ለሠላም እድል በመስጠት የጋራ አሸናፊ እንሁን !

ከትዝታ ማስታወሻ

ስለጦርነት አስከፊነት ለማውራት መነሳቴ በጉዳዩ ላይ ባዳ አሊያም ለርዕሰ ነገሩ “እውቀት አጠር ነን” እንሆናለን ከሚል እሳቤ አይደለም። እኛ ኢትዮጵያውያን ለጦርነት ባዳ አይደለንም። ለዘመናት የውጪ ወራሪን ተዋግተን መክተናል። በውስጥ አለመስማማት አያሌ ግዜያት ግንባር ውለን አድረናል።

የረጅም ዘመናችን ትርክት ትልቁ አካል “ጦርነት ነው” ብል ያጋነንኩ ያህል አይሰማኝም። ስለዚህ ስለ ጦርነት አስከፊነት ከሩቅ ሳይሆን ደጃፋችን ደርሶብን በተግባር እናውቀዋለን። ዋናው ችግር ግን በታሪክ ከሰማናቸው የጦርነት አስከፊነት ብሎም በራሳችን አጭር የሕይወት ዘመን ካጋጠመን ጦርነቶች በሚገባው ልክ አለመማራችን ነው። ለዚህ ነው ዛሬም ደግሜ ስለጦርነት አስከፊነት ለማውራት የወደድኩት።

ስለ አውዳሚው ጦርነት ለመገንዘብ፤ ምን እንዳሳጣን ለመረዳት ቀደምት የጦርነት ታሪኮቻችንን ከዶሴዎች ማገላበጥ ላይኖርብን ይችላል። በቀላሉ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም የገባንበት ጦርነትና ያስከፈለን ዋጋ ብቻ መመልከትና ከዚያ መማር በቂ ነው። ይህ በሰሜኑ ክፍል የተካሄደ አውዳሚ ጦርነት ውዱን የሰው ልጅ ሕይወት ከማስከፈል ባሻገር መሠረተ ልማቶቻችንን እንዳልነበር አድርጓቸዋል።

በዚህ ጦርነት ቤተሰብ ተበትኖ ቤት ንብረቱን አጥቶ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ደርሶብናል። ይህ የቅርብ ጊዜ የሀገራችን ታሪክ ነው። ይህ እውነታ ከዚህ ቀደም እንደነበሩት አሉታዊ ጎኖቻችን በታሪክ ዶሴዎች ላይ በጥቁር መዝገብ የሚሰፍር ትዝታችን ነው።

እንደ ሕዝብ ተገደን በገባንበት በዚህ ጦርነት፤ በርካታ ወገኖች ላይመለሱ እችን ዓለም ተሰናብተዋል። በርካቶች ለአካለ ጎዶሎነት ተዳርገዋል፤ በርካቶች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው ለከፋ የሕይወት ፈተና ተዳርገዋል። በጦርነቱ የተፈጠረው የሀገር ስብራትም ለማገገም ጊዜ የሚጠይቅ ነው።

በርካቶች ለሀገራቸው ማገልገል በሚች ሉበት ዕድሜ ላይ በጦርነት የወጣትነት ግዜያቸውና ሕይወታቸውን ገብረዋል። ከራሳቸው አልፎ፤ ለቤተሰባቸውና ለሀገር አጉድለዋል። ሁለት ዓመት በቆየው ጦርነት “የሞተው ወንድምሽ የገደለው ባልሽ ኃዘንሽ ቅጥ አጣ ከቤትሽ አልወጣ” የሚለው ሀገራዊ እንጉርጉሮ በተግባር ታይቷል። በዚህም በርካቶች ደረሰልኝ ያሉትን ልጃቸውን አጥተው በኃዘንም በደጋፊ ማጣትም ልባቸው ተሰብሯል። በርካቶች የራሳቸውንና የቤተሰባቸውን ዕጣ ፋንታ ለመተንበይ የማይችሉበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል።

ይህ ሁሉ አልፎ ጥቅምት 23 ቀን 2015 ዓ.ም በደቡብ አፍሪካ ጆሀንስበርግ በኢትዮጵያ መንግሥትና በሕወሓት መካከል የሰላም ስምምነት ከተፈረመ አንድ ዓመት አስቆጥሯል። ይህንን ተከትሎ የጠፋውን መመለስ ባይቻልም ከጦር መሣሪያ ነፃ የሆነ አካባቢ መፍጠር መቻሉ ትልቅ ስኬት ነው። ሠላም ወረደ ተብሎ የወደመውን ወደ መጠገን፤ በሂደቱ ሁሉም ወገን ተጎጂ ቢሆንም ይበልጥ የተጎዳውን መልሶ ወደ ማቋቋም ተሄዷል። በዚህም እየተመዘገበ ያለው ውጤት ከጥፋቱ ስፋት አንጻር በቂ ነው ባይባልም ተስፋ ሰጭ መሆኑ ግን አጠያያቂ አይደለም።

የሰሜኑ ክፍል የተካሄደውን ጦርነት ይበልጥ ሳይረፍድ መቋጨታችን ይበል የሚያሰኝ ቢሆንም ከነበረው ክፍተትና ግዙፍ ስብራት ግን ይህንን ልንማር ይገባል። እኛ ኢትዮጵያውያን ልዩነቶቻቸውን በኃይል ከመፍታት የተሳሳተ እና በየዘመኑ ዋጋ ሲያስከፍለን ከቆየ ባሕል መውጣት አለመቻላችን ከራሳችን አልፎ ለሌሎች ማስተማሪያ መሆን እስክንችል ድረስ ከፍ ያለ ያልተገባ ዋጋ መክፈላችንን በወፍራሙ ልናሰምርበት ደጋግመን ልንማርበት ይገባል።

አባቶቻችን እንዲህ የሚል ብሂል አላቸው “ስትሄድ የመታህ እንቅፋት ስትመለስ ከደገመህ ጥፋቱ የድንጋዩ ሳይሆን ያንተ ነው” የሚል። ከትናንት ስህተቶችን አለመማር፤ በከፈልናቸው ያልተገቡ ዋጋዎች አለመቆጨታችን የተነሳ፤ በየዘመኑ ደጋግሞ የጦርነት እንቅፋት እየመታን ይገኛል። በዚህ መጥመድ የመያዛችን እውነታ፤ የእርግማን ያህል ጥላ ሆኖ እየተከተለን ይገኛል። ትናንት አውድመን መልሰን የገነባነውን ዛሬ በተመሳሳይ ስህተትና ጦርነት እያወደምነው እንገኛለን።

ዓለም ከመንደርነት ተላቀ ወደሉላዊነት እየተሸጋገረች ባለበት በዚህ ዘመን እኛ ሀገራችንን ለዘመኑ እንድትመጥን ለዜጎቿ ምቹ እንድትሆን ለመሥራት ከመንቀሳቀስ ይልቅ በመንደርተኝነት መንፈስ በማይመጥን አስተሳሰብ ተከብበን እንገኛለን። አንድነታችንን ከማጠናከር ይልቅ ልዩነቶቻችን ላይ በማተኮራችን ምክንያት እሴቶቻችን እየተናዱ ወደ ከፋ ግጭትና ጦርነት እየወሰዱን ይገኛሉ። በብዙ ያልተገባ ዋጋ እየከፈልን ነው።

ከአፈ ሙዝና ከጠብ-መንጃ ይልቅ በጠረጴዛ ዙሪያ ችግርን መፍታት ይገባናል። ይሄ ርምጃችን ዜጎች ከሚሞቱ፣ ከሚፈናቀሉ ያሉ ችግሮችን ቁጭ ብሎ መነጋገር መሸነፍ ሳይሆን መሠልጠን እንደሆነ የሚያስገነዝብ ነው። አለመግባባቶችን፣ የፖለቲካ ልዩነቶችን፣ የታሪክ ተቃርኖዎችን፣ የተዛባ ትርክትን በንግግር መፍታትና ልዩነትን ማጥበብ ሥልጡን አሰተሳሰብ የፖለቲካ ባሕላችን ማድረግ ይገባናል። ለዚህ የሚሆኑ ማኅበረሰባዊ ዝግጁነት መፍጠርም ይኖርብናል።

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሰሞኑን ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ማብራሪያ “ክላሽ አንግበው በየጫካው ላሉ ወንድሞቻችን እባካችሁ ሠላምን ናቅ አናድርጋት፤ ሰላምን እንጠብቃት የምትሻለው እሷ ናት” የሚል መልእክት አስተላልፈዋል።

ይህንን የጠቅላይ ሚኒስትሩን ንግግር በብዙ መንገድ ትርጉም ሰጥቶ በቀናነት መረዳት ይገባል። የመጀመሪያው ጉዳይ “እስካሁን ከገባንባቸው የእርስ በእርስ ግጭቶች ምን አተረፍን፤ ምንስ አጣን?” የሚለው ነው። ከሞት፣ ከሰብዓዊ ሰቆቃ፣ ከድህነት፣ ብዙ ዓመታትን ወደ ኋላ ከመቅረት ውጪ የጎደለብን እንጂ ያተረፍነው የለም። ስለዚህ የሠላምን ዋጋ ልንንቅና ልናጣጥል አይገባም።

አዎ ሠላም ከጦርነት በእጅጉ ይሻላልና ተፋላሚ ወገኖች ከጸብ፣ ከጦርነት፣ ከመናናቅ ሠላምን ማስበለጥ ይገባቸዋል። ሰላምን መምረጥ መሸነፍ ሳይሆን በጋራ ማሸነፍን መምረጥ ነው። ይህ ደግሞ ሀገርና ሕዝብን ካላስፈላጊ ጥፋት መታደግ የሚያስችል ዘመኑን የሚዋጅ የችግሮቻችን ሁሉ መፍቻ ቁልፍ ነው። በመሆኑም ለሰላም እድል በመስጠት የጋራ አሸናፊ ለመሆን ለመሥራት መዘጋጀት ይኖርብናል። ሰላም!

አዲስ ዘመን ህዳር 12/2016

Recommended For You