1ኛ፣2ኛ፣3ኛ፣… ሳተላይት

ኢትዮጵያ ETRSS-02 የሚል ስያሜ የተሰጣትን ሦስተኛዋን የመሬት ምልከታ ሳተላይት በሁለት ዓመታት ውስጥ ለማምጠቅ በዝግጅት ላይ መሆኗን የስፔስ ሳይንስና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት በዚያ ሰሞን ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ)ገልጿል፤ ከዚህ በፊት ወደ ሕዋ የመጠቁት ሳተላይቶች የተቀመጠላቸውን የአገልግሎት ጊዜ በመጨረስ ተልዕኳቸውን በስኬት አጠናቀዋል።

የስፔስ ሳይንስና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አብዲሳ ይልማ፤ ሦስተኛውን ሳተላይት መምጠቅን በተመለከተ መንግሥት የፋይናንስና የኢኮኖሚ አዋጪነት ጥናት ማድረጉን፤ ጥናቱ ከዚህ በፊት ወደ ሕዋ ከመጠቁት ሳተላይቶች ተሞክሮ በመውሰድ የቀጣዩን ሳተላይት መረጃ ከመጠቀም አልፎ ሌሎች ተልዕኮዎችን በግልጽ ማስቀመጡንም አስረድተዋል።

የሳተላይቱን ጨረታ የተመለከተ መረጃ የመንግሥት የኤሌክትሮኒክስ ግዢ ሥርዓት ውስጥ እንዲገባ መደረጉንና በቀጣይ ወራት ዓለም አቀፍ ጨረታ እንደሚወጣ ጠቁመው፤ በታኅሣሥ 2012 ዓ.ም ኢትዮጵያ በታሪኳ የመጀመሪያውን ETRSS-01 የመሬት ምልከታ ሳተላይት ከቻይና የሳተላይት ማስወንጨፊያ ጣቢያ ወደ ሕዋ መላኳን ያወሳሉ። በታኅሣሥ 2013 ዓ.ም ደግሞ ET-Smart-RSS የተሰኘችውን ሁለተኛዋን የመሬት ምልከታ ሳተላይት በተመሳሳይ ከቻይና ወደ ሕዋ አምጥቃለች።

የመጀመሪያዋ የመሬት ምልከታ ሳተላይት በሕዋ ከሁለት ዓመት ከግማሽ እስከ ሦስት ዓመት እንዲሁም ሁለተኛው ሳተላይት ደግሞ ቢያንስ ለአንድ ዓመት እንደምትቆይ በወቅቱ ተገልጾ ነበር። በዚሁ መሠረት ሁለቱ ሳተላይቶች በተቀመጠላቸው ጊዜ የአገልግሎት ጊዜያቸውን አጠናቀው የተሰጣቸውን ተልዕኮ ማሳካታቸውን፤ ETRSS-01 የተሰኘችው ሳተላይት ከተቀመጠላት ጊዜ በላይ ተጨማሪ ዘጠኝ ወራት አገልግሎት መስጠቷን፤ በቀጣይ ሳተላይቶቹን ከአጋር አካላት ጋር በመሆን የማስወገድ ሥራ እንደሚከናወንም የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ገልጸዋል።

ለETRSS-01 ሳተላይት 8 ሚሊዮን ዶላር እና ለ ET-Smart-RSS ሳተላይት 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር ወጪ እንደተደረገባቸውም ፤ ከሳተላይቶቹ የተገኙት መረጃዎች ለግብርና፣ ቱሪዝም፣ መሬት አስተዳደር፣ ተፈጥሮ ሀብት፣ ለአደጋ ስጋት ቅነሳና ሌሎች ሥራዎች በግብአትነት መዋላቸውን፤ ተቋማትም የወሰዷቸውን መረጃዎች ጥናትና ምርምርን ጨምሮ ለተለያዩ ሥራዎቻቸው እየተጠቀሙበት እንደሚገኝ፤ ከሳተላይት ጥራት ያለው መረጃ መቀበል የሚያስችል የብዝሃ ሳተላይት መረጃ መቀበያና መቆጣጠሪያ ጣቢያም በ2015 ዓ.ም ወደ ሥራ መግባቱን፤ ኢትዮጵያ ሳተላይት ማምጠቅን ጨምሮ ሌሎች የስፔስ ሳይንስ ሥራዎች ማከናወን የጀመረችው በቅርብ ዓመታት ውስጥ እንደሆነና ከዚህም አንጻር እየተገኙ ያሉ ውጤት መልካም የሚባሉ መሆናቸውን ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

ሳተላይቶች ለአካባቢ ጥበቃ፣ ለግብርና እና ለከተሞች ልማት እንዲሁም ለሌሎች ተቋማት ሥራ ጠቃሚ የሆኑ የተለያዩ ምስሎችን ልከዋል። ኢትዮጵያ የራሷን ሳተላይት ከማምጠቋ በፊት እነዚህን መረጃዎች ሳተላይት አምጥቀው ፎቶ ከሚያስነሱ ሀገሮች በመግዛት ትጠቀም ነበር። በዚህም ሳቢያ የሳተላይት መረጃውን ለመግዛትም በዓመት 250 ሚሊዮን ብር ስታወጣ የቆየች ሲሆን ይህም ከዓመት ዓመት ይጨምር እንደነበር የዘርፉ ባለሙያዎች ከዓመታት በፊት የተሠራ ጥናትን በመጥቀስ ይናገራሉ።

 አፍሪካ ውስጥ ካሉ ሀገራት በሕዋ ጥናት ናይጄሪያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ አልጄሪያ እና ግብፅ ጥሩ ስም መገንባት የቻሉ ሲሆን ኢትዮጵያ ግን ከእነርሱ አንጻር ገና ጀማሪ ናት። የሕዋ ጥናት በዓለም ላይ በፍጥነት እየዘመኑ ካሉ ዘርፎች መካከል ይጠቀሳል። የሰው ልጅ ስለሚኖርባት ምድር ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት ካለው ፍላጎት ባሻገር ሕዋን አብጠርጥሮ ለማወቅ ጥረት እያደረገ ነው። ለዚህ ደግሞ ሳተላይቶች ዋነኛ መሣሪያዎቹ ናቸው። ከህዋ ላይ በመሆን መሬትን ማሰስ የመሬት ምልከታ ሳተላይት ተግባር ነው። ሳተላይቱ መረጃ ሲሰበስብ ይህ ቀረህ አይባለውም። ከግዙፍ ክንውኖች እስከ ጥቃቅን እንቅስቃሴዎች ይመዘግባል።

እንደ ባለሙያዎች አባባል ሳተላይቱ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ አለው። የአየር ንብረት ለውጥን ለመቆጣጠር፣ የተፈጥሮ አደጋዎች ከመድረሳቸው በፊት አስቀድሞ ለመተንበይ፣ ደኅንነትን ለመጠበቅ እና ለሌላም ይውላል። የአየር ንብረት ለውጥ የመላው ዓለም ስጋት በሆነበት በዚህ ዘመን፤ አንዳች ተፈጥሯዊ አደጋ ከመድረሱ በፊት አስቀድሞ መረጃ ማግኘት የበርካቶችን ሕይወት ለመታደግ ያስችላል።

ለአብነትም በአንድ አካባቢ ያሉ የዛፎችን ቁጥር፣ የአየርንብረት ለውጥ እና ሌሎች መረጃዎች ከተሰበቡ በኋላ እንደ ጎርፍ ያሉ አደጋዎች ከመከሰታቸው በፊት መተንበይ የሚቻልበት ዕድል አለ። ግብርና ቀዳሚ መተዳደሪያ በሆነባቸው እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ሀገራት የቱ አካባቢ ምርታማ ነው? የአየር ንብረት ለውጥ ሊኖር ይችላል? የሚሉ ጥያቄዎች በቀላሉ ለመመለስ የሳተላይት መረጃ አስተማማኝ እና አስፈላጊ ነው።

አንድ የግብርና አካባቢን የሚያሳይ የሳተላይት ፎቶግራፍ ስለ እርሻ መሬቱ፣ ስለ ውሃው፣ ስለ አፈሩ ዝርዝር መረጃ ይሰጣል። መረጃዎቹን በመጠቀም ምርታማ የሆኑ አካባቢዎችን መለየት እና የሚገኘውን የምርት መጠን በትክክል ማወቅም ይቻላል። በተጨማሪም ኢንዱስትሪዎች ሲስፋፉ ፋብሪካዎች የት መገንባት አለባቸው? ለሚለው ጥያቄ ከሳተላይት የሚገኙ መረጃዎች ጠቃሚ ናቸው።

ሳተላይት ማምጠቅ ብዙ ትርጉም እንዳለውና በሳይንስና ቴክኖሎጂ ያደጉ ሀገራት የዕድገት ምስጢርም መነሻው ይህ ነው። ይህ ጅምር ለኢትዮጵያ ዕድገት ትልቅ ትርጉም አለው ይላሉ የዘርፉ ልሒቃን። በዜጎችና ምሁራን ዘንድም አዲስ ነገር ለመፍጠር ትልቅ መነሳሳት ይሆናል። የምትመጥቀው ሳተላይቷ ለከተማ እና ገጠር መሬት አስተዳደር፣ ማኅበራዊ ጉዳዮች፣ ሕዝብ አሰፋፈር፣ ምርጫና ሕዝብ ቆጠራ፣ ለማኅበረሰብ ልማቶችና ተያያዥ ጉዳዮች መረጃ ለመሰብሰብ ትልቅ ድርሻ ይኖራታል። በድንበር አካባቢ የሚስተዋሉ ተላላፊ ወንጀሎች፣ ሕገ ወጥ የመሣሪያ ዝውውርና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን ለመከላከል በሀገሪቱ የሚከናወኑ ታላላቅ የልማት አውታሮችን ለመጠበቅና ከጥቃት ለመከላከልም አበርክቶዋ የጎላ ነው።

ማዕድናት፣ መሬት፣ ውሃና ሌሎች የተፈጥሮ ሀብቶች አጠቃቀም፣ የገጠርና የከተማ መሬት አያያዝና አጠቃቀምና ፍትሃዊ አሠራርን መሠረት ለማስያዝ ብሎም አዳዲስ ፖሊሲዎችን ለማርቀቅም ከሳተላይት የሚገኘው መረጃ የላቀ ሚና አለው። እንደ ዘርፉ ምሁራን ገለፃ፤ አሁን ባለው ጅምር ኢትዮጵያ በስፔስ አስተዳደር ሥርዓት ውስጥ በቀላሉ ትገባለች።

ይህም በዓለም አቀፍ ሕግ ላይ የመወሰንና የመደራደር ሚና ይኖራታል። ኢትዮጵያ የሌሎች ሀገራት መረጃ ስለሚኖራት በመተባበርና በመከባበር እንድትሠራ ያግዛታል። ሉዓላዊ ሀገራትን መብት እንዳይጣስም ሌሎች ሀገራትም በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ እንዳይገቡ ከማገዙ ባሻገር የመደራደር አቅም ስለሚፈጥርላት ተሰሚነቷ ይጨምራል።

ይሁንና ሀገራችን ከ3 እና 4ሺህ ዓመታት በፊት በህዋ ምርምር ዘርፍ የዛሬዎቹን ልዕለ ኃያላን ከፊት ሆና ስትመራ እንደነበር የጥንት ብራና መጽሐፍትና ስንክ ሳሮች ዋቢ ከመሆናቸው ባሻገር ዓለምአቀፉ የአስትሮኖሚ ኅብረት በሀገራችን ልዕልት፣ ንግሥትና ንጉሥ ስም ሕብረ ከዋክብት constellations መሰየሙን ስንቶቻችን ይሆን የምናውቀው!? ስለ ቀደምት ኢትዮጵያውያን የሥነ – ፈለክ (የሕዋ) እውቀትና በዘመን አቆጣጠር ምን ያህል የተራቀቁ እንደነበሩ በማስረጃ የሚተነትነው የሮዳስ ታደሰና ጌትነት ፈለቀ (ሁሉም ፒ ኤች ዲ ሠርተዋል)::

በጋራ በደረሱቱ ፤ «አንድሮሜዳ» መጽሐፍ 5ኛ ዕትም ላይ ፤«… ከጥንት ጀምሮ እስከ ዛሬ ያሉ የውጭው ዓለም ታሪክ ጸሐፊዎች …’ ጥንታዊ ዘር ‘ በመባል የምትታወቀውን ኢትዮጵያን … አውሮፓና እስያ ባልሠለጠኑበት ዘመን …ፍልስፍና፣ ሥነ ጽሑፍ ፣ ሒሳብ ፣ ግብርና፣ ሕክምና፣ የክዋክብት ጥናት …የኢትዮጵያውያን ነባር ሀገር በቀል እውቀቶች እንደነበሩ ተናግረዋል::… » ይህ ቀደምት ኢትዮጵያውያን ለሥነ ፈለክ የማይናወጥ መሠረት እንደነበራቸው ያረጋግጣል::

በሌላ በኩል ኢትዮጵያ የጥንት ሥልጣኔ ባለቤት መሆኗን እና ለሥነ – ፈለክ ምርምር ወረት፣ መነሻ እንደነበራት የሚያረጋግጡ የቀደምት ሊቃውንት እማኝነት ከፍ ሲል በተገለፀው መጽሐፍ እንደሚከተለው ተዘግቧል:: «60 ዓመት ቅድመ ልደት ክርስቶስ የነበረው ዲዎዶርስ ሴኩለስ የተባለ የታሪክ ሊቅ ‘ አውሮፓውያን ኋላ ቀር እድገት አኗኗር ላይ በነበሩበት ወቅት ኢትዮጵያ ታላቅ ሥልጣኔ ላይ የነበረች …ኢትዮጵያውያን ለግብጻውያን ሥልጣኔ ያስጀመሩና እስከ ሕንድ ድረስ የገዙ ናቸው::

‘ … በ700 ዓ.ም የነበረው የቤዛንታይኑ እስቲፋንስ ባካሄደው ጥልቅ ጥናት ‘ ኢትዮጵያ መሬታችን ላይ የተመሰረተች የመጀመሪያ ሀገር ናት ‘ ሲል አርኖልድ ኸርማን ሉድዊግ የተባለ የጀርመናዊ የታሪክ ፀሐፊ ደግሞ ‘ ኢትዮጵያን የመሰለ ጥንታዊ ሀገር ወዴት ይገኛል!? ‘ ሲል ይሞግታል … ከ800 ዓመት ክርስቶስ ልደት በፊት የኖረው ሆሜር አሊያድና እና ኦዲሴይ በተባሉ ዘመን ተሻጋሪ ሥራዎቹ ኢትዮጵያውያን ‘ እስከ መሬት ጫፍ ድረስ የሚኖሩና ከአምላክ ጋር ቅርበት ያላቸው ‘ በማለት ይገልጻቸዋል::

የታሪክ አባት በመባል የሚታወቀው ሔሮዶቶስ ኢትዮጵያውያንን ‘ከሰሐራ በታች የሚኖሩ፣ ጥቁር ቆዳ ያላቸው …ብልሆች፣ በዓላቶቻቸውና ሀሴታቸውም ሳይቀር አማልክትን ስለሚያስደስት የአማልክት አምላክ እየሄደ በዓላቱን በደስታ አብሯቸው ያሳልፋል ‘ ብሏል:: …ዲዮዶር የተባለ የሮም ፀሐፊ ደግሞ ‘ከግብፅ በፊት ሥልጡንና ገናና ነበረች:: ግብፅን ቀኝ ገዝታ 18 የኢትዮጵያ ነገሥታት ተፈራርቀውባታል:: …’ ይላል::

«መጽሐፉ ሀገራችን የጥንታዊ ሥልጣኔ ባለቤት መሆኗን በአደባባይ ካስመሰከረ በኋላ በዓለምአቀፉ የአስትሮኖሚ ሕብረት የተሰጣትን ቦታ ይተነትናል :: “…ሕብረ ከዋክብት constellations ማለት በሰማይ ላይ የሆነ ዓይነት ቅርፅ የሚሠራ የከዋክብት ስብስብ ሲሆን ቅርጹም ከማይቶሎጂ ጋር በተያያዘ መልኩ የሰው፣ የእንስሳት ወይም ሕይወት የሌለው ነገር ሆኖ ሊገለጽ ይችላል::…ዓለምአቀፉ የአስትሮኖሚ ሕብረት በ1930 ዓ.ም ከ88 ሕብራተ ከዋክብት ውስጥ ሦስቱን ማለትም አንድሮሜዳን ፣ ካሲዮፕያንና ሴፌውስን በኢትዮጵያውያን ስም መዝግቧል:: … አንድሮሜዳ የኢትዮጵያ ልዕልት ስትሆን ፤ ካሲዮፕያን ደግሞ የኢትዮጵያ ንግሥት ናት:: ሴፌውስ ደግሞ የኢትዮጵያ ንጉሥ ነው :: …»

ለሥነ ፈለክ አርፋጅም ፣ ኮራጅም አይደለንም:: አልፋ ነን:: ለ4 ሺህ ዓመታት ተዳፍኖ የነበርን ፍም በETRSS – 1 ሳታላይት እፍ ብለን አፈገግነው እንጂ:: ከፍ ብለን እንደተመለከትነው በህዋ ጥበብ ፣ እውቀት ከበኩራን ተርታ ተሰላፊ ነበርን:: ለእልፍ አእላፍ ዓመታት የተጠናወተን አፍርሶ ከዜሮ የመጀመር አባዜ ብኩርናችንን ቢያስነጥቀንም:: የአክሱም ሐውልት ፣ የላሊበላ ወቅር አብያተ ክርስቲያናት ፣ የፋሲል ግንብ ፣ የጥያ ትክል ድንጋዮች ሳያፈርሱ እንዴት እንዳቆዩን ይገርመኛል:: ከሦስት አመት በፊት ወደ መጠቀችው ሳታላይት ስንመለስ ከዚያ ባለ ብዙ ገድላት የእነ ሴፌውስ ትውልድ ጋር ድልድይ ሆና እንደገና ታገናኛለች:: መንኮራኮር ሆናም በምናብ በምልሰት flash back 4ሺህ ዓመት ወደ ኋላ ትወስደናለች::

ሻሎም ! አሜን ።

 በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)fenote1971@gmail.com

አዲስ ዘመን ህዳር 11/2016

Recommended For You