ተራ ከሚጠብቁ ሦስት ሰዎች ውስጥ ሁለቱ ተቀምጠው አንደኛው ግን ቆሟል። ከፍጥነቷ በተጨማሪ ለሥራዋ ጥራት ከሚገባው በላይ እንደምትጠነቀቅ ለመረዳት አጠገቧ ያሉ የሥራ መገልገያ መሳሪያዎች ምስክር ናቸው።
በርካታ ብሩሾች፣ ሁለት ባለ አምስት ሊትር ጀሪካኖች ንጹህ ውሃ ተሞልተውና ሌሎች መገልገያ ቁሳቁስ ከአጠገቧ ይገኛሉ። የምትሠራበት ሥፍራም ንፁህ ነው። ትኩረቷ በሙሉ ሥራዋ ላይ ነው፤ የደንበኞቿ ቆሞ መጠበቅ ያስጨነቃት ይመስላል። በየመሃሉ ብታወራም ፈጣን እጆቿ ከመደበኛ ሥራቸው አልተላቀቁም።
የመጀመሪያ ደንበኛዋን ጫማ አፅድታ ሌላ ደንበኛ እንዲተካ በሚጋብዝ መልኩ በብሩሹ የሊስትሮ ዕቃዋን ደጋግማ «ቂው! ቂው!» አደረገችው። አገልግሎቷን አግኝቶ ቦታ የለቀቀው ሰው 100 ብር ሲሰጣት 90 ብር መለሰችለት። እርሱም በድጋሜ ጉርሻ 10 ብር ሰጥቶ 80 ብር ወደ ኪሱ አስገብቶ አመስግኖ ሄደ። ቀጣዩ ደንበኛ ተተካ።
በሌላ በኩል ግን እርሷ ከምትሠራበት ከአስፋልት ትይዩ በርከት ያሉ ‹‹ሊስትሮዎች›› ይታያሉ። እነሱ ወንበራቸው ላይ ቁጭ ብለው ደንበኛ ይጠባበቃሉ። ብርቱካን ዘንድ ደግሞ ደንበኞቿ ቆመው ተራቸውን ይጠባበቃሉ። እኛም የዚህን ምክንያት ለማወቅ ጠጋ አልን።
ብርቱካን ባልቻ ትባላለች። የ21 ዓመት ወጣት ስትሆን እትብቷ የተቀበረው የንጉሥ ካዎ ጦና የትውልድ ሥፍራ ወላይታ ነው። ከወላይታም ኦፋ ወረዳ ደግሞ ከእኩዮቿ ጋር ድብብቆሽ ተጫውታ ያደገችበት፣ በተወሰነም ደረጃም ቢሆን ክፉና በጎውን ያየችበት ‹‹ሀ! ሁ! …›› ብላ ከፊደል የተዋወቅችበት፣ አብዛኛው የልጅነት ዕድሜዋን ያሳለፈችበት መንደር ነው።
10ኛ ክፍል ድረስ ቤተሰቧ እያገዟት በተወለደችበት አካባቢ ተምራለች። ከሥድስት ዓመት በፊት ነበር ማትሪክ ተፈትና ውጤቷ ወደ 11ኛ ክፍል እንደማያስገባት ስታውቅ ሥራ ፍለጋ ወደ አዲስ አበባ ከአጎቷ ልጅ ጋር የመጣችው። ከዚያን በኋላ በቄራ እና በሌሎች አካባቢዎች ለሦስት ዓመታት በመስተንግዶ ሙያ ተቀጥራ ሠርታለች። ይሁንና በዚህ ሥራ ጠብ የሚል ገቢ አላገኘችም።
ስለዚህ የሥራ ዘርፏን ቀይራ የሊስትሮ ሥራ ጀመረች። ቀደም ሲል ስለዚህ ሙያ ምንም ዕውቀት አልነበራትም። ግን እርሷ በአሁኑ ወቅት የምሠራበት ከአምባሳደር ሲናማ ወደ አራት ኪሎ ታክሲ መሳፈሪያ ቦታ ላይ የአጎቷ ልጅ ሊስትሮ ይሠራ ነበር። እርሱ ሙያውን አለማመዳት። ጫማ ሲያስጠርጉ አንዳንድ ወጣ ያለ ባህሪ ያላቸውን ሰዎች እንዴት ማስተናገድ እንዳለባት ከልምዱ አካፈላት። ብርቱካን በሂደት ሥራውን ተላምዳ፤ ደንበኞችን ማፍራት ጀመረች።
በእርግጥ ሁኔታዎችን እስክትላመድ ድረስ ፈተናዎችን መጋፈጡ አልቀረላትም። አንዳንድ ሰዎች ‹‹ውሃ ቀጠነ›› የሚል ሰበብ እየፈለጉ ገላምጠዋታል። በንትርክ ብዛት ያፀዳችውን ጫማ ‹‹አላማረኝም እንደገና ይፅዳ›› ብለው በድጋሜ ጫማቸውን አፅድታለች። አልፎ አልፎ ደግሞ የማንጓጠጥና ክብረ ነክ ስድቦች አጋጥሟታል።
እንደ ሰዎች ዕድሜና ፆታ ስብጥር፣ እንደየጫማቸው ቀለም መለያየት የተለያዩ ባህሪያትን ለመጋፈጥ ተገድዳለች – ብርቱካን። ሌሎች ደግሞ ሴት ሆና ሊስትሮ በመሥራቷ እያደነቋት ያበረታቷታል፣ ያዝኑላታል፣ ይጨነቁላታል። ጥቂቶች ደግሞ በሳንቲም ደረጃ የሚከፈል ሥራ ሠርታ 10 ብርና ከዚያ በላይ ጉርሻ እየሰጧት አስደምመዋታል። አሁንም ቢሆን አልፎ አልፎ ያልጠበቀችው እንግዳ ነገር ያጋጥማታል። ግን ከአጎቷ ልጅ የሰማችው ምክር፣ ለሦስት ዓመታት በመስተንግዶ ሥራ የቀሰመችው ዕውቀትና የነገ ሕይወቷ
የፈካ እንዲሆን አብዝታ ከመሻቷ የተነሳ ብዙ ነገሮችን በትዕግስት እያለፈች ዛሬም ከኑሮ ጋር ግብግብ ገጥማለች።
ብርቱካን በአሁኑ ወቅት በምትሠራው ሥራ ከቀድሞ የተሻለ ገቢ አገኛለሁ ትላለች። በመስተንግዶ ሥራ በወር 800 ብር ይከፈላት ነበር። የሊስትሮ ሥራ ከጀመረች ወዲህ ግን በወር ከ3,000.00 እስከ 4,000.00 ብር ታገኛለች። በሰው ቤት ተቀጥራ ስትሠራ ከደመወዟ ማነስ በተጨማሪ የአሠሪዎቿ ግልምጫ ሰብዕናን የሚፃረሩ ድርጊቶች ብሎም በቂ ምግብ ማግኘቱ የቅንጦት ይሆንባት ነበር።
ያለፉ ነገሮችን ስታስታውስ አንዳንድ ኢትዮጵውያን የመተሳሳብ ባህልን ዘንግተው፣ ሰብዓዊነትን አሸንቀጥረው ጥለው ገንዘብን ከሰው ሲያስበልጡ በማየቷ ልቧ ክፉኛ ያዝናል። ግን እርሷ አገር ቤት የተላመደችው አብሮ የመብላት መተሳሰብና መረዳዳት ብሎም የጎለበተ አብሮነትን ልትረሳው አልፈለገችም። ወዲህ ከሰፈሯ ወደ አዲስ አበባ እንድትሄድ ከሰማይ መና የሚወርድ አስመስለው የነገሯትን ሰዎች በዓይነ ህሊና ትቃኛለች። ሁሉም ውሸት፤ ሁሉም ተረት መሆኑን ተረዳች።
ግን ተስፋ አልቆረጠችም፤ ወደ ትውልድ ቀዬዋም መመለስ አልፈለገችም። ይልቁኑ ሰከን ብላ ማሰብ ጀመረች። በአሁኑ ወቅት የምትሠራበት ቦታ በዓመት ለአንድ ግለሰብ 3,000.00 ብር ትከፍላለች። በተጨማሪም እንደምንም ተፍጨርጭራ ከዕለት ጉርሷም ቀንሳ 100.00 ብር ዕለታዊ እቁብ ትጥላለች።
ብርቱካን በታታሪነቷ፣ በአርቆ አስተዋይነቷ፣ በጠንካራነቷና ብሎም ለወንዶች ብቻ የተፈቀደ የሚመስለውን ሥራ ደፍራ በመሥራቷ ብዙ ደንበኞችን አፍርታለች። ለዚህ አብነት ፍለጋ ብዙ ማማተር አላስፈለገኝም። በዘውዲቱ ሆስፒታል ከአራት ዓመታት ወዲህ በነርስነት ሙያ እያገለገለች የምትገኘው ሃና ገበየሁ ከቋሚ ደንበኞቿ መካከል አንዷ ናት፤ በወቅቱም ጫማዋን ለማስጠረግ ከሥፍራው ነበረች።
‹‹ብርቱካን በጣም ጠንካራና የተሻለ ነገን ለማየት የምትጓጓ፣ በጥረቷ ብዙ ደንበኞችን ያፈራች፣ ሥራዋን የምታከብርና ለብዙ ሴቶችም አርዓያ የምትሆን ናት›› ስትል ትገልፃታለች። ሃና ገበየሁ አዲስ አበባ ውስጥ እስካለች ድረስ ጫማዋን ሌላ ቦታ አታስጠርግም። ቋሚ ደንበኛዋ ብርቱካን ናት። ሌሎች ሰዎችም ጫማቸውን ብርቱካን ዘንድ እንዲያስጠርጉ ተናግራ ደንበኞች እንድታፈራ አድርጋለች።
ሃና የቅርብ ቤተሰቦቿንና ጓደኞቿን ከብርቱካን ጋር አስተዋውቃለች። ከጤና ጋር የተያያዙ ሙያዊ ምክሮችንም ትለግሳታለች። ሥራ ላይ በምትሆንበት ወቅት አመቺ የሆነ አለባበስ እንድታዘወትርም ትመክራታለች። ብርቱካንም ነርሷ ብዙ ነገር እንደመከረቻትና ብዙ ደንበኞችን እንዳመጣችላት ትናገራለች።
ብርቱካን ከትውልድ መንደሯ ወደ አዲስ አበባ ያቀናችው የሥራ ዕድሎች እንደ አሸን መሆኑ ተነግሯት ነበር። በተለይ ደግሞ ሴቶች በአዲስ አበባ ኑሮ እንደሚደላደልዳቸውና በአጭር ጊዜ ሀብት ማጉረፍ እንደሚችሉ እንዲሁም ለበርካቶችም አርዕያ እንደምትሆን ነበር በቃላት ጋጋታ ያስረዷት።
ሌሎች ሰዎች ደግሞ ዓረብ አገር ብትሄድ በአጭር ጊዜ ጠብሰቅ ያለ ገንዘብ እንደምታገኝና በአንድ ጀንበር ‹‹ቱጃር›› እንደምትሆን ምስል ከሳች በሆነ ስብከት ደጋግመው ለማሳመን ሞክረዋል። የሆነው ሆኖ እርሷ ያለፈውን ጊዜና ክስተት ሳይሆን ነገ በሚሆነው ላይ ታተኩራለች። ከሰው አገር ዶላር፤ የአገሬ አንድ ብር ጥፍጥናዋ ይበልጥብኛል ስትል ከኢትዮጵያ ልትሸሽ አልፈለገችም።
ብርቱካን ባለፉት ስድስት ዓመታት በአዲስ አበባ ብዙ ውጣ ውረዶችን አይታለች። ከኑሮ ጋር ተፋጣ ከእጅ ወደ አፍ በሆነው የአብዛኛው የኢትዮጵያን አኗኗር ጉዞ ውስጥ ተጉዛለች፤ እየተጓዘችም ነው። እጅግ የተጋነነ ባይሆንም ለውጦችን እያስመዘገበች ነው። ቤተክርስቲያን በአጋጣሚ ከተዋወቀችው የባንክ ባለሙያ ጋር ከስምንት ወራት በፊት ወደ ሦስት ጉልቻ ተሸጋግረዋል።
ቦሌ አካባቢ 1ሺ800 ብር ቤት ተከራይተው እየኖሩ ነው። ቤተሰቦቿ አርሶ አደር ሲሆኑ፤ እጅ አጠር ናቸው። በተቻላት አቅም እነርሱንም ለመርዳት ትሞክራለች። ብዙ ጊዜ ለፋሲካ አሊያም ለመስቀል በዓል ስትሄድ ልብስና የሚያስፈልጋቸውን ነገሮች ሸማምታ ትሄዳለች።
ብርቱካን ከዕለት ወደ ዕለት አኗኗሯ፣ አስተሳሰቧና የእይታ አድማሷ እየሰፋ ነው። ቅርበትና ርቀት የማይወስኗቸው የኑሮ ፈተናዎች አሁንም አብረዋት ይጓዛሉ። አንድ ቀን በአሁኑ ወቅት ካለችበት ኑሮ ወደ ተሻለ ደረጃ መሸጋገር እንደምትችልም በልበ ምሉነት ትናገራለች።
ላለፉት ስድስት ዓመታት በሰው ቤት ተቀጥራም ሆነ የራሴ ምትለውን ሥራ ጀምራ ገቢና ወጪውን አስልታለች። ተቀጣሪ ሆኖ በሰው ከመታዘዝ ራስን በራስ ወደ ማዘዝ ተሸጋግራለች። አሁን ላይ ብዙ ነገሮችን ታስባለች። ሊስትሮ ሆና መቀጠሉን አትፈልግም። ብዙ ፍላጎቶቿን ገታ አድርጋ የቁጠባ ደብተር አውጥታ 70ሺ ብር አጠራቅማለች። በቀጣይ ግን አቅሟን አጠናክራ ከሊስትሮ ሌላ ሥራ ለመጀመር እያሰበች ነው። በተለይም ደግሞ ሱቅ ከፍታ ሸቀጣ ሸቀጥ እየነገደች፤ ቤተሰቧንም እየረዳች ወደ ሌላ ምዕራፍ መሸጋገር ትፈልጋለች።
በዚህ ጥረቷ ላይ ግን መንግሥት ትንሽ እገዛ ቢያደርግላት ምኞቷ ነው። አዲስ አበባ ውስጥ ሰማይ ከነካው የቤት ኪራይ ጋር የሱቅ አሊያም ሌላ መስሪያ ቦታ ለመከራየት መሞከር የማይታሰብ ነው ትላለች። ስለዚህ መንግሥት ወጣቶችን እንደሚያደራጀው ሁሉ እርሷም የዕድሉ ተጠቃሚ መሆን ትሻለች።
የተለያዩ ሙያ ባለቤቶች ደግሞ የቢዝነስ ሃሳብ ቢያካፍሏት፣ ቀረብ ብለው ቢመክሯት፣ ከልቧ ለመስማት፣ በሥራም ለመለወጥና በተግባርም ለማሳየት ዝግጁነቷና በራስ መተማመኗ ከፍ ያለ ነው። በእርግጥ እንዲህ እየተኖረ፤ እንዲህም እየተለፋ የኑሮ ኮሮጆ አይሞላምና ብርቱካን ወደ ላቀ ብርታት እንድትሸጋገርና ለሌሎች ሚሊዮን እንስቶች አርዓያ ትሆን ዘንድ ድጋፍ ያስፈልጋታል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 17/2011
ክፍለዮሐንስ አንበርብር