የሀገሪቱን ኢኮኖሚ በከፍተኛ ሁኔታ እየጎዱ ካሉ ሕገወጥ ድርጊቶች መካከል ሕገወጥ ንግድ በተለይ የኮንትሮባንድ ንግድ ይጠቀሳል። ይህንንም በሀገሪቱ በኮንትሮባንድ ሲዘዋወሩ እየተያዙ ካሉ ግምታቸው ብዙ ቢሊየን ብር የሚያወጡ ሸቀጦች መረዳት ይቻላል። የግምሩክ ኮሚሽን የቅርብ ጊዜ መረጃ እንዳመለከተው፤ ኮሚሽኑ በ2015 በጀት ዓመት ብቻ 80 ቢሊየን ብር የሚገመቱ የኮንትሮባንድ ሸቀጦችን በቁጥጥር ስር አውሏል። በኮንትሮባንድ ሲዘዋወሩ በቁጥጥር ስር የዋሉ ሸቀጦች ግምታዊ ዋጋ በየዓመቱ እየጨመረ መጥቶ ነው እዚህ ደረጃ ላይ የደረሰው።
የኮንትሮባንድ ንግድ ወደ ሀገር ውስጥም ከሀገር ወደ ውጭ ሀገር የሚደረግ ሕገወጥ ንግድ ነው። ወደ ሀገር ውስጥ በኮንትሮባንድ ከሚገቡት መካከል አልባሳት/ ያገለገሉትን ጨምሮ/፣ የኢንዱስትሪ ምርቶች፣ መድኃኒቶች፣ አደገኛ እጾች፣ ወዘተ. ሲሆኑ፣ በኮንትሮባንድ ከሀገር ከሚወጡት መካከል ደግሞ የቁም እንስሳት፣ ወርቅና የከበሩ ማዕድናት፣ ጫት፣ የሰብል ምርቶች ይገኙበታል።
የኢትዮጵያ ጉምሩክ ባለስልጣን ይህን የኮንትሮባንድ ንግድ ለመከላከልና ለመቆጣጠር አቅሙን አጎልበቶ እየሰራ ይገኛል። ለእዚህም ነው ግምታቸው ብዙ ቢሊየን ብር የሆነ ቁሳቁስን በቁጥጥር ስር እያዋለ የሚገኘው። ተቋሙ ኮንትሮባንድን ለመቆጣጠርና ለመከላከል አቅሙን እያጎለበተ እንደመሆኑ ሁሉ፣ ሕገወጦችም የተለያዩ መንገዶችን በመጠቀም ሕገወጥ ድርጊቱን ማካሄዳቸውን አጠናክረው መቀጠላቸውን እየገለጸ ይገኛል። ይህን የሀገር ችግር ለመፍታት ብቻውን ውጤታማ መሆን እንደማይችል እያስታወቀ፣ መላውን ሕዝብ ጨምሮ ሌሎች ሕገወጥነትን የሚከላከሉ አካላትን ርብርብ እየጠየቀ ይገኛል።
መንግሥት የኮንትሮባንድ ንግድን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያደርገውን ርብርብ በወርቅና መሰል ማዕድናት ሕገወጥ ዝውውርና ፍለጋ በተሰማሩ አካላት ላይም አጠናክሮ መቀጠሉ ይታወቃል። በወርቅ ላይ በተንሰራፈው የኮንትሮባንድ ንግድ የተነሳ ወደ ብሔራዊ ባንክ መግባት የነበረበት የወርቅ ምርት መጠን በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሶ እንደነበር ይታወሳል።
መንግሥት በወርቅ ላይ እየተፈጸመ ያለውን ሕገወጥና የኮንትሮባንድ ንግድ ለመቆጣጠር ካለፈው ዓመት ጀምሮ ግብረ ኃይል አቋቁሞ እየሰራ ነው፤ በዚህም የውጭ ዜጎችን ጨምሮ በርካታ ሕገወጦችን ከእነ ኤግዚብቶቹ በቁጥጥር ስር ማዋል ተችሏል። ሕገወጦቹ በሕግ እየተጠየቁ ሲሆን፣ ከእነዚህ መካከልም ከ100 በላይ የውጭ ሀገር ዜጎች በሕግ እንዲጠይቁና ከሀገር እንዲወጡ መደረጉን በቅርቡ የወጣ የማዕድን ሚኒስቴር መረጃ ጠቁሟል።
በሕገወጥና ኮንትሮባንድ ንግድ ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰበት ያለው ሌላው የሀገሪቱ ምርት ጫት ነው። ከፍተኛ መጠን ያለው የውጭ ምንዛሬ ከሚያስገኙ የግብርና ምርት ጫት በአራተኛ ደረጃ ላይ መቀመጡን መረጃዎች ይጠቁማሉ። ይህ የውጭ ምንዛሬ ምንጭ ነው እንግዲህ የኮንትሮባዲስቶች ሲሳይ የሆነው። በዚህም የተነሳ የሚጠበቅበትን የውጭ ምንዛሬ ማስገኘት እየተሳነው መጥቷል።
በጫት ንግድ ላይ የሚስተዋለው ሕገወጥና የኮንትሮባንድ ንግድ ጫት አምራች አርሶ አደሩን፣ ሕጋዊ የጫት ላኪውን እንዲሁም የሀገሪቷን ኢኮኖሚ በእጅጉ እየጎዳ ስለመሆኑ የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል። ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በቅርቡ በሰጠው መግለጫ በጫት የወጪ ንግድ ላይ የተንሰራፋውን ሕገወጥነትና የኮንትሮባንድ ንግድ ለመከላከል አዲስ የአሰራር ሥርዓት እስከ መዘርጋት ደርሷል።
የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትር አቶ ገብረመስቀል ጫላ በመግለጫው ላይ፤ ባለፉት ዓመታት ከጫት ወጪ ንግድ የሚገኘው የውጭ ምንዛሪ በከፍተኛ መጠን መቀነሱን አስታውቀዋል። እሳቸው እንዳሉት፤ በ2013 በጀት ዓመት የኢትዮጵያ የጫት ወጪ ንግድ 402 ሚሊዮን ዶላር ነበር። ይህ ገቢ በ2014 በጀት ዓመት ወደ 392 ሚሊዮን ዶላር ዝቅ ብሏል። ይህም የ10 ሚሊዮን ዶላር ቅናሽ የታየበት ነበር። በ2015 በጀት ዓመት የጫት የወጪ ንግድ 248 ሚሊዮን ዶላር ብቻ ነው የተገኘው። ይህም ከጫት የወጪ ንግድ የሚገኘው ገቢ ለተከታታይ ዓመታት እየቀነሰ ለመምጣቱ ማሳያ መሆኑን ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።
እሳቸው እንዳሉት፤ ሀገሪቷ በጫት ወጪ ንግድ በተለይም ከ2014 ወደ 2015 በጀት ዓመት 144 ሚሊዮን ዶላር አጥታለች። ከአንድ የጫት ምርት ይህን ያህል ገቢ ማጣት በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ የሚያሳድረው አሉታዊ ተጽዕኖ ከባድና በዘርፉ እየተስተዋለ ያለው ኪሳራም ከፍተኛ ነው። ለችግሩ የተለያዩ ምክንያቶች ተጠቅሰዋል። የጫት ንግድ የሚካሄድበት ምሥራቁ የኢትዮጵያ አካባቢ ሜዳማ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ጫት የጫኑ መኪኖች በየትኛውም አቅጣጫ ማምለጥ ያስችላቸው ሁኔታ መኖሩ አንድ ምክንያት ሆኖ ቀርቧል። ይህም ሕገወጥና የኮንትሮባንድ ንግዱ እየተስፋፋ እንዲመጣ ማድረጉን ተጠቁሟል።
በ2013/14 በጀት ዓመት የኬንያ ጫት ሙሉ ለሙሉ ወደ ሶማሊያ አይገባም ነበር ያሉት ሚኒስትሩ፤ በዚህ ምክንያት የኢትዮጵያ ጫት ገበያውን በብቸኝነት ተቆጣጥሮት እንደነበርና ወቅቱም ከጫት የወጪ ንግድ በከፍተኛ ደረጃ ተጠቃሚ መሆን የተቻለበት እንደነበር ገልጸዋል። ይሁንና በ2015 በጀት ዓመት የኬንያ ጫት ወደ ሶማሊያ መግባት ሲፈቀድለት የኢትዮጵያ ጫት ተወዳዳሪ እንደገጠመው ሚኒስትሩ አስታውቀዋል። ይህን ተከትሎም በርካታ የገበያ ችግሮች መግጠማቸውን ጠቅሰው፣ በተለይ ሕገወጥና የኮንትሮባንድ ንግድ በእጅጉ ፈትኖታል ሲሉ አመልክተዋል። በየአካባቢው የሚገኙ ኬላዎችም እንዲሁ ለጫት የወጪ ንግዱ ማነቆ ሆነው መቆየታቸውን አስታውቀዋል።
ሚኒስትሩ አቶ ገብረመስቀል እንዳስታወቁት፤ ጫት እንደሌሎች የግብርና ምርቶች ውሎ የሚያድርና በጎተራ የሚገባ ምርት አይደለም፤ ከደረሰ መቆረጥ አለበት፤ ከተቆረጠ ደግሞ መሸጥ አለበት። በቶሎ አገልግሎት ላይ መዋል ካልቻለ የመበላሸት ዕድሉ ሰፊ ነው። በዚህ ሳቢያ አርሶ አደሩ የጫት ምርቱን በቅናሽ ዋጋ በቶሎ ለመሸጥ ይገደዳል። በተለይ በ2015 በጀት ዓመት አርሶ አደሩ ያመረተውን ጫት በርካሽ ለመሸጥ ተገዶ ነበር። ነጋዴውም በየቦታው ለሚገጥመው ኬላ ተደጋጋሚና ተደራራቢ ቀረጥ ከፍሎ የሚያሳልፍ መሆኑን ጠቅሰው፣ ከአርሶ አደሩ በርካሽ ገዝቶ ለገበያ ሲያቀርብ እንደነበር ገልጸዋል።
እሳቸው እንዳብራሩት፤ ሌላው የኬንያ ጫት ከኢትዮጵያ ጫት ጋር ሲነጻጸር በዋጋ ቅናሽ ያለው በመሆኑ ከኬንያ ጫት ጋር ተወዳዳሪ መሆን አልቻለም። ይህም የጫት ሕገወጥና የኮንትሮባንድ ንግዱን አስፋፍቶታል። በአሁኑ ወቅት የጫት ሕገወጥና የኮንትሮባንድ ንግድ በእጅጉ እየተስፋፋ መሆኑንም ሚኒስትሩ አመልክተው፣ ከሕገወጥና ኮንትሮባንድ ንግዱ ጋር ተያይዞ በድንበር ከተሞች ጫት በኮታ ይገባ እንደነበርም ገልጸዋል። በቀን 27ሺ ኪሎ ግራም ጫት ወደ ሶማሌ ክልል ይገባ እንደነበርም አስታውሰው፤ በኋላም ወደ 48ሺ ኪሎ ግራም ማሳደግ እንደተቻለ አስታውቀዋል። ሕገወጥና የኮንትሮባንድ የጫት ንግዱን ለቁጥጥር አመቺ ሁኔታ ባለመፈጠሩ ሳቢያ አቅርቦቱ ወደ 17 ሺ ኪሎ ግራም ወርዶ እንደነበርም ገልጸዋል።
ይህ አሰራር በአርሶ አደሩ በኩል ችግር የፈጠረ ሲሆን፤ በተለይም በሶማሊያ በኩል የሚወጣው ጫት ተወዳዳሪ ሆኖ ለመሸጥ አልቻለም። ከዚህ በተጨማሪም የሶማሌ ክልል ጫት መጠን ዝቅ ባለበት ጊዜ የአርሶ አደሩ ጫት ሊሸጥ አልቻለም። ይህም በአርሶ አደሩ ላይ ከፍተኛ ችግር መፍጠሩን ተከትሎ የጫት ኮታው ተነስቷል ያሉት ሚኒስትሩ፤ የኮታ ገደቡ ሲነሳ ጫት የጫኑ መኪኖች በሙሉ የሀገር ውስጥ ጫት ነው በማለት ወደ ሶማሊያ ሲያሻግሩ እንደቆዩና በዚህም የተነሳ ሀገሪቷ ከዘርፉ ተጠቃሚ ሳትሆን መቅረቷን ጠቁመዋል። በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ በጫት የወጪ ንግድ ላይ ተመዝግበው ፈቃድ የወሰዱና የተሰማሩ ጫት ነጋዴዎች ከአራት ሺ 991 አያነሱም ያሉት ሚኒስትሩ፤ በጫት ወጪ ንግድ ፈቃድ አሰጣጥ ላይ ክፍተት እንደነበር አንስተዋል።
እሳቸው እንዳሉት፤ ለወጪና ገቢ ንግድ ፈቃድ መስጠት ያለበት የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ነው። ይሁንና ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የንግዱ ማህበረሰብ እንዳይንገላታና በተለይም በጫት ንግድ ላይ የተሰማራው ነጋዴ ባለበት አካባቢ ሆኖ የወጪ ገቢ ንግድ ፈቃድ ማውጣት እንዲችል ለክልሎች ፈቃድ ሰጥቷል። በመሆኑም ከክልሎች በርካታ ፈቃዶች ተሰጥተዋል። ከክልሎች ባለፈም በወረዳ ደረጃ ሳይቀር የወጪ ገቢ ንግድ ፈቃድ ሲሰጥ መቆየቱን ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በጥናት አረጋግጧል ሲሉ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።
ከተሰጠው ፈቃድ ውስጥም በአዲስ አበባ ከተማ የወረዳ ጽ/ቤቶች ብቻ ከሶስት ሺ በላይ ፈቃዶች መሰጠታቸውን ሚኒስትሩ ጠቅሰው፤ ከእነዚህ ውስጥ ግን የጫት ግብይቱ በተለይም የወጪ ንግዱ እየቀነሰ በመጣበት ጊዜ የነበሩት ላኪዎች ቁጥር አነስተኛ እንደነበር አስታውሰዋል። እሳቸው እንዳሉት፤ በ2014 በጀት ዓመት 680 የሚደርሱ በ2015 በጀት ዓመት ደግሞ ከዛም ያነሱ ላኪዎች ነበሩ። በጥቅሉ ከ1000 የሚያንሱ ጫት ላኪዎች ብቻ ሲልኩ ነበር። ፈቃድ የያዙና በየዓመቱ እያደሱ ያሉ ነጋዴዎች ጫት በሕገወጥ መንገድ እያወጡና በኮንትሮባንድ እየነገዱ ስለመቆየታቸው እነዚህ መረጃዎች ያሳያሉ ብለዋል።
በጫት ወጪ ንግድ ላይ የተስፋፋው ሕገወጥና የኮንትሮባንድ ንግድ ሕጋዊ ነጋዴዎችን ከገበያው እያስወጣ መሆኑንም ነው ሚኒስትሩ ያመለከቱት፤ ከዚህም ባለፈ የኮንትሮባንድ ንግዱ አርሶ አደሩም ሆነ ሀገሪቷ ከዘርፉ ተጠቃሚ እንዳይሆኑ ሲያደርግ ቆይቷል ብለዋል። በጫት ወጪ ንግድ ላይ የተሰማሩ ነጋዴዎች የተቀመጠላቸውን መስፈርት ማሟላት ሲችሉ ብቻ ወደ ሥራው እንደሚገቡ አመልክተው፣ ይህ ካልሆነ ግን የንግድ ፈቃዳቸው እንደሚሰረዝ አስገንዝበዋል።
እሳቸው እንዳሉት፤ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በዘርፉ ያሉትን ችግሮች በመለየት ለችግሮቹ መፍትሔ ያላቸውን አዳዲስ አሰራሮችም ተግባራዊ ለማድረግ ተዘጋጅቷል፤ አሰራሮቹ ጫት የሚልከው ነጋዴ በሕጋዊ መንገድ የንግድ ሥራውን ማካሄድ የሚችልባቸው ናቸው። አዲሱ መስፈርት በሕጋዊ መንገድ ጫት ለመላክ ለሚፈልጉ ነጋዴዎች ከባድ አይደለም። ጫት መነገድ እፈልጋለሁ የሚል ማንኛውም ነጋዴ በንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ቀርቦ በመመዝገብ ፈቃዱን በአዲስ መልክ ማውጣት ይጠበቅበታል።
የጫት ነጋዴዎች በአዲሱ አሰራር ከሚጠበቅባቸው አምስት መስፈርቶች መካከልም የጫት ምርትን ማጓጓዝ የሚችል መሸፈኛ መረብ ያለውና ጂፒኤስ የተገጠመለት ተሽከርካሪ ማቅረብ አንዱ ግዴታቸው ነው፤ አዲስ ፈቃድ ጠያቂ ከሆነ በበጀት ዓመቱ ቢያንስ ከ100 ሜትሪክ ቶን ጫት በላይ ለመላክ ግዴታ ይገባል፤ ነባር ከሆነ ደግሞ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ100 ሜትሪክ ቶን በላይ ጫት ለመላኩ ማረጋገጫ ማቅረብ ይጠበቅበታል። ይህ ነጋዴ በሀገር ውስጥ የጫት ንግድ ሥራ ላይ በማናቸውም ክልሎችና የከተማ መስተዳደሮች የማይሰማራ መሆኑ ከመስፈርቶቹ መካከል የሚጠቀሱ ናቸው።
ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ባዘጋጀው አዲስ የቅድመ ፈቃድ ብቃት መስፈርት መሠረት በዳግም ምዝገባ ተካትተው የጫት ወጪ ንግድ ሥራቸውን ለማከናወንም ፈቃድ ፈላጊዎች እስከ ኅዳር 15 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ መቅረብ ይጠበቅባቸዋል። በተጠቀሰው ወቅት መስፈርቱን አሟልተው ያልቀረቡ ነጋዴዎች ከንግድ ሥርዓቱ የሚወጡና የንግድ ፈቃዳቸውም የሚሰረዝ ይሆናል ሲሉ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።
እስከ አሁን ባለው ሁኔታ በንግድ ፈቃድ ሽፋን በርካታ ሕገወጥ ሥራዎች እየተሰሩ መሆናቸውንም ሚኒስትሩ ተናግረዋል። ሕገወጥ ንግድ እንዲሁም የፈቃድ ኪራይ እየተካሄደ እንደሆነም ጠቅሰው፣ ከእነዚህ በስተጀርባም በርካታ ወንጀሎች ሊሰሩ እንደሚችሉ ገልጸዋል። ሚኒስትሩ እንዳሉት፤ ኬላዎችን በተመለከተም ለጫት ብቻ ሳይሆን ለማንኛውም ወጪ ንግዶች በየአካባቢው የሚገኙ ኬላዎች ክፍት እንዲሆኑ ክትትል ይደረጋል። ሌላው የኢትዮጵያ የጫት ዋጋ ሶማሊያ ወይም ሶማሌ ላንድ እንዲሁም ኬንያ ካለው ዋጋ ጋር ይመጣጠናል ወይስ አይመጣጠንም የሚለው በጥናት ተፈትሾ ምላሽ በመስጠት ተወዳዳሪ መሆን እንዲችል ይሰራል።
የኦፕሬሽን ሥራም በተመሳሳይ በማያዳግም ሁኔታ እንደሚሰራም ሚኒስትሩ አስታውቀዋል። ከዚህ በተጨማሪም ተለይተው ወደሚታወቁ የድንበር ከተሞች የሚሄደው የጫት ኮታ እንደሚወሰን ገልጸው፣ ለሀገር ውስጥ ፍጆታ የሚውለው ጫት ብቻ ተለይቶ ወደ ድንበር ከተሞች ጫት እንዲወጣ ይደረጋል ብለዋል። እነዚህንና መሰል ተግባራትን በማከናወን በጫት ወጪ ንግድ ያጋጠመውን ችግር ለመፍታት ጥረት እንደሚደረግ የገለጹት ሚኒስትሩ፤ በተለይም ከፈቃድ ጋር ተያይዞ በሚፈጸሙ ሕገወጥ ድርጊቶች ላይ በማያዳግም ሁኔታ ርምጃ እንደሚወሰድም አስገንዝበዋል።
የጫት ወጪ ንግድ ሥራ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት በሚያረጋግጥ አግባብ መመራት እንዳለበት የተገለጸ ሲሆን፣ ሀገሪቱም ከጫት ወጪ ንግድ ማግኘት የሚገባትን የውጭ ምንዛሪ ማግኘት እንድትችል የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር እየሠራ መሆኑም ተጠቁሟል። በተለይም በዘርፉ የተንሰራፋውን ሕገወጥና የኮንትሮባንድ ንግድን ለማስቀረት መንግሥት የተለያዩ ርምጃዎችን እየወሰደ መሆኑም ተመላክቷል።
ሕገወጥ ነጋዴዎችን ከግብይት ሥርዓቱ እንዲወጡ በማድረግ ሕጋዊ ነጋዴዎችን ማበረታታት አስፈላጊ መሆኑን ሚኒስቴሩ አስታውቋል። በውድድር ላይ የተመሠረተ፣ የግብይት ተዋናዮችንና ሀገሪቱን ተጠቃሚ የሚያደርግ የግብይት ሥርዓት መዘርጋት ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ እንደሚጠበቅ አስታውቆ፣ ሚኒስቴሩም በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጎ እየሠራ ይገኛል ብሏል።
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ህዳር 12/2016