የምሥጋና በረከቱ

የመነሻ ወግ፤

ኅዳር በበርካታ የዓለም ሀገራት የሚታወቀው “የምሥጋና ወር” እየተባለ ነው፡፡ ከሰሜን አሜሪካ እስከ ላቲኑ የዓለማችን ክፍል፣ ከሩቅ ምሥራቅ እስከ አውሮፓና የእኛይቱ አህጉር አፍሪካ ድረስ ብዙ ሀገራት “የኅዳር ቀናትን አየር የሚያጥኑት” በምሥጋናና በመመሠጋገን ነው፡፡ በእኛ ሀገር የኅዳር ወር በአብዛኛው የሚታጠንለት ከመቶ ዓመት በፊት ተከስቶ በርካታ ሺህ ወገኖቻችንን በፈጀው ወረርሽን ወይንም ክፉ ቀን እየተባለ የሚጠራውን “በላ” (Spanish flue) በማስታወስ ነው፡፡

በተጠቀሱት ሀገራት በኅዳር ወር ውስጥ የሚከበረው ብሔራዊ የምሥጋና ቀን (Thanksgiving Day) የቀናት መለያየት ቢታይበትም የዝግጅቶቹ ድምቀት፣ በዓሉን በሚያከብሩ ዜጎች ዘንድ የሚስተዋለው ደስታና መፍለቅለቅ፣ በጋራ የሚታደሙበት ማዕድ ሞገስና ክብር የሁሉም ሀገራት የጋራ መለያ ተደርጎ ይቆጠራል፡፡

በአሜሪካ፣ በካናዳ፣ በጃፓን፣ በጀርመን፣ በአውስትራሊያ፣ በግሪናዳ፣ በቅዱስ ሉቺያ፣ በላይቤሪያ፣ በብራዚል፣ በፊሊፒንስና በሌሎችም በርካታ ሀገራት በኅዳር ወር የሚከበረው የምሥጋና ቀን ታሪካዊ አመጣጥ የተለያየ ቢሆንም ዓላማው ግን እጅግም ልዩነት የማይስተዋልበት ተመሳሳይና ተቀራራቢ ነው፡፡

ፈጣሪ የገበሬዎቻቸውን አዝመራ ስለባረከላቸው ያመሠግናሉ፡፡ ተፈጥሮ በተለያዩ ቀለማት ዛፍ ቅጠሉን አሽሞንሙና ለምታሳምራቸው የመፀው ወራት በሠላም ስለመድረሳቸው ያመሠግናሉ፡፡ የመፀው ወራት ልክ እንደ እኛው ሀገር (ከመስከረም 26 እስከ ታኅሣሥ 25 እንደሚዘልቀው) በሌሎች ሀገራትም እንዲሁ የኅዳር ወር የአበባና የተፈጥሮ ውበት ጎልቶ የሚደምቅበትና የሚታይበት ወር ነው። ዛፎች በተለያዩ ኅብረ ቀለማት አብበውና ፈክተው ማየት ስሜትን በሐሴት ያረሰርሳል፡፡

ይህም ብቻ አይደለም፡፡ ሀገራቱ ሰላምና መረጋጋት የሕዝባቸው ትሩፋት ስለሆነ ያመሠግናሉ። የተራራቀ ቤተሰብ ከየቦታው ተሰባስቦ በፍቅር ማዕድ የሚቆርስበት በዓል በመሆኑም ያመሠግናሉ። የምሥጋናቸው ዓይነትና ብዛት፣ የአከባበራቸው ዘይቤም እንደየሀገራቱ ባህልና ወግ መሠረት የሚከናወን ቢሆንም የሚፈጥረው ስሜትና ድባብ ግን ሁሉም ሀገራት የሚጋሩት የጋራ መገለጫቸው ነው፡፡

ይህ ጸሐፊ በኅዳር አራተኛው ወር “የምሥጋና ቀን – Thanksgiving day” የብሔራዊ ክብር ተጎናጽፎ በሚከበርበት በአሜሪካ ሀገር በቆየባቸው ዓመታት በምን ምክንያት ሳምንቱና ዕለታቱ በደማቅ በዓልነት እንደሚከበሩ በንባብ ካገኘው ዕወቀት በተጨማሪነት ይኖርበት በነበረው ክፍል ግዛት ውስጥ ነዋሪ የሆኑ ወዳጆቹን የቃል ምሥክርነት እንዲሰጡት መጠየቁን ያስታውሳል፡፡ የተሰጠው የቃል ትረካም የሚከተለውን ይመስላል፡፡

“በሚኒሶታ ክፍለ ግዛት የሰፈሩት የመጀመሪያዎቹ ቀዳሚ ቅድመ አያቶቻችንና ምንጅላቶቻችን ኑሯቸው እንዲህ እንደ ዛሬው ያማረና የተሳካላቸው አልነበሩም። ክፍለ ግዛቱ በክረምት ወራት ከሚጥለው የበረዶ ዶፍ የተነሳ እንኳንም ሊኖርበት ቀርቶ ለአንድ ቀንም ቢሆን የሚቆይበት አልነበረም፡፡ እንደዛሬው የረቀቀ ሥልጣኔ ባልነበረበት በዚያ “የኋላ ቀርነት ዘመን” ክረምት በመጣ ቁጥር ከፍተኛ የምግብ እጥረት ስለሚከሰት የተለመደ የክፍለ ግዛቱ መከራ ነበር፡፡”

“ብዙ ዜጎችም ነፍሳቸውን ከክረምቱ ‹መቅሰፍት› ለማትረፍ ይጥሩ የነበረው የዱር ዳክዬዎችን (ተርኪ በመባል የሰየሟቸውንና ያላመዷቸውን ዶሮ መሰል ዝርያዎች) በማደንና የበረዶውን ግግር ተቋቁሞ የሚበቅለውን ድንች ‹ለነፍስ አድንነት› በመመገብ ነበር። ስለዚህም ያንን ክፉ ጥንታዊ ዘመን ለማስታወስና ፈጣሪን ለማመስገን ሲባል በዓሉ እንዲከበር ተወሰነ። በእነዚህ የምሥጋና ቀናት የሚቀርበው ማዕድም ሙሉ አካሉ እንዳለ ተጠብሶ የሚቀርበው የተርኪ ሥጋ የድንችና የበቆሎ ገንፎም ያንን ዘመን ለማስታወስ ታስቦ የሚዘጋጅ ማዕዳችን ነው፡፡” በሀገራችን “አውጥ” የሚባለው ዓይነት የዱር ፍሬም ከማዕዳቸው ጋር አብሮ ሲቀርብ ተመልክቻለሁ፡፡

የምሥጋና ቀናቱ ተከብረው የሚውሉት ከላይ በዝርዝር በቀረቡት ውስን ምክንያቶች ብቻም አይደለም፡፡ በጋራ ማዕዳቸው ዙሪያ የተሰባሰቡት ልጆችና ወላጆችም ይመሠጋገናሉ፡፡ በየመሥሪያ ቤቱም አለቃና ምንዝር ይደናነቃሉ፡፡ ተማሪዎችና መምህራን ይሞጋገሳሉ፡፡ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችም ሕዝባቸውን ያመሠግናሉ፤ ሕዝቡም የፌዴራል፣ የክልልና የአካባቢ መሪዎቻቸው ለፈጸሟቸው መልካም ተግባራት ምስጋና ያቀርባሉ።

ከዚሁ ጎን ለጎንም በዓሉ ሲከበር አንዳንድ ወጣ ያሉ ድርጊቶች በየሀገራቱ መስተዋላቸው አልቀርም፡፡ ድርጊቶቹም የፌሽታቸውን ቀናት ለየት ስለሚያደርጉላቸው በልዩ ትዝታ የሚታወሱ ይሆናሉ። አንዱን ብቻ ለምሳሌ እናስታውስ። በቀደም ኅዳር 11 ቀን 2016 ዓ.ም የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን የ2023 ዓ.ምን የምሥጋና ዕለታት ምክንያት በማድረግ በስጦታ ለእርድ ከቀረቡላቸው ሁለት ባለ ነጭ ላባ ግዙፍ ተርኪዎች መካከል ሁለቱ “እንዳይታረዱ ምሕረት አድርጌላቸዋለሁ” በማለት መግለጫ መስጠታቸው ይታወሳል፡፡

ይህ ዜና በዓለም ብዙኃን መገናኛ የናኘውም እንደሚከተለው ተዘግቦ ነበር፡- “United States presi­dent Joe Biden pardoned two enormous white plumed Turkeys from Minnesota on Monday, granting liberty and Bell freedom from Thanks­giving dinner tables as Americans prepared for their annual feasts.” ይህ ድርጊት ምሳሌነቱ በኅዳሩ የምሥጋና ወር እንኳንስ ለሰብዓውያን ዜጎች ቀርቶ ለእንስሳትም ቢሆን ፍቅርና ርህራሄ ማሳየት ተገቢ እንደሆነ መልዕክት ለማስተላለፍ ታስቦ ይመስላል፡፡

የአንጋፋው ቤተ ኅትመት ተጠቃሽ አርዓያነት፤

በሀገራችን የኅትመት ታሪክ 102 ዓመታትን በማስቆጠር በዕድሜ የተባረከው የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት በዚሁ በያዝነው ወር ኅዳር 8 ቀን 2016 ዓ.ም በምርት ዕቅድ አፈጻጸሙ ከፍተኛ ስኬት ያስመዘገበበትን የ2015 ዓ.ም የበጀት ዓመት ውጤት ምክንያት በማድረግ በቅጥር ግቢው ውስጥ የሠራተኞችን ዓመታዊ በዓል አክብሮ ነበር፡፡

በዕለቱ የማተሚያ ድርጅቱ ሠራተኞች ላስመዘገቡት ስኬታማ ውጤት የሥራ አመራር ቦርዱና የማኔጅመንት አባላት ምሥጋና አቅርበዋል። ሠራተኞቹም በበኩላቸው ለተገኘው ውጤት የማስተባበሩንና የአመራሩን ድርሻ በከፍተኛ ትጋት ለተወጡት የማኔጅመንት አካላትና የቦርድ አባላት ዋንጫዎችንና ልዩ ልዩ ሽልማቶችን በማበርከት ምሥጋናቸውን በምልአት ገልጸዋል፡፡

መመሠጋገኑ ከተጠናቀቀ በኋላም የተቋሙ ሠራተኞች በራሳቸው ተነሳሽነት በ2016 ዓ.ም የበጀት ዓመት ሌትና ቀን በመሥራት የላቀ ውጤትና ስኬት ለማስመዝገብ በጋራ ቃል ኪዳን ገብተዋል፡፡ ይህን መሰሉ አርዓያነት በሌሎች ተቋማት ዘንድም እንደ ባሕል ተወስዶ ቢለመድ የነገይቱ ኢትዮጵያ መልክ እንደምን ሊፈካ እንደሚችል ለመገመት አይከብድም፡፡

በዚህ አጋጣሚ ይህ ዓምደኛ የኮሌጅ ትምህርቱን ባጠናቀቀበት ማግሥት የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ባልደረባ በመሆን የሥራና የኃላፊነትን “ሀ ሁ!” መማር ብቻ ሳይሆን የተቋሙን መላ ሠራተኞች ፍቅር ያተረፈበት፤ ዛሬም በሥራ አመራር ቦርድ አባልነት ለማገልገል ዕድል ያገኘበት ተቋም ስለሆነ ለዚህ አንጋፋ ድርጅት ሠራተኞች፣ የማኔጅመንትና የቦርድ አባላት ከፍ ያለ ምሥጋና እያቀረበ ለተጎናጸፉት ስኬትም ደስታውን በአክብሮት ይገልጻል፡፡ የመመሠጋገን ትሩፋት ለተሻለ ውጤት የሞራል ስንቅ ስለሚሆን በስፋት ሊለመድ ይገባዋል የሚባለውም ስለዚሁ ነው፡፡ ባሕር ማዶኞች “Thank you is the best prayer that anyone could say” የሚሉትም ውጤቱ ስለገባቸው ይመስላል።

ሌላው የሚበረታታ አርዓያነት፤

የአዲስ አበባ ከተማ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት በዚሁ በያዝነው ሣምንት ውስጥ “የሠላምና የምሥጋና ኮንፍረንስ” ኅዳር 25 ቀን 2016 ዓ.ም ለማካሄድ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን በኃላፊዎቹ በኩል ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰጥቷል፡፡

የምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት ሼህ ሡልጣን ሐጂ አማን ኤባ ፕሮግራሙን አስመልክተው ሲገልጹ እንዲህ ብለዋል ፤ “የኢትዮጵያ ሙስሊሞች የዘመናት የተቋም ጥያቄያቸው መልስ ማግኘቱንና ኢስላማዊ እሴቶችን ያከበሩ የፋይናንስ ተቋማት መስፋፋታቸውን ምክንያት በማድረግ ታላላቅ እንግዶች በሚገኙበት መርሐ ግብር ለማመሥገን መወሰናቸውን” አስታውቀዋል። በተከታታይ ቀናትም በበርካታ የሀገሪቱ አካባቢዎች ይሄው የምሥጋና ኮንፍረንስ እንደሚካሄድም አረጋግጠዋል።

እንደ ሀገር ከተቆራኙን ብሔራዊ በሽታዎቻችን መካከል በቀዳሚነት የሚጠቀሰው አንዱ ችግራችን ለማመሥገንና ለመመሠጋገን ንፉግ መሆናችን እንደ ባሕል የተጣበቀ ደዌ ሆኖብን ይሆንን ብለን ብንጠይቅ ክፋት የለውም፡፡ በሀገር አቀፍም ይሁን በከተሞች ደረጃ መልካም ስኬቶች ሲመዘገቡ ቀድሞ ለማመሥገን ከመቸኮል ይልቅ አቃቂር ለማውጣት መሽቀዳደም እንደ ወግና ልማድ ተጣብቶን ያለ ክፉ በሽታ ሆኖብንስ እንደሆን?

መልካም ውጤት ያስመዘገበን ሠራተኛ አመስግኖ፣ ሸልሞና አድንቆ ማበረታታት ተዘውትሮ በተግባር ሲተረጎም አይስተዋልም፡፡ እርግጥ ነው በከተሞችና በክልል መስተዳድሮች አማካይነት በአሥራ ሁለተኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች የሚሰጠው ምሥጋናና ሽልማት በወደፊቶቹ ሀገር ተረካቢ ወጣቶች ሕይወት ውስጥ በጎ ተፅዕኖ እንደሚያመጣ ፍሬው የሚታየው ውሎ አድሮ ነው። ይህ ማበረታቻ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ፈጻሚዎቹን በማመስገን አደራ ማለቱ አግባብ ይሆናል፡፡

በግል፣ በቡድንም ሆነ እንደ ሀገር በስኬቶቻችንና ውጤታማ በሆንባቸው ጉዳዮቻችን በሙሉ ማመሥገንና መመሠጋገን ባሕላችን ሆኖ ሥር እንዲሰድ ተግተን ልናስተምርና በተግባር ልናሳይ ይገባል፡፡ ባለ ውለታዎቻችንን ማመሥገንና መዘከር፣ ላበረከቱትና ትተውት ላለፉት መልካም ሌጋሲም ከዘመን ዘመን እየተመሠገኑ እንዲኖሩ በየአደባባዮቻችን መታሰቢያ ማቆም ትርፉና ትሩፋቱ ከፍ ያለ ስለሚሆን በአግባቡ ልንመካከርበት ይገባል፡፡

ተቋማትም በአቅማቸው ልክ ውጤታማ ሠራተኞቻቸውንና ኃላፊዎችን በማመሥገን መደናነ ቅና መከባበር መልሶ ያስከብራል እንጂ ጉዳት የለውም፡፡ ነገሮች እንደተጠበቀው ባይሆኑስ ፈጣሪ በሕይወታችን ውስጥ የተበላሸውን ጅምራችንን ለማቃናት ድርሻ አይኖረውምን? በሚገባ ይኖረዋል እንጂ፡፡ ስለዚህም ስለ ስኬታችንና ስላስመዘገብነው ውጤት ግዙፍነት ብቻ ሳይሆን በጉድለታችንም ቢሆን ፈጣሪን ስለ ብዙ ጉዳዮች ልናመሠግነው ይገባል፡፡

አንድ የሀገራችን ጎምቱ ዘማሪ ባዜመው የመንፈሳዊ መዝሙር ግጥም ውስጥ እንደተቀኘው ነገሮች እንኳን እንደተጠበቀው ባይሳኩ ፈጣሪን ከልብ በማመሥገን ድል ማግኘት ይቻላል፡፡ በምሥጋና የሚናፈቀው ስኬት ሊገኝ ይችላል፡፡ ከላይ የጠቀስናቸው ሀገራት ታሪክ የሚያስታውሰን ይህንን እውነታ ነው፡፡

«በምሥጋና ሆ! በምሥጋና

ድል ይገኛልና፡፡

ሸለቆ አሽቆልቁለው ሲያለቅሱ፣

ሰዎች ለምሥጋና ቢነሱ፤

በኃዘኑ ፈንታ ደስታ፣

በልቅሶውም ምትክ ዕልልታ፡፡

ሰማያት እንደ ናስ ሲዘጉ፣

በምሥጋና ሕይወት ቢጠጉ፣

ያንዣበበው ጥላ ሲገፈፍ፣

አመስግኖ በአምላክ መደገፍ፡፡

በዓሉ የሀገራችን ባሕል ባይሆንም በውጭ ሀገራት ለተበተኑት ትውልደ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን በሙሉ መልካም የምሥጋና ቀናት (Happy Thanks­giving!) በማለት ምኞታችንን እንገልጻለን፡፡

ሰላም ለሕዝባችን፤ ለዜጎችም በጎ ፈቃድ።

 (በጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)

gechoseni@gmail.com

አዲስ ዘመን ህዳር 15/2016

Recommended For You