– በቴክኖሎጂ እጥረት በዓመት 7 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሊትር ደም ይባክናል
– የዶሮ ቄራ ለሚገነቡ ድጋፍ ይደረጋል
አዲስ አበባ፡- በአሁኑ ወቅት አገልግሎት እየሰጠ ያለውን የአዲስ አበባ ቄራዎች ደርጅትን የሚተካ ዘመናዊ ቄራ ለመገንባት ታስቦ 70 ሚሊዮን ዩሮ በብድር ቢገኝም በችግሮች ምክንያት በተያዘለት መርሐ ግብር መጀመር አለመቻሉ ተገለጸ፡፡
የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ንብረቱ በቃ ለአዲስ ዘመን እደገለጹት፤ በመሃል ከተማዋ የሚገኘው የአዲስ አባባ ቄራዎች ድርጅት አሁን ካለው የከተማዋ ህዝብ ፍላጎት አንፃር አይመጣጠንም፡፡ በመሆኑም አዲስ ቄራ ለመገንባት ታስቦ ብድር ቢገኝም ተቋሙ ባጋጠመው ችግር ምክንያት ግንባታውን መጀመር አልተቻለም፡፡
ከስምንት ዓመታት በፊት የአዋጭነት ጥናት ተከናውኖ ሀብት ማፈላለግ ሥራው ተጠናቆ ከፈረንሳይ የልማት ድርጅት በአነስተኛ ወለድ 70 ሚሊዮን ዩሮ በብድር እንዲሁም 500 ሺ ዩሮ ደግሞ በዕርዳታ ተገኝቶ ይህም በ2010 ዓ.ም በህዝብ ወተካዮች ምክር ቤት ቀርቦ በአዋጅ መፅደቁን አቶ ንብረቱ አመልክተዋል፡፡ በዚህ መሰረትም ግንባታውንም እ.ኤ.አ በ2019 ዓ.ም ለመጀመር ታቅዶ ዓለም አቀፍ ጨረታ ወጥቶ እንደነበር ገልጸዋል፡፡
ብድሩ ከተገኘ በኋላ የአካበቢ ጥናት፣ የቄራውን ዲዛይንና ተያያዥ ሥራዎችን የሚያከናውን ድርጅት ለመምረጥ ዓለም አቀፍ ጨረታ ወጥቶ አንድ የፈረንሳይ ኩባንያ ማሸነፉን አመልክተዋል፡፡ ይሁንና በኢትዮጵያ የገቢዎች ህግ መሠረት በአገሪቱ ውስጥ አንድ ደርጅት ከ183 ቀናት በላይ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚቆይ ከሆነ የቲን ቁጥርና ንግድ ፈቃድ ማውጣት፣ የተጨማሪ እሴት ታክስ መክፈል እንዳለበት የሚደነግግ በመሆኑ አማካሪ ድርጅቱ ይህን ለማድረግ ፈቃደኛ ሳይሆን መቅረቱን አስረድተዋል፡፡
ይህም አሠራሩ አገሪቱን የታክስ ህግ የሚፃረር በመሆኑ ጨረታው መታገዱን አስገንዝበዋል፡፡ በመሆኑም ሌላ ዓለም አቀፍ ጨረታ ለማውጣት መገደዱን አቶ ንብረቱ አመልክተዋል፡፡
በተጨማሪም ከቦታው መረጣ ጋር በተያያዘም የሲቪል አቬየሽን ባለስልጣን የተቃረበ የነበረ በመሆኑ ተቃውሞ ገጥሞት
እንደነበር ጠቁመዋል፡፡ ለግንባታው የሚሆን ቦታ ማፈላለግና ወሰን ማስከበር አስቸጋሪ ሆኖ መቆየቱና በአሁኑ ወቅትም ቢሆን የወሰን ማስከበር ሥራ ቢከናወንም በቦታው ላይ ሰዎች መስፈራቸውንና አንዳንዶች ደግሞ ከካሳ ክፍያ ጋር በተያያዘ ቅሬታ መኖሩን ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል፡፡
እንደ ማኔጂንግ ዳይሬክተሩ ገለፃ፤ በአሁኑ ወቅት ፕሮጀክቱን ሊያከናውኑ የሚችሉ ድርጅቶችን ለመምረጥ ዓለም አቀፍ ጨረታ የወጣ ሲሆን 15 ድርጅቶች ተመርጠው በአሁኑ ወቅት የተለያዩ ሂደቶችን አልፈው አራት ድርጅቶች ብቻ ቀርተዋል፡፡ አሸናፊዎችም እስከ ሀምሌ 30 ቀን 2011 ዓ.ም በግልፅ የሚለዩ ይሆናል፡፡ በተጨማሪም በንፋስ ስልክ ወረዳ 01 ካርታ ያለው 20 ሄክታር መሬት የታጠረ ሲሆን፤ ፕሮጀክቱ በፈረንጆቹ አቆጣጠር ከ2024 እስከ 2025 ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በአሁኑ ወቅት አገልግሎት እየሰጠ ያለው የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት የሚያረካና በቴክኖሎጂ የተደገፈ አገልግሎት እየሰጠ አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡ ለአብነትም አንድ በሬ ሲታረድ 48 ከመቶ የሚሆነው ተረፈ ምርት መሆኑንና ይህንን በተፈለገው መጠን ጥቅም እየሰጠ አለመሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
በየቀኑ ቄራው በአማካይ 800 በሬዎችን የሚያርድ መሆኑንና ከአንድ በሬ ከ20 እስከ 25 ሊትር ደም እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡ በይህም በዓመት 7 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሊትር መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ ይህ ደም ለመድሃኒት፤ ለመኖ እና የተለያዩ አገልግሎቶች ሊውል ሲገባው በቴክኖሎጂ እጥረት የተነሳ ጥቅም ላይ እንደማይውል አስረድተዋል፡፡
በተጨማሪ በርካታ ተረፈ ምርቶች ጥቅም ላይ እንደማይውሉ ተናግረው፤ ሆኖም የውጭ ገበያ በማፈላለግ የተጀመሩ ሥራዎች መኖራቸውን አብራርተዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ አገልግሎት እየሰጠ ያለው ቄራ የዘመናዊ ቴክኖሎጂ ችግር እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡ በተለይም የጎድንና ፍሪንባ መቁረጫና መበለቻ ቢላዎች በውጭ ምንዛሪ ከውጭ የሚገዙ በመሆኑ ከዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም እያሳጣ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በሌላ በኩልም በኢትዮጵያ አሁን ከምትሰጠው የቄራ አገልግሎት በተጨማሪ የዶሮ ቄራ ብትጀምር ተጠቃሚ እንደምትሆን አቶ ንብረቱ ጠቁመው፤ በተለይም ባለሀብቶች የዶሮ ቄራ የመገንባት ውጥን ካላቸው የክህሎትና እውቀት ድጋፍ እንደሚደረግ አስገንዝበዋል፡፡
የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ቄራ የሚል ስያሜ በአፄ ኃይለስላሴ ቤተሰቦች 1949 ዓ.ም የተመሰረተው ይኸው ድርጅት በአሁኑ ወቅት የከተማው የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ውስጥ ተካቶ ይገኛል፡፡ ድርጅቱ በአሁኑ ወቅት ከ2004 እስከ 2010 ዓ.ም 1ነጥብ6 ሚሊዮን በሬዎችንና 986ሺ በግና ፍየሎችን ያረደ ሲሆን፤ በ2011 ዓ.ም ደግሞ 388ሺ እንስሳት የማረድ ውጥን አለው፡፡ ቋሚ፣ የኮንትራት፣ ጊዜያዊ ባለሙያዎችን ጨምሮ 1ሺ 500 ሠራተኞች አሉት፡፡
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 17/2011
ክፍለዮሐንስ አንበርብር