በሕጻናት ላይ ተስፋ፣ ፍቅርና በጎነትን መዝራት የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት ነው!

የሰው ልጆችን ነገዎች ከሚወስኑ መሠረታዊ እውነታዎች አንዱና ዋነኛው በሕጻናት /ነገን ተረካቢ ትውልዶች/ ላይ ትኩረት ተደርገው የሚሠሩ ሥራዎች እንደሆኑ ይታመናል። ይህንንም ታሳቢ በማድረግም ኅዳር 11 በዓለም አቀፍ ደረጃ የሕጻናት ቀን ተደርጎ እንዲከበር ስምምነት ላይ ተደርሷል ።

የሕጻናት መብቶች ኮንቬንሽን/ስምምነት እና የሕጻናት መብቶች መግለጫ የጸደቀበትን ቀን ለማስታወስ እ.ኤ.አ 1990 ጀምሮ መከበር የጀመረው የዓለም ሕጻናት ቀን፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ34ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ18ኛ ጊዜ “ለዛሬዎቹ ሕጻናት ፍቅርና በጎነትን እናውርስ” በሚል መሪ ቃል ተከብሯል ።

ኢትዮጵያ የሕጻናትን መብቶች በሁለንተናዊ መልኩ ማስከበር የሚያስችል ሕገ-መንግሥታዊ ድንጋጌዎችን ተግባራዊ በማድረግ ተጠቃሽ ሀገር ናት። የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት፣ ሕጻናት በሕግ የተደነገጉና በግልጽ የተጠቀሱ የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ከአዋቂዎች እኩል የመጠቀም መብት እንዳላቸው ይደነግጋል።

በዚህ ረገድ የሕጻናትን መብትን በተለየ ሁኔታ ለመጠበቅ የሚያስችል ድንጋጌም የሕጻናት መብት በሚል በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 36 ላይ አካቷል። በብሔራዊ የሕጻናት ፖሊሲውም፤ የሕጻናት ጉዳይ በማንኛውም ወቅት የቅድሚያ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ መሆኑንና ሁሉም አካላት ይህንን መሠረት ያደረገ ሥራ መሥራት እንዳለባቸው ያሳስባል።

ከዚህም ባለፈ በፍትሐ ብሔር ሕጋችን ሕጻናት በእድሜ ያልበሰሉ እና በቂ ትምህርትም ሆነ የሕይወት ልምምድ የሌላቸው ናቸው ተብሎ ስለሚታመን በሌሎች ሰዎች በመታለል ወይም በሌላ ምክንያት በግል ጥቅማቸው ላይ ጉዳት እንዳይደርስባቸው ልዩ ጥበቃ ይደረግላቸዋል ይላል።

ይህ እንደ ሀገር ለሕጻናት የሰጠነው ትኩረት፤ አንድም እንደ ሀገር ቀጣይ ዕጣ ፈንታችን የሚወሰነው በእነዚህ ሕጻናት ላይ መሆኑን ከመረዳት፤ ከዚያም በላይ እንደ ሕዝብ ተስፋ የምናደርጋቸው ብሩህ ነገዎች በአንድ ትውልድ ተበጅተው የሚያበቁ ሳይሆኑ፤ በአግባቡ በጥንቃቄ በተዘጋጁ ትውልዶች ቅብብሎሽ ላይ የተመሠረተ መሆኑን ከመገንዘብ የመነጨ ነው።

ኢትዮጵያውያን ደግሞ ለሕጻናት ያለን ከሰብዓዊነት የሚመነጭ ርህራሄ መብቶቻቸውን ለማክበር ሆነ ለማስከበር ትልቁ አቅማችን እንደሆነ ይታመናል። ይህ ከመንፈሳዊ፣ ባሕላዊ እና ማኅበራዊ እሴቶቻችን የሚመነጨው ሰብዓዊ ርህራሄ፤ እንደ ቤተሰብ ሆነ እንደ ሀገር ለሕጻናት ልዩ ትኩረት እንድናደርግ አስችሎናል። ይህም በዕለት ተዕለት ሕይወታችን የሚታይ ተጨባጭ እውነታ ነው።

የሕጻናትን ቀን ስናከብርም፤ ይህንን የማኅበራዊ ማንነታችን አንዱ መገለጫ የሆነውን ስለ ሕጻናት ያለንን ሰብዓዊ ርህራሄ አጠናክረን ለመቀጠል ቃል ለመግባት እንጂ፤ በሕጻናቱ ጉዳይ ላይ አዲስ ትርክት ለመፍጠር እና በዚህም ራሳችንን እንደ ማኅበረሰብ ለመግራት አይደለም ።

በተለይም ቀኑን “ለዛሬዎቹ ሕጻናት ፍቅርና በጎነትን እናውርስ” በሚል መሪ ቃል ማክበራችን፤ ሕጻናቱ ከሁሉም በላይ ለራሳቸው ሆነ ለሀገራቸው ጤናማ ትውልድ ሆነው የሚያድጉበትን መልካም ዕድል መፍጠር የሚያስችል ነው። ከትናንት የግጭት ታሪክ ለዘለቄታው መውጣት የሚያስችለንን የመሠረት ድንጋይ የማስቀመጥም ያህል ነው።

ሕጻናቱ ከትናንት ሀገራዊ የግጭት ትርክቶች ወጥተው የራሳቸውን ዕጣ ፈንታ በፍቅርና በበጎነት መገንባት የሚያስችላቸውን አቅም እንዲያጎለብቱ፤ ነገዎቻችንን ብሩህ ለማድረግ የጀመርነው ትግል በትውልዶች ቅብብሎሽ የተሻለ ተስፋ እንዲላበስ የሚያስችል ነው።

በፍቅርና በበጎነት ተኮትኩቶ ያደገ ትውልድ የሀገርና የሕዝብ ተስፋነቱ በብዙ መልኩ ለጥያቄ የሚቀርብ አይደለም። ከዚህ አንጻር እንደ ቤተሰብም ሆነ እንደ ማኅበረሰብና ሕዝብ ተስፋ ያደረግናቸውን ነገዎች ፍጹም በሆነ መተማመን እንዲሳኩ በሕጻናቱ ላይ ተስፋ፣ ፍቅርና በጎነትን መዝራት የሁሉም ዜጋ ሰብዓዊ፣ ማኅበራዊና ሀገራዊ ሀላፊነት ነው!

አዲስ ዘመን ህዳር 12/2016

Recommended For You