ብዙዎች ክንደ ብርቱ ብሎም በአዕም ሮም በሳል መሆናቸውን ይመሰክራሉ። በሥራ ምክንያት ከኢትዮጵያ ያልረገጡት አካባቢ እንደሌለ ይናገራሉ። በምሥራቅ አፍሪካ አገራት ጭምር እየተዘዋወሩ ሰርተዋል። በተለይም ለንግድና ለእርሻ ሥራዎች ትልቅ ፍቅር አላቸው። አልችልም የሚባል ነገርን በሥራ ውስጥ አያውቁም በዚህ ድፍረታቸው ሴትነታቸው ሳይበግራቸው የጦርነት ቀጣ ናዎች ጭምር ገብተው እህል በማጓጓዝ ሥራ ውስጥ ተሳትፈዋል።
አባታቸው ነጋዴ እና የተከበሩ የአገር ሽማግሌ ናቸውና ከእርሳቸው ሁልጊዜም የሚለገሳቸው የትችያለሽ ማበረታቻ በርካታ ሥራዎች ውስጥ እንዲሳተፉ እንደረዳቸው ይመሰክራሉ። ባለታሪካችን ወይዘሮ ሃዲያ መሐመድ ይባላሉ። ውልደትና እድገታቸው በፍ ቅር እና መተሳሰብ ከተማዋ ድሬዳዋ ነው። በልጅነታቸው እናታቸው ስፌት ያሰፏቸው እንደነበር ያስታውሳሉ። ከትምህርት ቤት መልስ ደግሞ ሕንዶች፣ ግሪኮች እና አረቦች ቤት እየሄዱ የተለያዩ የልብስ ጥልፎችን ይለማመዳሉ።
ሲንጀር እና ሳባ የተባሉ ተቋማት ጋር በትርፍ ሰዓታቸው የልብስ ስፌት ሙያን ተለማምደዋል። ለጎረቤቶቻቸው ያማሩ ልብሶችን በማዘጋጀትም ምርቃትን ከአንዳንዶቹ ደግሞ ሁለት እና ሦስት ብሮችን ይሰጣቸው እንደነበር ይናገራሉ። በድሬው ኤኮል ኑተርዳም ትምህርት ቤት እስከ ስምንተኛ ተከታትለው በጥሩ ውጤት አጠናቀቁ።
ከዚያም ከፍተኛ ውጤት በማምጣ ታቸው ወደ አዲስ አበባ አቅንተው ሊሴ ገብረማርያም ትምህርት ቤትን ተቀላቀሉ። በሊሴም ኮሜርስ የተባለውን የሴክሬታሪነት ትምህርት አጠናቀው ወደትውልድ መንደራቸው መመለሳቸው አልቀረም። በሼመንደፈር ወይም የድ ሬዳዋ ባቡር ጣቢያ በሴክሬታሪነት ተቀጠሩ። ሕይወት ግን መንገዷን ቀይ ራለችና ለስድስት ወራት እንደሰሩ በል ጅነታቸው የታጨላቸውን ባል አግብተው ወደ አዲስ አበባ ተመለሱ።
በመዲናዋም የሞሮኮ ኤምባሲ ጸሐ ፊነት ሲወዳደሩ እንግሊዝኛ ትችያለሽ ሲባሉ ጊዜ ባይችሉም «አዎ» ብለው የታይፕ ብቃታቸውን አስመስክረው ይቀጠራሉ። የሚተረ ጎሙ ጽሑፎችን ለባለቤታቸው እያሳዩ ሥራውን በቅጡ ለመዱት። አሁን ሁለት ልጆችንም ወልደዋል። በኤምባሲው ለስድስት ዓመታት ከሰሩ በኋላ ደግሞ በአፍሪካ የመንግሥታቱ ድርጅት የኢኮኖሚ ኮሚሽን (ኢሲኤ) ለሦስት ዓመታት በታይፒስትነት ሰርተዋል።
በወቅቱ ግን ደርግ ወደሥልጣን የመጣበት ጊዜ ነውና ቤተሰባቸው የባላባት ዘር ነው በሚል ወከባ ደረሰባቸው። ባለቤታቸው ተገደሉ። ወይዘሮ ሃዲያም ወደ ኬንያ አመሩ። ቀድሞ በኢሲኤ ሲሰሩ የቀድሞዋ ዛየር ባለሥልጣናት ጋር ግንኙነት ፈጥረው ስለነበር ታይፒስት እንደሚፈልጉ ነግረዋቸዋል። በመሆኑም ቀድመው ኬንያ ለሚገኘው የዛየር ኤምባሲ ጸሐፊ ለመሆን ሁኔታዎችን አመቻችተው ነበር ያቀኑት።
በኤምባሲው ጥቂት ጊዜያት እንደሰሩ ወደተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት መከላከል ቢሮ ተቀጥረው መስራት
ጀመሩ። ፖርቹጋል ድረስ ለስድስት ወራት ቆይተው ሰርተዋል። በኋላ ግን በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም ስር መስራቱን መርጠው ተዘዋወሩ። በዚያው ኬንያ እያሉ ነበር እንግዲህ አንድ በኬንያ ኦሮሞ እና በሶማሌ ድንበር መካከል የተወለዱ ባለሀብት ጋር ተዋውቀው ከኢትዮጵያ ውጪ የተጀመረውን ትዳር የመሰረቱት። ትዳር ደግሞ ወደ ልጅ አመራና ወልደው እስኪያሳድጉ በወሰዱት ፈቃድ የባለቤታቸው የትራንስፖርት ድርጅት ውስጥ መስራት ጀመሩ።
ባለቤታቸው ደግሞ «የቅጥር ሥራ አያዋጣምና የራስሽን ሥራ ጀምሪ» እያሉ መወትወታቸውን ቀጥለዋል። ለሦስት ዓመታት ከሰሩበት የመንግሥታቱ ልማት ፕሮግራም ሥራ ግን መውጣት አልፈለጉም። ምክንያቱም በሥራው ምክንያት የያዙት ፓስፖርት የዓለም አቀፍ ተቋም በመሆኑ ኢትዮጵያ በየጊዜው ገብተው እናታቸውን ጠይቀው የደርግ ሰዎች ሳይነኳቸው በሰላም እንዲንቀሳቀሱ ረድቷቸዋል። ይሁንና የግል ሥራ ነፃነት ያለው መሆኑን በወሊድ እረፍት ጊዜያቸው የተረዱት ወይዘሮ ሀዲያ የባለቤታቸውን ድርጅት በረዳትነት መቆጣጠሩን ቀጠሉ። ሩዋንዳ፣ ቡሩንዲ እና ዩጋንዳ ድረስ በመሄድ የትራንስፖርት ድርጅቱን ሥራ ይመሩ ነበር።
አሁን ደግሞ ንግዱ ውስጥ መሰማራት ፈለጉ። በመሆኑም ከሞያሌ ኬንያ የገዙትን ቆርቆሮ ወደ አዲስ አበባ በመላክ ሥራውን ጀመሩ። ሳሙና ወደ አዲስ አበባ ሲያስገቡ ከአሰብ የሚመጣውን ጨው ደግሞ ወደ ኬንያ በማስገባት ንግዱን አጧጧፉት። በኢትዮጵያ የነበረውን የኢትዮ ሊቢያ ድርጅት እምነበረድ ምርት ወኪል ሆነው ወደ ናይሮቢ ማስገባታቸውን ተያያዙት።
ፈረንሳይ ሄደው የሕንፃ ውስጥ ዲዛይን አጫጭር ትምህርቶችን ቀስመው ሲመለሱ ደግሞ የኮንስትራክሽን ፈቃድ አውጥተው በርካታ የኬንያ ሕንፃዎችን በኢትዮጵያ እምነበረድ ማስዋቡን ተካኑበት። የሀገር ነገር መቼም አይለቅምና በሽግግሩ ወቅት ደግሞ ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ ሥራ መስራት ፈልገዋል። በመሆኑም ለእርዳታ የሚሆን እህል ለማጓጓዝ እንዲቻል መኪናዎችን ከባለቤታቸው ድርጅት ተውሰው ኢትዮጵያ ሞያሌ ቢያቆሙም ሥራውን አይሰሩም ብለው ይከለከላሉ።
በዚህ ጉዳይ እልህ የያዛቸው ወይዘሮ ሀዲያ ታዲያ ሀገሬ ላይ እሰራለሁ ብለው ወደ አዲስ አበባ ገቡ። አዲስ አበባ ላይ ጥቂት እንደቆዩ ግን ጂቲዜድ የተሰኘው የውጭ ድርጅት በ148ሺ የአሜሪካን ዶላር ስደተኞችን ከጠረፍ ወደ ኢትዮጵያ የማጓጓዝ ሥራ ያወጣል። አንድም መኪና እጃቸው ላይ የሌላቸው ወይዘሮ ሃዲያ ታዲያ ኃላፊው ቢሮ ገብተው ፈረንጁን «መኪናዎች አሉኝና ሥራው ይሰጠኝ» ብለው ይጠይቃሉ። «እስኪ ያሉሽን መኪናዎች አሳይን» ሲባሉ ደግሞ በቡና ንግድ የተሰማሩ የእህታቸውን ባል የኪራይ መኪናዎች እንዲያቀርብላቸላውና እርሳቸው ደግሞ 25 በመቶ ከሥራው እንደሚያካፍሉ ይነግሩዋቸዋል።
ሥራውን የማያውቁት የእህታቸው ባል «መኪና ያለው ለገሃር ነው እንጂ እኔ ምን አውቃለሁ» ቢሏቸውም በቀን ስንት ነው የሚከራዩት ቢሉ «250 ብር» ይባላሉ። «እኔ በቀን አንድ ሺ ብር እሰጣቸዋለሁ» ብለው 20 የሕዝብ ማመላለሻ መኪናዎችን እንዲያመጡላቸው ይነጋገራሉ። ለመኪና ሾፌሮቹ ባጅ እና ኮፍያ እንዲሁም ተመሳሳይ ጋዋን አሰርተው ሁሉንም በአንዴ ስታዲየም አካባቢ አቁመው ፈረንጆቹ ሲመጡ እንዲዘጋጁ አደረጉ።
በወቅቱ የተደራጀ የትራንስፖርት አማራጭ ያቀርባሉ ተብለው ያልተጠበቁት ወይዘሮ ፈረንጆቹን በማስገረማቸው 50 በመቶ ክፍያ ተፈጽሞላቸው ወዲያውኑ ሥራው ተሰጣቸው። አንድም መኪና ሳይኖራቸውና የትራንስፖርት ተቋም ሳይከፍቱ የ148ሺ ዶላሩን የስደተኞች ማጓጓዝ ሥራ በ21 ቀናት አጠናቀው በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ወደመሃል አገር አመላለሱ።
ከዚህ በኋላ በመዲናዋ ቢሮ ተከራይተው ከፊያት በብድር የገዟቸውን አምስት ተሽከርካሪዎች እና ከኬንያው ባለቤታቸው የተሰጣቸውን ሁለት ተሽከርካሪዎች ይዘው የትራንስፖርት ድርጅት በኢትዮጵያ ከፈቱ። ከዚያም በመላው ኢትዮጵያ ለእርዳታ የሚሆን እህል በማስገባትና በማድረስ ከሰሜን ጫፍ እስከ ደቡብ እና ኦጋዴንና ጅቡቲ ድረስ ተጉዘዋል። በተለይ በኦጋዴን የጦርነት ቀጣና አካባቢዎች እህሉ በሚዘረፍበት ወቅት ታጣቂዎችን በአካል አግኝተው እኔ እዚህ ድረስ አመጣለሁ እናንተ ከዚያ በኋላ ውሰዱ በማለት ክፍያ እየፈጸሙ ለሚፈለገው አላማ እህሉን ያዋሉ ባለውለታ ናቸው።
በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ወቅት ግን በሁመራ አካባቢ እህል ሲያስገቡ በዘራፊዎች እጅ ይወድቃል። ሰባት ሚሊዮን ኪሳራ ስለደረሰባቸው መኖሪያ ቤታቸውን እስከመሸጥ ደርሰው እንደነበር ያስታውሳሉ። ቀስ በቀስ ግን እያንሰራሩ ሥራቸውን ቀጠሉ። በጎን ግን የተሽከርካሪ ማህበራት ሥራችንን ወሰዱ በማለት በየጊዜው ወቀሳ ያደርሱባቸው ነበር። ከዚህ በኋላ ያሰቡት ወደ ሱፐር ማርኬት ንግዱ መግባት ነው። እናም ስታዲየም አካባቢ የሚገኘውን የመንግሥት ሱፐርማርኬት በ700ሺ ብር ገዝተው ሀዲያ ብለው ሰይመው ሥራ ጀመሩ። እስከአሁን ድረስም በሱፐር ማርኬቱ የተለያዩ ምርቶችን በማቅረብ እየሰሩ ይገኛል።
ጎን ለጎን ደግሞ በእርሻ ሥራም ተሰማርተዋል። በአንድ ወቅት በሆለታ አካባቢ የአበባ እና አትክልት እርሻ ከሕንድ ባለሀብት ጋር ጀምረው አላዋጣ ቢላቸው ጠቅለው ለሕንዱ ሸጠው አለምገና ላይ የአትክልት ኤክስፖርት ሥራ ጀምረው ነበር። ቦታው ግን ለባቡር ሥራ ይፈለጋል በመባሉ አርሲ ላይ ምትክ ተሰጥቷቸው አትክልትና ፍራፍሬ ከልጃቸው ጋር እያለሙ ነው። ትልቁ የግብርና ሥራቸው የነበረው ግን በ1993 ዓ.ም ወለጋ ውስጥ የጀመሩትና 500 ሄክታር ላይ ያረፈው የምርጥ ዘር እርሻ ነው።
ለሦስት ዓመታት እያመረቱ ገዥ በማጣት ቢከስሩበትም በኋላ ላይ ግን ትንሽ ትርፍ መያዙ አልቀረም ነበር። የሆነ ሆኖ የእርሻ ሥራው መዳረሻው ውድመት ነው የሆነው። በዘንድሮ ዓመት በአካባቢው በተነሳው ግጭት ምክንያት ምርጥ ዘሩ እና አብዛኛው ንብረት ወድሞ የ25 ሚሊዮን ብር ጉዳት መድረሱን ነው ወይዘሮ ሃዲያ የሚናገሩት። ጉዳዩ በመንግሥት የተያዘ በመሆኑ አንድ መፍትሄ ይሰጠኛል ብለው እየጠበቁ ይገኛል። በሌላ በኩል የሱፐርማርኬት ንግዳቸው ቢዳከምም አልችልምን የማያውቁት የ68 ዓመቷ ወይዘሮ ግን ንግዳቸውን ቀጥለዋል።
ወይዘሮ ሃዲያ በስማቸው በከፈቱት ሱፐርማርኬት ተገኝተው ይቆጣጠራሉ። በሌላ የኃላፊነት ደረጃ ደግሞ የኢትዮጵያ ሴት ኤክስፖርተሮች ማህበር ፕሬዚዳንት ሆነው እያገለገሉ ይገኛሉ። እንስት ሥራ ፈጣሪዎችን ከማበረታታት ባለፈ ኢትዮጵያን ወክለው በተለያዩ መድረኮች በሚናገሯቸው በፈረንሳይኛ፣እንግሊዝኛ እና አማርኛ ቋንቋዎች አገራቸውን እያስተዋወቁ ነው።
ማንም ሴት መስራት ከቻለች እና ጠንካራ አዕምሮ ካላት ፈተናዎችን ማለፍ ትችላለች የሚሉት ወይዘሮ ሃዲያ በትራንስፖርት፣ በሱፐርማርኬት እና በግብርና ሥራዎች ፈር ቀዳጅ ለመሆን ያደረጉት ጥረት አሁን ላይ በርካታ ሴቶች በዘርፉ እንዲሰማሩ በማድረጉ መደሰታቸውን ነው የሚናገሩት።
እርጅና ቢጫጫነኝም ኪሮሽ እና ዳንቴል ከእጄ እንደማይጠፋ አይተው የሚቀልዱብኝ ሰዎች አሉ የሚሉት ወይዘሮ ሀዲያ፤ ያለሥራ መቀመጥን ይጠየፋሉ። በአጠቃላይ ማንኛውም ሰው ሌት ተቀን ሰርቶ ሙያውን ማሳደግ ከቻለ መለወጡ አይቀርም የሚል ምክራቸውን ይለግሳሉ።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 17/2011
ጌትነት ተስፋማርያም