ራስን ከዘመን ጋር ማስታረቅ

ሶስቱ ጓደኛሞች ከሌላ ጊዜ ለየት ያለ ቦታ መሔድ ፈልገዋል። ቀድመው በመነጋገራቸው ጋባዡ ተሰማ መንግስቴ የሚያውቀው መዝናኛ ቤት ሊጋብዛቸው ሁለቱም ጋር ደወለ። ዘውዴ መታፈሪያ እና ገብረየስ ገብረማርያም አዲስ ቤት በመግባት ጓደኝነታቸውን ለማደስ በመጓጓታቸው የተሰማን የሥልክ ጥሪ ተከትለው ወዲያው ተገኙ። ገና ሳይመሽ በጊዜ ከማምሻ ግሮሰሪ ውጪ፤ አለ የተባለ በዘመኑ አለኝ የሚል ሰው የሚጠጣውን መጠጥ ለመጠጣት እና በሰፊው ለመዝናናት በተቀናጣው መጠጥ ቤት ተገናኙ።

መቀመጫው እንደማምሻ ግሮሰሪ ደረቅ ወንበር ሳይሆን የተቀናጣ ሶፋ ነው። ገና በጊዜ በመግባታቸው ብዙ ሰዎች እና ሰፊ መስተንግዶ አላገኙም። እየቆየ ቤቱ መሙላት ሲጀምር ግን መስተንግዶ ተቀላጠፈ። የሙዚቃ ባንድ ቆሞ ዘፋኞች በየተራ እየወጡ መዝፈን ጀመሩ። አስተናጋጆች ሳይጠሩ፤ ‹‹ ምን እናምጣ? ምን ይጨመር?›› እያሉ ተክተለተሉ። አሻሻጭ ሴቶች ተኮለኮሉ። ለጠጪዎች ‹‹ ይህ መጠጥ እኮ ምርጥ ነው። ይህኛው ከዚህኛው ይሻላል። ያንን አምጡላቸው ይህንን ቀይሩላቸው።›› እያሉ በየጠረጴዛው የሚዞሩት አጫፋሪዎች፤ ምንም እንኳ ተኳኩለው መልካቸው ቢያምርም፤ ዘውዴ ግን ትኩረት ነፈጋቸው ።

ዘፋኞቹ ደጋግመው ተቀራራቢ ዘፈን ይዘፍናሉ። መጠጡም ሆነ ዘፈኑ አጠቃላይ የቤቱ ሁኔታ ዘውዴ እና ገብረየስን ብዙም አላዝናናቸውም። ተሰማ ግን እጅግ ደስ ብሎት አልፎ አልፎም ሲጨፍር ነበር። ብዙም ሳይቆይ ዘውዴ መውጣት ፈለገ፤ ነገር ግን ጓደኞቹ አልፈቀዱለትም። ተሰማ የዘውዴ አለመደሰት አልገባውም፤ እንደ እርሱ የተደሰተ መስሎት ነበር። የሚወደው ዘፈን ሲዘፈን ተሰማ ተነስቶ መጨፈር ቀጠለ። ገብረየስ ለዘውዴ፤ ‹‹እኛ ባንደሰት እንኳ እርሱ ሲደሰት ለማየት መፍቀድ አለብን። ያለበለዚያ ጓደኝነት ምንድን ነው?›› ብሎ ለጓደኛቸው ሲሉ እንዲቆዩ ገብረየስ ዘውዴን ጠየቀው።

ዘውዴ የተለመደ ግትርነቱን ማንፀባረቅ ጀመረ። ‹‹ ምንም ነገር የሚያስደስተው በጋራ ሁሉንም ሲያዝናና ነው። ለጋራ የማይሆን ነገር ያስጠላል። ከመታደስ ይልቅ የባሰ ያስረጃል፤ ከማስማማትና ከማቀራረብ ይልቅ ያቃቅራል፤ ያራርቃል።›› ሲል ገብረየስ ግን መለስ ብሎ፤ ‹‹ ዛሬ ፖለቲካ አይደለም። ዛሬ ፍሬ ነገሩ መዝናናት ነው። የጋራ ጥቅም፤ የጋራ ዕድገት የምትለውን ነገር ለዛሬ ተወት አድርገው። ተሰማ በቀናነት ሊያዝናናን ሞከረ፤ ነገር ግን ሁኔታው እኛን የሚያዝናና አልሆነም። በዚህ ጊዜ እርሱ ሲዝናና እያዩ መደሰት ይሻላል።

እኛም ከማምሻ ግሮሰሪ ትንሽ ራሳችንን ነጠል አድርገን እንየው። በተሰማ ስምም ቢሆን፤ ሌላውን ዓለም እንቃኝ። ሁሉን ነገር ደፍነህ፤ ብርሃን ቢሆን እንኳ የሚታይህ በፖለቲካ አይን ፅልመት ሆኖ ነው። ከብዙ ሰላም ይልቅ፤ ስለትንሿ ጦርነት እያሰላሰልክ ሰውነትህን አደከምክ። አሁን ስለአረጀው ሃሳብ ስለሰው ልጆች መሞት፤ ስለጦርነት ሳይሆን ሰለሰው ልጆች ደስታ ማሰብ ጀምር፤ የዛን ጊዜ መድከምህ ቀርቶ ትታደሳለህ፤ መዛልህ ቀርቶ ትጠነክራለህ።

እባክህ ቢያንስ አንዳንድ ቀን ስለሰላም አስብ፤ የሰዎችን ደስታ ለማየት በእነሱ ደስታ ደስተኛ ለመሆን ሞክር። ዘመንህን ወደ ኋላ ከመጎተት ከዘመን ጋር ለዛውም በሰላማዊ መንገድ ለመሮጥ ጥረት አድርግ። ከጊዜውም ከሰውም ጋር ተጣልተህ አይሆንም። ምናልባት ከሰው ጋር ለመታረቅ ስትሞክር ከዘመኑም ጋር ትታረቃለህ። ከዘመኑ ጋር ስንታረቅ ምናልባት የምናስበው ደስታ እና ሰላም ይሆናል። በዚህ መንገድ ብንታደስ ይሻላል።›› አለው።

ዘውዴ በበኩሉ፤ ‹‹ እኔ ከዘመን ጋር ለመታረቅ፤ ስለሰላም ለማሰብ እና ሰላም እንዲሆን ከመመኘት አልፌ ስለሰላም ለፈጣሪዬ እፀልያለሁ። እኔ አንዱ ብቻውን ከሚበላ እና ከሚኖር፤ ሁሉንም ያሳትፍ። አንዱ እየሞተ ሌላው ከሚገድል ሰላማዊ መንገድን እንምረጥ ሁላችንም እንሥራ፤ ሁላችንም እንብላ እና ሁላችንም በሰላም እንኑር እያልኩ ነው። ያለፈ ጥፋት ቢኖር እንኳ ማፈናቀል እና በቀል የሚያመጣው መልካም ውጤት አይኖርም።

የሚሻለው ተመካክሮ ከዘመኑ ጋር ታርቆ፤ ያለፈውን ለታሪክ ትቶ ወደ ፊት መቀጠል ብቻ ነው። ነገር ግን ይህንን ሃሳብ አንቀበልም የሚሉ ትዕቢተኞችን ሳይ የሚፈፅሙትን ስህተት ሳስብ ያመኛል። ምንም ማድረግ አልችልም። አንተ እንዳልከው ሁሉ ነገር በብርሃን ተቃራኒ በፅልመት ውስጥ ሆኜ እንዳይ ያስገድደኛል።›› ሲል ሙዚቃው በማለቁ ተሰማ ጭፈራውን ጨርሶ ተቀላቀላቸው።

ገብረየስ ‹‹ በእርግጥ ትክክል ብለሃል። ሁላችንም አብረን ሰርተን፣ በልተን መኖር አለብን። ነገር ግን ሰዎች የተለያየን ነን። ለጋራ ጥቅም ከመሥራት እና ከማሰብ ይልቅ ያለፈውን ታሪክ እየጠቀሱ፤ በሃይል ፍላጎታቸውን ለመጫን የሚጥሩ ደካሞች የሉም ማለት አይቻልም። ነገር ግን ፍላጎትን ለማሳካት ወንድም ላይ ቃታ መሳብ በምንም በኩል ከማንም ጋር አያኗኑርም። ፍፁም የሰላም መደፍረስ እና ሞትን ማስቀረት ተገቢ ነው። ስለዚህ ጉዳይ ለምን አሰብክ ጭራሽ ማሰብ አልነበረብህም ማለት አልችልም። ምክንያቱም ሆን ተብሎም ባይሆን ተደጋጋሚ ስህተቶች ይኖራሉ። ነገር ግን ራሳችንን ከስህተት ነጻ ለማድረግ በማያቋርጥ መልኩ ራሳችንን ማረም አለብን።

ራሱን በራሱ የሚያርም ከሰፊው ሕዝብ ጋር የሚጣመር በእርግጥም ከዘመን ጋር ለመታረቅ የፈቀደ ነው። ስህተት ይኖራል፤ ስህተቱን ለማረም ዝግጁነት ካለ አንተም ያለፈው ላይ ተተክለህ ከምታላዝን ቢያንስ አሁን ዛሬ ብቻ ያለውን በጎ ነገር አስተውለህ ከጊዜው ጋር ትታረቃለህ ማለት ነው። አንድን ሰው ከሩቅ ሆነህ መልኩን እና ፀባዩን ሳታውቅ መጥላት ትልቅ ስህተት ነው። ቀርበህ ማየት አለብህ። ቀርበህ ማየት ካቃተህ ደግሞ ቢያንስ በደፈናው ከመጥላት መታቀብ ይገባሃል። ሌላውም አንተም እኔም ሁላችንም ከዘመኑ ጋር ለመታረቅ ራሳችንን በየጊዜው በደንብ ማረም አለብን። ይህ እያንዳንዳችንን የሚመለከት ጉዳይ ነው።›› አለው።

ተሰማ በበኩል፤ ‹‹ እንደው በጣም የምንገርም ሰዎች ነን። ‹ማምሻ ቦታ ቀይረን፤ ራሳችንን እናድስ ከጊዜው ጋር እንራመድ› ብለን ተነጋግረን ዞረን ያው ነን። ቢያንስ ምናልባት ዛሬ እንኳ ፖለቲካ ቢቀርብን። ምናለበት መዝናናት ስናስብ፤ ትኩረታችን መዝናናት ላይ ብቻ ለምን አይሆንም? ከሥራችን እና ከኃላፊነታችን እየወጣን በማያገባን እየገባን ልባችንን እና ምኞታችንን ሙሉ ንግግራችንን ፖለቲካ አድርገነው እየተሰቃየን ፣ ስቃያችን ሲያዝለን ወጣ ብለን ከመታደስ ይልቅ የነበርንበት ላይ እየተንከባለልን ዘመናችንን እናሳልፋለን።ደግሞስ ሁሉም ሰው እኮ እንዴት የፖለቲካ ጠበብት መሆን ይችላል።ፖለቲካውን ለፖለቲከኞች ብንተውላቸው የሚሻል ይመስልኛል ›› አለ።

ዘውዴ በመዝናኛ ቦታም ሆነ ሥራ ላይ ሰዎች ስለፖለቲካ የሚያወሩት ፈልገው ሳይሆን ሁኔታው አስገድዷቸው መሆኑን ለማስረዳት፤ ‹‹ ሰው ስለመዝናናትም ሆነ ስለ ሥራ የሚያስበው ሰላም ሲሆን ነው። ሰው ሰላም አለመሆኑን በየማህበራዊ የትስስር ገፅ እየተመለከትን ስለእዛ ጉዳይ አለማሰብ በእኔ እምነት ይቻላል ብዬ አላስብም።›› ሲል ገብረየስ ቀበል አድርጎ፤ ‹‹ ዋናው ጉዳይ ማሰብ አለማሰብ አይደለም። ሥራህን እና መዝናናትህን ትተህ ስለጦርነት ማሰብ የሚያስገኘው ጥቅም ምንድን ነው? የሚለው ነው። ወይ ስራህን አልሰራህ፤ ወይም ደግሞ መዝናናትህን አልተዝናናህ፤ ወይም ለሚያሳስብህ ጉዳይ መፍትሔ አላስገኘህ? ይሔ ምንም የሚያስገኘው ውጤት የለም።

በእኔ እምነት ተሰማ እንዳለው ከአንዱ ሳንሆን ዘመናችንን ከምናሳልፍ፤ ከአሁን ጋር እንታረቅ። መዝናናት ሲኖርብን መዝናናት፤ መሥራት ሲኖርብን መሥራት ይህ ከሆነ እንደውም ባልታሰበ መልኩ ሠላም እንዲመጣ አስተዋፅኦ እናደርጋለን። ከስራ ውጪ በወሬ ተጨንቀን፣ ወሬ ስናመላልስ ውለን ወንድም በወንድሙ ላይ እንዲነሳ ሁኔታዎችን ከማመቻቸት ይልቅ፤ ወንድም ወንድሙን በመልካም መልኩ እንዲደግፈው እና እንዲቀበለው ማበረታታት ይሻላል።›› ሲል በእርሱ በኩል ያለውን እምነት ገለፀ።

ተሰማ በበኩሉ፤ ‹‹በነገራችን ላይ መንግሥትም ሕዝብን ያምናል። ዕምነትን ማጉደል ትልቅ በድል ነው። መንግሥት እንዲሳካለት ጦርነት ሳይሆን ሰላም፤ ውድቀት ሳይሆን በዚህ ዘመን ዕድገት እንዲኖር የሚፈልግ ማንኛውም የዚህ ዘመን ሰው የመንግሥትን እምነት ማጉደል የለበትም። መንግሥት የሠጠውን እምነት አጉድሎ በሥራ ሰዓት ጦርነት የሚሰብክ ማህበራዊ የትስስር ገፅ እየተመለከተ መልስ እየተሰጣጠ መዋል በምንም መልኩ ከዘመን ጋር አብሮ መዘመን አይደለም።

ቴክኖሎጂውን ለጥሩ ነገር መፈፀሚያ፤ ሰውን ለበጎ ጉዳይ ማነሳሻ ከማድረግ ይልቅ የመጥፎ ቃላት አቅም ማሳይ ማድረግ አይገባም። በቴክኖሎጂው በተለይ በማህበራዊ የትስስር ገፅ ላይ እየፈፀምን ያለው ስህተት ወደ ፊት ብዙ ዋጋ እንዳያስከፍለን እሰጋለሁ። ባለፈው ታሪክ ላይ ተቸንክረን ዛሬን ከማበላሸት አልፈን ነገን እንዳናጣ እሰጋለሁ። ስለዚህ ትናንትን ትተን ከጊዜው ጋር እንታረቅ። ሀገር ውስጥ እየኖሩ ከሩቅ ሆነው እየተሳለቁ ‹አጀማመሩ ጥሩ ነበር።

ነገር ግን መጨረሻው ሲያልቅ አያምር እንደሚባለው ነው› ብሎ ማሾፍ ምንም አያተርፍም። በዚህ ጊዜ ለሚኖር ልማትም ሆነ ጥፋት መንግሥት ብቻ ሳይሆን ተመስጋኝም ሆነ ተወቃሽ በዘመኑ ያለው አጠቃላይ ሕዝቡ ነው። ስለዚህ ገብረየስ እንዳለው ራሳችንን እንመልስ፤ ያለፈው ስህተት ይብቃን፤ ራሳችንን እናድስ፤ አትቃወሙ ማለት ባይቻልም። ተቃውሟችን ምክንያታዊ ይሁን።›› ብሎ ንግግሩን ሲጨርስ፤ ባንዱ ሞቅ ያለ ሙዚቃ ጀመረ። ተሰማ ፈጠን ብሎ ተነስቶ መደነስ ጀመረ።

ከአስር ዓመት በፊት በብዙ መልኩ ስታዝን፣ ስትከፋ እና በብዙ መልኩ ስትቸገር ነበር። ከአስር ዓመት በኋላ ዛሬም ተመሳሳይ ሁኔታ ላይ ነህ። ዛሬ ላይ ከራስህ ጋር መታረቅ ካልቻልክ ነገም ህይወትህ ተመሳሳይ ነው። ስለዚህ ያለፈው አልፏል፤ ቢያንስ ከዛሬ ጋር ታርቀህ ዘመንህን በደስታ አሳልፍ።›› ሲል ገብረየስ ለዘውዴ የጓደኝነት ምክሩን ለገሰው። ንግግራቸውን ከሩቅ ሆኖ ሲገምት የነበረው ተሰማ ዘውዴ ተነስቶ እንዲጨፍር ጋበዘው።

ተሰማ ደስ ሳይለው እየፈራ ከመቀመጫው ተነሳ። ገብረየስ በዘውዴ ሁኔታ መሳቅ ጀመረ። ቀድሞ የነበረው የድብርት መንፈስ ርቆት ሲሔድ ታወቀው። የደስታ ስሜት ሲወረው፤ ‹‹ምን ዘውዴ ብቻ ለካ እኔም ከዛሬ ጋር አልታረቅኩም ነበር። መታረቁ ያዋጣኛል።›› ብሎ እርሱም እየሳቀ እየጨፈሩ ከነበሩት ከተሰማ እና ከዘውዴ ጋር አብሮ መጨፈር ጀመረ። ገብረየስ ተነስቶ ሲጨፍር ዘውዴ ከልቡ ፈገግ ሲል ተሰማም ተደሰተ። ሁለቱንም መሃል ገብቶ ወንድሞቼ ብሎ አቀፋቸው።

የፌኔት እናት

አዲስ ዘመን ህዳር 13/2016

Recommended For You