በማስታወቂያ ላይ የሚታዩ፤ ሊስተካከሉ የሚገቡ ችግሮች

በየእለቱ በየስልኮቻችን እና በየቤታችን በሚገኙ የመገናኛ ብዙኃን ፕሮግራሞች በርካታ ማስታወቂያዎችን ማድመጥም፣ መመልከትም የተለመደ ነው። እነዚህ ማስታወቂያዎች የተለያዩ ተቋማት ምርትና አገልግሎቶች የሚተዋወቁባቸው እንደመሆኑ፤ የማስታወቂያ አስነ ጋሪው ገንዘብ እና የማስታወቂያ ነጋሪው የአየር ሰዓት ተዳምረው ለጆሮና ዓይኖቻችን የሚደርሱ ናቸው።

በማኅበራዊ ሚዲያዎችም ሆነ በብሮድካስት ሚዲያዎች የሚለቀቁት እነዚህ ማስታወቂያዎች እንደሚ ተዋወቅባቸው ምርትና አገልግሎት መለያየት ሁሉ፤ አቀራረባቸውም የተለያየ ነው። አንዳንዱ አማላይ፣ አንዳንዱ አስደማሚ፣ አንዳንዱ አስገራሚና አስደንጋጭ፣ አንዳንዱም አናዳጅ፣ አንዳንዱ ደግሞ ሃሳብ አስለዋጭና አወናባጅ ሆኖ የሚገኝበት አጋጣሚ የበዛ ነው።

ይሄን ለተመለከተ፣ ሀገራዊ የማስታወቂያ ሥራው የሚመራበት ሕግና ሥርዓት የለምን ብሎ እንዲጠይቅ መገደዱ የማይቀር ነው። መልሱም ቢሆን ብዙ የሚያጠያይቅ አይደለም፤ አለ የሚል ነው። ትልቁ ጉዳይ ግን የሕጉ መኖር ሳይሆን፤ የሕጉ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ መሆን በአለመቻል ነው።

እዚህ ላይ በመገናኛ ብዙኃን/በሚዲያዎች የሚተላለፉ ማስታወቂያዎች የማስታወቂያ አዋጁን ሙሉ በሙሉ የሚተገብሩ ናቸው፣ ወይንስ አይደሉም ከሚለው ምልከታዬ በፊት የተወሰኑ ነጥቦችን ለማንሳት ልሞክር። በተለይ የምናወራው ስለ ማስታወቂያ እንደመሆኑ፤ ከዚህ ጋር ተያይዘው ስለሚነሱ ጉዳዮች ጠቀስ አድርጎ ማለፉ መልካም ይሆናል። ከዛም ወደ ዋናው ጉዳዬ እመለሳለሁ።

በቅድሚያ ማስታወቂያ ስንል፣ የአንድ የምርት ወይም የአገልግሎት ስም፣ ዓርማ፣ የንግድ ምልክት ወይም ዓላማ በማስታወቂያ ማሰራጫ መንገድ እንዲተዋወቅ በማድረግ ሽያጭን ማስፋፋት ነው። ይሄም በማስታወቂያ አማካኝነት ስለ ምርቱና አገልግሎቱ ለኅብረተሰቡ ተገቢ መረጃ በመስጠት የኅብረተሰቡን መብትና ጥቅም ባስጠበቀ መልኩ ጤናማ የገበያ ውድድር እንዲኖር ያስችላል።

ማስታወቂያ የአንድ ድርጅት ወይም ተቋም መልዕክት ሲሆን፤ ይሄም ምርትና አገልግሎትን ለሕዝብ በማስተዋወቅ በገበያው ውስጥ ተወዳዳሪነቱን ከፍ ለማድረግ የሚጠቀምበት መንገድ ነው። ይህ እንዲሆን ደግሞ ማስታወቂያዎች ምርቱን ወይም አገልግሎቱን በትክክል በሚገልጽ መልኩ መቀረጽም፤ መተላለፍም ይኖርባቸዋል። ግን እንዴት?

የማስታወቂያ ይዘት ምን መሆን አለበት?

በማስታወቂያ አዋጁ መሠረት ማንኛውም ማስታወቂያ ሕግን ወይም መልካም ሥነ ምግባርን የማይጻረር፣ አሳሳች ወይም ተገቢ ካልሆነ አገላለጽ ነፃ የሆነ፣ የኅብረተሰቡን ማኅበራዊና ባሕላዊ እሴት የሚያከብርና የሸማቹን ሕጋዊ ጥቅም የማይጎዳ መሆን አለበት። ለዚህም ደግሞ እውነተኛ ባሕርይ፣ ጥቅም፣ ጥራትና መሰል መረጃዎችን የሚገልጽ ሊሆን የግድ ነው።

ከዚህ ባለፈም ማስታወቂያ፣ የሌሎችን ተመሳሳይ ምርት የማያንቋሽሽ፣ የሀገርን ክብርና ጥቅም የሚጠብቅ፣ የሙያ ሥነ ምግባርን የሚያከብር ይዘት ያለው መሆን አለበት። ይሄ በሕጉ የተቀመጠ የማስታወቂያ አስነጋሪውም፣ የማስታወቂያ ነጋሪውም ግዴታ ነው።

ነገር ግን ምን ያህሎቹ ተቋማት ናቸው ይህንን አክብረው ማስታወቂያዎቻቸውን የሚያስነግሩት የሚለው አጠያያቂ ነው። ለምሳሌ፣ በመዓዛው አውዶ ቢራቢሮዎችን ይጠራል፤ በዚህ ማጠቢያ የሚታጠብ ልብስ ለዓመታት ቢለብሱትም ነግቶ አዲስ ይሆናል የሚባልነት የዱቄት ሳሙና፤ እንኳን ልብስ ሊያጠራና፤ መዓዛው ቢራቢሮ ሊጠራ ይቅርና በወጉ አረፋ እንኳን የሌለው፤ ከእንዶድ የማይሻል ሆኖ ማግኘት የተለመደ ነው።

ሌላኛው ደግሞ ትውልድ ገዳይ የሆነው ማስታወቂያ ደግሞ በየስልክ እና የመብራት እንጨቶች(ፖሎች) በየቦታው የተለጠፉ የትዳር አገናኝ፤ ሹገር ማሚ እና ሹገር ዳዲ እናገናኛለን በሚል በኩራት የሚለጠፉ ማስታወቂያዎች ናቸው፤ ይህንን አይነቱስ ማስታወቂያ እነማናቸው የሚያነቡት? ማነውስ ስለዚህ ጉዳይ ኃላፊነት ያለበት? ነገ የኛ ልጆች በዚህ አይነቱ ማስታወቂያ ተስበው እንደማይገቡበት ምን ዋስትና አለን? እነዚህ ማስታወቂያዎች በሕጉ የተከለከሉ፤ የኅብረተሰቡን ወግና ባሕል የሚጻረሩ እና የወሲብ ንግድን የሚያስፋፉ ናቸው።

እነዚህን የፖል ማስታወቂያዎች ለአብነት አነሳሁ እንጂ፤ ከአዋጁ ድንጋጌዎች የሚቃረኑ አያሌ ማስታወቂያዎችን ማየትም፣ መስማትም የተለመደ ነው። ለዚህ ማሳያ የሚሆን የሚከተሉትን እንመልከት።

በማስታወቂያ አዋጁ የተከለከሉ እና የተፈቀዱ ይዘትና አገላለጾች ቀደም ብዬ ለመጥቀስ እንደሞከርኩት፣ በማስታወቂያ አዋጁ መሠረት አንድ ማስታወቂያ ሲነገር ሕግን፣ ሥነምግባርን፣ ማኅበራዊ እሴትን እና የሀገር ክብርን ማዕከል አድርጎ ሊሆን ይገባል። ከዚህ ባለፈ ከሕግ አፈንግጦ፤ ከሥነምግባር ወጥቶ፣ ከማኅበራዊ እሴት ተፋትቶና የሀገርን ክብር አዋርዶ በሐሰትና ግነት ተሞልቶ ሊነገር እንደማይገባው በግልጽ ተመላክቷል። በዚህ ረገድ በማስታወቂያ ሂደት ሊታሰቡ የሚገባቸውን የተወሰኑ ነጥቦች ላንሳ፤

1ኛ. ሕግን ወይም መልካም ሥነ ምግባርን ስለሚፃረር ማስታወቂያ፡-

አንድ ማስታወቂያ ቋንቋን፣ ፆታን፣ ዘርን፣ ብሔርን፣ ብሔረሰብን፣ ሙያን፣ ሃይማኖትን፣ እምነትን፣ ፖለቲካዊ ወይም ማኅበራዊ አቋምን አስመልክቶ የሰው ልጅን ስብዕና፣ ነጻነት ወይም እኩልነት የሚጻረር ምስልን፣ አነጋገርን ወይም ንጽጽርን መያዝ፤ የአካል ጉዳተኛን፣ የኤች አይ ቪ/ኤድስ ቫይረስ በደሙ ውስጥ ያለበትን ወይም በሌላ ሕመም የተያዘ ሰውን ክብርና ሥነ ልቦና የሚነካ መሆን የለበትም።

ይሄ ድንጋጌ ማስታወቂያዎች ምርትና አገልግሎትን በማስተዋወቅ ሂደት ምን አይነት ጉዳዮች ላይ ጥንቃቄ ሊያደርጉ እንደሚገባቸው በግልጽ የሚያሳይ፤ በዋናነትም አስተዋዋቂው አካል ምርትና አገልግሎቶቹን ለሚያደርሰው ሕዝብ ከፍ ያለ የማኅበራዊም የሞራልም ጥበቃ ሊያደርግ እንደሚገባው የሚያሳስብ ነው። በዚህ ረገድ በተለየም በብሮድካስት ሚዲያው በሚለቀቁ ማስታወቂያዎች እንብዛም ክፍተት አይታይም።

2ኛ. በሕጉ በአሳሳች የሚባለው የማስታወቂያ ይዘት፡-

አንድ ማስታወቂያ ሲነገር ምርቱ የተመረተበትን ቦታ፣ ቀን፣ ባሕሪ፣ በውስጡ የያዘውን ንጥረ ነገር፣ ክብደት፣ መጠን፣ ያለውን ጠቀሜታ ወይም ተቀባይነት በሐሰት የሚያስተዋውቅ፤ ምርቱ የሌለውን ጥቅም፣ አገልግሎት፣ ጥራት፣ ጣዕም፣ ንጥረ ነገር፣ ጥንካሬ፣ ዕድሜ ወይም ብርካቴ እንዳለው አስመስሎ የሚያስተዋውቅ፤ የአገልግሎት ጊዜው ለማለፍ የደረሰን ወይም ያለፈበትን ምርት የሚያስተዋውቅ፤… በአዋጁ አሳሳች ማስታወቂያ ከሚባሉት ውስጥ ይመደባል።

በዚህ መሠረት በሀገራችን የሚነገሩ በርካታ ማስታወቂያዎች ክፍተት አለባቸው። በተለይም በማኅበራዊ ድረገጾች በርካታ ተከታዮች ያሏቸው መገናኛ ብዙኃን እነዚህን የምርትና የአገልግሎት መስፈርቶችን በአግባቡ ሳያጣሩ መልእክቶችን ሲያስተላልፉ ይስተዋላል። ከነዚህም ውስጥ ለኮስሞቲክስ እቃዎች የሚሠሩ የሽያጭ ማስታወቂያዎች እጅግ የተጋነኑ ስለመሆናቸው በዋቢነት ማንሳት ይቻላል።

ለምሳሌ በቅርቡ በብዙ ማኅበራዊ መገናኛዎች በርካታ ማስታወቂያ ሲሠራለት ሕዝቡም ለምርቱ የማይገባውን ዋጋ ሲጠየቅበት የነበረ አንድ የፊት ሳሙናን እናንሳ፤ ሳሙናው በማስታወቂያው እንደተነገረን ብጉር እና ማዲያትን የሚያጠፋ ነው የሚል ነበር ነገር ግን እንኳን ማዲያት ሊያጠፋ ይቅርና ማዲያቱን በማባባስ እንዲሁም ፊታችንን ለፀሐይ የሚያጋልጥ ነበር። ምስጋና ለአንዳንድ ኃላፊነት ለሚሰማቸው የቆዳ ሐኪሞች ይሁንና በቻሉት መጠን ሰዎች ከመግዛት እንዲቆጠቡ ማድረግ ቻሉ።

በተጨማሪም አንዳንዶቹ ማስታወቂያዎች ሕግን ወይም መልካም ሥነ ምግባርን በሚጻረር መልኩ የቆዳ ቀለምን መሠረት ያደረገ ማንቋሸሽም ይታይባቸዋል። ይሄ ደግሞ እጅጉን አደገኛ አካሄድ እንደመሆኑ የሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማት ቁጥጥር እና ክትትል በማድረግ እርምጃ ሊወስዱ ይገባል። ለምሳሌ አንዳንድ የሰውነት ሎሽኖች እና ቅባቶች የሚያስተዋውቁት ሰዎች ወዲያው ሲቀቧቸው የሰውነት ቆዳ ቀለማቸውን ቀይረው የነጭ ወይም የፈረንጅ የቆዳ ቀለም ሲሰጧቸው ያሳያል የዚህ ትርጉም ምንድነው የሚለውን ለናንተ ልተወው።

ሌላኛው እንዲሁ የጸጉር ቅባቶች ማጠቢያ ሻንፖና ኮንዲሽነሮች የሩቅ ምሥራቆቹን እና የምዕራባውያን የጸጉር ይዘት የሚያስመስሉ መሆናቸው የሚያሳዩ ናቸው። ማነው የጸጉር ውበት መለኪያ የምዕራባውያኑ ነው ያለው? አፍሮ የሚባለው የአፍሪካውያን የጸጉር ይዘትስ ማነው መጥፎ ነው ያለው? ማስታወቂያዎቻችን ለምንስ መለኪያዎቻቸው እነሱ ሆኑ? ለማንኛውም የዚህ አይነቱ የማስታወቂያ ይዘት በሕጉ የተከለከለ ነገር ግን እየተተገበረ ያለ ነው።

3ኛ. በሕጉ የተከለከሉ ማስታወቂያዎች፡-

በማስታወቂያ አዋጁ መሠረት የእፅ ማስታወቂያ፤ ያለ ሐኪም ትእዛዝ የማይሰጥ ወይም በጥቅም ላይ የማይውል መድኃኒትን ወይም የሕክምና መገልገያን ተጠቃሚው በቀጥታ እንዲጠቀም የሚገፋፋ ማስታወቂያ፤ ናርኮቲክ መድኃኒትን ወይም ሳይኮቴራፒክ ንጥረ ነገርን የሚመለከት ማስታወቂያ፤ የጦር መሣሪያ ማስታወቂያ ማሰራጨት መንገርና የተከለከለ ነው።

ከዚህ ውጪም የቁማር ማስታወቂያ፤ የሕገ ወጥ ምርት ወይም አገልግሎት ማስታወቂያ፤ የአራጣ አበዳሪ ማስታወቂያ፤ የጥንቆላ ማስታወቂያ፤ የሲጋራ ወይም የሌሎች የትምባሆ ውጤቶች ማስታወቂያ፤ የፖለቲካ ግብ ያለው ማስታወቂያ፤ የአልኮል መጠኑ ከ0.5 በመቶ በላይ የሆነ ማናቸውንም መጠጥ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገርና ማሰራጨት የተከለከለ ነው።

እነዚህ ነገሮች በሕጉ ይቀመጡ እንጂ፤ ጥቂቶቹም ቢሆኑ በተለያዩ አግባቦች ማስታወቂያ እየተሠራላቸው በየስልኮቻችን ይደርሳሉ። ለምሳሌ፣ ያክልም የባሕል ሐኪም ውጤቶች በሚል የጥንቆላ ሥራ የሚመስሉ ወይም ሳይንሳዊ ተቀባይነት የሌላቸው የማስታወቂያ መልእክቶች በየማኅበራዊ ሚዲያዎቻችን ሲዘዋወሩ ማየት የተለመደ ነው።

በተሳሳተና ከሕግ ውጪ የሚሰራጩት እነዚህ ማስታወቂያዎች ደግሞ በርካቶችን ለገንዘብ መጭበርበር፣ ብሎም ለጤና እክል እየዳረጉ ይገኛሉ። ይሄም ከወዲሁ ሃይ ባይ ካልመጣለት ከፍ ወዳለ ማኅበራዊም ኢኮኖሚያዊም ችግር መሸጋገሩ አይቀሬ ነው።

4ኛ. በማስታወቂያ መቋረጥ የሌለባቸው ፕሮግራሞች፡-

በመገናኛ ብዙኃን የሚተላለፉ ማስታወቂያዎች በይዘት ብቻ ሳይሆን በሰዓትና በፕሮግራም ላይ የተመሠረቱም ሊሆን እንደሚገባ የማስታወቂያ አዋጁ ያስቀምጣል። ለምሳሌ፣ የሕፃናት ፕሮግራም፤ የዜና ወይም የወቅታዊ ጉዳይ ዘገባ፤ የቅጅ መብት ባለቤቱ ካልፈቀደ በስተቀር ሙዚቃ፣ ድራማ ወይም ዶክሜንተሪ ፊልም፤ የስርጭት ጊዜው ከ20 ደቂቃ የማይበልጥ ማንኛውም ፕሮግራም፣… አቋርጦ ማንኛውም ማስታወቂያ ሊነገር/ሊተላለፍ አይገባውም።

በዚህ ረገድ በመገናኛ ብዙኃን ዘንድ በርካታ ክፍተቶች አሉ፤ በተለይም የሕጻናት ፕሮግራሞችን በማስታወቂያ ማቋረጥና ከ20 ደቂቃ የሚያንሱ የአየር ሰዓት ያላቸውን ፕሮግራሞች በዋናነት ድራማዎችን በማስታወቂያ የማቋረጡ አካሄድ እጅግ ጎልቶ የሚታይ ነው ። ይሄም በሁሉም አካል (ፈጻሚውም አስፈጻሚውም) ግንዛቤ ተወስዶበት ሊሠራበትና ሊታረም የሚገባው ጉዳይ ነው።

5ኛ. ከስፖንሰር መግለጫ አጠቃቀም አንፃር፡-

በማስታወቂያ አዋጁ ከስፖንሰር መግለጫ አጠቃቀም አንፃር የተቀመጡ ነጥቦች እንደሚያመለክቱት፤ የፕሮግራሙ ይዘት እና የጊዜ ሰሌዳ በስፖንሰሩ ተፅዕኖ ስር መውደቅ የለበትም። በፕሮግራሙ ይዘት ውስጥም የስፖንሰሩ ምርት/አገልግሎት እንዲሸጥ መቀስቀስ የለበትም፤ ከዚህ ባለፈ ግን ለስፖንሰሩ የሚቀርብ ምስጋና በፕሮግራሙ መጀመሪያ፣ አካፋይ ወይም መጨረሻ ላይ ሊተዋወቅ/ሊገለፅ ይችላል።

ምሳሌ፡- አካፋይ ሳይጠብቁ ፕሮግራምና የስፖንሰር መግለጫን መቀላቀል፣ እንዲሁም በሲዲ የቀረበን ማስታወቂያ ጋዜጠኛው መልሶ በቃሉ በመድገም አሻሻጭ መሆን እንደሆነ በአዋጁ በግልጽ ያስቀምጣል። ነገር ግን በተለይም በሬዲዮ ፕሮግራሞች ላይ የስፖንሰሮች ተፅዕኖ ጎልቶ ይታያል። ጋዜጠኞችም ቢሆኑ አሻሻጭ የሆኑ በሚመስሉ መልኩ የስፖንሰሩ ምርትና አገልግሎቶችን በቃል በመደጋገም አድማጮችን የማሰልቸት አካሄድ ይስተዋልባቸዋል።

በመሆኑም ይሄም አካሄድ ተመልካች አግኝቶ ፈር ሊይዝ የሚገባው የማስታወቂያ አሠራር ችግር ነው። ለምሳሌ ያክል በአንድ የሬዲዮ ፕሮግራም ጋዜጠኛው አንድ ሬስቶራንትን ያስተዋውቃል በውነት ያንን ማስታወቂያ ለሰማው ሰው እራሱ ጋዜጠኛው በሬስቶራንቱ ተገኝቶ ሸብ ረብ ብሎ የሚያስተናግድ እንጂ ጋዜጠኛ ነው ለማለት በሚያስቸግር መልኩ ማስታወቂያ ሲሠራ ታዝቤያለሁ።

እነዚህ ክፍተቶች ለማስተካከል ምን ይደረግ?

ከላይ የጠቃቀስኳቸውን አይነት የማስታወቂያ አካሄዶች አንድም የንግድ ሥርዓቱ ላይ ጫና የሚፈጥሩ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ኅብረተሰቡን ባልተገባ መልኩ የሚያሳስቱም የሚያሰለቹም መሆናቸው እሙን ነው። በመሆኑም እነዚህን ችግሮች ማረም የተገባ ነው፤ በዚህም የአሰራጭና ወኪሎች የየራሳቸውን ሚና በአግባቡ መጫወት አለባቸው።

ምሳሌ አንድ፣ ማስታወቂያ ነጋሪዎች ከማስታወቂያው አስነጋሪዎች የቀረበላቸው መረጃ ትክክለኛነት ማረጋገጥ፣ ማስታወቂያው ሕግን አለመጣሱን ማጣራት፣ የማስታወቂያ ሥራ ፈቃድ፣ የንግድ ሥራ ፈቃድ መኖሩን፣ የጥራት ማረጋገጫ ሰርተፍኬት/ምልክት መኖሩን ማጥራት አለባቸው። ይሄም ካልተገባ የማስታወቂያ ሕግ ጥሰት ይታደጋቸዋል።

በዚህ ረገድም የነበረውን ክፍተት በጉልህ የሚያሳየውና የቅርብ ጊዜ ምሳሌ የሚሆነው በየሚዲያው የሞላው የጁስ ማስታወቂያን እናንሳ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚመረት የፍራፍሬ ጁስ አለመኖሩን በቅርቡ ተቆጣጣሪ አካላት ለሚዲያዎች አሳውቀዋል። ነገር ግን እነዛ ምርቶች ለበርካታ ጊዜያት የጁስ ምርት እንደሆኑ ተነግረው ሲቀርቡ ነበር ይህ የሆነው በሚዲያዎቹ ግዴለሽነት እና ከተቆጣጣሪ አካላት ጋር ባለመናበባቸው የተፈጠረ ስህተት ነው።

ምሳሌ ሁለት፣ “ብቸኛው፣ ወደር የሌለው፣ ዋስትና፣ ሽልማት የሚሰጥ፣ ቅናሽ የሚያደርግ፣…” የሚል ማስታወቂያ ካለ፤ እውነት መሆኑን ማጣራት ይኖርባቸዋል። በሕግ አስከባሪዎችና በጥራት ተቆጣጣሪ አካላት ይሄን ከማድረግ አኳያ የተጀመሩ መልካም ሥራዎች ያሉ ቢሆንም፤ ጅምሩ ግን በአልኮልና ሌሎች ጎጂ የተባሉ ምርቶች ላይ የታየውን ውጤት በሌሎች ላይ መድገም ያላስቻለ ነው።

ምክንያቱም በርካታ ሬዲዮ ጣቢያዎች ላይ ጋዜጠኞች አሻሻጥ የሚያስመስላቸውን ማስታወቂያ ሲሠሩ (ያውም በተጋነነ አቀራረብ) ይውላሉ። በማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን የሚተላለፉ መልእክቶች ላይም ክፍተት በመኖሩ ለኅብረተሰቡና ለሚዲያ አካላት ተገቢውን ሥልጠናና የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን መሥራት ይጠበቅባቸዋል። ከዚህ በተጓዳኝም አዋጁን ተላልፈው የሚገኙት ተቋማት ላይ በቂና ተመጣጣኝ ብሎም ሌሎችን የሚያስተምር እርምጃ መውሰድ ይኖርባቸዋል።

በዚህ መልኩ ማስታወቂያ አስነጋሪውም፣ ነጋሪውም ሕግና ሥርዓትን አክብረው እንዲሠሩ መምከር፤ ይሄን እንዲቆጣጠር እና እንዲያስፈጽም የተሰየመውና ከሕዝብ በሚሰበሰብ ግብር የሚተዳደረው አካልም የሕዝብን ማኅበራዊ፣ ሞራላዊ፣ ባሕላዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ሌሎችም እሴቶቹን ከሚጎዱ የማስታወቂያ ነገራ ሂደቶች ሕዝቡን ሊታደገው ይገባል።

ይሄን ሰምቶ በሕግ መገዛትና ሕግን ማስከበር ደግሞ ከሁሉም የሚጠበቅ ብቻም ሳይሆን፤ የመተግበር ግዴታም መሆኑን በማወቅ ፈጻሚም አስፈጻሚም የናፈቀውን የማስታወቂያ አዋጅ ከተግባር ማገናኘት ነገ ሳይሆን ዛሬ ሊሠራ፤ ይሄን ካለማድረግ የሚፈጠርን ኢ-ፍትሐዊ የገበያ ውድድርና የሕዝቦች መወናበድ በቃ ሊባል ይገባል፤ ሰላም!።

 መክሊት ወንድወሰን

አዲስ ዘመን ህዳር 12/2016

Recommended For You