አሰባሳቢ ትርክት፤ ሀገርን በጸና መሠረት ላይ ለማነፅ

በእያንዳንዷ የሀገር ሁነት እና ክስተቶች ውስጥ ሰው አለ፣ ፖለቲካ አለ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ እሳቤዎች አሉ። ይህች ዓለም የበርካታ የፖለቲካ ሥሪቶችን ያለፈች፣ እያለፈች ያለችና ወደፊትም የምታልፍ ነች፡፡ በታሪክ ውስጥ አንድ ሀገር የነበሩ ብዙ ሆነው አይተናል፡፡ ብዙ የነበሩ ሀገራት ደግሞ አንድ ላይ ተዋህደው አይተናል፤ ሰምተናል፤ እየሆነም ነው፡፡

ኢትዮጵያም በእነዚህ ውስጥ በአንዱ ወይንም በሌላው አልፋለች፡፡ ኢትዮጵያ ረጅም ታሪክ ያላት ሀገር ብትሆንም የተረጋጋ የፖለቲካ ሥርዓት ሳይኖራት ብዙ ክፍለ ዘመናትን ተሻግራለች፡፡ በአያሌው መንግሥታት ስልጣን የሚያስረክቡት በኃይል ሲሆን፤ ይህም ብዙ ዋጋ አስከፍሏታል፡፡

በአንድ ወቅት የኢትዮጵያ አካል የነበሩ እንደ ሀገረ ኤርትራ እና ጅቡቲ በታሪክ አጋጣሚ ራሳቸውን ችለው ሀገር ሆነዋል። እነዚህ ሁሉ የሆኑት ግን እንዲሁ በአንዲት ጀንበር አይደለም፡፡ በርካታ ውስጣዊና ውጫዊ ገፊ ምክንያቶች ነበሩ፡፡

በኢትዮጵያ አሁናዊ የፖለቲካ ትርክት ውስጥም ለሚስተዋሉ ችግሮች ብዙ መልክ ያላቸው አስተያየቶች ይሰማሉ፤ ይስተዋላሉም። አንዳንዶች በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ የሚስተዋለው ችግር ምንጩ ሕገ መንግሥቱ ነው የሚል ድምዳሜ አላቸው፡፡

ሕገ መንግሥቱ፤ ዘመናት የመጣንበትን የፖለቲካ ትርክትና ሥርዓት ብሎም ነባራዊ ዓለም ባገናዘበ ሁኔታ፤ በየጊዜው ለሚፈጠሩ የዓለም ፖለቲካ ቀውሶችና ከፋፋይ ባህሪያቶች ወይንም አባባሽ ምክንያቶችን እራሱን መታደግ የሚያስችሉ እንዳልሆነም ያመለክታሉ፡፡

ሕገ-መንግሥቱ ከብሔራዊ መግባባት አኳያ ገፊ ሁኔታዎችን የሚንከባከብና ለብሔራዊ መግባባትን በሰፊው ትኩረት ያልሰጠ ነው ብለው ይኮንኑታል፡፡ ከፌደራል ሕገ መንግሥት በትይዩ የተቀረፁ የክልል ሕገ መንግሥቶችም በዚህ የተዛባ እሳቤና ሀገራዊ ስሜት መሸርሸር ላይ ድርሻ የትዬሌለ ስለመሆኑ የሚናገሩ በርካቶች ናቸው፡፡

የሀገሪቱን ሰላምና መረጋጋት፤ ብሔራዊ አንድነት መጎልበት ካስፈለገ ሕገ መንግሥቱን መሻሻል ያስፈልጋልም ይላሉ፡፡ ከዚህ ተቃራኒ የቆሙ ደግሞ፤ የሀገሪቱ አሁናዊ ፈተናዎች ከሕገ መንግሥት ትርክት የዘለለ ወደኋላ ብዙ ክፍለ ዘመናትን የሚጓዝና የተነባበሩ የቤት ሥራዎች ናቸው የሚል የመከራከሪያ ሃሳብ አላቸው።

ችግሮቹ በጊዜያቸው በወቅቱና በአግባቡ መፍትሔ ሳይበጅላቸው መቆየቱ፤ የችግሮች ሁሉ ችግር ነው፤ ችግሮቹን ለመፍታት ወደኋላ ተመልሰን እውነታውን በአግባቡ መገንዘብ ያስፈልገናል ይላሉ።

በርግጥ ለኢትዮጵያ ፈተና የሆናባትን ችግር ከሥር መሰረቱ ማወቅና መረዳት፤ መፍትሔም ማፈላለግ ተገቢ ነው፡፡ አሁን ላይ በልዩነት መነፅር ውስጥ የምትዋልል ሀገር ለነገው ትውልድ አስቀምጠን ማለፍ ለታሪክ ተወቃሽነት፣ ለህሊና ፀፀት የሚዳርገን ነው።

ነገን ዛሬ እንስራ የሚል እሳቤና ፍልስፍና በዓለም ላይ በናኘበት በዚህ ዘመን እኛ በትናንት ላይ ቆመን መቆዘም ረብ የለውም። ለዚህም ከፋፋይ ትርክቶችን እየዘጋን ወደ አሰባሳቢ ትርክቶች የሚወስዱ መንገዶችና አሰራሮች ብሎም የርዕየተ ዓለም እሳቤዎችም ተግባራዊ ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡

 ለዚህ ደግሞ ከሁሉም በላይ ወጣቱ ትውልድ አደባባይ የሞሉ ትርክቶችን ከራሱ ከማህበረሰቡና ከሀገር ተጠቃሚነት አንጻር በሰከነ መንፈስ ሊመረምራቸው ይገባል። ለምን ብሎ የሚያጠይቅ እና ሁኔታዎችን በጥልቀት የሚመረምር መሆን አለበት፡፡

በርካታ ሀገራት ብዙ ፈተናዎችን አልፈው አሁን ላይ ደርሰዋል፡፡ ለዘመናት ለሁለት ተከፍለው ይቆራቆዙ የነበሩ ሀገራት ዛሬ አንድነታቸውን አጠናክረው በዓለም ላይ የሚፈሩ ሆነዋል፡፡ ለዚህም አባት ሀገር ጀርመንን ማንሳት ጥሩ ምሳሌ ነው፡፡

የጀርመን ድምፅ ሬዲዮ የጀርመን መዋሃድን 30ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ ባሳፈረው ጽሑፍ እንዲህ ሲል ያትታል፡፡ ‹‹አራት አሥርት ዓመታት ከዘለቀው የቀዝቃዛው ጦርነት በኋላ ነበር በጎርጎሮሳዊው ጥቅምት 3 ቀን 1990 ምሥራቅና ምዕራብ ጀርመን በይፋ የተዋሃዱት። ከውህደቱ አስቀድሞ በምሥራቅ ጀርመን እየበረታ በሄደው ተቃውሞ ጫና ሰበብ በጎርጎሮሳዊው ኅዳር 9 ቀን 1989 ጀርመንን ለሁለት የከፈለው የበርሊን ግንብ ፈረሰ፣ ድንበሩም ተከፈተ። ግንቡ ከፈረሰ ዓመት ሊሆነው ጥቂት ሲቀር የዛሬ 30 ዓመት የሁለቱ ጀርመኖች ውህደት እውን ሆነ። ከውህደቱ በኋላ ብዙ እድገቶች ተመዘገቡ›› ሲል የአንድነት ኃይልነትን ያወሳል፡፡ ይህ ታሪካዊ ክስተት አሰባሳቢ ትርክት የቱን ያህል ኃይል እንደሚያጎናፅፍ አመላካች ነው፡፡

እኛም እንደ ሀገር መሰረታችንን ለማጽናት ከሁሉም በላይ አንድ በሚያደርጉን ትርክቶች ዙሪያ አብዝተን መሥራት ይኖርብናል። ይህንን ለማድረግ ደግሞ ትርክቶቻችን መሠረት ሊያደ ርጉባቸው በሚገቡ እውነታዎች ዙሪያ የጋራ መግባባት ላይ ልንደርስ ይገባል።

‹‹በሽታውን ያልተናገረ፤ መድኃኒት አይገኝለትም›› እንዲሉ አበው፤ በውስጣችን የተሰነቀሩ አያሌ የተዛቡ አስተሳሰቦችን ማረም ይገባል፡፡ እንደ ሀገር ብሔራዊ መግባባትን ለማምጣትም ፖለቲከኞች፣ የመገናኛ ብዙሃን አውታሮች፣ ምሁራን፣ ማህበረሰብ አንቂዎች፣ እልፍ ኪሎ ሜትሮችን በመጓዝ መፍትሔዎች ምን መሆን አለባቸው በሚለው ላይ መሥራት ይጠበቅባቸዋል፡፡

ለብሔራዊ መግባባት መሠረት የሚጥሉ እና የነጠሩ ሃሳቦችን በማፍለቅ፣ በመተንተን፣ በማስገንዘብ እና ለሀገራዊ አንድነት የተሻሉ እንዲሁም አብዛኛው ሊያስማሙ ወይንም ሊያቀራርቡ የሚችሉ አማራጮችን በማፍለቅ፤ ሀገራችንን እየተፈታተናት ከሚገኘው አደገኛ ትርክት ወደ አሰባሳቢ ትርክት ልንመጣ ይገባል።

ሀገራዊ ተክለ ቁመና በሚያላብሱ ቅቡል ብሎም ዘመን ተሻጋሪ እሳቤዎች ላይ ተመስርተን የነገይቱን ኢትዮጵያ በማይናወጥ ጠንካራ መሠረት ላይ ማዋቀር ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ ጊዜው አላለፈም፤ ብዙ ጊዜ አለን።

እንደ ሀገር ድባቴ ውስጥ ያስገቡን ከዛም አልፈው፤ በመከፋፈል፣ በመነታረክና እርስ በእርስ ወደ መቆራቆዝ የወሰዱንን የተዛቡ ትርክቶችን ማስተካከል አለብን፤ ለዚህ ደግሞ ሰፊ የታሪክ ሀብት፤ ከትናንት የወረስናቸው የአኗኗር ዜይቤዎች አሉን፡፡

የነገው ትውልድ መልካም ልምድና ትምህርት የሚቀስምበት የኢትዮጵያን ሕልውና በላቀ ደረጃ የሚያስቀጥልበት የጋራ ትርክት መፍጠር የዚህ ትውልድ አሁናዊ ሥራ ነው፡፡ ለሀገር አንድነት ፈተና የሆኑ ከፋፋይ እና ከስንዴ ምርት ለመቀላቀል የሚቋምጡ እንክርዳድ የሆኑ አስተሳሰቦች ከታሪክ ገጽ ማስወገድም ዘላቂ መፍትሔ ነው፡፡

ክፍለዮሐንስ አንበርብር

 አዲስ ዘመን ሰኞ ኅዳር 10 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You