የሕዝቦች ምክክር ለዘላቂ ሰላም!

 ምክክር የችግሮች መፍቻ አንዱ ቁልፍ ነው፡፡ ሰዎች በርስ በርስ መስተጋብራቸው በመልካምም፣ በክፉም ሊወሳ የሚችል ሁነትና ሁኔታዎችን ይፈጥራሉ፡፡ እነዚህ በመልካምም በክፉም የሚወሱ ሁነትና ሁኔታዎች ደግሞ የአሁናዊውን ብቻም ሳይሆን የቀጣይ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ሌሎችም መስተጋብሮቻቸው ላይ በአዎንታዊም፣ በአሉታዊም የሚገለጹና የሚንጸባረቁ ጉዳዮችን/አጀንዳዎችን ማሳረፋቸው አይቀሬ ነው፡፡

እነዚህ እንደየ ሁኔታው የሚከሰቱ አሉታዊም ሆኑ አዎንታዊ ጉዳዮች ታዲያ፤ ሰዎች በትናንት ታሪካቸው፤ በዛሬ ኑረታቸው አልያም በነገ የአብሮነት ጉዟቸው ላይ የሚያሳድሩት ተጽዕኖ በዚያው ልክ የሚገለጽ ነው፡፡ ምክንያቱም በመስተጋብሮቻቸው ወቅት የፈጠሯቸው አዎንታዊ ነገሮች በዛሬውም ሆነ በነገው የአብሮነት ጉዟቸው የትብብር አቅም የሚፈጥሩላቸውን ያህል፤ በመስተጋብሮቻቸው ምክንያት የፈጠሯቸው አሉታዊ ክስተቶች በዛሬው መገኘታቸውም ሆነ በነገ የአብሮነት ጉዟቸው ላይ ትልቅ እንቅፋት መሆናቸው አይቀሬ ነው፡፡

ለዚህም ነው የሰው ልጆች በትናንት ተረካቸው፤ በዛሬ ንግግራቸው፤ በነገ ትልምና ሕልማቸው መካከል ለሚታዩ ጉዳዮች ቁጭ ብለው ሲመክሩ፤ መልካሙን አጽንተው እኩይ የተባለውን አቅንተውና አጽድተው ዘመናትን ሲሻገሩ የኖሩት፡፡ ይሄ ደግሞ በግለሰቦች መካከል ለሚኖር መስተጋብር ብቻ የሚወሳ ጉዳይ አይደለም፡፡ ይልቁንም በቡድኖች፣ በማኅበረሰቦች፣ ብሎም በሀገር ደረጃ ሊኖርም፤ ሊገለጽም የሚችል ነው፡፡

በቤተሰብ ደረጃ የሚኖር ግንኙነት የሚፈጥረው መልካምም መጥፎም አጋጣሚ ደስታውም መከፋቱም የሚታየው በተመሳሳይ በሚኖር መስተጋብር ውስጥ ነው፡፡ እናም ቤተሰብ ውስጥ መጠራጠር፣ ቂምና ጥላቻ ብሎም ጠብና መለያየት እንዳይፈጠር፣ በሚያለያዩና በሚያቀያይሙ ጉዳዮች ላይ ቁጭ ብሎ በመነጋገር በይቅርታና እርቅ ይቋጫሉ፡፡ በፍቅርና ሰላም ይፈታሉ፡፡ ይሄ ሲሆን በመተማመን ላይ የተመሠረተ ቤተሰባዊ ኅብረት ይጸናል፡፡

በጉረቤትም፣ በአካባቢም በማኅበረሰብ ደረጃም የሚኖሩ መሰል መስተጋብሮች የጋራ ደስታንም፤ የጋራ ቂምና ቂርሾንም ሊፈጥሩ የሚችሉ እንደመሆናቸው፤ እነዚህ ቂምና ቁርሾዎች በዛሬው አኗኗራቸው፣ በነገው መንገዳቸው ላይ እንከን እንዳይሆን፤ በሽምግልናው መድረክ ቁጭ ብለው ይመክራሉ፡፡ ይወቃቀሱና ይቅር ተባብለው ይታረቃሉ፡፡ እናም በንጹህ ልብ፤ በፍጹም ኅብረት ዛሬያቸውን እየኖሩ፤ ወደ ነጋቸው በጠነከረ ኅብረት ይራመዳሉ፡፡

በአንድ ሀገር የሚኖሩ ሕዝቦችም እንዲሁ ናቸው፡፡ በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ የበዛ ማንነትን አቅፈው በያዙ ሀገራት ጉዳዩ ከፍ ብሎ የሚታይ ነው፡፡ ምክንያቱም በበዛ ማንነት ውስጥ የበዛ ባህልና ቋንቋ ብቻ ሳይሆን፤ የበዛ ፍላጎትና አለመግባባትም እንደሚኖር ይጠበቃል፡፡ ይሄ የበዛ ፍላጎት ደግሞ የሚፈጥረው የጥቅም ግጭት፤ የፍላጎት አለመጣጣም፤ የሃሳብና ዕይታ ልዩነት ይኖራል፡፡

ኢትዮጵያውያን በኅብረት ቆመው የጻፏቸው ዘመን ተሻጋሪ የአብሮነት ድንቅ እሴቶች የመኖራቸውን ያህል፤ በበዛው ማንነት ውስጥ በሚፈጠሩ የፍላጎት መንገዶች ምክንያት እዚህም እዚያም የተከሰቱ አለመግባባቶችና ግጭቶች መኖራቸው የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡ ሆኖም ከሚያቀያይሙት ይልቅ የሚያፋቅሩት፤ ከሚያለያዩት ይልቅ የሚያስተሳስሩት ጉዳዮች ገዝፈውና ጠንክረው በመገለጣቸው እነዚህ ጥቃቅን የቅያሜ አጀንዳዎች ከአብሮነት ሰገነታቸው ሳያወርዱ ዛሬ ላይ አድርሰዋቸዋል፡፡

ይሁን እንጂ እነዚህ ጥቃቅን ችግሮች በየጊዜውና በየዘመኑ እየታዩና እየተለዩ እልባት ስላልተሰጣቸው ብሎም እየተመከረባቸው ሁሉም ድርሻውን ወስዶ በይቅርታና እርቅ ባለመቋጨታቸው፤ ትልሹ ትልቅ እየሆነ በሕዝቦች መካከል ጥርጣሬን፣ ቂምና ቁርሾን እያረገዘ ጉዳት አስከትሏል፡፡

ይሄ ደግሞ የሕዝቦችን አብሮነት፣ የሀገርን ሁለንተናዊ ከፍታና ብልጽግና በማይፈልጉ አካላት እየተጠለፈ በሕዝቦች መካከል የበለጠ የመጠራጠር ብቻ ሳይሆን የተበዳይነትና የበቀልተኝነት መንፈስ እንዲሰፍን እየተሠራበት ይገኛል፡፡ ይሄም የበለጠ ችግሩን የሚያጎላ፤ ሕዝቦች የኖረ አብሮነትና ሕብር የደመቀው አንድነታቸው እንዲፈተን ያደርጋል፡፡

ለዚህም ነው ዛሬ ላይ ሕዝብን እንደ መሸሸጊያ እየተጠቀሙ እኩይ ዓላማቸውን ለማሳካት የሚውተረተሩ ኃይሎች እዚህም እዚያም ሰላምን ሲያደፈርሱ ማየት የተለመደው፡፡

ይሄ ችግር ደግሞ በጊዜ ካልተቋጨና ካልተገታ ለዜጎችም፣ ለሀገርም ትልቅ በሽታ ነው፡፡ ይሄ በሽታ ደግሞ ሕዝብን እንደ ሕዝብ፣ ሀገርንም እንደ ሀገር ሉዓላዊነትንም የሚገዳደር፤ አንድነትንና አብሮነትን የሚንድ ነው፡፡ ይሄ እንዳይሆንም ነው ዛሬ ላይ ዜጎች በችግሮቻቸው ላይ በግልጽ መክረው፤ በይቅርታና እርቅም ቋጭተው ከዛሬው ያለፈውን ነጋቸውን ብሩህ እንዲያደርጉ ለማስቻል ሀገራዊ ምክክር እንዲደረግ መንገዱ የተጀመረው፡፡

ይሄ ሀገራዊ ምክክር ደግሞ የተወሰኑ ቡድኖች አልያም የተወሰኑ ኃይሎች ብቻ ተገናኝተው የሚመክሩበት፤ በብዙሃኑ ፈንታ የራሳቸውን ጥቅምና ፍላጎት የሚያስፈጽሙበት አይደለም፡፡ ይልቁንም ገለልተኛ ተቋም ተቋቁሞ ዜጎች ያለ ልዩነት የሚሳተፉበት፤ ያለ ተጽዕኖ ሃሳባቸውን የሚያራምዱበት፤ ያለ መሸማቀቅ ለይቅርታና እርቅ ራሳቸውን የሚያዘጋጁበት፤ ይሄንኑም የሚያደርጉበት ነው፡፡

ይሄን እውን ለማድረግም የሕዝቦች መድረክ እየተዘጋጁ ሕዝቦች በጋራ እንዲወያዩ፤ ችግሮቻቸውን፣ ስሜቶቻቸውን፣ ቅሬታና መጎዳታቸውን ብቻ ሳይሆን፤ ከዚህ ችግር የመውጫ መንገዳቸውን አንስተው እንዲወያዩ እየተደረገ ነው፡፡ ይሄ ደግሞ እንደ ሀገር የገጠመንን ችግር ለመሻገር የሚያስችል ብቻ ሳይሆን፤ በቀጣይም የሚገጥሙንና ሊገጥሙን የሚችሉ እክሎችን በጽናት ማለፍ የሚያስችል አቅም ስለሆነ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል!

አዲስ ዘመን ኅዳር 11 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You