ኅዳር፣ፖለቲካው፣ኢኮኖሚው…፣ሁሉም ይታጠን !

ወረርሽኙ ኅዳር ወር ላይ ስለገባ ” የኅዳር በሽታ” ተባለ ፡- ወደ ወለጋ ሲዛመት ደግሞ የንፋስ በሽታ ‘ዱኩባ ቂሌንሳ’ ተሰኘ።“… ይህ መቅሰፍት በሀገራችን በ1911 ዓ.ም ወርዶ ብዙ ሰው ጨርሷል። ወረርሽኙ በጉንፋን በሳል ይጀምርና ትኩሳት፣ ማስለቀስ፣ ነስር፣ ተቅማጥና ተውከት ከማስከተሉ ባሻገር አእምሮም ያስት ነበር። ከዚያም በሦስት በአራት ቀን ይገድላል። የቤተሰቡ አባላት በሙሉ አልጋ ላይ ይውሉ ስለነበር አስታማሚ ስለሚጠፋ በርሀብና በውሃ ጥም ብዙ ሰው ይጎዳ ነበር። ከአራት ቀን ያለፈ ሕመምተኛ ግን ይድናል። አፍላው በሽታ ከኅዳር 7 እስከ 20፣ 1911ዓ.ም ነበር።

በየቀኑም ሁለት ሦስት መቶ ከዚህ በላይም ይሞት ነበር። በአንድ መቃብር ሁለት ሦስት ሬሳ እስከ መቅበር ተደረሰ። በዚህ ሰሞን መቃብር የሚቆፍርና ሬሳ ተሸክሞ ወደቀብር የሚወስድ ሰው ማግኘት ችግር ነበር። ባል የሚስቱን፡- አባት የልጁን ሬሳ እየተሸከመ ቀበረ። መቃብር ይቆፍርና ቤቱ ሄዶ ሬሳ ይዞ ሲመለስ ሌላው ቀብሮበት ያገኘዋል።

ቤተሰብ በሙሉ የታመመባቸው በየቤታቸው እየሞቱ አውሬ በላቸው። በበሽታው ልዑል አልጋ ወራሽ ራስ ተፈሪና ልዕልት ወ/ሮ መነን በጠና ታመው ነበር፡- ንግሥት ዘውዲቱም አልጠናባቸውም እንጂ ታመው ነበር። ከመኳንት ከንቲባ ወሰኔ ዘአማኒኤል፡- ከካህናትም ሐዲስ አስተማሪው አለቃ ተገኘ ሞቱ። አለቃ የመምህር ወ/ጊዮርጊስ ደቀ መዝሙር ነበሩ።

በዚያ ወራት በአዲስ አበባ የነበረው ጭንቀት በስፍራው ተገኝቼ ተመልክቼዋለሁ። የኔታ ወልደጊዮርጊስ በሰፈራቸው በጉለሌ ክፍል በየቤቱ እየዞሩ ለበሽተኞችና ለገመምተኞች እንጀራና ውሃ ሲያድሉ ሰነበቱ። በእግዚአብሔር ቸርነት ከበሽታውአምልጠን ነበርና እኔንና ጎጃሜ ኃይለማርያምን ውሃ በገንቦ እያሸከሙ እሳቸው ቁራሽ እንጀራ ይዘው ይሄዱና ከቤቱ ደጃፍ ሲደርሱ እኛን ውጪ አስቀርተው ውሃውንና ቁራሹን ይዘው ይገቡ ነበር።

እኛን ማስቀረታቸው በሽታ እንዳይዘን ስላሰቡልን ነው። በሌላ ስፍራም የዚህን ዓይነት ትሩፋት የሰሩ መንፈሳውያን ሰዎች ነበሩ። ለምሳሌ ሙሴ ሴደርኩይስት የተባሉ ስዊድናዊ ሚስዮናዊ አስተማሪ በየሰፈሩ እየዞሩ ለበሽተኞች እህልና ውሃ መድኃኒት በመስጠት ትሩፋት መስራታቸውን ሰምቻለሁ። እኒህ ሽማግሌ ከጥቂት ቀናት በኋላ በዚሁ በሽታ ታመሙና ሞተው ጉለሌ ተቀብረዋል።

የኅዳር በሽታ (ግሪፕ) በአዲስ አበባ ብቻ አልተወሰነም። ወደ ባላገር ተላልፎ ብዙ ሰው ፈጅቷል። ሆኖም በባላገር የአዲስ አበባን ያህል አልጠነከረም ይባላል። በዚህ በሽታ በመላ ኢትዮጵያ የሞተው የሕዝብ ቁጥር እስከ 40 ሺህ ድረስ መገመቱንም አስታውሳለሁ።በተለይ ኅዳር 12፣ የሚካኤል ዕለት ብዙ ሰው ሞተ። ስለሆነም ወረርሽኙ እስከዛሬ በየዓመቱ የኅዳር ሚካኤል ዕለት በየሰፈሩ ቆሻሻ ሰብስቦ በማቃጠል ‘ኅዳር ሲታጠን ‘ በሚል ይዘከራል። …” በማለት ‘ የሃያኛው ክፍለ ዘመን መባቻ ‘ ደራሲ መርስኤ ኅዘን ወ/ቂርቆስ ይነግሩናል። …”

የ20ኛው ክፍለ ዘመን የመጀመሪያ ሁለት አስርት ዓመታት ለመላው የዓለም ህዝብ የሰቆቃ ዓመታት ነበሩ፡- ምክንያቱ ደግሞ የወቅቱ ሃያላን መንግሥታት በሁለት ጎራ ሆነው ጦርነት ውስጥ ገብተው ስለነበር ነው። እ.ኤ.አ ከ1914 ዓ.ም እስከ 1918 ድረስ የዘለቀውና የ15 ሚሊዮን ሰዎችን ህይወት የቀጠፈው ይህ ጦርነት፣ በታሪክ የመጀመሪያው የዓለም ጦርነት ተብሎ የሚታወቀው ነው።

የጦርነቱ ማብቃት ሊታወጅ ጥቂት ሲቀረውና ዕልቂቱ ቆመ ሲባል ግን የዓለም ህዝብ ሌላ ፍዳ ማስተናገድ ግድ ሆነበት፡- በሰው ሰራሽ ችግሮች (በዋነኝነት በጦርነት) ተወጥሮ የቆየው መላው የአለም ህዝብ አሁን ደግሞ በእንፍሉዌንዛ በሽታ ከዳር እስከ ዳር ተጠቃ ይሉናል ሀብታሙ ግርማ የተባሉ ጸሐፊ በአንድ ድረ ገጽ ለንባብ በበቃ ጹሑፋቸው።

በተለምዶ የስፓኒሽ ፍሉ ተብሎ የሚታወቀው ይህ ወረርሽኝ፣ መነሻው ከወደ አሜሪካ እንደሆነ ይታመናል። እ.ኤ.አ በጥር ወር 1918 ዓ.ም በአንደኛው የአለም ጦርነት ማብቂያ ዋዜማ፣ በጦርነቱ ለመካፈል የአሜሪካ ወታደሮች ወደ አውሮፓ ለመጓዝ ዝግጅት በሚያደርጉበት ወቅት ከተከሰተው ወረርሽኝ ጋር ይያያዛል። በካንሳስ በሚገኘው ፉንስተን የወታደራዊ ማሰልጠኛ ማዕከል የተቀሰቀሰው ወረርሽኙ፣ በሶስት ቀናት ብቻ 45 ሺህ የሚሆኑ ወታደሮችን አጠቃ፡- ወታደሮቹ አትላንቲክን አቋርጠው አውሮፓን እንደረገጡ በሽታውም አውሮፓ ደረሰ።

የእንፍሉዌንዛ በሽታው በአውሮፓ ለመጀመሪያ ጊዜ የታየው በፈረንሳይ ቢሆንም በጦርነቱ ምክንያት ለፕሮፓጋንዳ መጠቀሚያ ይሆናል በሚል ወረርሽኙ ለህዝብ ሳይገለጽ ተደብቆ ቆይቷል። በሽታው ይፋ የሆነው እ.ኤ.አ በህዳር ወር 1918 ዓ.ም በስፔን ለመጀመሪያ ጊዜ በሽታው መታየቱን ተከትሎ ነበር። የበሽታው አማጪ ቫይረስ ባለመታወቁ መድኃኒትም ሆነ ማስታገሻ አልተገኘለትም። (እ.ኤ.አ በ1933 ዓ.ም በእንግሊዛዊያን ሳይንቲስቶች እንደተረጋገጠው የበሽታው አማጪ ቫይረስ በሳይንሳዊው አጠራር H1N1 ተጠራ /በዚህም የተነሳ የበሽታውን ስርጭት ለማቆም አልተቻለም።

በጥቂት ጊዜም ከአሜሪካ እስከ አውሮፓ፣ ከኤሽያ እስከ አፍሪካ፣ከአርክቲክ እስከ ፓስፊክ ደሴቶች ድረስ በከፍተኛ ፍጥነት ተዛመተ። በሽታው እንዲዛመት የአለም የወቅቱ ነባራዊ ሁኔታ ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል። ይህም ወታደሮች ከአንዱ የአለም ክፍል ወደ ሌላው ለዘመቻ መንቀሳቀሳቸው ነበር። አንድ ሶስተኛው የአለም ህዝብ በዚህ በሽታ እንደተያዘም ይነገራል፡- በበሽታው ከተያዙት ውስጥ ከ10 እስከ 20 በመቶ የሚሆኑት ለሞት ተዳርገዋል። ሲኖ ባይሎጂካ የተሰኘ የህክምና ጥናት ማዕከል ባደረገው ጥናት መሰረት፡- በአሜሪካ እስከ 28 በመቶ የሚሆነው ህዝብ በበሽታው ተጠቅቶ ነበር፡- 675 ሺህ ገደማ የሚሆነው ህዝብ ደግሞ በበሽታው ሞቷል። ወረርሽኙ በህንድ የከፋ ነበር።

መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፡- 17 ሚሊዮን ህንዳዊያን በበሽታው ህይወታቸውን አጥተዋል። በጃፓን 23 ሚሊዮን ህዝቦችን ያጠቃ ሲሆን 400 ሺህ ገደማ የሚሆኑትንም ገድሏል። እንግሊዝ ሩብ ሚሊዮን፣ ፈረንሳይ ደግሞ 400 ሺህ ዜጎቻቸውን በበሽታው አጥተዋል። እ.ኤ.አ ከጥር ወር 1918 ዓ.ም እስከ ታህሰስ 1920 ዓ.ም በመላው ዓለም ተንሰራፍቶ የቆየው የእንፍሉዌንዛ ወረርሽኝ፣አንድ መቶ ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብ ፈጅቷል፡- የሟቾቹ ቁጥር እስከ 200 ሚሊዮን ይደርሳል የሚሉ መረጃዎችም አሉ።

የወረርሽኙን ጉዳት የከፋ ያደረገው አምራች ዜጎችን በከፍተኛ ሁኔታ በማጥቃቱ ነበር። በበሽታው ከሞቱት መካከል ዕድሜያቸው ከ25 እስከ 34 ዓመት የሆኑ ወጣቶች አብዛኛውን ድርሻ ይወስዳሉ፡ – በመሆኑም በሽታው ካደረሰው ሰብዓዊ ውድመት ባለፈ ጥሎት ያለፈው ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጠባሳ የከፋ ነበር።

ወረርሽኙ በአፍሪካ በሁለት ዙር ነበር የተከሰተው፡- የመጀመሪያው በፈረንጆቹ በ1918 ዓ.ም የጸደይና የበጋ ወራት ሲሆን ሁለተኛውና የከፋ ጉዳት ያደረሰው ደግሞ በበልግ ወራት የታየው ነበር። በሽታው ለመጀመረያ ጊዜ በአፍሪካ የታየው በወቅቱ የእንግሊዝ ቅኝ ግዛት በነበረችው በሴራሊዮን ዋና ከተማ ፍሪታዎን ሲሆን በአጭር ጊዜ ወደ ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ተስፋፋ።

ሚስተር መሪ (Murray) የተባሉ አጥኚ Glob­al Pandemic በተሰኘ ጥናታቸው እንዳሰፈሩት፡ – የበሽታው ስርጭት ከሰሃራ በታች በሚገኙ ሀገራት ላይ ሰፊ ነበር፡- በክፍለ አህጉሩ የተከሰተው የሞት መጠን በመላው ዓለም በበሽታው ከተከሰተው ሞት ውስጥ የ29 በመቶ ድርሻ አለው። በተለይም በምዕራብና ደቡባዊ አፍሪካ ጥፋቱ የከፋ ነበር፡ – በጋና እስከ መቶ ሺህ ዜጎች እንዳለቁ ይገመታል፡ – በምስራቅ አፍሪካም ቀላል የማባል ቁጥር ያላቸው ዜጎች ህይወታቸውን አጥተዋል፡- በእንግሊዝ ሶማሊ ሰባት በመቶ የሚሆኑ ህዝቦች በበሽታው ሲሞቱ፣ በኢትዮጵያም ከአርባ ሺህ በላይ ሰዎች በቫይረሱ ሳቢያ ህይወታቸውን አጥተዋል።

ከሰብዓዊ ውድመቱ ባለፈ ወረርሽኙ በአፍሪካ ከባድ ኢኮኖሚያዊ ቀውስ አስከትሏል። በጊዜው አጠራር ደቡብ ሮዴሺያ (የዛሬዋ ዚምባብዌ) አምራች የሰው ሀይል በበሽታው በመያዙ የወርቅ ማውጫ ስፍራዎች እንዲዘጉ ሆኖ ነበር፡- በዚህም በማዕድን ዘርፍ ላይ የተንጠለጠለው የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ክፉኛ ተጎዳ። ወረርሽኙ በማላዊና በዛምቢያም ያደረሰው ኢኮኖሚያዊ ኪሳራ ከፍ ያለ ነበር። በናይጀሪያም፣በተለይ በደቡባዊ የሀገሪቱ ክፍል በሽታው የከፋ ጥፋት በማድረሱና ምርት በማሽቆልቆሉ፣ ቀድሞ ለምግብነት የማይውለው ካሳቫ ለምግብነት መዋል ጀመረ። በአነስተኛ ጉልበትና ያለ ብዙ ልፋት የሚመረተው ካሳቫ ተመራጭ ምግብ ሆነ።

የ1918ቱ የእንፍሉዌንዛ ወረርሽኝ በአፍሪካ ያስከተለው ማህበራዊ ቀውስ ቀላል አልነበረም። በሽታው ዘር፣ ቀለም፣ ሀይማኖት፣ የኢኮኖሚ ደረጃን ሳይለይ ሁሉንም ሰው የሚያጠቃ ቢሆንም ቅኝ ገዢዎች በሽታው ከጥቁር ህዝቦች የመጣ እንደሆነ በማናፈስ የዘር መድልኦ ለማድረግ ተጠቅመውበታል። ይህ ችግር በተለይም በደቡብ አፍሪካ የጎላ ነበር፡- በዚህም ነጮችና ጥቁሮች ማንኛውንም ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎችን በአንድ ላይ እንዳያደርጉ የሚደነግግ አዋጅ እንዲጸድቅ ተደረገ።

በቦትስዋናም በሽታው በርካታ ህጻናትን ወላጅ አልባ አድርጓል። በጋና የሆነው ደግሞ ትንሽ ለየት ያለ ነበር፡- በሽታው ተንሰራፍቶ በርካታ ሴቶች በመጠቃታቸው፣ ከነባራዊው የጋናዊያን ባህልና ወግ ባፈነገጠ መልኩ ባሎች የሴቶች ድርሻ ተደርጎ ይወሰድ የነበረውን የቤት ውስጥ ስራዎች መስራት ግድ ሆነባቸው። ወንዶች ማዕድ ቤት ገብተው በቆሎ መፍጨት፣ ምግብ ማብሰል የመሳሰሉትን ስራዎች ይከውኑ ጀመር።

በኢትዮጵያ በሽታው የታየው የመጀመሪያው የበሽታው ምልክት በዓለም ላይ ከታየ ከአስር ወራት በኋላ በህዳር ወር 1911 ዓ.ም ነው። ከጥቂት ወራት ቀደም ብሎ በሽታው መግባቱ አይቀርም በሚል የቅድመ ጥንቃቄ ስራዎች መስራት እምብዛም የተለመደ አልነበረም። በዚህ ረገድ ሊጠቀስ የሚችለው በኢትዮጵያ የኢጣሊያ ቆንስላ ያደረገው ነገር ነበር።

የታሪክ ምሁሩ ፕሮፌሰር ሪቻረድ ፓንክረስት እ.ኤ.አ በ1990 ዓ.ም ባሳተሙት An Introduc­tion to the Medical History of Ethiopia በሚለው የምርምር ስራቸው ላይ እንደጻፉት፡ – በሽታው በውል ያልታወቀ ነበርና ምናልባትም የፈንጣጣ በሽታ ይሆናል በሚል በወቅቱ በኢጣሊያ ቆንስላ ትብብር በሀምሌ ወር 1910 ዓ.ም አስር ሺህ ዶዝ የፈንጣጣ ክትባት ወደ ኢትዮጵያ እንዲገባ ተደርጎ ነበር። የሆነው ሆኖ ከዘመናዊ ህክምና ጋር ለማይተዋወቀው የኢትዮጵያ ህዝብም ወረርሽኙ ታላቅ መቅሰፍት ነበር። በሽታው ከቁጥጥር ውጪ ወጥቶ በመላው ሀገሪቱ ከባድ ዕልቂት ማስከተል ጀመረ።

ዶ/ር እናውጋው መሃሪ፣ዶ/ር ክንፈ ገበየሁ እና ዶ/ር ዘርጋባቸው አስፋው የተባሉ የህክምና ባለሙያዎች በጋራ ያሰናዱትና በ2013 እ.ኤ.አ የታተመው The Manual of Ethiopian Medical History ላይ እንደሰፈረው፡- የ1918ቱ የእንፍሉዌንዛ ወረርሽኝ ክትባት ለመጀመሪያ ጊዜ የተገኘው በአሜሪካን የቫንደርቢልት ዩኒቨርሲቲ (Vanderbilt University) ምሁራን ሲሆን ወቅቱም በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ነበር።

ከዚያ በኋላ ባሉት ዘመናት በየጊዜው የተሻሻሉ ክትባቶች በምርምር ተገኝተዋል። በ1918 ዓ.ም እንደተከሰተው እንፍሉዌንዛ በወረርሽኝ መልክ ተከስቶ ባያውቅም ዛሬም ድረስ ግን የሰው ልጆች የጤና ፈተና መሆኑን አላቆመም። እ.ኤ.አ በ2012 ዓ.ም ብቻ በመላው ዓለም አምስት መቶ ሺህ ሰዎች በበሽታው ህይወታቸውን አጥተዋል። በዘርፉ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚጠቁሙት፡- የእንፍሉዌንዛ ክትባቶች የዋጋ ውድነት መፍትሄ ካላገኘ፣ ህዝቡ ስለ በሽታው በቂ ግንዛቤ ካላገኘ፣ መንግሥታት በሽታውን ለመከላከል ከፍ ያለ ትኩረት ካልሰጡ በእንፍሉዌንዛ ምክንያት የሚከሰተውን ሞት መቀነስ አዳጋች ነው።

የትናንቱን የታህሳስ ወረርሽን ዛሬ ላይ ሆነን ስናስብ ፡- በ1960ዎቹ የተማሪዎች እንቅስቃሴ ከሶቭየት ሕብረት ከአልባንያና ከቻይና ተዳቅሎና እንዳለ ከእነ ኮማው ተኮርጆ እንደ ሕዳር በሽታ ወይም ተስቦ ባሕርና ውቅያኖስ ተሻግሮ የገባው የባዕድ ርዕዮተ አለም ሀገራችንና ሕዝባችንን ካለፉት 50ና60 አመታት ጀምሮ ታማሚ አድርጎ አልጋ እንዳሲያዛቸው እያሰብን ፡- እንደ ሕዳር በሽታ ቀለል ባለ ጉፋንና ትኩሳት ወይም በዩኒቨርሲቲ ግቢ ውይይት ትንተና ስሁት መደምደሚያ ተጀምሮ ለሞት እየዳረገን መሆኑን እያስተዋልን ሊሆን እንደሚገባ ይሰማኛል ።

ወደ ፓርቲ እርዮተ አለም ጎልምሶ ልዩነትን ጥላቻን መጠራጠርን አለመተማመንና መጠፋፋትን ጎንቁሎ የሀገራችንን ህልውና አደጋ ላይ ጥሏል።አሳሯን አብዝቷል። ርዕዮተ አለሙ ይፈታቸዋል ተብሎ ታስበው የነበሩ ችግሮች ሳይፈቱ ይበልጥ ተካረውና ተወሳስበው ባለፉት አምስት አመታት ብቻ ሶስት ጦርነቶችን ቀስቅሶ ኅልቆ መሳፍርት የሌለው ጉዳት በሀገራችንና በሕዝባችን ላይ እያደረሰ ነው።

የሕዝባችንን ጥያቄ ይፈታልናል ብለው ይሄን ርዕዮተ አለም ፕሮግራማቸው ያደረጉ ኃይሎች ለ17 አመታት የትጥቅ ትግል አድርገው ለ27 ገዢ ሆነው ዛሬም ለትግል የተነሱበት አላማ/ኮዝ/ካልተፈታ ትንተናቸውም ርዕዮተ አለሙም ስሁት ነው ማለት ነው።ላለፉት 50ና ከዚያ በላይ አመታት በትጥቅም በፖለቲካ ታግለው ስልጣን ላይ ወጥተው ልሒቃኑ ዛሬም መግባባት ካልቻሉና ከጦርነት አዙሪት ካልወጡ ያንኑ ስህተት እየደገሙ ከሆነ አሁንም ርዕዮት አለሙም ትንተናውም መደምደሚያውም ስሁት ነበር ማለት ነው።

ሀገርንም ሕዝብንም ታማሚ ያደረገው ይሄ ፖለቲካዊ ግሳንግስና ቆሻሻ ሊቃጠልና እንደ ሕዳር ሊታጠን ይገባል እላለ ። እስኪ ሁላችንም ፖለቲካዊ ቆሻሾቻችን ከየቤታችን ወደ አደባባይ አውጥተን እናቃጥላቸው።በምትኩ በአመዱ ላይ ሕዝብን ሀገርንና ትውልድን የሚዋጅ አዲስ ሀገረኛ ፖለቲካዊ ደመራ እንደምር። እዚህ ያላነሳኋቸው ይሄው ስሁት ርዕዮተ አለም የቀፈቀፋቸው ብዙዎቻችን የምናውቃቸው ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ቆሻሾቻችንንም ማጠን ወይም ማቃጠል አንርሳ ።

ሻሎም ! አሜን።

 በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን) fenote1971@gmail.com

አዲስ ዘመን ህዳር 13/2016

Recommended For You