ኢትዮጵያ ለጀመረችው የዕድገትና ብልጽግና ጉዞ ይጠቅሙኛል ብላ ከመረጠቻቸውና ቅድሚያ ከሰጠቻቸው ዘርፎች ውስጥ ቴክኖሎጂ ቀዳሚው ነው፡፡ በተለይም እንደ ሀገር በወጣው የ10 ዓመት ፍኖተ ካርታ ሁሉንም የዕድገት ዘርፎች በማስተሳሰርና ወደ ብልጽግና በማቅናት ረገድ ቴክኖሎጂ የማይተካ ሚና እንደሚጫወት ታምኖበታል፡፡
ቴክኖሎጂ መጪውን ጊዜ የሚቆጣጠር መሳሪያ ነው፡፡ ከቴክኖሎጂ የተራራቀ ሕዝብና ሀገር በእድገትና ብልጽግና ወደ ኋላ መቅረቱ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ ከዚህም ባለፈ ቴክኖሎጂ የሚሰጣቸውን ትሩፋቶች ተጠቅሞ የሕዝብን ኑሮና የሀገርን ዕድገት ማረጋገጥ ካለመቻሉም በላይ ከሌላው ዓለም ጋር የመወዳደር አቅም ያጥረዋል፡፡ እንደ ሀገር የሚቃጣውንም የሉአላዊነት አደጋ ለመጋፈጥ ይሳነዋል፡፡
በተለይ በዚህ የቴክኖሎጂ ዘመን ወሳኝ ከሆኑና በበጎም ሆነ በክፉ ከሀገር ጥቅም ጋር ከሚያያዙ ጉዳዮችና የቴክኖሎጂ ዘርፎች አንዱ ሰው ሰራሽ አስተውሎት (አርቴፊሻል ኢንተሌጀንስ) ነው፡፡ ብዙዎች እንደሚስማሙበት የወደፊቱ የሰው ልጅ ስልጣኔ በቀጥታ ከሰው ሰራሽ አስተውሎት (አርቴፊሻል ኢንተሌጀንስ) በቀጥታ የተያያዘ ነው።
ይህንን እውነታ በመረዳት መንግስት ዘርፉን የሚመራ ተቋም ከማቋቋም ጀምሮ በዘርፉ ብቁ ባለሙያዎችን ለማፍራት የሚያደርገው ጥረት የሚመሰገን ነው፡፡ እንደ ሀገርም ለዘርፉ የተሰጠው ትኩረትና በተለይም ካለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ በዘርፉ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት መጪው ጊዜ ብሩህ እንደሚሆን አመላካች ነው፡፡ በተለይም ኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተሌጀንስን ከራሷ ነባራዊ ሁኔታ ጋር አጣጥማ ለመጠቀም መሞከሯ በዘርፉ የሚስተዋሉ አሉታዊ ጎኖች ለመቀነስ ያስችላታል፡፡
አርተፊሻል ኢንተለጀንስ ኮምፒዩተሮችና ማሽኖች እንደ ሰው ልጅ እንዲያመዛዝኑ፤ ነገሮችን እንዲገነዘቡ፤ ማንኛውንም ነገር እንዲማሩ፤ እንዲያቅዱና ፈጠራዎችን እንዲከውኑ በማድረግ የሚሰጣቸውን ተልዕኮ እንዲያሳኩ የሚያስችል ቴክኖሎጂ ነው፡፡ ስለዚህም እንደ ሀገር ከሰለጠን የሰው ኃይል ብቃት ጋር የሚነሱ ክፍተቶችን ለመሙላት ከማስቻሉም በላይ ዘመኑ ያፈራቸውን ዕውቀቶች ለመጠቀምም በር የሚከፍት ነው፡፡
በተለይም በእርሻ፣ በጤና፣ በትምህርት፣ በመልካም አስተዳደርና በአጠቃላይ ወሳኝ በሆኑት ነገሮቻችን ላይ ሰው ሰራሽ አስተውሎትን እንደ አንድ መሳሪያ በመጠቀም ያልተሸጋገርናቸውን ችግሮች ለመሻገርና ወደ ዕድገትና ብልጽግና ለማምራት ያስችላል፡፡
አርተፊሻል ኢንተለጀንስ በተለያዩ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የሚታየውን እንግልትና ውጣ ውረድ በማቃለል ረገድ ወሳኝ ሚና ያለው ሲሆን አገልግሎት አሰጣጥን ብቁና ተደራሽ በማድረግ የሚስተዋለውን ተደራራቢ ጫና ለመቀነስ የሚያስችል ነው፡፡ በወረዳዎች፤ በክፍለ ከተሞችና አገልግሎት ፈላጊ በሚበዛባቸው ዘርፎች አካባቢ ያለውን እንግልት ለመቀነስና የሚስተዋለውን የመልካም አስተዳደር ችግር ለመቅረፍም ያስችላል፡፡
ከግብር ጋር ያሉ ማጭበርበሮችና ስወራን ለማስወገድ፤ ከትራንስፖርት መጉላላትና ከመንገድ መዘጋጋት ጋር የተያያዙ ችግሮችን ለመቅረፍና ብሎም የብዙ ሰዎችን ሕይወት እየቀጠፈ የሚገኘውን የትራፊክ አደጋ ለመቀነስ አርተፊሻል ኢንተሌጀንስ የማይተካ ሚና አለው፡፡
በከተሞች አካባቢ አሳሳቢ እየሆነ የመጣውን የቆሻሻ አወጋገድ ስርዓት ለማስያዝ፤ የኃይል አቅርቦትና ስርጭትን ለመምራት፤ የንጹህ መጠጥ ውሃን በፍትሃዊነት ለማዳረስና ብሎም በሀገር ሕልውና ላይ የሚቃጣ ጥቃትን ለመከላከል አርተፊሻል ኢንተለጀንስ የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ ነው፡፡
በአሁኑ ወቅት አርተፊሻል ኢንተለጀንስን በመጠቀም ዲጂታል የገንዘብ አሰባሰብ ስርዓት መከተል፤ ግብርን የማሳወቅና የመክፈል፤ የፍርድ ስርዓቱን በዲጂታል የታገዘ ማድረግ፤ የመታወቂያ አሰጣጡን ወደ ዲጂታል የመቀየርና እና ለብክነትና ብልሹ አሰራሮች ተጋልጦ የቆየውን የነዳጅ አቀዳድና ክፍያ በዲጂታል ስርዓቱ ውስጥ ብቻ እንዲያልፍ ተደርጓል፡፡
በርካታ ሙስናና ብልሹ አሰራር ይስተዋልበት የነበረው የግዢ ስርዓትም ዲጂታላይዝ መደረጉ የዚሁ ቴክኖሎጂ ትሩፋት ነው፡፡ ከእነዚህ ውጤቶች ባሻገርም ማንኛውን ግብይት እና ከፍያ በዲጂታል ስርዓት ውስጥ እንዲያልፍ የማድረጉ ተግባር ተስፋ የሚሰጥ ነው፡፡
በአጠቃላይ ኢትዮጵያን ዘመኑ በደረሰበት ቴክኖሎጂና ሰው ሰራሽ አስተውህሎት በማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መስኮች ተጠቃሚ ለመሆን እየሠራችው ያለው ሥራ የሚበረታታና በቀጣይም በዘርፉ የአፍሪካ ኩራት የመሆን አቅም እንዳላት አመላካች ስለሆነ የተጀመሩት ተስፋ ሰጪ ጥረቶች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል!
አዲስ ዘመን ህዳር 14/2016