‹‹ መንግሥት በጤና ዘርፍ ትኩረት አድርጎ እየሠራ ያለው ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ላይ ነው›› – ዶክተር ዮሐንስ ጫላ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ ኃላፊ

ጤና ከሰው ልጅ የቅድሚያ ፍላጎቶች ውስጥ አንዱ ነው። ከግለሰብም አልፎ እንደ ማህበረሰብና ሀገር ጭምር የጤና ጉዳይ ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጠው ነው።ጤናማ ትውልድ እስካልተገነባ ድረስ ጤናማ ሀገር ሊኖር አይችልም።

ይህን መነሻ በማድረግም መንግሥት ለጤና ዘርፍ ሰፊ መዋዕለ ነዋይ በመመደብ የተለያዩ የጤና መሰረተ ልማቶችን እያስፋፋ ከመሆኑም ባሻገር አክሞ ለማዳን እና ለቅድመ መከላከል ግዙፍ መዋዕለ ንዋይ በመመደብ የህብረተሰቡን ጤና ለመጠበቅ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል።

ይህ የመንግሥት ጥረት ከሚታይባቸው አካባቢዎች አንዱ አዲስ አበባ ነው።በአዲስ አበባ ጤና ቢሮ አማካኝነት የህብረተሰቡን ጤና ሊያስጠብቁ የሚችሉ የተለያዩ መሰረተ ልማቶች እየተገነቡ ከመሆኑም ባሻገር ባሉት የጤና ተቋማት አማካኝነት የቅድመ መከላከልና የፈውስ ህክምናዎች በመከናወን ላይ ይገኛሉ።

በአዲስ አበባ ከተማ በጤና አገልግሎት ተደራሽነትና መሠረተ ልማት ግንባታ የተከናወኑትን ተግባራት፡- እንዲሁም በአገልግሎት ዙሪያ ከተጠቃሚው የሚነሱትን ቅሬታዎች በተመለከተ በእንግድነት ከጋበዝናቸው ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዮሐንስ ጫላ ጋር ያደረግነውን ቆይታ እንደሚከተለው አቅርበናል።

 አዲስዘመን፡- ለከተማዋ ነዋሪ የጤና አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ የተሰሩ ሥራዎች ምን ይመስላሉ?

ዶክተር ዮሐንስ፡– በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሥር 7 ሆስፒታሎች፣ 101 ጤና ጣቢያዎች በአገልግሎት ላይ ይገኛሉ። ከነዚህ በተጨማሪ በፌዴራልና በግል አገልግሎት የሚሰጡ በርካታ የጤና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በመኖራቸው የተደራሽነት ላይ ችግር የለም።

አዲስ ዘመን ፡- ተደራሽነት ላይ በዚህን ያህል ከተሰራ ፍትሀዊነትን በማረጋገጥ በኩል ያለው ሁኔታ ምን ይመስላል?

ዶክተር ዮሐንስ፡– የከተማ አስተዳደሩም ሆነ የጤና ቢሮ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ የሚገኘው ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ላይ ነው። በከተማ አስተዳደሩ ውስጥ ወደ 119 ወረዳዎች ይገኛሉ። ሁሉም የጤና ጣቢያ የላቸውም። ወደሌላ ወረዳ ሄደው ነው አገልግሎት የሚያገኙት። ይሄ የፍትሐዊነት ጥያቄ ያስነሳል። በሌላ በኩልም ሆስፒታሎቹ በመኻል ከተማ ውስጥ ነው የሚገኙት። ሰፊ ቁጥር ያለው ማህበረሰብ የሚኖረው ደግሞ ከመኻል ከተማ የራቀ በመሆኑ የጤና አገልግሎት ፍለጋ ረጅም ርቀት ይጓዛሉ። ሌላው ፍትሐዊነትን ለማረጋገጥ ከፍለው መታከም የማይችሉ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ማድረግ ሲሆን እነዚህን የማህበረሰብ ክፍሎች በማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ኢንሹራንስ አገልግሎት እንዲያገኙ በማድረግ ፍትሐዊነትን ለማረጋገጥ እየተሞከረ ነው።

የጤና መድህን ኢንሹራንስ እንደሀገር ከ10 አመት በፊት የተጀመረ ሲሆን፣ በከተማ አስተዳደሩ ደግሞ 2009 ዓ.ም በ10 ወረዳዎች ላይ መተግበር ተጀምሯል። በአሁኑ ጊዜ ግን በሁሉም የከተማ አስተዳደሩ ወረዳዎች ማህበረሰቡን ያቀፈ ሥራ ተሰርቷል።

በማህበረሰብ የጤና መድህን ኢንሹራንስ ወደ ሁለት ሚሊዮን ሁለት መቶ ሺ የሚሆኑ የከተማዋ ማህበረሰብ ክፍሎች ተካተዋል። ከነዚህ ውስጥም ወደ 350 ሺ የሚሆኑት ከፍለው መታከም የማይችሉ በመሆናቸው የከተማ አስተዳደሩ ሙሉ ወጪያቸውን ሸፍኖላቸዋል። የከተማ አስተዳደሩ እነዚህ የማህበረሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ በ2015 በጀት አመት ወደ ስድስት መቶ ሚሊዮን ብር ለማህበረሰብ የጤና መድህን ኢንሹራንስ ድጎማ አድርጓል። መክፈል ለሚችሉትም የከተማ አስተዳደሩ ለመመዝገቢያ 500 ብር ድጎማ ያደርጋል።

የማህበረሰብ ጤና መድህን ኢንሹራንሽ ተጠቃሚዎች በፌዴራልም ሆነ በአዲስ አበባ ከተማ ሥር በሚገኙ የጤና አገልግሎት መስጫዎች በነፃ አገልግሎት ማግኘት ይችላሉ። በዚህ መልኩ ነው ፍትሐዊነትን ከማስፈን አንጻር ሥራዎች እየተሰሩ ያሉት። በተያዘው በጀት አመትም ማህበረሰቡ በማህበረሰብ የጤና መድህን ኢንሹራንስ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ምዝገባ እየተካሄደ ነው።

አዲስዘመን፡- በፍትሐዊነት ላይ ሥራዎች መሰራታቸው ተደራሽነትን ያረጋግጣል?

ዶክተር ዮሐንስ፡- ተደራሽነት ከህዝብ ቁጥር፣ ካሉት ጤና ተቋማትና ባለሙያዎች ጋር ይያያዛል። ከዚህ አንጻር ተደራሽነት ላይ ችግር የለም። አካባቢው ላይ አገልግሎቱን ማግኘት ሲገባው ወደሌላ አካባቢ መሄዱ የፍትሐዊነት ጥያቄ ያስነሳል። ከፍሎ መታከም በሚችልና በማይችል መካከል የሚፈጠረውም ክፍተት እንዲሁ የፍትሐዊነት ጥያቄ ያስነሳል። ከዚህ አንጻር ነው ልዩነቶቹ የሚገለጹት።

አንድ ጀነራል ሆስፒታል ከአንድ ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ አገልግሎት ፈላጊዎች፣ሪፈራል ሆስፒታል ደግሞ እስከ አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ህዝብ አገልግሎት ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል። በዓለም ጤና ድርጅት በተቀመጠው መስፈርት መሠረት ተደራሽነት ላይ ችግር የለም።

አዲስ ዘመን፡- የጤና መሠረተ ልማት ግንባታ ላይ የተከናወኑት ተግባራትን ቢገልጹልን

ዶክተር ዮሐንስ፡- ቀደም ሲል እንዳነሳሁት የፍትሐዊነት ጥያቄን ለመመለስ የጤና ተቋማት በሌለባቸው ክፍለ ከተሞች በዚህ ሶስት አመታት ግንባታዎች ተከናውነዋል። ለዚህም ማሳያ የሚሆነው በክብርት አበበች ጎበና የተሰየመ «የእናቶችና ህፃናት አገልግሎት » የሚሰጥ ሆስፒታል ግንባታ ነው። ሐያት አካባቢ የሚገኘው ይህ ሆስፒታል ወደ 400 መኝታ ክፍሎችና የተለያዩ አገልግሎቶችን ያካተተ፣በግብአትና በባለሙያ የተደራጀ ምቹና ዘመናዊ ሆኖ የተገነባ ሆስፒታል ነው።

ይህ ሆስፒታል መገንባቱ ቀደም ሲል ወደ ዳግማዊ ሚኒልክ፣የካቲት፣ጋንዲ ሆስፒታሎች የሚላኩ እናቶች ይደርስባቸው የነበረው እንግልት ሆስፒታል ከደረሱ በኃላም ፈጣን አገልግሎት ሳያገኙ ቀርተው ወንበር ላይ እስከ መውለድ የሚደርሱበት አጋጣሚ እንዲያበቃ አድርጎታል ። ሆስፒታሉ በማዋለድ አገልግሎት ከፍ ያለ ሥራ የሚሰራና በወር ከአንድ ሺ በላይ ለሚሆኑ እናቶች የወሊድ አገልግሎት በመስጠት ሌሎች ሆስፒታሎች ላይ የነበረ ጫና በመቀነስ እፎይታ ሰጥቷል። በዚህ መልኩ የጤና አገልግሎቱን ተደራሽ በማድረግ ፍታዊነትን ከማረጋገጥ በተጨማሪ ጥራትንም አብሮ ማስጠበቅ ተችሏል።

ሌላው ኮልፌ ቀራኒዮና በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተሞች ውስጥ ግንባታቸው ከ50 በመቶ በላይ የደረሰና በጥሩ ሁኔታ በመካሄድ ላይ ያለው አጠቃላይ ሆስፒታሎች ናቸው። ሆስፒታሎቹ እያንዳንዳቸው ከ450 በላይ መኝታዎች ያሏቸው ዘመናዊ ሲሆኑ፡- እያንዳንዳቸው የግንባታ ወጪያቸው ከሶስት ነጥብ አምስት ቢሊየን ብር በላይ ነው።

እነዚህ ግንባታቸው በመፋጠን ላይ የሚገኙት ሆስፒታሎች በ 2002 ዓ.ም ላይ ነበር ይገነባሉ ተብለው ለህዝቡ ቃል ሲገባ የነበረው። በዚህ አምስት አመት የለውጥ ሂደት ውስጥ ግን ብዙ ሥራዎች መሥራት ተችሏል። እነዚህ ሆስፒታሎች ለአገልገሎት ሲበቁ በተለይም በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ በመገንባት ላይ ያለው ቤተል ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎችና በዙሪያው ላሉ አጎራባች ከተሞች ተደራሽ በማድረግ የነበረባቸውን ችግር ያቃልላል።

ሌላው የጤና መሠረተ ልማት ደግሞ የማስፋፊያ ሥራ ነው። እንደ ሚኒልክ፣የካቲት ሆስፒታሎች አንድ መቶ አመት አገልግሎት የሰጡ ናቸው። ሚኒልክ ሆስፒታል በአይን ህክምና ይታወቃል። ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚመጡ ታካሚዎችን ያስተናግዳል። ሆኖም ግን አገልግሎቱን በተለያየ ክፍል መስጠቱ ምቹ አልነበረም። አሁን ላይ በተከናወነው በማስፋፊያ ሥራ ባለ አራት ወለል ዘመናዊ ህንጻ ተገንብቶ የነበረውን የመኝታ ክፍል በአራት እጥፍ እንዲሁም የቀዶ ጥገና ህክምና ክፍልን በሁለት እጥፍ፣ የተመላላሽ ታካሚ ክፍል ሥራንም በአራት እጥፍ በማሳደግ የነበረውን ችግር ማቃለል ተችሏል።

ዘውዲቱ መታሰቢያ ሆስፒታልም የነበረው መሠረተ ልማት ከሚሰጠው አገልግሎት ጋር የተመጣጠነ አልነበረም። በዚህ ሆስፒታል ውስጥም አሁን ላይ ሆስፒታሉ እየሰጠ ካለው አገልግሎት በላይ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችለው፡- በአንድ ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ብር ባለ ስምንት ወለል ዘመናዊ ህንፃ በመገንባት ላይ ይገኛል። በዚሁ ሆስፒታል ውስጥ ተዘግቶ የቆየው የአይን ህክምና ክፍል አገልግሎት እንዲሰጥ ተደርጓል።

ለእናቶችና ህፃናት አገልግሎት እንዲሰጥ ታስቦ የተገነባው ጥሩነሽ ቤጂንግ ሆስፒታል፡- በአካባቢው ላይ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች የተለያየ የህክምና አገልግሎት እንዲሰጥ ከ300 በላይ የመኝታ አገልግሎት የሚሰጥ የማስፋፊያ ግንባታ ሥራ በመከናወን ላይ ይገኛል።

በጤና ጣቢያዎች የሚሰጠው አገልግሎት እየሰፋ በመሄዱ ነባር ጤና ጣቢያዎችንም ከማጠናከር አንጻር፡- በ2015 በጀት አመት ብቻ ወደ 28 የማስፋፊያ ፕሮጀክቶች በየጤና ጣቢያዎች ተተግብሯል። የማስፋፊያ ሥራዎች ማስፋፊያ ይባሉ እንጂ ለየተቋማቱ የህክምና አገልግሎት ትልቅ አቅም የሚፈጥሩ ናቸው። ባለፉት አምስት አመታት በተከናወኑት ሥራዎች 18 ጤና ጣቢያዎች በቀዶ ህክምና የማዋለድ አገልግሎት መስጠት ችለዋል። ። ይሄ በጤናው ዘርፍ የተመዘገበ ውጤት ነው።

አዲስ ዘመን፡- ከሀገራዊ ለውጡ በፊት በተለይም ከመኻል ከተማ ወጣ ባሉ አካባቢዎች የጤና መሠረተ ልማት ግንባታ ለማከናወን ተብለው የመሠረት ድንጋይ ተጥሎ አንዳንዶችም ግብአት ቀርቦ ግንባታቸው ሳይከናወን ለረጅም ጊዜ የቆዩትን ለይቶ ወደ ሥራ በማስገባት በኩል የተከናወነ ተግባር ካለ ቢገልጹልን?

ዶክተር ዮሐንስ፡– ከ10 አመት በፊት የመሠረት ድንጋይ ተጥሎ ሳይሰሩ የቀሩትን ነው በዚህ ሶስት አመት ውስጥ መሥራት የተቻለው። በ2016 በጀት ወደ አምስት ጤና ጣቢያዎች ለመገንባት ታቅዷል። የግንባታ ሥራዎችንም ከዲዛይንና ኮንስትራክሽን ተቋም ጋር በመሆን ቅድሚያ በሚሰጣቸው ላይ ትኩረት በማድረግ ነው ሥራዎች በመከናወን ላይ የሚገኙት።

ለግንባታ ተብለው ታጥረው የተቀመጡት ላይም ክፍተቶች ነበሩባቸው፡ ለምሳሌ የባለቤትነት ማረጋገጫ ( ካርታ) አለመኖር፣ ጨረታ ከወጣባቸው በኋላ ቅሬታዎች መምጣት ጋር በተያያዘ በርካታ ምልልሶች ያጋጥሙ ነበር። አሁን ላይ እንዲህ ያሉ ችግሮችን ለማስቀረት ወደ ግንባታ ከመገባቱ በፊት ቀድመው ሥራዎች እንዲሰሩ በከተማ አስተዳደሩ አቅጣጫ ተቀምጦ በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረት ነው ሥራዎች የሚሰሩት።

አዲስ ዘመን፡- የጤና መሠረተ ልማት ከፍተኛ በጀት የሚጠይቅ በመሆኑ ስለበጀት ሁኔታውም ቢገልጹልን?

ዶክተር ዮሐንስ፡- ከተማ አስተዳደሩ በራሱ በጀት እንደሚተዳደር ይታወቃል። ከተማው ነዋሪም ሰፊ የልማት ጥያቄዎች ያቀርባል። የከተማ አስተዳደሩ ለምገባ፣ለኩላሊት እጥበት ታካሚዎች፣ ለማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ኢንሹራንስ ተጠቃሚዎች እና ሌሎችም ፕሮግራሞች ወደ ዘጠኝ ቢሊዮን ብር ድጎማ ያደርጋል። ሆኖም ግን ከተማ አስተዳደሩ ጤናው የተጠበቀ አምራች ዜጋ ማፍራትን ታሳቢ ያደረገ ለጤናው ዘርፍ የሚመጥን በጀት በጅቷል። ምንም እንኳን ከተማው ከሚፈልገው የጤና አገልግሎት አቅርቦት አንጻር የሚቀር ነገር ቢኖርም ባለፉት አምስት አመታት አበረታች ተግባሮች ታይተዋል።የተሰሩት ስራዎችም ባለፉት 50 አመታት ያልተሰሩ ናቸው ማለት ይቻላል።

ከጤና መሠረተ ልማት ግንባታ ጋር በተያያዘ ሌላው የተከናወነው ሥራ የመረጃ ሥርዓትን ማዘመን ነው። ከወረቀት አሰራር መውጣት መረጃዎችን በተደራጀ መልኩ ለመያዝና የተቀላጠፈ አገልግሎትም ለመሥጠት ከማገዙ በተጨማሪ ለክፍተቶች ፈጣን የእርምት እርምጃ ለመውሰድ፣ ለወረቀትና ለተያያዥ ጉዳዮች የሚወጣ ወጪንም ለማዳን ያግዛል። የዲጂታል ትግበራው በአብዛኛው የጤና አገልግሎት መስጫዎች ውስጥ የተከናወነ ሲሆን፣የቀሩትንም በማዳረስ ሙሉ ለሙሉ ዲጂታላይዝ ለማድረግ እየተሰራ ነው።

ከጽንስ ጀምሮ የሚደረግ ኢንቨስትመንት የሚያስገኘው ውጤት ከፍተኛ እንደሆነም ጥናቶችን መሠረት በማድረግ በዚህ ረገድም ከተማ አስተዳደሩ በቀዳማዊ የልጅነት እድገት ልማት ፕሮጀክት በመጀመር በትኩረት እየሰራ ይገኛል። በዚህ ፕሮጀክት ለራሱም ለሀገርም ጠቃሚ የሆነ ትውልድ ለማፍራት ምቹ የሆነች ከተማ በመፍጠር ከአፍሪካ ሀገራት ቀዳሚ ለመሆን ነው እየተሰራ ያለው።

ፕሮጀክቱን ተግባራዊ ለማድረግም የቤት ለቤት የወላጅና የአሳዳጊዎች ምክር አገልግሎት የሚሰጡ ወደ አምስት ሺ ባለሙያዎች ተመልምለው ስልጠና እየተሰጠ ይገኛል። ከነዚህ ውስጥ 2 ሺ 500 ዎቹ ወደ ሥራ የገቡ ሲሆን፡- የተቀሩት እየሰለጠኑ ነው። ይህን ጅምርም ከአንድ ወር በፊት የክልል አስተዳደሮችና ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የመጡ ከንቲባዎች የተገኙበት አንድ የልምድ ልውውጥና የተሞክሮ መድረክ ተካሂዶ በመልካም ጎኑ ተወስዷል። በተለይም ከተማ አስተዳደሩ ለሌሎች ልምድ ያካፈለበት መድረክ ነበርም ማለት ይቻላል ።

አዲስ ዘመን፡- ከተማዋ የህክምና ቱሪዝም መዳረሻ እንድትሆንም የሚደረጉ ጥረቶች በምን ደረጃ ላይ ይገኛሉ ?

ዶክተር ዮሐንስ፡– ሁሉንም የጤና አገልግሎት በመንግሥት ብቻ መሸፈን ስለማይቻል የግሉን ዘርፍ ማበረታታት አስፈላጊ ከመሆኑም በላይ አሁን ላይ መንግሥት አገልግሎት ሰጪዎችን ከማበረታታት አልፎ የቁጥጥር ስራም ይሰራል ። ይህ ግን በሰለጠነው ዓለም የለም ። በመሆኑም ከተማዋ የጤና ቱሪዝም ማዕከል እንድትሆን ማስቻል አስፈላጊ በመሆኑ ሜዲካል መንደር (ሲቲ) እንገነባለን ብለው ጥያቄ ለሚያቀርቡ አስፈላጊውን ሁኔታ እያመቻቸን ሲሆን በጤናው ዘርፍ ኢንቨስት ለማድረግ ጥያቄ ላቀረቡ 20 ለሚሆኑ ኢንቨስተሮች የመሬት አቅርቦት ተከናውኗል ።

እዚህ ላይ ጥያቄ ካቀረቡት ባለሀብቶች 13 ቱ በቡድን ሆነው ሜዲካል ሲቲ ለመገንባት ዝግጁ የሆኑ ናቸው። በአሁኑ ወቅትም ወደ ግንባታ ለመግባት አስፈላጊውን የቅድመ ዝግጅት ሥራ በማድረግ ላይ ይገኛሉ። በግል አገልግሎት እየሰጡ ያሉ ነባር ሆስፒታሎችም ለማስፋፊያ የሚሆን መሬት ጠይቀው ወደ 13 ለሚሆኑ ምላሽ ተሰጥቷል።

በዚህ ረገድ ክፍተቶች እንዳይኖሩም ክትትል ይደረጋል። ለአብነትም በየአመቱ አንዳንድ ሆስፒታል በመሥራት አምስት ሆስፒታሎችን ለመገንባት ቦሌ ላይ መሬት የተሰጣቸው ሆራ የተባለ ስያሜ ያላቸው ባለሀብቶች በገቡት ቃል መሠረት አምስቱን ሳይሆን፣ የአንዱን ብቻ ግንባታ ነው የጀመሩት። የጀመሩትን ብቻ እንዲያጠናቅቁ በከተማ አስተዳደሩ አቅጣጫ ተሰጥቶ እየሰራ ይገኛል።

እዚህ ላይ ካለፈው ተሞክሮ መውሰድ የሚቻለው ወደ ልማት ሳይገቡ መሬት ይዘው ረዘም ላለ አመታት የቆዩ አጋጥመዋል። ከተማ አስተዳደሩ በመንግሥትም ሆነ በግል ለግንባታ የተወሰደ ወደ ልማት ያልገባ መሬት ላይ እርምጃ እየወሰደ ይገኛል።

ከዚህ ቀደም ያለው ተሞክሮዎች የሚያሳዩት ባለሀብቶቹ መሬቱን ከወሰዱ በኋላ ነው ለግንባታ ዝግጅት የሚያደርጉት። ይሄ ደግሞ ወደ ሥራው እንዳይገቡ አድርጓቸዋል። አሁን ባለው አሰራር ግን ችግሩ እንዳይደገም በግልም ሆነ በተናጠል ለማልማት ጥያቄ የሚያቀርብ ያለውን የገንዘብ አቅም ጨምሮ በወረቀት ላይ በሰፈረ እቅድ(ፕሮፖዛል) መሰረት ነው ወደ ኢንቨስትመንቱ መግባት የሚችሉት።

አዲስ ዘመን፡- በአንዳንድ የህክምና ዘርፍ ላይ ተኪ ባለሙያዎች የሉም የሚባል ነገር ይነሳል። ለአብነትም የአስክሬን ምርመራ የሚያካሂዱ ባለሙያዎችን ማንሳት እንችላለን ፡- እርስዎ በዚህ ላይ ምን ይላሉ ?

ዶክተር ዮሐንስ፡- የዓለም ጤና ድርጅትም ሆነ ጤና ሚኒስቴር ባስቀመጠው መስፈርት (ስታንዳርድ) መሠረት አንድ የጤና ባለሙያ ለነዋሪው ጥመርታ ሲሰራ በከተማ አስተዳደሩ ውስጥ የሚገኙ በፌዴራልም በግልም የጤና አገልግሎት የሚሰጡትን ተቋማት ያካትታል። በከተማ አስተዳደሩ የሚገኙ የጤና ባለሙያዎች ከአጠቃላይ የከተማዋ ነዋሪ ጋር ያለው ጥመርታ ሶስት ነጥብ አራት አካባቢ ነው። በአጠቃላይ የጤና ባለሙያ ጥመርታ ከተቀመጠው መስፈርት በላይ ነው። እዚህ ላይ ክፍተት የለም።

በተተኪ ባለሙያዎች ዙሪያ ለተነሳው ጥያቄ በተለይም የአስክሬን ምርመራ የሚያደርግ ባለሙያ እንደ ከተማም ሆነ እንደ ሀገር እጥረት የለም። ቀደም ሲል በሀገር ውስጥ የፎረሲንክ ህክምና ትምህርት አይሰጥም ነበር። አገልግሎቱም ከኪዩባ ሀገር በሚመጡ ባለሙያዎች ነበር የሚሰጠው። አሁን ላይ ግን ቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ ውስጥ ትምህርቱ እየተሰጠ ምርመራው ምኒሊክና አቤት ሆስፒታሎች ውስጥ በሀገር ውስጥ ባለሙያዎች እየተሰጠ ይገኛል።

በቀደሙት ጊዜያቶች ከነበሩት ጋር በንጽጽር ሲቀርብ እንደሀገር ባለሙያዎች እያፈራን በመሆኑ ክፍተቶችን ለመቀነስ ጥረት ይደረጋል ። አሁንም ግን ከፍተኛ ባለሙያ ወይንም ሰብእስፔሻሊስት የሚያስፈልጋቸው መስኮች ግን እንደተግዳሮት የሚነሳው የግብአት አቅርቦት እጥረት ነው። ለምሳሌ የልብ ቀዶ ህክምና፣ከአጥንት ዳሌ ሥብራት ቅያሬ ለማድረግ ካለመቻል፣ የጨረር ህክምና ጋር ተያይዞ በሚሰጡ አገልግሎቶች ዙሪያ አሁንም የአቅርቦት እጥረት በመኖሩ ታካሚዎች ለረጅም ጊዜ ወረፋ ይጠብቃሉ።

አዲስ ዘመን፡- አንድ ታማሚ የሚከታተለው ሀኪም የተለያየ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በሚታዘዙ መድኃኒቶችና ሌሎችም ችግሮች እያጋጠሙ እንደሆነ ቅሬታዎች ይነሳሉ። እዚህ ላይ ምን ይላሉ?

ዶክተር ዮሐንስ፡- እንዲህ አይነት ችግሮች የሚፈቱት አንድ ሀኪም እስከ መጨረሻው አንድን ታማሚ እንዲከታተል በማድረግ ሳይሆን፡- የታማሚውን የበሽታ ታሪክ በተደራጀ መልኩ ለመያዝ የመረጃ አያያዝ ሥርአትን በማዘመን ነው። ሀኪም ሲቀየር ህክምናው የተቀየረ አድርጎ ማሰብ ተገቢ አይደለም። ታማሚውን የሚያየው ሌላው ሀኪም ቀደም ሲል የነበረውን መረጃ መሠረት አድርጎ በመሆኑ ስጋቶችን መቀነስ የሚቻለው የመረጃ አያያዝን የተሻለ በማድረግ ነው።አንድ ሀኪም ያለው ክህሎትና የሥራ ልምድ እንዲዳብር በተለያዩ የህክምና ክፍሎች ተዘዋውሮ እንዲሰራ ይደረጋል።

አዲስ ዘመን፡-የተገልጋዩን እርካታ ለማረጋገጥ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ምን ይመስላሉ?

ዶክተር ዮሐንስ፡- የአገልግሎት ጥራትን ለማሻሻል፣ የተገልጋዩንም እርካታ ለመጨመር ዋን ስቶፕ ክሊኒክ የሚባል የአሰራር ሥርአት ተዘርግቷል። በዚህ የአሰራር ሥርአት ውስጥ ሰብስፖሻሊስት፣ስፔሻሊስት፣ሌሎችም ሀኪሞች ተካትተዋል። ታካሚው መመላለስ ሳይኖርበት በሁሉም ሀኪሞች ታይቶ አገልግሎቱን አግኝቶ ይሄዳል። ውሳኔ ሳያገኙ የሚቀሩ ታማማዎች እንዳይኖሩ ቅኝት (ራውንድ) ይደረጋል። በዚህ አሰራር የታካሚውን ቅሬታ ለመቅረፍ ጥረት እየተደረገ ነው። ቀድሞ በሚሰራ የበሽታ ልየታ ሥርዓት ቀጥታ ስፔሻሊስት ሀኪም የሚያየው ሆኖ ከተገኘ ታካሚው ስፔሻሊስት ሀኪም ጋር ይቀርባል።

የውጤት ተኮር ሥርዓት ትግበራ (ቢፒአር) ሲሰራ ታማሚዎችን ወይንም ታካሚዎችን ማዕከል ያደረገ ነበር። ቀደም ሲል የነበረው የህክምና ቡድን በጣም አነስተኛ በሆነ መልኩ ነበር የተደራጀው። በቢፒአሩ ግን ችግሮችን ሊፈታ በሚችል ከፍ ባለ አደረጃጀት ነው የህክምና ቡድን የተዋቀረው። በዚህ አሰራርም እያንዳንዱ የህክምና መስጫ ክፍሎች ባለቤት እንዲኖራቸው ተደርጓል። በተጨማሪም በተቀመጠው የህክምና አሰጣጥ መስፈርት መሠረት ህክምና መሰጠቱን የጥራት ተቆጣጣሪ በጤና ተቋማት ውስጥ ዳይሬክቶሬት ተቋቁሟል።

ሌላው ከጤና አገልግሎት መሻሻል ጋር የሚያያይዘው የመድኃኒት አቅርቦት ነው። በዚህ ረገድም ብክነትን የሚቀንስ፣ተጠያቂነትን የሚያሰፍን፣ ለብልሹ አሰራርም እንዳይጋለጥ የሚያደርግ የአሰራር ሥርዓት ተዘርግቷል። የፌዴራል ህክምናና መድኃኒት አቅርቦት ኤጀንሲ ከጤና ቢሮው ፋርማሲ ዳይሬክቶሬት ጋር ተናብበው የሚሰሩበት አሰራርም ተዘርግቷል። በዚህ አሰራርም አንዱ ተቋም ያለው መድኃኒት ምን አይነት እንደሆነ፣ እጥረት ያለበት ቦታ ደግሞ ክምችቱ ካለበት እንዲደርሰው በማድረግ ክፍተቶችን የመሙላት ሥራ እየተሰራ ነው።

ክፍተቶች ሲያጋጥሙ በተለይ ማህበረሰብ የጤና መድህን ኢንሹራንስ ተጠቃሚዎች ይጠይቁናል። በዚህ በኩል ሞጋች የሆነ ማህበረሰብ በመፍጠራችን አገልግሎታችንን ለማሻሻል አግዞናል። ለምሳሌ የማህበረሰብ የጤና መድህን ኢንሹራንስ ተጠቃሚዎች በከነማ የመድኃኒት አገልግሎት መስጫዎች እንዲጠቀሙ እድሉ ተመቻችቶላቸዋል። እነዚህ ሁሉ ሥራዎች ቢሰሩም በቂ ተብሎ እጅ አጣጥፎ ለመቀመጥ የሚያስችሉ እንዳልሆኑ ግንዛቤ ሊያዝ ይገባል።

አዲስ ዘመን፡- ከግብአት አቅርቦት ጋር በተያያዘ በጣም አነስተኛ ከሆነ የእጅ ጓንት ጀምሮ ታካሚው ከውጭ እንዲገዛ የሚጠየቅበት አሰራር መኖሩን እኔም አጋጥሞኛል። በሀኪም የሚታዘዙ የላብራቶሪ ምርመራዎችም በአብዛኛው ወደ ውጭ ነው የሚላኩት የሚሉ ቅሬታዎች ይነሳሉ። እዚህ ላይ ምን ይላሉ?

ዶክተር ዮሐንስ፡- የእጅ ጓንትን ጨምሮ መሠረታዊ የሚባሉ መድኃኒት አቅርቦቶች ላይ የሚስተዋል ችግርን በተመለከተ የጥናት ሥራ ሰርተን አነሰተኛ የሚባለው የመድኃኒት ዋጋ ገበያው ላይ መቶ በመቶ ነው ጭማሪ ያሳየው። እስከ አስር እጥፍ የጨመረ ግብአትም መኖሩም ተረጋግጧል። በተጋነነ ዋጋና በበቂ ሁኔታ አቅርቦት ካለመኖር ጋር ተያይዞ ችግሮች ይስተዋላሉ። ሌላው ጤና ጣቢያዎች በቂ በጀት የላቸውም። ቶሎ ይጨርሳሉ።

አንዳንድ ጊዜ በጀትም ኖሮ ገበያ ላይ የማይገኙ ግብአቶች አጋጥመዋል። ኮቪድ 19 ቫይረስ ወረርሽኝ ከተከሰተ በኃላ ከፍተኛ እጥረት ያጋጠመው የጓንት አቅርቦት ላይ ነው። እስከ አራት እጥፍ ነው ዋጋው የጨመረው። የውጭ ምንዛሪ አቅርቦትም የራሱ የሆነ ተግዳሮት ፈጥሯል። እነዚህን ተግዳሮቶች ምክንያት በማድረግ ሰው ሰራሽ የሆነ ክፍተትም አይጠፋም። እነዚህ ሁሉ ተደራርበው ነው ችግሮች የሚፈጠሩት፡- ያም ሆኖ ግን የክትትልና ቁጥጥር ሥርዓት በመዘርጋት መፍትሄ ለመስጠት ጥረት እየተደረገ ነው።

አሁን ላይ ለሚነሱ ችግሮች በጤና ቢሮው በኩልም ሆነ በከተማ አስተዳደሩ ዘላቂ መፍትሄ ተደረጎ የተያዘው፡ – የህክምና አገልግሎቶችን በአጋርነት (ፓርትነርሺፕ) ውል በመግባት እንዲያቀርቡ (አውትሶርስ) ማድረግ ነው። በተለይም ህክምናቸው ወሰብሰብ ያሉና ከፍተኛ የህክምና መሳሪያ የሚያስፈልጋቸውን በውጭ አገልግሎት ለመፍታት ነው የታሰበው።

ችግሮች ቀጣይነት ስለሚኖራቸው የህክምና አይነቶችን ለይቶ በውጭ እንዲስተናገዱ በማድረግ ነው በዘላቂነት መፍታት የሚቻለው። ከመድኃኒት አቅርቦት ጋር የተያየዙ ችግሮችን ለመፍታትም ኢንቨስትመንት መሳብ ሌላው አማራጭ በመሆኑ በዚህ በኩልም በፌዴራልም በከተማ አስተዳደሩም ጥረቶች እየተደረጉ ነው።

አዲስ ዘመን፡- ለከፍተኛ የህክምና አገልግሎት የሚውሉ እንደ ሲቲስካን ያሉ የህክምና መሣሪያዎች በመለዋወጫ እቃና በጥገና ምክንያት ያለ ሥራ መቀመጣቸው ይነገራል። እዚህ ላይም ሀሳብ ቢሰጡበት ?

ዶክተር ዮ ሐንስ፡– ችግሩ ፈታኝ ሆኖ ነው የተገኘው። ይህንንም ልንወጣው የምንችለው በውጭ አገልግሎት ከሚሰጡ ጋር አብሮ በመሥራት ነው። በዚህ በኩል ያለውን ችግር ለመፍታት የኩላሊት እጥበት ላይ ተሞክሯል። በሌሎችም የህክምና አገልግሎቶች ላይ በተመሳሳይ በመተግበር ወደ ሥርዓቱ ለመግባት ነው የታቀደው።

አዲስ ዘመን፡- ለህክምና የሚጠየቀው ዋጋ ውድ እየሆነ መምጣትም አንዱ የቅሬታ ምንጭ ነው ።

ዶክተር ዮሐንስ፡- ከ30 እስከ 50 በመቶ የዋጋ ማሻሻያ ተደርጓል። ሆኖም ግን በመንግሥት የጤና አገልግሎቶች የሚጠየቀው ክፍያ የሚሠጠውን አገልግሎት የሚመልስ አይደለም። መክፈል የማይችለው በማሕበረሰብ የጤና አገልግሎት ኢንሹራንስ በመርዳት፣መክፈል የሚችለው ደግሞ በተመጣጣኝ ዋጋ አገልግሎቱን እንዲያገኝ ነው የተደረገው። እንደውም መክፈል ለሚችለውም ህብረተሰብ ድጎማ ተደርጓል ማለት ይቻላል። በተለይ ደግሞ ለእናቶችና ህፃናት በነፃ ነው አገልግሎት የሚሰጠው።

አዲስ ዘመን፡- በአጠቃላይ በተግዳሮትና በጥንካሬ የሚነሱ ነገሮች ካሉ አያይዘውም ከህክምና ተቋማት የሚወገዱ ደረቅና ፍሳሽ ቆሻሻ ብክለት እንዳያስከትል እየተደረገ ስላለው ጥንቃቄ ቢገልጹልን?

ዶክተር ዮሐንስ፡- በጥንካሬ የማነሳው ተጠያቂነትን ሊያሰፍን የሚችል የመረጃ አያያዝ ሥርዓት መዘርጋቱ ሲሆን ቀደም ሲል አንድ ሰራተኛ ፊርማ መፈረሙ እንጂ ምን ሠራ የሚለው አይታይም ነበር። አሁን አንድ ባለሙያ የሰጠው አገልግሎት ነው የሚለካው።

ሰዎች በሰሩት ልክ እንዲበረታቱ የሚደረግበት አሰራር መኖር እንዳለበት ታምኖበታል። በሥነምግባር ብልሹ የሆኑትን ተጠያቂ በማድረግ ሥራዎች ይሰራሉ። የህክምና ስህተት ተፈጽሞ ሲገኝ ባለሙያው በምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን በኩል ተጠያቂ የሚሆንበት አሰራር በመዘርጋቱ በዚህ በኩልም ተገቢው ሥራ መሰራቱ በጥሩ ጎን ይወሰዳል።

ከቆሻሻ አወጋገድ ጋር ተያይዞ ለተነሳው፡- አሁን ላይ እየተሰራበት ያለ ቢሆንም ጊዜው የሚጠይቀው ዘመናዊ የቆሻሻ ማስወገጃ ወይንም ማቃጠያ ያስፈልጋል።ለጤና ተቋም ብቻ ሳይሆን ኬሚካል ለሚጠቀሙ ተቋማትም ጭምር ያገለግላል። ቆሻሻ የሚወገድብት አንድ ማእከል እንደሚያስፈልግም በከተማ አስተዳደሩ ግንዛቤ ተይዞ ታቅዷል። ትልቅ ኢንቨስትመንት ስለሚፈልግም ወደፊት ከአጋር ድርጅቶች ጋር መሥራት የሚያስፈልግበትም ሁኔታ ሊኖር ይችላል።

አዲስ ዘመን፡- ባለሙያዎችን በሥራ ላይ ለማቆየት የተሰሩ ሥራዎች ካሉ ይገልጹልኝና በዚሁ እናጠናቅቅ

ዶክተር ዮሐንስ፡- የጤና ባለሙያዎች ሊመሰገኑ ይገባቸዋል። ባለፉት አምስት አመታት እንደ ከተማም እንደሀገርም ኮቪድን ጨምሮ በርካታ ፈተናዎች አጋጥመዋል። የጤና ባለሙያው ህይወቱን እስከ መስጠት ነው ሙያዊ ግዴታውን ሲወጣ የነበረው። ጦርነት በተካሄደባቸው ቦታዎች እኔን ጨምሮ በመሄድ አገልግለናል።

ከተማ አስተዳደሩ ይህን የሚተጋ ባለሙያ የቤት ኪራይና የተለያዩ ድጎማዎችን በማድረግ ለማገዝ ጥረት አድርጓል። ማገልገል መታደል ነው። በጤናው ዘርፍ ለውጦች ሲመጡ ባለሙያው ከሚከፍለው ገንዘብ ይልቅ በውጤቱ ሊደሰት ይገባል።

አዲስ ዘመን፡-አመሰግናለሁ።

ዶክተር ዮሐንስ፡- እኔም አመሰግናለሁ።

ለምለም መንግሥቱ

አዲስ ዘመን ኅዳር 13 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You