ሊያመልጠን የማይገባ ወርቃማ ዕድል!

 ኢትዮጵያውያን እንደ አንድ ማኅበረሰብ የሚለያዩን ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ እና ኢኮኖሚያዊ እሳቤዎች አሉ። እነዚህ እሳቤዎች ልዩነቶችን ማስተናገድ የሚያስችል ማኅበረሰብ ለመገንባት ለጀመርናቸው ጥረቶች ስኬታማነት ትልቅ አቅም ሊሆኑ እንደሚችሉ ይታመናል።

በቀደሙት ዘመናት እነዚህን ልዩነቶች በሰላማዊ መንገድ ቁጭ ብሎ ማስታረቅ የሚያስችል የፖለቲካ ሥርዓት መፍጠር ባለመቻላችን፣ ሀገሪቱ በግጭት አዙሪት ውስጥ ዘመናትን አስቆጥራለች። በዚህም በየዘመኑ የነበሩ ትውልዶች ያልተገባ ዋጋ ለመክፈል የተገደዱበት ሁኔታ የታሪካችን ሰፊ ትርክት የያዘ ነው።

አሁን ላይ ይህንን ችግር ለዘለቄታው በመፍታት፤ ልዩነቶችን በሰላማዊ መንገድ ማስተናገድ የሚያስችል የፖለቲካ ሥርዓት ለመፍጠር በሚያስችል ሀገራዊ መነቃቃት ላይ እንገኛለን። ለዚህም ብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን አቋቁመን፣ ለዓላማው ስኬት እንደ ዜጋ የሚጠበቅብንን ለማበርከት እየተንቀሳቀስን ነው።

በርግጥ ይህ ትውልድ እንደ ትውልድ ሰፊ ያደሩ የቤት ሥራዎች በእጁ እንዳሉ ይታመናል። እነዚህ የቤት ሥራዎች ዛሬ ላይ ሕይወትን ጨምሮ ብዙ ያልተገባ ዋጋ እንዲከፍል፣ የራሱን እጣ ፈንታ ወስኖ፣ በራሱ መንገድ እንዳይኖር ተግዳሮት እየሆኑበት ነው።

ትውልዱ እየተፈተነባቸው ካሉ ያደሩ ሥራዎች በአሸናፊነት ለመውጣት ከሁሉም በፊት፣ በእጁ ያሉትን የቤት ሥራዎች /ችግሮች/ ምንነት በቅጡ ማጤን፣ በቤት ሥራዎቹ ምንነት ዙሪያ የጋራ መግባባት ላይ መድረስ ይኖርበታል። ለዚህ የሚሆን ሁለንተናዊ ዝግጁነት እና ቁርጠኝነትም መፍጠር ይጠበቅበታል።

ለዚህ ደግሞ ለውይይት /ለመነጋገር/ ቅድሚያ መስጠት እንዳለበት ብዙም አነጋጋሪ አይደለም። ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ሲንከባለሉ የመጡ ሀገራዊ ችግሮቻችንን በሰለጠነ መንገድ ተነጋግረን ለመፍታት የሚያስችል ትልቅ ዕድል መሆኑን አምኖ መቀበልም ያስፈልጋል።

በተለያዩ ወቅቶች፣ በተለያዩ ኃይሎች የኮሚሽኑ መቋቋም በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ወሳኝ እንደሆነ ሞግተዋል ፤ ድምጻቸውን ከፍ አድርገው አሰምተዋል። አሁን ላይም መላው ሕዝባችን በኮሚሽኑ ላይ ያለው ተስፋ ቀን ተቀን እየጨመረ፤ ለተልዕኮው ስኬት በቁርጠኝነት እየተንቀሳቀሰ ነው።

በርግጥ ከነበርንበትና አሁንም ካለንበት የግጭት አዙሪት ወጥቶ በሰላም መኖር የሚያስችል ሀገራዊ አውድ ተፈጥሮ ማየት የሁሉም ዜጋ መሻት ብቻ ሳይሆን የዕለት ተዕለት ጸሎት ከመሆኑ አንጻር፤ በሕዝባችን ዘንድ ይህንን ዕድል ለመጠቀም የሚታየው መነሳሳት ብዙም ሊያነጋግር የሚገባ አይደለም።

ከዚህ ቀደም በተፈጠሩ የተዛቡ ትርክቶች ሀገራችን ከአንድም፣ ሁለቴ ሕልውናዋ ከፍተኛ አደጋ ውስጥ ገብቶ ተዓምር በሚመስል መልኩ ተርፋለች። ከእንግዲህ ሦስተኛ ዕድል ላይኖራት ይችላል። ይህንን ዕድል በተገቢው መልኩ መጠቀም ሀገርን እንደ ሀገር ከጥፋት መታደግ የሚያስችል መሆኑንም በአግባቡ መገንዘብ ተገቢ ነው፡፡

ለአብሮነታችን ከአፍራሽና ከነጠላ ትርክት ወጥተን ሁሉንም ኢትዮጵያውያንን ሊሰበስብ የሚችል ትልቅ ሀገራዊ ትርክትን ለመከተል መነጋገር /መወያየት ይገባል፡፡ ይህን እውን ለማድረግ ሀገራዊ ምክክሩ ከእጁ ሊወጣ የማይገባ ወርቃማ ዕድል ነው። ይህንን ተገንዝቦ መንቀሳቀስም የሁሉም ኢትዮጵያዊ ኃላፊነት ነው፡፡

የኢትዮጵያ የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት ሊከበር የሚችለው፣ ከራስና ከቡድን ፍላጎት በላይ ለጋራና ብሔራዊ ጉዳዮች ትኩረት ሲሰጥ ነው፡፡ ለሀገራዊ ምክክሩ ሂደት የማይበጁ ቁርሾዎች ሲበዙ፣ ዘለቄታዊ ሰላምና መረጋጋት ለማምጣት አዳጋች እንደሚሆን መረዳት አያቅትም፡፡ ከዚህ አንጻር ኢትዮጵያን ከራሳቸው ፍላጎት በታች ለማድረግ የሚሹ ካሉ ከታሪክ መማር እንዳለባቸው ማስታወስም ይጠቅማል፡፡

አንድነትና እኩልነት የሰፈነባት ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ በሀገራዊ ምክክሩ የመሠረት ድንጋይ ማስቀመጥ የዚህ ትውልድ ትልቁ የቤት ሥራ ነው፡፡ ቁርሾን አስወግዶ በመግባባት ላይ የተመሠረተ የጋራ ትርክት መፍጠርም እንዲሁ፡፡ በሰከነ መንፈስ ከራሳችን ታሪክ በጎ በጎውን መማርም ያስፈልጋል፡፡

ይህንን ተጨባጭ እውነታ ታሳቢ በማድረግ፤ ገዥው ፓርቲን ጨምሮ ሌሎች ተፎካካሪ ፓርቲዎችና የሀገር ጉዳይ የሚመለከታቸው ወገኖች፣ ይህ የሕዝብ ምክክር በተቀላጠፈ መንገድ ይከናወን ዘንድ እንቅፋት ሊሆኑ የሚችሉ መሰናክሎች እንዳይኖሩ ማገዝ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ለጭቅጭቅና ለውዝግብ በር ከሚከፍቱ ድርጊቶች መራቅም ይጠበቅባቸዋል።

ለተጀመረው በጎ አካሄድ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሕዝብ ወኪሎችና የፖለቲካ ልሂቃን የሰላም ሃሳቦችን በማቅረብ ምክክሩ ውጤታማ እንዲሆን የበኩላቸውን ሊወጡ ይገባል። የምክክር ጉዳይ የተወሰነ ቡድን አጀንዳ ሳይሆን ሀገርን ከጥፋት፤ ሕዝብን ከሁከትና ከሰላም እጦት መታደግ የሚያስችል ሕዝባዊ አጀንዳ ነው !

አዲስ ዘመን ሰኞ ኅዳር 10 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You