«ኢትዮጵያ ጥንታዊ የሆነ የዲፕሎማሲ ታሪክ ያላት ሀገር ነች»-ኤመሬትስ ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ

ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲ ረጅም ታሪክ ያላት ሀገር ነች፡፡ በጥንታዊ፣ በመካከለኛው እንዲሁም በዘመናዊ የዲፕሎማሲ ታሪኳም በየዘመኑ በነበሩ መሪዎች የተለያዩ ሥራዎች ተሰርተዋል፡፡ ይህ የዲፕሎማሲ ታሪክም ዛሬ ድረስ ቀጥሏል፡፡ ለመሆኑ ኢትዮጵያ ከድሮ እስከ ዘንድሮ በዲፕሎማሲ ረገድ ያላት ታሪክ እንዴት ይታያል ስንል በታሪክ ምርምር ዘርፍ ስመጥር የሆኑትን ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴን አነጋግረናል፡፡ መልካም ንባብ፡፡

አዲስ ዘመን፤ ከጥንት ጀምሮ ኢትዮጵያ ከሀገራት ጋር የነበራት የዲፕሎማሲ ግንኙነት ታሪክ ምን ይመስላል?

ፕሮፌሰር ባህሩ፤ የኢትዮጵያ የጥንት መገለጫ የአክሱም መንግሥት ሲሆን፣ የውጭ ግንኙነቱም በንግድና በኃይማኖት ላይ የተመሰረተ ነው። አክሱም ከዓለም ጋር በጣም ሰፊ የሆነ የንግድ ግንኙነት ነበራት። በተለይም ከሜዲትራኒያን ዓለም ጋር በጊዜው ሰፊ የንግድ ልውውጦች እንደነበሩ የታሪክ ሰነዶች ያሳያሉ፡፡

በወቅቱም በዓለም ውስጥ ዝነኛ ወይንም እውቅና ካላቸው ወደቦች መካከል አንዱ የሆነው አዶሊስ ወደብ ነበር፡፡ በተለይም አንድ በተጓዥ መልኩ የተጻፈ ዘገባ በዝርዝር እንደገለጸው ብዙ ሸቀጦች እንደሚገቡና በዚያውም ልክ ይወጡ እንደነበር። የንግድ ግንኙነቱ የኋላ የኋላ ደግሞ ለኃይማኖት ግንኙነት መሠረት ሆነ፡፡

በዚሁ መሠረት በኢዛና ዘመን፤ ከመካከለኛው ምሥራቅ ወይንም ከሜዲትራንያን የመጡ ሰዎች ንጉሱንም ቤተሰቡንም አጥምቀው የክርስትና ኃይማኖት በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ሊመሰረት ቻለ፡፡ በገዥው መደብ አካባቢ በዚህ መልኩ ከተፈጸመ በኋላ ደግሞ ከአንድ መቶ ዓመት በኋላ ወደ ሰፊው ሕዝብ ሊሰርጽ ችሏል፡፡ ምክንያቱም ተሳእቱ ቅዱሳን የሚባሉ፤ አሁን ቱርክና ሶሪያ ከሚባሉ አካባቢዎች የመጡ፤ እነርሱ ደግሞ በስፋት አቡነ ገሪማ፣ አቡነ ባታሊዮን የሚባሉ የክርስትና ኃይማኖትን ለማስፋፋት ቻሉ፡፡

የኃይማኖት ጉዳይ በስድስተኛው መቶ ዓመት በአጼ ካሌብ ዘመን አንድ አዲስ ምዕራፍ የታየበት ነበር። በዚያን ጊዜ በየመን አካባቢ የሚኖሩ ክርስቲያኖችን አንድ የየሁዲ ንጉሥ በጣም ያሰቃያቸውና ይጨቁናቸው ነበር፡፡ በወቅቱ የአክሱም መንግሥት በተለይም ቢዛንታይን ከሚባለው ጋር ጥብቅ ግንኙነት ስለነበረው ወደ 60 የሚሆኑ መርከቦችን ተልኮለት ይሰቃዩ የነበሩ ክርስቲያኖችን ለማዳንና የዩሁዲውን ንጉስንም ለማሸነፍ በቅቷል፡፡፤ ከዚያም አልፎ አብርሃም የሚባል እንደራሴ እዛው በማቆም ለተወሰነ ጊዜ በአስተዳደሩ ቁጥጥር ሥር ለማቆየት ችሏል፡፡

ስለዚህ የንግድ ግንኙነቱ ወደ ኃይማኖት ሊዞር ችሏል ማለት ነው፡፡ የኃይማኖት ግንኙነቱ በዚህም አላበቃም።እንደሚታወቀው የእስልምና ኃይማኖት በሚጀምርበት ጊዜ በወቅቱ የነበሩት የአካባቢው ገዢዎች ስልተቀበሉት ነብዩ መሃመድ የተወሰኑ ተከታዮቻቸውን ወደ ኢትዮጵያ ወደ ሀበሻ ልከዋል።

‹‹ፍትህ የሚያውቅ ነው ንጉሥ ሀበሻ ምድር አለና እርሱ ጋር ሄዳችሁ ጥገኝነት ጠይቁ›› ተብሎ የመጀመሪያዎቹ ሙስሊሞች ወደ ኢትዮጵያ የመጡት ነው በአክሱም ዘመን የመጨረሻው ዓመታት አካባቢ ነበር፡፡

በዛጉዬ ስርዎ መንግሥት ያን ያህል የጠበቀ የዲፕሎማሲ ግንኙነት አልነበረም፡፡የተገደበ ነበር። ግን ደግሞ እየሩሳሌም የሁሉም ክርስቲያኖች በተለይም የኢትዮጵያ ክርስቲያኖች፤ አንድ መዳረሻ ነበረችና በዚህ አንዱ ትልቁ ነገር ወደ ኢየሩሳሌም ለመሄድ የሚደረገው ጥረት ነበር፡፡

ብዙ ጊዜ ግብጾችንና ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖችን የሚያጨቃጭቀው ዴር ሱልጣን ገዳም በዚህ ዘመን ለኢትዮጵያውያን እንደተሰጠ ነው የሚተረከው፡፡ ይበልጥ ግንኙነት የነበረው በመካከለኛ ዘመን ነው፡፡

ከ13ኛው መቶ ዓመት መጨረሻ ጀምሮ እስከ 16ኛው መቶ ዓመት ከአውሮፓ ጋር መልከ ብዙ ግንኙነት የተካሄደበት ጊዜ ነው፡፡

አውሮፓውያን በዚያን ጊዜ የመስቀል ጦርነት ያካሂዱ ነበር፡፡ በአውሮፓ ክርስቲያኖችና በሙስሊሞቹ መካከል የሚደረግ ጦርነት ነው የነበረው፡፡ ጦርነቱ እየተራዘመ በሄደ ቁጥር የአውሮፓ ነገሥታት የክርስቲያን አጋር መንግሥት ይፈልጉ ነበር፡፡

ቄስ ጆን የሚባል ኃይማኖተኛ የሆነ ገናና የክርስቲያን ንጉሥ አለ፤ እርሱን ማግኘት አለብን፤ እርሱን ካገኘን ሙስሊሞችን በሁለት አቅጣጫ ወጥረን ይዘን እናሸንፋቸዋለን፤ እኛ ከምዕራብ እርሱ ከምሥራቅ የሚል ትልቅ እምነት ነበራቸው፡፡

ቄስ ጆንን ለማግኘት ያልዳሰሱትና ያላሰሱት ቦታ አልነበረም፡፡ በመጨረሻ ግን ዓይናቸው እና ቀልባቸው ያረፈው ኢትዮጵያ ላይ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በወቅቱ ገናና የሆነ የክርስቲያን ንጉሥ ስለነበራት፤ የአውሮፓና የኢትዮጵያ ግንኙነት በዚህ ላይ የተመሰረተ ነው ማለት ይቻላል፡፡

ግን ይሄ ከአውሮፓውያን ብቻ ሳይሆን፤ በኢትዮጵያዊያንም በኩል ተነሳሽነቱ ወይንም እንቅስቃሴ ነበር ፡፡ አጼ ዳዊት የሚባለው ንጉሥ በ14ኛው መቶ ዓመት መጨረሻና በ15ኛው መቶ ዓመት መጀመሪያ ላይ ከአውሮፓውያኑ ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለመመሥረት ጥረት አድርጎ ነበር፡፡

ከዚያ በኋላም ተከታታይ ነገሥታት ልዑካንን ወደ አውሮፓ ይልኩ ነበር፡፡ አውሮፓውያኑ በብዛት የሚጠይቁት ንዋየ ቅዱሳን፣ ሙያተኞች ግንበኞች፣አናጢዎች፣ ጌጣጌጥና ልብሶች የመሳሰሉትን ነበር፡፡

በወቅቱም ከ10 በላይ የሚሆኑ ልዑካን ወደ አውሮፓ ሄደዋል፡፡ አውሮፓ ሲባል እንግሊዝ፣ ፈረንሳይ ማለታችን አይደለም፡፡ ስፔን፣ ፖርቹጋልና ጣሊያን ናቸው፡፡ በዚያን ጊዜ ጣሊያን ውስጥ ቤኒስ የሚባል የታወቀ መንግሥት ነው የነበረው። እና ከነዚህ ሀገራት ጋር ግንኙነት ለመመስረትና ይጠይቋቸው የነበሩ ቁሳቁሶች እንዲሄዱላቸው በየጊዜው ልዑካን ይላኩ ነበር፡፡

በአንድ ወቅት እንደውም በአጼ ይሳቅ ጊዜ ከስፔን ነገሥታት ጋር በጋብቻ ለመተሳሰር ጥያቄ ቀርቦ ነበር። በርግጥ ለፍሬ አልበቃም፡፡ ግን ግንኙነቱ ጥልቀትና ስፋት ያለው እንደሆነ አመላካች ነው፡፡

የመካከለኛው ማሳረጊያ፤ በኢትዮጵያ በኩል ትልቅ ተነሳሽነት ተደርጎ የሚወሰደው ንግሥት እሌኒ የወሰደችው ርምጃ ነው፡፡ ንግሥት እሌኒ ማቲዎስ የሚባል መልእክተኛ ወደ አውሮፓ ልካ፤ ግንኙነት ለመመስረት ጥረት አድርጋለች፡፡ በዚያን ጊዜ ከሙስሊም ሱልጣኖች መንግሥታት ጋር የነበረው ውጥረትና ጦርነት እያየለ ሲመጣ፤ አጋር ያስፈልገኛል በሚል ወታደራዊ ግንኙነት ለመመስረት ንግሥት እሌኒ በ16ኛው መቶ ዓመት መጀመሪያ ላይ ልዑክ ላከች፡፡

ይሄን ተከትሎ አልቫሬስ የሚባል በታሪክ በጣም የሚታወቅ ቄስ፤ አባል የሆነበት በወቅቱም ትልቅ የሆነ የፖርቹጋል ልዑክ ወደ ኢትዮጵያ መጣ፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ ትልቅ የሆነ የውጭ ሀገር ልዑክ ወደ ሀገር መጥቶ ግንኙነት ሲመሰርት የመጀመሪያው ነበር፡፡ ከዚያ የልዑክ መምጣት ጋር ተያይዞ ያተረፍነው ነገር ቢኖር አልቫሪየስ የጻፈው መጽሐፍ ነበር፡፡ (ዘ ፕሪስተርስ ኦፍ ዘ ኢንድ) የሚለው መጽሐፍ የወቅቱን ሁኔታ በአግባቡ ያስረዳል። ወደ ሀገሩ ሲመለስ የመካከለኛው ዘመን መንግሥት ከግራኝ አሕመድ ጦርነት በፊት ምን ይመስል እንደነበር ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ትልቅ የታሪክ ሰነድ ትቶልናል።

በዚህ የተጀመረው እንቅስቃሴ፤ በመጨረሻ የግራኝ አሕመድ ጦር፤ ጠቅላላ ኢትዮጵያን አዳርሶ እስከ ሰሜን ኢትዮጵያ ደረሰ፡፡ በመጨረሻም የንግሥት እሌኒ ጥያቄ መልስ አግኝቶ ወደ 400 የሚሆኑ የፖርቹጊስ ወታደሮች ለእርዳታ ወደ ኢትዮጵያ መጡ፡፡ በፖርቹጋል አጋዥነት የአሕመድ ግራኝ ጦር ተሸንፎ የክርስቲያኑ መንግሥት እንደገና ለማንሰራራት ቻለ፡፡

ድሉን መሠረት በማድረግም ኢየሱሳውያን የሚባሉ ካቶሊክ ሚሲዮናውያን በብዛት ወደ ኢትዮጵያ መጡ። የኦርቶዶክስ ኃይማኖትን በማስቀየር ኢትዮጵያን ካቶሊክ ለማድረግ እንቅስቃሴ ጀመሩ፡፡ እንደውም ንጉሡን ካቶሊክ ለማድረግ ባደረጉት እንቅስቃሴም ተሳካላቸው፡፡ አጼ ሲንሲዮስ የካቶሊክ እምነት ተቀበሉ። ወደ ሕዝቡም ለማስረጽ ሲፈልጉ ነበር የእርስ በርስ ጦርነት የተከተለው። ጦርነቱ ካቶሊክ ትሆናላችሁ፤ አንሆንም በሚል የተቀሰቀሰ ሲሆን በወቅቱም በጦርነቱ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ አለቀ፡፡

በመጨረሻ ግን ንጉሡ በመጸጸት ‹‹መስሎኝ ነበር›› በማለት ዙፋኑን ለልጁ ፋሲለደስ ለቀቀለት። እርሱ ዙፋኑን ከለቀቀ በኋላም የቀድሞ ሥርዓት ተመለሰ፡፡ አጼ ፋሲለደስ ከነገሠ በኋላ መጀመሪያ የወሰደው ርምጃ ኢየሱሳውያንን ከኢትዮጵያ ማስወጣት ነበር፡፡

ከአውሮፓውያን ጋር የተጀመረው ግንኙነት ብዙ ጣጣ እያመጣ ነው በሚል ኢትዮጵያ ከአውሮፓ ጋር ያላት ግንኙነት መቋረጥ እንዳለበት ወሰነ፡፡ በዚህም ኢትዮጵያና አውሮፓ ለ200 ዓመታት ሳይገናኙ ቀሩ፡፡ አጼ ፋሲለደስ እንደውም ከሙስሊም ባለሥልጣኖች ጋር የመቀራረብ ፖሊሲ ነበር የሚከተለው፡፡

አውሮፓውያን በ19 መቶ ዓመት ነው እንደገና በአዲስ መንፈስ ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን፤ በጠቅላላ አፍሪካ በኃይማኖት፣ በንግድና በዲፕሎማሲ ከፍተኛ ዘመቻ በማድረግ ወደ አፍሪካ ለማቅረብ የተለያዩ ጥረቶችን ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡

አዲስ ዘመን፡- ለ200 ዓመት ከአውሮፓ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት አልተደረገም ማለት ነው?

ፕሮፌሰር ባህሩ፡– አልፎ ከሚመጡ ተጓዦችና ጸሐፍት በስተቀር ከ200 ዓመት በፊት እንደነበረው እዚህ ግባ የሚባል ግንኙነት አልነበረም፡፡ ደብዘዝ ያለ ግንኙነት ነው የነበረው፡፡

አዲስ ዘመን፡- በየዘመናቱ የነበሩ ነገሥታት ኢትዮጵያን የባህር በር ባለቤት ለማድረግ ያደረጉት ጥረት ምን ይመስላል?

ፕሮፌሰር ባህሩ፡- ሁሉም ነገሥታት የባህር በር ጉዳይ ዋነኛው አጀንዳቸው ነበር ማለት ይቻላል፡፡ አጼ ቴዎድሮስ እንደሚታወቀው ሁለት ዓላማ አንግበው ነበር የተነሱት፡፡ አንዱ ተከፋፍላ የነበረችውን ኢትዮጵያ አንድ በማድረግ ተዳክሞ የነበረውን የንጉሠ ነገሥት ሥልጣን መልሶ ለማደስ ነበር፡፡ ሁለተኛው ኢትዮጵያን ለማዘመን ነው፡፡ በተለይ ኢትዮጵያ እንድትዘምን ቁርጠኝነቱ ከፍተኛ ስለነበር ከፈረንጆቹ ጋር መወዳጀት ጀመሩ፡፡ እንደ አጋጣሚ ደግሞ ወደ ኢትዮጵያ የመጡ ሁለት እንግሊዛውያን ቤንና ፕራውደን የሚባሉ ወዳጅ ሆነዋቸው ነበር፡፡

በነዚህ እንግሊዛውያን አማካኝነት የአውሮፓን እርዳታ አግኝቼ ኢትዮጵያን አዘምናለሁ የሚል ከፍተኛ እምነት ነበራቸው፡፡ በዚህ መካከል ነበር ያ ጣጠኛ የተባለውን ደብዳቤ እኤአ በ1862 ለንግሥት ቪክቶሪያ የላኩት፡፡ ለላኩት ደብዳቤ መልስ ሳያገኙ ቀሩ፡፡ በዚያም ተናድደው ኢትዮጵያ ውስጥ የነበሩትን ፈረንጆች አገቱ፡፡ እንግሊዞችም የታገቱትን ለማስፈታት በናፔር የሚመራውን ጦር ላኩ፡፡ አጼ ቴዎድሮስም እጄን አልሰጥም በሚል እራሳቸውን ሰዉ፡፡

በአፄ ቴዎድሮስም ሆነ በአፄ ዮሐንስ ዘመን የምናየው ነገር የዋህነት ነበር፡፡ እኛም እነርሱም ክርስቲያን ነን፣ ክርስቲያን ለክርስቲያን ደግሞ ማገዙ አይቀርም የሚል እሳቤ ነው የነበራቸው፡፡ ስንጠይቃቸው ይረዱናል የሚል እምነት ነበራቸው። ሁልጊዜም በቱርኮች ተከበናል የሚል ስጋት አዘል ደብዳቤ ለአውሮፓ መንገሥታት ይልኩ ነበር።

ቱርክ የሚሉት ግብጽን ነበር፡፡ ተከብቤያለሁና ለመግዛት አልቻልኩም፤ እናንተም ክርስቲያን ሲጠቃ እንዴት ዝም ብላችሁ ትመለከታላችሁ ነበር የሚሉት። እነርሱም ክርስቲያን ስለሆኑ ይረዱናል የሚል እሳቤ ነበራቸው፡፡ አፄ ዮሐንስም ይህንኑ ነበር የሚደግሙት። በዲፕሎማሲ ዓለም ትንሽ የዋህነት ነበራቸው፡፡ የውጭዎቹ መንግሥታት በኃይማኖት ሳይሆን በጥቅም ነው የሚመሩት፡፡ ምን እጠቀማለሁ እንጂ በኃይማኖት አንድ ስለሆንን እናግዛለን የሚሉ አልነበሩም፡፡

በአጼ ዮሐንስ ዘመን ኢትዮጵያ ስለተከበበች በርካታ ደብዳቤዎችን ለእንግሊዞች ይጽፉ ነበር። እርሳቸው ትኩረታቸውን የሳበውና ለጦርነትም መንስኤ የሆነው የግብጽ መስፋፋት ፖሊሲ ነው። ግብጾች ሙስሊም ስለሆኑና እኛ ክርስቲያን ነን በሚል ግብጽን ለመቋቋም አውሮፓውያን ይረዱኛል የሚል ነበር፡፡ በዘመኑ የነበረው የዲፕሎማሲ ስሌት እንደዚያ አልነበረም፡፡ በወቅቱ ጦርነት ሁለት ጊዜ ተካሂዶ የነበረውን ጦርነት በመዋጋት ግብጾችን ማሸነፍ ችለዋል፡፡ በመጨረሻም ድሉን መሥመር ለማስያዝ በተለይም የባህር በር ለማግኘት፤ ከእንግሊዞች ጋር ያልሆነ ውል ተዋዋሉ፡፡

እኤአ 1884 የዓድዋ ስምምነት ተደረገ። በዚህ ወቅት የማህዲስቶች ንቅናቄ ሱዳንን አጥለቅልቀዋታል፡፡ ማህዲስቶች ሱዳንን ይገዙ ነበር። በወቅቱ ብዙዎች ግን ተሸንፈው በካምፕ ውስጥ ተከበው ነበር እንዲቀመጡ የተደረገው፡፡ በዚያ በኩል ወደ ግብጽ መሄድ ስለማይችሉ፤ በኢትዮጵያ በኩል እንዲወጡ አፄ ዮሐንስ ድጋፍ እንዲያደርጉ፤ በልዋጩ ደግሞ እንግሊዞች ነፃ ወደብ ምጽዋን ሊሰጧቸው ነበር ስምምነቱ፡፡

እኤአ 1884 የዓድዋ ስምምነት ከተፈረመ በኋላ እንግሊዞች ቃላቸውን መጠበቅ አልቻሉም። አጼ ዮሐንስ የገቡትን ውልም አክብረው እስከ መጨረሻው ድረስ በመሄድ ግብጾቹን በራስ አሉላ አማካኝነት፤ ከተከበቡበት አውጥተው በኢትዮጵያ በኩል ወደ ሀገራቸው እንዲሄዱ ወይንም እንደመለሱ አደረጉ፡፡

 በእንግሊዞች በኩል ግን የተገባው ቃል አልተከበረም፡፡ ወይንም ምንም ነገር አልተደረገም፡፡ ነፃ ወደብ የማግኘት ነገር አልተተገበረም።

አፄ ዮሐንስ ከማህዲስቶች ጠላትነትን ነው ያተረፉት፡፡ ‹‹በማህዲስቶቹ በኩል የነበረው የጠላቴ ወዳጅ ጠላቴ ነው የሚል ነበር›› ግብጾቹ በኢትዮጵያ ንጉሥ በአፄ ዮሐንስ አማካኝነት በራስ አሉላ እርዳታ ነው ያመለጡት፡፡ ስለዚህ ፍልሚያችን ከኢትዮጵያ ጋር ነው ብለው፤ለተከታታይ አራት አመታት በኢትዮጵያና በማህዲስቶች መካከል ውጊያ ተካሄደ። በመጨረሻ አፄ ዮሐንስ መተማ ላይ ተሰዉ። ስለዚህም የኢትዮጵያ መንግሥታት ይከተሉት የነበረው የዲፕሎማሲ አካሄድ የዋህነት የተሞላበት ነበር ማለት ይቻላል፡፡

አዲስ ዘመን፡- በአፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት የባህር በር ለማግኘት የተደረጉ ጥረቶች ምን ይመስላሉ?

ፕሮፌሰር ባህሩ፡– የአፄ ምኒልክ ጉዳይም ቢሆን፤ ያለፉት ተቀጽላ ነው፡፡ የባህር በር የማግኘት ጉዳይ አንገብጋቢ ጥያቄ ነበር፡፡ እኤአ በ1883 አንድ በጣም ዝነኛ የሆነ ሰልኩላር ለአውሮፓ ነገሥታት በሙሉ ይጽፋሉ፡፡ በዚህ የነበረው ጥረት የኢትዮጵያ ዳር ድንበር ይህ ነው ብሎ ለማሳወቅ ነው፡፡ ይህን የሚያደርጉትም አውሮፓውያን እየተስፋፉ ስለሆነ እነርሱ መጥተው ከማጥለቅለቃቸው በፊት እኔ ግዛቴ ይሄ ነው ብዬ ላሳውቃቸው ብለው ሰፋ ያለ ሃሳብ በመያዝ ለዓለም መንግሥታት በሙሉ ሰርኩላር በትነዋል፡፡ በመጨረሻ ሁሉም መንግሥታት ኢትዮጵያ የባህር በር እንድታገኝ እንዲረዷቸው ተማጽነዋል፡፡

ዳግማዊ ምኒልክ ከአብዛኞቹ መንግሥታት ጋር ጥሩ ግንኙነት ነበራቸው፡፡ ከጣሊያን ጋር ግን አይዋደዱም ነበር፡፡ አንድም ከአፄ ዮሐንስ ጋር በነበራቸው የስልጣን ሽሚያ፤ የነርሱን አጋዥነት ስለፈለጉ፤ ከእነርሱ ጋር በመቀራረብ ውል መዋዋል ጀመሩ፡፡ አሁን ሰው የውጫሌ የውል ስምምነትን ብቻ ነው የሚያውቀው፤ ነገር ግን ከዚያ በፊት፤ አንድ ሁለት ውሎች ተዋውለዋል። አውሮፓውያን ሲመጡ የንግድና የወዳጅነት ውል የሚል ስላላቸው በ1930ዎቹና በ1940ዎቹ አካባቢ የተለያዩ ውሎች ነበሩ፡፡ አፄ ምኒልክ በዚህ መልኩ ሁለት ውሎችን ተዋውለው በመጨረሻ ደግሞ የውጫሌን ውል ተዋዋሉ፡፡ የውጫሌውን ውል ደግሞ በርካታ ጦሶችን ይዞ መምጣቱ የሚታወቅ ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ ዓድዋ ላይ የተቀዳጀችው ድል ለውጭ ግንኙነት ፖሊሲዋ ያለው አበርክቶ እንዴት ይገለጻል?

ፕሮፌሰር ባህሩ፡- የዓድዋው ድል ሁሉን ነገር ነው የለወጠው፡፡ ከዓድዋ በፊት፤የአውሮፓውያን ፍላጎት፤ እምነትም ሊባል ይችላል አፍሪካን በሙሉ በቁጥጥራችን ሥር እናደርጋለን የሚል ነበር የነበረው፡፡

በጀርመናዊው ቢዝማርክ አስተናባሪነት የበርሊን ኮንፈረንስ ከሚባለው እኤአ 1885 በአውሮፓ፤ ካደረጉት ስምምነት ጀምሮ ወደ አፍሪካ በስፋት እየገቡ መከለል ጀመሩ፡፡ ባንዲራ መስቀል እና አገዛዛቸውን ማጠናከር ጀመሩ፡፡ ጣሊያንም በዚህ ስሌት ነው ወደ ኢትዮጵያ መስፋፋት የጀመረችው፡፡ በመጀመሪያም ኤርትራን ያዘች። ኤርትራ የሚለውን ስያሜም በ1890 የሰጠችው ጣሊያን ናት፡፡ ኤርትራ ቀደም ሲል መረብ ምላሽ ነበር ተብላ የምትጠራው፡፡

ኤርትራን እንደ መፈናጠጫ ነበር የተጠቀመችው፤ ምክንያቱም ዋናው ሀብት ያለው ኢትዮጵያ ስለሆነ፤ ቀስ በቀስ እየሸረሸረች ወደ ዓድዋ ጦርነት ውስጥ እንዲገባ አደረገች፡፡ ዓድዋ ላይ የተደረገው ጦርነት በድል መጠናቀቁ፤ አውሮፓውን የነበራቸውን ምኞት ሙሉ በሙሉ ቀይሮታል፡፡

በተከታታይ በተደረጉ ጦርነቶች ኢትዮጵያ በቅኝ እንደማትገዛ ከአንዴም ሁለቴም አረጋገጠች። ከዚያ በኋላ ያለው አማራጭ አንደኛው በአቻነት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መመስረት ነው፡፡ ያኔ ለጋሲዮን ነበር የሚባለው። ለጋሲዮን ማቋቋም ሲሆን፤ በአንድ ዓመት ውስጥ ሶስት ለጋሲዎች ተቋቋሙ፡፡ በጣም የሚገርመው፤ ከዓድዋ ድል በኋላ በዓመቱ መጀመሪያ የተቋቋመው የጣሊያን ለጋሲ ነበር፡፡ ሁለተኛ ፈረሳይ፣ ሶስተኛ እንግሊዝ ነበሩ፡፡ በሂደት እነ አሜሪካን፣ ጀርመን መጡ፡፡

ኢትዮጵያ በዓድዋ ላይ ድል መቀዳጀቷ ከአሁን በኋላ ኢትዮጵያን ቅኝ መግዛት አንችልም፤ ያለን አማራጭ ጥቅማችንን ማስከበር፣ ጤናማ የሆነ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ማቋቋም ነው፡፡ ሁለተኛ ደግሞ ኢትዮጵያ አሁንም የበለጠ መስፋፋት ስለምትችል መገደብ አለባት፤ ለመገደብ ደግሞ ሁነኛው ዘዴ ድንበር ማካለል ነው የሚል ውሳኔ ላይ ደረሱ፡፡

ከዓድዋ ድል በኋላ እንደዚሁ በዓመቱ ጀምሮ የድንበር ማካለሉ ሥራ በ10 ዓመት ጊዜ ውስጥ ተከናውኖ የኢትዮጵያ ድንበሮች በሙሉ ተካለሉ። ከኤርትራ፣ ከሱዳን፣ ከጅቡቲ ጋር የመጀመሪያው ድንበር የማካለል ሥራ ተከናወነ፡፡ ከሶማሊያና ከኬንያ ጋርም ቀጠለ፡፡

የሶማሊያው ከጣሊያን ጋር፣ የኬንያው ደግሞ ከእንግሊዝ ጋር በመሆን ነበር የማካለል ሥራው የተከናወነው፡፡ ኢትዮጵያ ከ10 ዓመት በኋላ ያላትን ቅርጽ የምናየው በዚህ መልኩ ነው፡፡ የድንበር ቅርጽ የያዘው ይሄኔ ነው፡፡

ሆኖም ዓድዋ ትልቅ ድል አንፀባራቂ የሆነውን ያህል፤ ኤርትራን ማስመለስ ባለመቻሉ፤ ወደብ አልባ ሆና ቆየች። ስለዚህ የወደብ ማጣት፣ አፄ ምኒልክ እየተዳከሙ በሚሄዱበት ጊዜ ኢትዮጵያ ትፈርሳለች ከአፄ ምኒልክ በኋላ አትቆይም የሚል ሃሳብ ስለነበራቸው እንዴት አድርገን እንቀራመታለን የሚል ውል እስከመዋዋል ደረጃ ላይ ደርሰዋል፡፡

ምኒልክ ከሞቱ በኋላ እያንዳንዳቸው ይሄ የኔ ይሆናል እስከ ማለት ደርሰው ነበር፡፡ የሶስትዮሽ ውል እኤአ 1906 እንግሊዞች ድንበራቸው አካባቢ፣ ጣሊያኖችም እንዲሁ በሁለት በኩል ድንበራቸውን ተከትለው፤ ፈረንሳዮች የባቡር ሃዲድ ተከትለው ያለውን ግዛት እንደሚወስዱ ነው የተዋዋሉት፡፡

ይህንኑ እውን ለማድረግ ከጊዜ በኋላ ደግሞ ኢትዮጵያ ላይ የመሣሪያ ማዕቀብ ጣሉ፡፡ የመሣሪያ ማዕቀብ ጠንቅ የታወቀው፤ ሞሶሎኒ እስከአፍጢሙ ታጥቆ ሲመጣ ነበር። በዚህ ወቅት ኢትዮጵያ በማዕቀቡ ምክንያት መሳሪያ ማስገባት ስለማትችል እስከአፍጢሙ የታጠቀውን የጣሊያንን ጦር የመመከት አቅም አልነበራትም፡፡ ሆኖም በባዶ እጅም ቢሆን ለአምስት ዓመታት በዱር በገደሉ በተደረገ መስዋዕትነት ኢትዮጵያን ማትረፍ ተችሏል፡፡

አዲስ ዘመን፡- በአፄ ምኒልክ ዘመን ከአሜሪካን፣ ፈረንሳይና ሩሲያ ጋር የነበረው ግንኙነት ምን ይመስል ነበር?

ፕሮፌሰር ባህሩ፡– በመቻቻል ነው ያሳለፉት ማለት ይቻላል፡፡ እነርሱ ኢትዮጵያ ውስጥ ሌጋሲዮኖች አሏቸው በዚያ አማካኝነት ጥቅማቸውን ያስከብራሉ። ለምሳሌ ፍርድን በተመለከተ ልዩ ፍርድ ቤት ነበር፤ የውጭ ዜጎች በልዩ ፍርድ ቤት ነበር የሚዳኙት፡፡ ዳኞቹ ግን ኢትዮጵያውያን ነበሩ። የቆንሲሎቻቸው ተወካዮች በሚገኙበት ነበር ፍርድም የሚሰጠው፡፡ ከዚህ በተረፈ ግን ሙሉ ለሙሉ የአቻ ግንኙነት ነበር ማለት ይቻላል፡፡

አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ ከአሜሪካን ጋር የንግድ ግንኙነት ነበራት?

ፕሮፌስር ባህሩ፡- የንግድ ስምምነት እኤአ በ1903 ነበር የተጀመረው፡፡ ግን ከንግድ ውጭ ብዙም ግንኙነት አልነበራቸውም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ሌጋሲዎን እንኳን ያቋቋሙት በጣም ዘግይተው ነው። አሜሪካውያኑ ጉዳያቸውን ሲከታተሉ የነበረው ከኤደን ነበር፡፡ በኋላ ላይ የፍትሃ ኃብተጊዮርጊስ ግቢ የነበረው አሁን አሜሪካን ግቢ የሚባለውን ተከራይተው አቋቋሙ፡፡ ንግዱን ብቻ የማበረታታት እንጂ ዲፕሎማሲው እንደነእንግሊዝ፣ ጣሊያንና ፈረንሳይ የጎላ ተሳትፎ አልነበራቸውም ማለት ይቻላል፡፡ የነርሱ ተሳትፎ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ነው የሚመጣው፡፡

አዲስ ዘመን፡- በዓድዋው ጦርነት ሩሲያ ድጋፍ አድርጋለች የሚባል ነገር አለ፡፡ ድጋፉ ምን ነበር?

ፕሮፌሰር ባህሩ፡– ሩሲያ ድጋፍ ያደረገችው ቀይ መስቀል በመላክ እና ቁስለኞችን በመንከባከብ ነበር። ያ ድጋፍ አድጎ መሠረቱ ደጃዝማች ባልቻ ሆስፒታል ለመመስረት በቃ፡፡ የዲፕሎማሲ እንጂ የመሣሪያ ድጋፍ ግን አልነበረም፡፡

አዲስ ዘመን፡- በልጅ እያሱ እና በንግሥት ዘውዲቱ ዘመን የነበረው የዲፕሎማሲ ግንኙነት ምን መልክ ነበረው ?

ፕሮፌሰር ባህሩ፡- ልጅ እያሱ ኢትዮጵያ በኃያላን መንግሥታት ሥር እንዳትውደቅ፤ከሁሉም ጋር ግንኙነት እንዲኖራት ማድረግ የሚለውን የአፄ ምኒልክን ፖሊሲ ነው የተከተሉት፡፡ በኋላ ላይ ግን በመጥፎ ተተረጎመባቸው። በተለይ ከጀርመን ጋር የነበራቸው ግንኙነት ጠበቅ ስላለ በአንደኛው የዓለም ጦርነት የጀርመንና የቱርክ ደጋፊ ናቸው ተብለው ተፈረጁ። በዚህም ምክንያት ፈረንሳይ፣ እንግሊዝና ጣሊያን አብረው አብረው ከውስጥ ካሉት ጋር የፀረ ኢያሱ ኃይሎች ጋር በመተባበር ሊያስወግዷቸው የቻሉት። ግን ከጊዜ በኋላ የወጡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት እርሳቸው ወደዚያ ካምፕ አልገቡም፡፡

እንደሚባለውም አልሰለሙም፡፡ እኔም አልሰ ለምኩም፣ ሕዝቡም እንዲሰልም አልፈልግም፣ ሲሉም በግልጽ ተናግረዋል፡፡ እድሊፕ የሚባል አንድ የቅርብ ወዳጃቸው የሕይወት ታሪካቸውን በጻፈው መጽሐፍ ላይ በደንብ አድርጎ እንደገለጸው፤ በአንደኛው የዓለም ጦርነት ላይ ማን ቢያሸንፍ ይሻልሀል ወይንም ትመርጣለህ ሲባል እንደ እውነቱ ከሆነ ሁሉም ጦርነት ቢራዘምና ሁሉም ቢዳከሙ ነው የምመርጠው ብለው የተናገሩት አለ፡፡ ኢትዮጵያ የማንም ጥገኛ ሳትሆን ተቻችላ እንድትቀጥል ነበር ፍላጎታቸው፡፡

ንግሥት ዘውዲቱ በውጭ ጉዳይ አመራር ውስጥ አይገቡም ነበር፡፡ አልጋ ወራሹ ራስ ተፈሪ በኋላ አፄ ኃይለሥላሴ የተባሉት ነበሩ የሚመሩት፡፡ አንዱ ትልቁ ነገር የነበረው ከምዕራባውያን መንግሥታት ጋር ያላቸውን ግንኙነት የማጠናከር ጉዳይ ነው። ሁለተኛ ደግሞ ኢትዮጵያ በነፃ መንግሥትነቷ ዓለም አቀፍ እውቅና እንዲያገኝ ጥረት አድርገዋል። የመጀመሪያውን በተመለከተ የአንደኛው የዓለም ጦርነት እንዳለቀ፤ በራስ ናደው አባወሎ የሚመራ ልዑክ ወደ አሸናፊዎቹ ኃያላን መንግሥታት የእንኳን ደስ ያላችሁ መልእክት ተልኳል፡፡ ከዚያ ግን ዋናው ወሳኙ፣የተባበሩት መንግሥታት ነው፡፡

ያኔ የተባበሩት መንግሥታት የሀገራት የመንግ ሥታት ማህበር ነው የነበረው፡፡ ሊግኦፍኔሽን ውስጥ ኢትዮጵያን ለማስገባት በርካታ ተጋድሎ ተደርጓል። በተለይ እንግሊዞች ኢትዮጵያ ውስጥ የባርነት ንግድ ስለሚካሄድ ኢትዮጵያ አባል መሆን የለባትም የሚል ከፍተኛ ተቃውሞ ነበር፡፡ በወቅቱም ከጣሊያን በበለጠ ነበር እንግሊዞቹ የተቃወሙት። ሆኖም በከፍተኛ ትግል ኢትዮጵያ አባል ልትሆን ችላለች፡፡ በ1923 ነበር አባል የሆነችው፡፡

በርግጥ ይሄ አባልነት ምን ጠቀማት የሚለው ሌላ ጥያቄ ነው፡፡ የቁርጡ ቀን ሲመጣ ኢትዮጵያን ሊረዱ አልሞከሩም፡፡ አንድ የማህበር አባል ሌላኛውን የማህበር አባል በኃይል ሲያጠቃ እነርሱ አቋም መውሰድ ነበረባቸው፤ ግን አልቻሉም፡፡

ከጣሊያን መውጣት በኋላ የኢትዮጵያ እና አውሮፓውያን ግንኙነት ሁለት ምዕራፎች ነው የነበሩት። የመጀመሪያው፤ እንግሊዞች ብዙውን ነገር ኢትዮጵያን በኃይል የሚቆጣጠሩበት አካሄድ ነው የነበረው። ይሄን የሚያደርጉት ደግሞ ጣሊያንን ለማስወጣት የተጫወቱትን ሚና እንደውለታ በመቁጠር ነው፡፡እንደውም ኢትዮጵያ ከማለት ይልቅ በጠላት ተይዞ የነበረ ግዛት አስተዳደር የሚል መስርተው ነበር፡፡ በዚሁ ምክንያትም ኢትዮጵያ ነጻነቷን ለማወቅ ብዙ ጊዜ ፈጅቶባቸዋል፡፡

እኤአ በ1942 ከአፄ ኃይለሥላሴ ጋር ያደረጉት ስምምነት፤ ኢትዮጵያን ሙሉ በሙሉ በእነርሱ መዳፍ ሥር የሚያስገባ ነበር፡፡ ባቡሩም፣ ፋይናንሱም፣ ወታደሩን ሁሉ በእነርሱ ቁጥጥር ሥር የሚያስገባ ነው። ከዚያ በኋላ እኤአ በ1944 ይህንን የሚያለዝብ እና የኢትዮጵያን ነፃ መንግሥትነት የሚያረጋግጥ አካሄድ ለመፍጠር ተችሏል።

ይሄ በአጠቃላይ ሲሆን በዝርዝር ሲታይ ደግሞ ኤርትራና ኦጋዴንን ለማስመለስ፤እንግሊዞች እንቅፋት ፈጥረው ነበር፡፡ ኤርትራ ውስጥ ኢትዮጵያን አንፈልግም የሚሉትን በመደገፍ፤ የአንድነት ኃይሉን በማዳከም ሚና ተጫውተዋል፡፡ኦጋዴንንም ከብዙ ትግል በኋላ ነው ማስመለስ የተቻለው፡፡ እንግሊዞች ታላቋ ሶማሌ የሚለውን መርዘኛ ሃሳብ ጥለው ነው የሄዱት፡፡

ከእንግሊዞች በኋላ ከአሜሪካኖች ጋር የተሻለ ግንኙነት ለመፍጠር ተሞክሯል፡፡ወታደሩ ትጥቁን የሚያገኘው ከአሜሪካኖች ነበር፡፡ በትምህርቱም፣ በወባ መከላከልና በሌላውም ግንኙነቱ እኤአ 1965 አካባቢ ድረስ የቀጠለ ነበር፡፡ በኋላ ላይ ግን አሜሪካኖቹ ገሸሽ እያሉ በመምጣታቸው የኢትዮጵያ ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ እየቀነሰ ስለመጣ ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- እንደ አጠቃላይ በኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ታሪክ የተሻለ የሚባለው በየትኛው ዘመን ነበር?

ፕሮፌሰር ባህሩ፡- የተሻለ ብሎ ለመምረጥ ከባድ ነው፡፡ ግን የአፄ ኃይለሥላሴ ዘመን ስኬት ያለበት ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ብዙዎች ሲታገሉ የነበረው የባህር በር ጉዳይ ለአጭር ጊዜም ቢሆን መፍትሔ ያገኘው በእርሳቸው ዘመን ነው፡፡ አፄ ምኒልክ በተወሰነ ደረጃ ተሳክቶላቸው ነበር፡፡

አዲስ ዘመን፡- ለሰጡኝ ሰፊ ማብራሪያ አመሰግናለሁ

ፕሮፌሰር ባህሩ፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡

ለምለም መንግሥቱ

አዲስ ዘመን ሰኞ ኅዳር 10 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You