት ላይ ተሠማርተዋል፤ ይህ አኃዝ ከአጠቃላይ የሀገሪቱ አርብቶ አደር 25 በመቶ የሚሆነውን የሚሸፍን ነው ፡፡
ይህም ሆኖ ግን እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ሀገሪቱ በየዓመቱ ከአንድ ቢሊዮን ዶላር ያላነሰ ወጪ በማድረግ ስንዴ ከውጪ ስታስገባ ቆይታለች፡፡ ለዚህ የሚሆን የውጪ ምንዛሪ ማግኘቱ በራሱ የቱን ያህል ትልቅ ሀገራዊ ፈተና እንደነበርም የሚታወስ ነው ፡፡
ይህንን እውነታ ለመለወጥ ባለፉት አራት ዓመታት በመንግሥት በኩል ሰፋፊ ሥራዎች ተሠርተዋል፤ እየተሠሩም ነው። በተለይም በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ዙሪያ እየተከናወኑ ያሉ ሀገራዊ ሥራዎች ተስፋ ሰጭ ከመሆን አልፈው፤ የሚጨበጥ ስኬት መገለጫ ሆነዋል፡፡
እስካሁንም በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ከአንድ ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በዘር ተሸፍኗል። በያዝነው ዓመት በበጋ በመስኖ ልማት ብቻ ሦስት ሚሊዮን ሄክታር መሬት በስንዴ ሰብል በመሸፈን 147 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሠራ ነው፡፡
ባለፉት አራት ዓመታት በስንዴ ልማቱ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ በመሠራቱ ቀደም ባሉት ጊዜያት ቢሊዮን ዶላሮችን ወጪ በማድረግ ወደ ሀገር ውስጥ ሲገባ የነበረውን ስንዴ ሙሉ በሙሉ ማስቀረት ተችሏል፡፡ ይህ በራሱ አዲስና ተስፋ ሰጪ ስኬት ነው፡፡
ከዚህም በላይ “በይቻላል” መንፈስ መነቃቃት ወደ ሥራ የተገባበት የበጋ የመስኖ ስንዴ ልማት፤ በርግጥም ቁርጠኝነት ካለ የሀገርን ትናንቶች የሚቀይሩ ሥራዎችን ዛሬ ላይ መሥራት እንደሚቻል በተግባር ያሳየ ነው።
እንደ ሀገር በምግብ እህል ራሳችንን በመቻል ከጠባቂነት ለመላቀቅ ለጀመርነው ሀገራዊ ጥረትም ሆነ ድህነትን ታሪክ ለማድረግ ለጀመርነው እልህ አስጨራሽ ትግል አቅም መሆን የሚያስችል ትልቅ ውጤት ነው። በግብርናው ዘርፍ እንደ ሀገር ያስመዘገብናቸው ስኬቶች ዋነኛ መገለጫ ተደርጎም የሚወሰድ ነው!
አዲስ ዘመን ህዳር 15/2016