ሀገር በቀል የፈጠራ ሥራዎችን መደገፍለተሻለች ሀገር ግንባታ

 ለዚህ ጽሑፍ መነሻ የሆነኝ ከ50 አመት በላይ ያስቆጠረ ታሪክ ነው፡፡ ጊዜው በ1960 ዓ.ም ሲሆን በንጉሠ ነገሥት አጼ ኃይለሥላሴ የንግሥና ዘመን ላይ የሆነ ነው፡፡ በወቅቱ የተለያዩ ተማሪዎች የሁለተኛ ደረጃና የኮሌጅ ትምህርታቸውን ሲያጠናቅቁ ለተሻለ ትምህርት ወደ ተለያዩ የውጭ ሀገራት የሚላኩበት ጊዜ ነበር፡፡

ወደ ውጭ የተላኩ ተማሪዎችም ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁ ወደ ሀገራቸው በመመለስ በተለያዩ ኃላፊነቶች ላይ ተሰማርተው ያገለግላሉ፡፡ በጊዜው ወደ ውጭ ሀገር ሄደው በኤሌክትሪካል ምህንድስና ትምህርት ተከታትሎ የመጣው የ25 አመት ወጣት ኢንጅነር ተረፈ ራስወርቅ ተጠቃሽ ነው።

ወጣቱ ኢንጅነር እንደመጣ፤ በኢትዮጵያ ቴሌኮሚኒኬሽን ቦርድ በሚባለው በአሁኑ ቴሌ- ኮም ተቋም ውስጥ የትራንስሚሽንና የረጅም ርቀት ስርጭት የሥራ ክፍል ውስ ጥ ተመድቦ መ ሥራት ይጀምራል፡፡

በጊዜው ፋክስ ባለመኖሩ የተለያዩ የመልዕክት ልውውጦች የሚደረጉት በቴሌግራፍ ነበር፡፡ እነዚህ የቴሌግራፍ መልዕክቶች የሚደረጉት በላቲን ፊደል ነበር፡፡ ወጣቱ ኢንጅነርም ሥራውን ከጀመረ በኋላ የራሷ ቋንቋ ያላት የራሷ ፊደል ያላት ሀገር በላቲን ፊደል መጠቀሟ ልክ ሆኖ አላገኘውም ፡፡

ለምን የራሳችንን ፊደል አንጠቀምም ብሎ በጠየቀበት ጊዜ ያገኘው ምላሽ ቴሌፕሪንተሩ የተፈጠረው ለላቲን ፊደል ነው የሚለው ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ፊደላት ብዙ ስለሆኑ መቼም የማይቻል ስለሆነ ይህንኑ ብንጠቀም ይሻላል የሚል ተስፋ አስቆራጭ ምላሽ ነበር የተሰጠው ፡፡

ወጣቱ ኢንጅነር ግን አይቻልም የሚለውን ምላሽ ተቀብለሎ የሚቀመጥ አልሆነም፡፡ ከዚያ ይልቅ የኢትዮጵያ ፊደላትን የያዘ ቴሌፕሪንተርን ለመሥራት ፊደላቱ ላይ ልዩ ጥናት ማድረግ ጀመረ፡፡ የፊደላቱን ንድፍ በወረቀት ላይ አውጥቶ ሲጨርስ ይህንን ለሚሠራ ሲመንስ ለተባለ የጀርመን ኩባንያ ልኮ እንዲሠራ አደረገ፡፡

ከዚያም በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የአማርኛ ቴሌፕሪንተር በኢትዮጵያዊው ኢንጅነር ተረፈ ራስወርቅ ተሠራ፡፡ ለሙከራ እንዲሆንም አራት ቴሌፕሪንተሮች ወደ ኢትዮጵያ ተሠርተው ሲመጡ ለስሪታቸው የኢትዮጵያ መንግሥት አንድም የገንዘብ ድጋፍ አላደረገም ነበር፡፡

ይህንን ጉዳይ ያለ ነገር አላነሳነውም ምክንያቱም ኢንጅነሩ መጀመሪያ ሃሳቡ በውስጡ ሲውጠነጠን፤ ከዚያም የእንስራው ጥያቄውን ሲያቀርብ የተቀበለው አልነበረም፡፡ እሠራዋለሁ ብሎ ሲነሳም ውጤቱ እስከሚወታቅ ድረስ የደገፈው ሰው አልነበረም ፡፡

ወጣቱ ኢንጅነር በወቅቱ ጥያቄው የላቲን ፊደልን በዚህ መልኩ መሥራት ከተቻለ ለምን አማርኛን አንችልም የሚል ነበር፡፡ የቴሌፕሪንተሩን በመሥራቱ የአማርኛ ቋንቋን ብቻ ሳይሆን ትግርኛ፣ ኦሮምኛ ሌሎች የሀገራችን ቋንቋዎች በፕሪንተሩ መጠቀም እንዲቻል አድርጓል፡፡

ኢንጅነር ተረፈ ራስወርቅ ለሠሩት ለዚህ ትልቅ የፈጠራ ውጤት ከንጉሠ ነገሥቱና ከጥቂት አካላት በስተቀር እውቅና የሰጣቸው አልነበረም፡፡ ያም ሆኖ ግን በይቻላል መንፈስ የሄዱበት መንገድ እስከዛሬ የችግሩ መፍትሄ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል።

ሀገር በቀል ለሆኑ የፈጠራ ሥራዎች ውጤት እውቅና በመስጠት እና በማበረታታት በኩል የሌሎች ሀገራትን ልምድ ስንመለከት ጃፓን እና ቻይና ዜጎቻቸው ለሚያመጧቸው የፈጠራ ሥራዎች እውቅና ይሰጣሉ፣ ያበረታታሉ፣ የተለያዩ ድጋፎችን ያደርጋሉ፡፡

ከማበረታታትም ባሻገር ዜጎቻቸውን ከልጅነታቸው ጀምሮ በዚህ ታንጸው እንዲያድጉ የተለያዩ የልህቀት ማዕከላትን ገንብተዋል፡፡ በዚህም ራሳቸውን በቴክኖሎጂም ሆነ በሌሎች ፈጠራዎች ያደጉና ምሳሌ መሆን የቻሉ ናቸው፡፡

ወጣቶች ከአካባቢያቸው ጋር ቶሎ የሚላመዱ እና በሃሳብም በጉልበትም ንቁ የሆኑ ናቸው፡፡ ለሀገር ትልቅ ሀብት ሲሆኑ የተለያዩ ችግሮችን መፍታት የሚችሉና የሀገራቸውን ቀጣይ ዕድልም ጭምር የመወሰን ሥልጣን አላቸው፡፡ ታዲያ እነዚህን የሀገር ሀብቶች የሚሰማሩበትን መንገድ መመርመር እና የራሳቸውን ዐሻራ እንዲያኖሩ ማድረግ ይገባል፡፡

በሀገራችን ያሉ በተለያዩ የፈጠራ ሥራዎች ላይ የተሰማሩ ወጣቶች፣ የሥራ ፈጣሪዎችና ባለሙያዎች የሚያነሱት ችግር የሥራ ፈጣሪዎችን ለመደገፍ እንደ ሀገር የሚበጀተው በጀት ዝቅተኛ መሆኑን ነው።

የሥራ ፈጣሪዎች በሃሳባቸው ያለውን ሥራ ወደ መሬት አውርደው ውጤታማና ችግር ፈቺ መሆኑን አረጋግጠው ወደ ገበያው ለማስገባት ሲጥሩ የገንዘብ እጥረት እያጋጠማቸው ስለመሆኑም በተጨማሪነት ያነሳሉ፡፡

ሀገር በቀል የሆኑ የፈጠራ ሥራዎችን ማበረታታት እና ውጤታማ እንዲሁ ማድረግ አለመቻል፤ ሀገር ከውጭ የምታስገባቸው ምርቶች እንዲጨምሩ፤ የራሷን አቅሞች በአግባቡ እንዳትጠቀም ተግዳሮት የሚሆን ነው። ይህ ደግሞ የማደግ ራእዪን ጭምር የሚፈታተን ነው ፡፡

መንግሥት በዚህ ረገድ በተለያዩ ጊዜያት እየሠራቸው ያሉ ሥራዎች የሚበረታቱ ቢሆንም አሁንም በቂ ነው የሚያስብል ደረጃ ላይ የደረሰ አይደለም። በዘርፉ ገና ብዙ መሥራት የሚጠይቅ ነው። በተለይም የወጣቶችን የፈጠራ አቅም በማጎልበት ረገድ የተቀናጀ ሥራ መሥራት ያስፈልጋል።

ለወጣት የሥራ ፈጣሪዎች ወርክሾፖችን በተገቢው መንገድ ከማደራጀት ጀምሮ፤ ሙያዊ ድጋፍ ማድረግን፤ የማበረታቻ ሥርዓት መዘርጋትን፤ ከዛም ባለፈ ጉዳዩን ከሀገራዊ የልማት ፖሊሲዎች ጋር በማስተሳሰር ከፍ ያለ ትኩረት የሚያገኙበትን መንገድ መቀየስ ወሳኝ ነው፡፡

የቴክኒክና ሙያ ልህቀት ማዕከላትን መገንባትና ማጠናከር፣ በተለያዩ የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚሠሩ የፈጠራ ሥራዎችና ጥናቶችን ወደ ትግበራ ማምጣት፣ ተማሪዎች የሚሠሩትን የፈጠራ ሥራ ተግባራዊ የሚደረጉበት ሥርዓት መዘርጋት ይገባል፡፡

የፈጠራ ሥራ ለሚሠሩ ወጣቶች እውቅና መስጠት (ሀገራዊ የእውቅና ሥርዓት መዘርጋት) ማበረታታት እና ወጣቶች በቀጥታ ከኢንዱስትሪዎች ጋር የሚተሳሰሩበትን መንገድ መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ ይህን ለነገ የማይባል ሥራ ዛሬ ላይ መሥራት ከጀመርን ነገዎቻችን በዛሬ የተሣሉ ብሩህ ስለመሆናቸው ደፍሮ መናገር ይቻላል !።

ሰሚራ በርሀ

አዲስ ዘመን ኅዳር 11 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You