መንግሥት ለሰላም ካለው ቁርጠኝነት የተነሳ የተወካዮች ምክር ቤት በአደባባይ ሽብርተኛ ብሎ ከሰየመው ከሸኔ ቡድን ጋር ወደ ሰላም መምጣት የሚያስችሉ ሁለት ዙር የሰላም ውይይቶችን አድርጓል። ልበ ሰፊ በመሆን ከቡድኑ ጋር ያደረጋቸው ውይይቶች በተለይ ሰላም ወዳድ በሆነው ሕዝባችን ዘንድ ከፍ ያለ ተስፋ ማጫሩ ይታወሳል።
ሰላም ለሀገራችን መረጋጋት፣ ከዚህ ለሚመነጨው ልማት ካለው ሁለንተናዊ አስተዋጽኦ አንጻር ፣ መንግሥት ቡድኑን በማነጋገር በሰላማዊ መንገድ በውይይት ለመፍታት የሄደበት ርቀት ፣ እንደ ሀገር በልማት ድህነትን ታሪክ ለማድረግ ለጀመርነው የአዲስ ታሪክ ግንባታ ትልቅ አቅም እንደሚሆን ይታመናል።
የመንግሥት ጥረት ከዚህም ባለፈ ልዩነቶችን በስክነትና በሠለጠነ መንገድ በጠረጴዛ ዙሪያ በውይይት የመፍታት ባህል በማዳበር፡- ሀገር እንደ ሀገር ካለችበት የግጭት አዙሪት እንድትወጣ ለማስቻል ሊኖረው የሚችለው አስተዋጽኦም ከፍ ያለ እንደሚሆን በብዙ መልኩ ለጥያቄ የሚቀርብ አይሆንም።
ይህንን ታሳቢ በማድረግም መንግሥት ከዚህ ቀደም ፡- ነፍጥ አንስተው ሕገ መንግሥቱን በመጣስ ሥልጣን ለመያዝ ከሞከሩት ኃይሎች ጋር ሳይቀር በተደጋጋሚ በውይይትና በሰጥቶ መቀበል መርህ ሰላምን ለማስፋት ጥረት አድርጓል፡- አሁንም እያደረገ ነው። በዚህ የተገኙ ውጤቶች ተስፋ ሰጪ ስለመሆናቸው የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ማሳያ ሊሆን የሚችል ነው።
መንግሥት ሕገ መንግሥቱንና የሀገሪቱን ሉዓላዊነት ለመቀበል ዝግጁ ከሆነ ከማንኛውም ኃይል ጋር ልዩነቶችን በሰላማዊ መንገድ በውይይት ለመፍታት በስፋት ተንቀሳቅሷል። ይህም ሆኖ ግን ይዘነው ከመጣነው፣ በመንግሥት ውስጥ መንግሥት የመሆን ልክፍት አንጻር ችግሮችን በውይይት ለመፍታት የሚደረጉ ጥረቶች ተገቢውን ከበሬታ ሳያገኙ የሚቀሩባቸው አጋጣሚዎች መከሰታቸው አልቀረም።
በኦሮሚያ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች በመንቀሳቀስ በሕዝቦች ሕይወትና ንብረት ላይ ጉዳት በማድረስ የሰላም ጠንቅ ሆኖ ከቆየው የሸኔ የሽብር ቡድን ጋር በታንዛንያ ዛንዚባር ከወራት በፊት የተጀመረው ውይይትም ይህንን የመንግሥትን እምነት መሬት በማውረድ ቡድኑ በሰላማዊ መንገድ የሚታገልበትን እድል ለመፍጠር ያለመ ነበር።
ይህም ሆኖ ግን የሽብር ቡድኑ ከ60 ዓመታት በፊት የኦሮሞም የሌሎች የኢትዮጵያ ብሔረሰቦችም ሁሉ ጥያቄዎች የነበሩ፡- ምላሽ አግኝተው አሁን ላይ ሕዝባችን ፍሬያቸውን በተጨባጭ እያጣጣማቸው ያሉ ቆሞ ቀር ጥያቄዎችን በማንሳት ውይይቱ ትርጉም አልባ እንዲሆን አድርጓል።
በተለይም ከለውጥ በኋላ በሥራ ላይ የዋሉ ፖለቲካዊ፡- ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ አጀንዳዎችን አንስቶ ከማነብነብ ውጪ የሚቆጠርና የሚቋጠር አጀንዳ ማምጣት ሳይቻለው ቀርቷል። “መንግሥት አዝሎ መንግሥት ያድርገኝ” ከሚል አጉራ ዘለልነት ያለፈ የድርደር ነጥብ ማምጣትም አልቻለም።
መንግሥት በኩል በሀገሪቱ ሰላም ሰፍኖ ኢትዮጵያ ያሏትን ጸጋዎች ወደ ተጨባጭ ሀብትና አቅም ቀይራ ብልጽግናዋን ታረጋግጥ ዘንድ ካለው ጉጉት በመነጨ ከግማሽ መንገድ በላይ ተጉዞ ለጉዳዩ እልባት ለመስጠት ቢሞክርም ፡- የሽብር ቡድኑ በሰላም ጊዜ እንዴት መኖር እንዳለበት ለማሰብ ቸግሮት ታይቷል። በዜጎች ደምና እንግልት መንገዱን መርጧል።
ሰላም በአንድ ወገን ፍላጎት ብቻ የሚሆን ካለመሆኑ አንጻር ፣መንግሥት ከቡድኑ ጋር ያለውን አለመግባባት በሰላማዊ መንገድ በድርድር ለመፍታት የሄደበት ርቀት ከፍያለ ከበሬታ እና እውቅና የሚሰጠው ነው። የመላው ሕዝባችን የሰላም መሻት መገለጫ ጭምር ነው።
ይህ አቋሙ በውይይት ሰጥቶ በመቀበል መርህ ዘመኑን የሚዋጅ የፖለቲካ ባህል እንደሀገር ለመገንባት ለጀመርነው ጥረት ትልቅ አቅም እና ተሞክሮ ተደርጎ የሚወሰድ ነው። አርቆ አሳቢነት፡- ከትናንት ተምሮ ዛሬን የተሻለ ለማድረግ የሚያስችል፡- ነገን ብሩህ ማድረግ የሚያስችል አቅም የተላበሰ በቀጣይም ተጠናክሮ ሊቀጥል የሚገባ ነው።
ይህም ሆኖ ግን መንግሥት ካለበት የሕዝብን ደኅንነት ጨምሮ ሕገመንግሥታዊ ሥርዓቱን ከመጠበቅ ኃላፊነት አንጻር ፡- አሸባሪው ቡድን የሕዝባችን የሰላምና የልማት ፀር የማይሆንበት ደረጃ ላይ ማድረስ ይጠበቅበታል፡- ለዚህ ሕገመንግሥታዊ ሥርዓቱን የመጠበቅ ተልዕኮውን በተቀናጀ መልኩ አጠናክሮ መቀጠል ይጠበቅበታል።
መላው ሕዝባችን በተለይም የኦሮሞ ሕዝብ አሸባሪ ቡድኑ የቱን ያህል ፀረ – ሕዝብ፣ ፀረ -ሰላም እና ፀረ ልማት መሆኑን ከቀደሙት ተግባሮቹ ባልተናነሰ ለሰላም የተዘረጉ እጆችን በመንከስ በተጨባጭ ያሳየ እንደመሆኑ የቡድኑን የጥፋት ተልዕኮ ለማምከን በሚደረገው ጥረት ከመንግሥት ጎን በቁርጠኝነት ሊሰለፍ ይገባል!።
አዲስ ዘመን ህዳር 13/2016