ነገረ የሴራ ትንተና፤

 ሰሞነኛ መነጋገሪያ ከሆኑ ጽንሰ ሀሳቦች አንዱ የሴራ ትንተና ነው።የሴራ ትንተና በእኛ የተጀመረ በእኛ የሚቋጭ አይደለም። በመላው አለም ያሉ ሀገራትንና መንግሥታትን እየፈተነ ያለ ፖለቲካው ደዌ ነው። እንደ አሜሪካ ባሉ ሀገራትም ሆነ ገና በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት ፖለቲካ ያለ የሚኖር ሕመም ነው። ዴሞክራሲን ግልጽነትንና ተጠያቂነትን እንዲሁም ጠንካራ ሚዲያና ተቋማት በገነቡ ሀገራት የሴራ ትንተና የሚያስከትለው ጉዳትና ዳፋ የጎላ ባይሆንም የሚናቅ ግን አይደለም።በተቃራኒው ዴሞክራሲን ግልጽነትንና ተጠያቂነትን እንዲሁም ጠንካራ ሚዲያና ዴሞክራሲያዊ ተቋማት ባልገነቡ ሀገሮች ግን መጠራጠርን ልዩነትን ጥላቻንና በቀልን እየጎነቆለ የሀገርን ህልውና አደጋ ላይ እስከመጣል ይደርሳል። ለመሆኑ የሴራ ትንተና ምንድን ነው?

ተፅዕኖ ፈጣሪ ሰዎች ፣ ባለስልጣናት አልያም የተወሰኑ የፖለቲካ ፣ የርዕዮተ አለምና የኢኮኖሚ ቡድኖች ሚስጥራዊ ዕቅድ ውጤት የሆነ ሁነት ወይም ክስተት የሴራ ትንተና ወይም ኀልዮት ሲል ይበይነዋል የእንግሊዘኛው መዝገበ ቃላት ሜሪያምዌቢስተር ። የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናትና ምርምር ማዕከል በ1993 ዓ .ም ባሰናዳው የአማርኛ ቋንቋ መዝገበ ቃላት ደግሞ ፤ አድማ ፣ ሴራ ዱለታ ሲል በአጭሩ ይተረጉመዋል።

በባለስልጣናት ፣ በመንግሥት ሆን ብሎ ጉዳት ለማድረስ በሚስጥር የሚፈፀም ደባም የሴራ ትንተና ነው ሲሉ ድርሳናት ትርጉሙን ሰፋ ያደርጉታል። ታዋቂው የፖለቲካ ሊቅ ማይክል ባርኩን በበኩሉ ኀልዮቱ አፅናፈ አለም universe በአፈታት በአቦሰጥ ሳይሆን በንድፍ በdesign ትመራለች በሚለው ተረክ ላይ የተዋቀረ ነው ይላል ። እንደ ባርኩን ትንተና የሴራ ትንተና ሶስት መገለጫዎች አሉት ።

የመጀመሪያው ምንም ነገር በአጋጣሚ አይሆንም የሚለው ሲሆን ፤ ሁለተኛው ደግሞ ምንም ነገር ለይተን እንደምናየው ፣ እንደመሰለን አይደልም ሲል ፤ ሶስተኛው ደግሞ ሁሉም ነገር እርስ በርሱ የተያያዘ ነው ብሎ ያምናል።ሌላ ባህሪው ይላል ባርኩን ውሸት መሆኑን በመረጃ ለማስተባበል ፈታኝ መሆኑ ነው። መነሻው የመሪዎች ግድያ ሲሆን ዘመኑም ከ20ኛው ክፍለ ዘመን መባቻ አንስቶ መሆኑ ድርሳናት ያትታሉ ። ከእያንዳንዱ ክስተት ጀርባ ሴራ ደባ አለ በማለት በዜጎችና በሕዝቦች መካከል መጠራጠርን የሚቀፈቅፍ ክፉ ትንተና ነው።

በታላቁ መጽሐፍ “ በእግዜአብሔር እናምናለን። “ እና “ አይኖቹ በምድር ሁሉ ያያሉ ። “ ከሚለው ቅዱስ ቃል ላይ ተመስርቶ በአሜሪካ የአንድ ዶላር ላይ ፈጠሪ ሁሉን እንደሚያይ ፤ አሜሪካ በቅጥሩ በጥበቃው ስር እንደሆነች የሚወክለውን ምስል ( the all seeing eye ) ሳይቀር በአሜሪካ መስራች አባቶች የተሸረበ ሴራ ተደርጎ መቆጠሩ ትንተናው ምን ያህል ጥርጣሬን ለመዝራት ምቹ እንደሆነ ያሳያል።

አንዳንድ የስነ ልቦና ሊቃውንት የሴራ ትንተና ወይም ኀልዮቱ በማኪያቬሊያዊ ፅንሰ ሀሳብ በዜጋውና በሕዝብ መካከል ፍርሀትን በመንዛት ላይ ያተኮረ መሆኑን ይተነትናሉ ። በአለማችን በሴራ ኀልዮት አብነትነት በቀዳሚነት ከሚጠቀሱት መካከል የአሜሪካዊ 35ኛ ፕሬዚዳንት ጆን ኤፍ ኬኔዲ ግድያ ላይ የሀገሪቱ የስለላ ድርጅት ሲ አይ ኤ እጁ አለበት የሚለው ተደጋግሞ ይጠቀሳል።

በ1971 ዓ.ም አፓሎ የተሰኘች የአሜሪካ መንኮራኮር ለመጀመሪያ ጊዜ ጨረቃ ላይ ማረፏን የሚክደው የሴራ ትንተና ፤ በተለምዶ በ9/11 አልቃይዳ በአለም የንግድ ድርጅት ህንፃዎች ፣ በፔንታጎንና በመንገደኞች አውሮፕላን ከ3ሺህ በላይ አሜሪካውያንና የውጭ ዜጎች ባለቁበት የሽብር ጥቃት አሁንም ሲ አይ ኤ ተሳትፎበታል የሚለው የሴራ ትንተና ፤ ኤች አይ ቪ / ኤድስን አሜሪካ ነች ጥቁሮችንና ሌሎች ለመጨረስ በቤተ ሙከራ የፈጠረችው ነው ፤ ኮቪድ 19ን ቻይና ናት የፈጠረችው የሚለውን እና የእንግሊዟን ልዕልት ዲያና ፈረንሳይ ፓሪስ በመኪና አደጋ የሞተችው በሀገሪቱ የስለላ ድርጅት ኤም አይ 6 እና ንጉሳዊ ቤተሰቡ ሴራ ነው የሚሉ ይገኙበታል።

የሴራ ትንተና ባህሪያት፦

ሀ . ጥርጣሬን ማንበር ፤

እነዚህን እና ሌሎቸን የሴራ ትንተናዎች ወይም ኀልዮቶች የሚያመሳስላቸው ሕዝብ በመንግስቱ ላይ ጥርጣሬ እንዲያድርበት ፣ እምነቱን እንዲያጣ በተፅዕኖ ፈጣሪዎች የሚሸረቡ መሆናቸው ነው ።

ለ . የሌለ ምስል መከሰት ፤

የሴራ ኀልዮት የማይገናኙ ሁነቶችን ነጥቦችን በማገናኘት በማገጣጠም ትርጉም መስጠት ፣ ምስል መከሰት መለያ ባህሪው ነው ።

ሐ . ተአማኒነት ፣ ተቀባይነት፤

አሜሪካውያኑ የሴራ ኀልዮት አጥኝዎችና የፖለቲካ ሳይንስ ሊቃውንት ጆሴፍ ኡዚነስኪ እና ባልንጀራው ከአምስት አመታት በፊት በሀገረ አሜሪካ ባካሄዱት ጥናት የሴራ ኀልዮት ጾታ ፣ ሀይማኖት ፣ ዘር ፣ ዕድሜ ሳይለይ ተቀባይነት ታማኝነት ቢኖረውም በወጣቶች ግን ይበልጥ ተቀባይነት እንዳለው አረጋግጠዋል ።

የተፈጥሮ አደጋዎች ፣ እንደ አሜሪካው የ2001 ዓም ያሉ የሽብር ጥቃቶች ፣ የስራ አጥነት ፣ ተስፋ መቁረጥና ድብርት ወጣቱን የትንተናው ሰለባ እንዳደረገው ጥናቱ አክሎ ጠቁሟል።

መ . የቡድን ማንነት፤

አንድ የህብረተሰብ ክፍልን ማለትም ነጭ ፣ ጥቁር፣ አይሁድ ፣ አስላም ኢላማ ያደረጉ የሴራ ኀልዮቶችን መንዛት ሌላው መለያው ነው። ኤች አይ ቪ / ኤድስ አሜሪካ ጥቁሮችን ለመጨረስ በቤተ ሙከራ የተፈጠረ በሽታ ነው ። ወደሀገራችን ስንመጣ ደግሞ በመካከላችን ጥላቻን፣ መጠራጠርን ለመንዛት በመሳሪያነት እያገለገለ መሆኑን ያጤኑአል።

ሰ . ፖለቲካዊ ርዕዮተ አለም፤

ሕዝበኝነት ፣ ሶሻሊዚም ፣ ካፒታሊዝም ቀኝ ዘመም ሆነ ግራ ዘመም አይዶሎጂዎች የየራሳቸው የሴራ የደባ ኀልዮት ትርክቶች አሏቸው ። ሕዝበኞች ሉላዊነትን ካፒታሊዝምን አውሮፓ ሕብረትን ኔቶን ስደተኝነትን የሚያጠለሹ ፣ የሚያሰየጥኑ ተረኮችን ሲነዙ ። ግራ ዘመሞች በበኩላቸው ሚዲያውንና የፖለቲካ ፓርቲዎችን በባለጠጋዎች ጭፍራነት የሚወነጅሉ የሴራ ኀልዮቶችን ያነብራሉ። የተቀሩትን አይዶሎጂዎች አሰላለፍ በዚህ አግባብ መለየት ይቻላል ።

ረ . የትምህርት ደረጃ ፤

መማር የሴራ ትንተናን ወይም ኀልዮት ምርኮኝነትን ሊቀንስ ይችላል የሚል አጠቃላይ ዕምነት ቢኖርም የእነ ኡዚነስኪ ጥናት የደረሱበት መደምደሚያ ግን ለየቅል ነው። የድህረ ምረቃ ትምህርታቸውን ከተከታተሉ 5 አሜሪካውያን አንዱ ለኀልዮት ልባቸውን ጆሮአቸውን ቀልባቸውን አሳልፈው የሰጡ ናቸው ይላል ። በእነዚህ ባህሪያት ማጥለያነት የትኛው የሴራ ኀልዮት ትርክት እንደሆነ ለመለየት እና አበክሮ ጥንቃቄ ለማድረግ ከውዥንብር ከመደናገር ለመውጣት ይቻላል።

የሴራ ኀልዮቶችን ማለትም የሴራ ትንተናዎችን እውነትነት እና ሀሰትነት ፈትኖ ማጣራት ኃላፊነት የሚሰማው ዜጋ ሚዲያና መንግሥት ቀዳሚ ተግባር ሊሆን ይገባል። በዘመነ ማህበራዊ ሚዲያ በጥቂት ደቂቃዎች ሀገር የሚያዳርሱ የሴራ የደባ ዋና ዋና ወሬዎችን እግር በእግር እየተከታተሉ በተጨባጭና ሀቀኛ መረጃዎችን ፉርሽ ማድረግ ማክሸፍ ካልተቻለ ሊፈጠረ የሚችለውን ሀገራዊ አደጋ እያየነው ነው። ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው እንዲሉ ፤ ሀገር፣ ወገን በበሬ ወለደ ወሬ ሴራ እንዳይፈታ አበክሮ በቅንጅትና በርብርብ ሊሰራ ይገባል ።

መደበኛ ሚዲያዎች ከእነ ማህበራዊ ገጾቻቸው መረጃን በጥራት በፍጥነት በሰፊ ተደራሽነት 24/7 ማሰራጨት ይጠበቅባቸዋል። አሰራራቸውን አደረጃጀታቸውን እና ብቃታቸውን ከዚህ አንጻር ቆም ብለው መፈተሽ ሰልፋቸውን ማሳመር ይጠበቅባቸዋል። ልሒቃን የፖለቲካ ፓርቲዎችና ተከታዮቻቸው በመጨረሻም መላ ሕዝብ አሉባልታ የሴራ የደባ ወሬ ሲሰሙ በተቻለ መጠን ማጣራት በተለያዩ ምንጮች ማመሳከር ፣ ማገናዘብና ማረጋገጥ ይጠበቅባቸዋል። ስውር አጀንዳ ያላቸው ኃይላት መጠቀሚያ እንዳያደርጓቸው ከመቼውም ጊዜ በበለጠ መጠንቀቅ ይኖርባቸዋል። መንግሥት ራሱም ከሰራ ትንተና በማውጣት አርዓያነቱን ሊያስመሰክር ይገባል።

ይሁንና የሴራ ትንተና ተዋንያን በቀላሉ መለየት አዳጋች ስለሆነ ኀልዮቱ የተዋቀረው መነሻው በውል በማይታወቅ ሚስጥራዊ አካል መሆኑ። የእያንዳንዱ ሴራ ስውር አላማ ሕዝብን ፣ ስልጣንን፣ ኢኮኖሚውን መልሶ ከመቆጣጠር የቡድን ፍላጎት የሚመነጭ ተፅዕኖ ፈጣሪ ሰዎችና ተቋማት የሚሳተፉበት በመሆኑ ለመቆጣጠር ለማክሸፍ የሚደረገውን ጥረት አዳጋች ያደርገዋል ። ይሁንና እነዚህ ትንተናዎች የዳበሩ የዴሞክራሲ ተቋማትና ሚዲያዎች ባሉባቸው ምዕራባውያን ዘንድ ያላቸው ተቀባይነት እንደኛ ካሉ ሀገራት ጋር ሲነጻጸሩ ያን ያህል ተፅዕኖ የማያሳድሩ መሆናቸውን ጥናቶች ያመለክታሉ ።

በአንጻሩ የዳበሩ ዴሞክራሲያዊ ተቋማት በተለይ ጠንካራ ሚዲያዎች ባልደረጁባቸው ሀገራት የሚያሳድሩት ተፅዕኖ ከፍ ያለ መሆኑን እነዚሁ ጥናቶች ያረጋግጣሉ ። የተቀናጀ የደባ የሴራ ፖለቲካ የሀገራችንን መጻኢ ዕድልም አደጋ ላይ እንደጣለው ከልብ ልብ ማለት ያስፈልጋል ። መንግሥት ሚዲያዎች ሀገር ወዳድ ዜጎች የችግሩን አደገኝነት የሚመጥን የተቀናጀና የተናበበ ስራ መስራት ይጠበቅባቸዋል ።

በተለይ መንግሥትና ሚዲያው አሉባልታው ወደ ሴራ ወይም ደባ ኀልዮት ፖለቲካ ከማደጉና በሕዝብ ዘንድ መደናገርን መጠራጠርን ውዥንብርን ከመፍጠሩ በፊት የሆነውን ከስር ከስር ለሕዝብ ማሳወቅ ይገባል። ቀደም ሲል እንዳሳሰብሁት አሰራርን አደረጃጀትን ከዚህ አንጻር መቃኘት መከለስ ያስፈልጋል ። የመንግሥት አሰራር ከዚህ ይበልጥ ግልፅ ፣ አሳታፊና ተጠያቂ ሊሆን ይገባል ።

የውሸት ፣ የተበረዘና የተዛባ መረጃ እና የሴራ ፖለቲካ አይደለም ፖለቲካዊ ግንዛቤያችን ዝቅተኛ ለሆነው እና የዳበረ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ላላቆምነው ይቅርና ለአሜሪካና ለምዕራባውያንም ፈተና ሆኗል ። የ2016ቱን የአሜሪካ ምሮጫ ፣ የእንግሊዝ ከሕብረቱ የመነጠል ሕዝበ ውሳኔን፤ የአሜሪካ 2020 ምርጫ ፤ የፈረንሳይ ምርጫ ፤ ወዘተረፈ ያስታውሷል ።

“ በዚህ ምርጫ ጮክ ብለው ከተሰሙ የሴራ ትንተናዎች ዲሞክራቶች ግራ አክራሪ ሶሻሊስት እና የባዕድ አምልኮ ተከታይ ናቸው ። ”የሚሉት ይገኙበታል ። የኩባን ሶሻሊዝም ሸሽተው በፍሎሪዳ በብዛት ነዋሪ የሆኑ ኩባ አሜሪካውያን ትራምፕን የመረጡት ከፍ ብዬ የገለጽሁትን የሴራ ወሬ አምነው እንደሆነ ሲኤንኤን በምርጫው ሰሞን አውርቶናል ።

ትራምፕ በአሜሪካ ታሪክ ሽንፈቴን አልቀበልም የሚሉት ራሳቸው አበክረው ምርጫው ሊጭበረበር ይችላል ሲሉ ያሟረቱትን ሟርት ሴራ ሰበብ አድርገው ነው ። እንደ ዋሽንግተን ፖስት ዘገባ ትራምፕ ከ20ሺህ በላይ ውሸቶችን በመዋሸት የነጩን ቤተ መንግስት ጥላሸት ቀብተውታል ። እሳቸው መች በዚህ ያበቁና እለት በእለት በቲዊተር ገጻቸው በሚያዥጎደጉዱት የሴራ ትንተና የተነሳ በአሜሪካውያን መካከል መከፋፈልን ፈጥረዋል ።

የምርጫው ሒደትና ውጤት ለዚህ ጥሩ አብነት ነው ። በአሜሪካ የተፈጠረውን ልዩነት ለማጥበብ ከአንድ ጊዜ በላይ ምርጫ ያስፈልጋል ያሉት ፕሬዚዳንት ኦባማ ፤ በገደምዳሜ የሚቀጥለውን የ2024 ምርጫም ዲሞክራቶች ማሸነፍ አለባቸው ማለታቸው ነው ።

ባራክ ሁሴን ኦባማ “ዘ ፕሮሚስ ላንድ “ የተሰኘውን አዲሱን መጻፋቸውን በዚያ ሰሞን ባስተዋውቁበት በቢቢሲ አርት የታሪክ ሊቅ ከሆነው ዴቪድ ኡሉሶጋ ጋር በነበራቸው ቃለ ምልልስ በአንድ የምርጫ ጊዜ “ የእውነትን መበስበስ “ ማስቀረት አይቻልም ። እንግዲህ የዴሞክራሲ ዋስና ጠበቃ በሆነችው እና የዴሞክራሲ ተቋማት በአስተማማኝ መሰረት የገነባችው አሜሪካ “እውነት” እንዲህ ፈተና ውስጥ ከገባች የእኛ “ እውነት “ በምን አቅሟና ጎኗ ትችለዋለች ።

አሜሪካ በዜጎቿ መካከል ልዩነትን በመጎንቆል ላይ የሚገኘውን የሴራ ትንትና የመቀልበስ ትልቅ ኃላፊነት ከፊት እንደሚጠብቃትም ፕሬዚዳንት ኦባማ ጠቁመዋል ። ፕሬዚዳንት ትራምፕ በ2016 ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህ በዜጎች መካከል ያለው ልዩነት ሰፍቷል ። በእንቅርት ላይ እንዲሉ በማንነት ላይ ለምትንጠራወዘው ሀገራችን የሴራ ትንተና ምን ያህል ፈታኝ እንደሆነ በተግባር እያየነው ነው ።

በተለያዩ ምክንያቶች በዜጎች መካከል የተፈጠሩ ልዩነቶችን ለማጥበብ የሚደረገው ጥረት ለአንድ ወገን ብቻ ማለትም ለፖለቲከኞች ወይም ለመንግሥት የሚተው ሳይሆን የመላ ዜጋውን ተሳትፎ ፤ መዋቅራዊ ለውጥ እና በዜጎች መካከል የመደማመጥ ባህልን ማጎልበት እንደሚጠይቅ ፕሬዚዳንት ኦባማ ይመክራሉ። የሴራ ኀልዮት ፣ ሚስ ኢንፎርሜሽን እና ዲስኢንፎርሜሽን እርስ በእርስ የሚመጋገቡና የሚናበቡ ሁነቶች ናቸው ።

ሚስ_ና_ዲስ ኢንፎርሜሽን ተመሳሳይ ትርጉም ያላቸው ስለሚመስል እየተተካኩ ጥቅም ላይ ሲውሉ ይስተዋላል ። ብያኔአቸው ግን ለየቅል ነው ። ሚስኢንፎርሜሽን የተሳሳተ ወይም አሳሳች መረጃ ሲሆን ዲስኢንፎርሜሽን ደግሞ እውነትን ለመሸፋፈን ወይም የሕዝብ አስተያየት ላይ ተዕጽኖ ለማሳደር ሆን ተብሎ የሚነዛ የሀሰት መረጃ ነው ።

በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)

ሻሎም ! አሜን።

አዲስ ዘመን እሁድ ኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You