ከመስከረም 29 እስከ ጥቅምት 28 ቀን 2016 ዓ.ም በቆየው የሳይንስ ሙዚየም የቱሪዝምና ሆስፒታሊቲ አውደ ርዕይ ላይ በርካታ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል። አውደ ርእዩን በአካል 170 ሺህ የሚጠጉ በዲጂታል አማራጭ ደግሞ 9 ሚሊዮን አካባቢ የሚደርሱ ጎብኚዎች እንደተመለከቱት መረጃዎች አመልክተዋል። በአውደ ርዕዩ ተሳታፊ ከሆኑ ተሳታፊዎች መካከል የሁሉም ክልሎች ባህልና ቱሪዝም ቢሮዎች ይገኙበታል።
ተቋማቱ መድረኩን በክልላቸው ያሉትን የመስህብ ሀብቶች፣ የባህል፣ የተፈጥሮ፣ የታሪክና መሰል የቱሪዝም ዘርፍ አቅሞች አሳይተውበታል። አውደ ርዕዩ ከሌሎች፣ ከዘርፉ አንቀሳቃሾች ጋር ግንኙነት መፍጠር ያስቻለ መድረክ በመሆኑም አቅማቸውን ለማስተሳሰርና በጋራ ለአንድ ዓላማ ለመስራት የሚያስችል አጋጣሚም ፈጥረዋል።
የክልሎቻቸውን የቱሪዝም ዘርፍ ወክለው በአውደ ርዕዩ ላይ ተሳታፊ ከነበሩት መካከል የደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ክልል ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ይገኝበታል። በቢሮው የባህል ታሪክና ቅርስ ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ወንድሙ ለማ አውደ ርእዩን የክልሉን የቱሪዝም እምቅ አቅሞች ለማስተዋወቅ፣ ለመሸጥና ከሌሎች ከክልሎች እና ከተለያዩ የቱሪዝም ተቋማት ጋር ትውውቅና ትስስር ለመፍጠር እንደተጠቀሙበት ይገልፃሉ። እሳቸው እንዳሉት፤ ክልሉ በግብርና ንብ በማነብ፣ በከብት እርባታ፣ ወተትና ቅቤ፣ በቡና፣ በኮረሪማ እንዲሁም በማእድን ሀብቱ ይታወቃል። የማጂ ወርቅ ልዩ የክልሉ መለያ ነው።
በስፍራው በተገኘንበት ወቅት ስለክልሉ የቱሪዝም መስህቦች ማብራሪያ የሰጡን አቶ ወንድሙ፣ ‹‹ደቡብ ምእራብ መጥው በአጋጣሚ አዳልጦት ቢወድቁ እንዳይደነግጡ፤ ሊወድቁ የሚችሉት ማር ወይም ቅቤ ላይ ሊሆን ይችላል። ሲነሱም በአንድ እጅዎ የማጂን ወርቅ፣ በሌላው እጅዎ ደግሞ የክልሉን ቡና፣ ኮረሪማ ይዘው ሊሆን ይችላል›› በማለት ክልሉ ምን ያህል በተፈጥሮ ሀብት እምቅ አቅም እንዳለው ገልጸውልናል። ባለሀብቶች በልዩ ልዩ ኢንቨስትመንት ዘርፎች የተሰማሩበት ክልል መሆኑንም ነው ያስታወቁት። በተፈጥሮ፣ በታሪክና በብሄር ብሄረሰቦች ባህል መስህብነቱ ታይቶ የማይጠገብ ሀብት እንዳለው ተናግረዋል።
ዳይሬክተሩ የክልሉ ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ የክልሉን የቱሪዝም ሀብቶች ለማስተዋወቅና የሀገር ውስጥ ጎብኚ ወደ ስፍራው እንዲያቀና ለማበረታታት በአውደ ርእዩ መገኘቱን ይገልጻሉ። እሳቸውም እነዚህን እምቅ ሀብቶች ወሩን ሙሉ ማስተዋወቃቸውን ይናገራሉ።
በዋናነት በቅርብ ጊዜ ውስጥ ተገንብቶ የተጠናቀቀውና በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የተመረቀው የገበታ ለሀገር ኮይሻ ፕሮጀክት አካል የሆነው ”ሀለላ ኬላ” ሪዞርት ፕሮጀክት ያለበት ክልል መሆኑን ጠቅሰው፣ ፕሮጀክቱ የሚገኘው በዩኔስኮ ለማስመዝገብ በተያዘው የሀላላ ኬላ ቅርስ በሚገኝበት አካባቢ እንደሆነ ጠቁመዋል። አንድ ሺህ 870 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ሀይል የሚያመነጨው የጊቤ ሶስት ሀይል ማመንጫ የሚገኘውም በዚያው አካባቢ መሆኑን ይጠቅሳሉ። ግድቡ የፈጠረው ሰው ሰራሽ ሀይቅ የሀላላ ኬላ ሌላው ውበት መሆኑንም ነው ያስታወቁት።
እሳቸው እንዳብራሩት፤ ሀላላ የድንጋይ ካብ ከ1532 እስከ 1822 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ ነው የተገነባው። ግንባታውም 350 ዓመታትን ወስዷል። በዳውሮ ንጉስ የተጀመረው የዚህ ካብ ግንባታ ንጉሱ ብቻ ከ30 ዓመት በላይ ግንባታውን ማካሄዳቸውን ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል።
በስራው ላይም የህዝቡ ተሳትፎ ከፍተኛ መሆኑን ዳይሬክተሩ ጠቅሰው፣ በመሪነታቸው፣ ታላቅ ራዕይን አስተባብረው ለማስገንባት በማቀዳቸው ምክንያት ለውለታቸው በሚል ካቡ በእሳቸው ስም እንዲጠራ መደረጉን ይገልፃሉ። የድንጋይ ካቡን እሳቸው ቢያስጀምሩትም 13 ነገስታት በግንባታው እንደተሳተፉበት ይናገራሉ። የሀላላ ኬላ ሪዞርት እርሱን መሰረት በማድረግና የቱሪዝም መሰረተ ልማትን ለማስፋፋት በማሰብ እንደተገነባም ዳይሬክተሩ ይገልፃሉ።
የክልሉን ልዩ ልዩ አካባቢዎች የቱሪዝም መስህቦችን ለማስጎብኘትና ለማስተዋወቅ በአውደ ርእዩ መገኘታቸውን የሚገልፁት አቶ ወንድሙ፣ ከሃላላ ኬላ ባሻገር በርካታ ተመልካችን በእጅጉ የሚስቡ የመስህብ ስፍራዎች በክልሉ እንዳሉም አስታውቀዋል።
ዳይሬክተሩ እንዳሉት፤ ከእነዚህ ውስጥ የጨበራ ጩርጩራ ብሄራዊ ፓርክ በእዚሁ ክልል ይገኛል። ፓርኩ ዝሆን፣ ጎሽ፣ አንበሳ በአጠቃላይ ወደ 38 የሚሆኑ አጥቢ የዱር እንስሳት መኖሪያ ነው። በተፈጥሮ ውበቱ የታደለው ይህ ፓርክ በውስጡ የያዛቸው የአእዋፍ ዝርያ ከሌሎች ይለያል። እንደ ሀገር በጥናት ከተለዩት ወደ አንድ መቶ 58 የሚሆኑ የአእዋፍ ዝርያዎች መካከል 35ቱ በደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ብቻ ይገኛሉ። ወደ ደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የሚመጡ ቱሪስቶችም ይህንን ፀጋ መመልከት ይችላሉ።
አቶ ወንድሙ የኦሞ ብሄራዊ ፓርክም በዚሁ ክልል እንደሚገኝ ይገልፃሉ። ፓርኩ በርካታ አጥቢ፣ ስጋ በልና ያልሆኑ የዱር እንስሳት ያሉበትና ተፈጥሮንና የዱር እንስሳትን የመመልከት፣ የማድነቅ ፍላጎት ላለው ማንኛውም ጎብኚ ምቹ እንደሆነ ጠቁመዋል።
የክልሉ የቱሪዝም ሃብት እነዚህ ብቻ እንዳልሆኑም ጠቅሰው፣ የታችኛው ኦሞ የፓለንቶሎጂና አርኪዎሎጂ የጥናት ምርምር ማእክል ሌላው የመዳረሻ ስፍራና መስህብ እንደሆነ ገልጸዋል። ክልሉ “አስትሮፒካተስ ራሚደስ” የሚባለው 4 ነጥብ 8 ሚሊየን አመት እድሜ ያስቆጠረው ቅሬተ አካል የተገኘበት መሆኑን ተናግረዋል። ይህ ክልል የኢትዮጵያን ምድረ ቀደምትነት እና የሰው ዘር መገኛነት ከሚያስመሰክሩ ስፍራዎች እንዱ እንደመሆኑም እንደ ጎብኚ ስፍራው ላይ መገኘትና መመልከት ለቱሪስቱ ልዩ ስሜት እንደሚፈጥር ይገልጻሉ።
“ በክልሉ ማንኛውም ጎብኚ ከተገኘ የባህልና ቱሪዝም ቢሮውም ሆነ ማህበረሰቡ እንግዳ ተቀባይ ነው” ያሉት ዳይሬክተሩ፤ ክልሉ በርካታ እሴቶች የቱሪስት መዳረሻዎች ያሉበት መሆኑን በመረጃ እያስደገፉ አቶ ወንድሙ በአውደ ርእዩ ላይ አስተዋውቀዋል። የክልሉ መንግሥትም ሆነ ባለሙያው ሁሌም በራቸውን ክፍት አድርገው ጎብኚዎችን እንደሚጠብቁም ጠቁመዋል። ተመራማሪዎችን እንዲሁም በቱሪዝም ዘርፍ በአካባቢው ኢንቨስት ማድረግ የሚፈልጉ ባለሀብቶችንም እንደሚጠብቅና በቀናነት እንደሚያስተናግድ ይገልፃሉ። የሀገር ውስጥ ቱሪስቶችም ሆነ ዓለም አቀፍ ቱሪስቱ በክልሉ ተገኝተው ሃብቶቹን እንዲመለከቱም ጥሪ አቅርበዋል።
በአውደ ርዕዩ ክልሉ ሀብቶቹን ለበርካታ ሺህ ጎብኚዎች ማስተዋወቁን ጠቅሰው፣ በቀን ብቻ በሺዎች የሚቆጠሩ ጎብኚዎች እየተገኙ በክልሉ የሚገኘውን ሀብት ምን እንደሆነ መረዳት መቻላቸውን ተናግረዋል።
“በአውደ ርዕዩ ላይ በዋናነት የሰራነው ክልላችን ማስተዋወቅና መሸጥ ላይ ነው” የሚሉት አቶ ወንድሙ፤ ለምሳሌ በዩኔስኮ በዓለም ቅርስነት የተመዘገበው የከፋና የሸካ ጥብቅ የተፈጥሮ ደን ከተዋወቁት መስህቦች ውስጥ በቀዳሚነት አንዱ መሆኑን ተናግረዋል። 75 በመቶ የሚሆነው የኢትዮጵያ ደን የሚገኘውም በዚህ ክልል ነው የሚሉት ዳይሬክተሩ፤ የደን ሀብቱ የኢትዮጵያ ደን ሊባል የሚችል መሆኑን ይገልፃሉ።
ንፁህ አየርና ውብ ተፈጥሮን ከማራኪ መስተንግዶ ጋር ለማግኘት በክልሉ ጎብኚዎች መምጣት ብቻ በቂ እንደሆነ ተናግረዋል። በምሳሌነት የጨበራ ጩርጩራን ብሄራዊ ፓርክ አንስተውም በሳይንሳዊ መጠሪያ ልዩ የሆነው “የፋውናና ፍሎራ ስፒሺየስ የእጽዋትና እንስሳት ዝርያ” ያለበት ነው ፓርክ መሆኑን ይገልፃሉ፤ ፓርኩ 1410 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ቆዳ ስፋት ያለውና በዳውሮና ኮንታ ዞን መካከል የተካለለ መሆኑን በመግለፅ፤ ለአካባቢ መጠበቅ “ኤኮ ቱሪዝም” እንዲሁም በከፍተኛ ደረጃ ለቱሪስት መዳረሻነት እንደሚውል ይናገራሉ።
በተጨማሪ በከፋና በሸካ የሚገኘው ኢኮ ቱሪዝም ደን ተብሎ የሚያበቃ አለመሆኑን ይናገራሉ፤ አካባቢው ከላይ ሲያዩት ጥቅጥቅ ያለ ደን ከስር ሲመለከቱት በተፈጥሮ የበቀለ ቡና፣ ኮረሪማ፣ ጥምዝ፣ ቀረፋ፣ ቁንዶ በርበሬ የሚገኝበት ብዝሀ ህይወት ያለበት መሆኑን ይናገራሉ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ቤንች ሼኮ የመሰረት ድንጋይ ለማስቀመጥ በመጡበት ወቅት “ይሄ አካባቢ እኮ የቃል ኪዳን መሬት፣ ምድረ ገነት ነው” ያሉትን ንግግር እንደ ምሳሌነት በማንሳትም አካባቢው በተፈጥሮ ሀብት የበለጸገ ስለመሆኑ ማረጋገጫ ሰጥተዋል ብለዋል።
በዚህ ቦታ (በሳይንስ ሙዚየም) ተገኝተን የማስተዋወቃችን ትልቁ ጠቀሜታ ክልላችንን የሚጎበኙ ሰዎች ቁጥር እንዲጨምር ያግዘናል የሚሉት ዳይሬክተሩ፤ ከዚህ ቀደምም ክልሉ በቱሪስት መዳረሻነት እንደሚታወቅ ይገልፃሉ። ቢያንስ በወር ውስጥ እስከ ሶስትና አራት ሺ የውጭ ሀገር ቱሪስቶች ፣ እስከ አንድ ሺ 500 የሀገር ውስጥ ቱሪስቶች የሚጎበኙት ቦታ መሆኑንም ይናገራሉ። በዓመት ውስጥ ከ50 ሺ በላይ የውጭ ሀገር ቱሪስቶች የሚጎበኙት አካባቢ መሆኑንም ይናገራሉ።
በሳይንስ ሙዚየም በመገኘት የክልሉን ሀብቶች ከለዩ በኋላ ከአንድ ሺህ 900 በላይ የሚሆኑ የውጭ ሀገር ቱሪስቶች በቦታው ተገኝተው ጉብኝት ለማድረግ አድራሻ መውሰዳቸውን የሚገልፁት አቶ ወንድሙ፤ ይህን መሰል አውደ ርዕይ የቱሪስት ፍሰትን ለመጨመር እንደሚረዳ ተናግረዋል። አጋጣሚውን በአግባቡ መጠቀማቸውንና የክልላቸውን የቱሪስት መስህቦች በሚፈለገው ልክ ማስተዋወቃቸውንም ያስረዳሉ። አድራሻው የወሰዱት ጎብኚዎችም አስጎብኚ ድርጅትና ቱር ጋይድ በምን መልኩ ማግኘት እንደሚችሉ በቀላሉ በሳይንስ ሙዚየም ተገኝተው ከማግኘታቸውም በላይ ከቅርብ ግዜ ወዲህ እውቅና ያገኘው ሀላላ ኬላ ሪዞርት እንዴት ማረፍ እንደሚችሉ በቂ መረጃ ማግኘታቸውን ይገልፃሉ።
“በዚህ አውደ ርእይ ላይ የመገኘታችን ዋናው አላማ አካባቢያችንን ማስተዋወቅ ነው፤ አውደ ርእዩ እንደ ሀገር በእዚህ መልኩ መካሄዱም ለሀገር ገጽታ ግንባታ ፋይዳው ከፍተኛ ነው” ብለዋል። ቱሪዝም በዓለም አቀፍ ደረጃ ኢትዮጵያ ከፍተኛ ስፍራ እንዲኖራት ይጠቅማል። ኢትዮጵያ በቱሪዝምና ኤኮ ቱሪዝም ከዓለም ሰባተኛ ከአፍሪካ አንደኛ ሆናለች፤ ይህን አውደ ርእይ መጎብኘት ደግሞ ስለ ኢትዮጵያና ስለ ሁሉም ክልሎች ለማወቅ አስተዋጽኦው ከፍተኛ ነው ሲሉ አብራርተዋል።
በተጨማሪ ለአንድ ወር እዚህ በመቆየታችን የልምድ ልውውጥ አድርገናል፤ ሁለተኛ የትኛው ክልል ምን ቅርስ ምን መስህብ እንዳለው ተረድተናል። አውደ ርእዩ የማህበራዊ ግንኙነት ጥንካሬንም ይፈጥራል፤ በዚህ ረገድ አላማችንን አሳክተናል ብለዋል።
ደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ለመጎብኘት የሚመጣ ቱሪስት ሁለትና ሶስት ቀን ለመቆየት እቅድ ቢኖረው በመስተንግዶና ሆስፒታሊቲያችን ሳምንትና አስራ አምስት ቀን እንዲቆይ ማድረግ ዋናው እቅዳችን ነው የሚሉት አቶ ወንድሙ ለማ፤ በተጨማሪ ሌሎች ክልሎችንም የሚያይበት ለምሳሌ ደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ላይ ጉብኝት የሚያደርጉ ጎብኚዎች ደቡብ ክልልና ማእከላዊ ኢትዮጵያን የመጎብኘቱ እድሉ እንዲኖረው የሚያስችል አጋጣሚ ለመፍጠር እንደሚሰራ ይገልፃሉ።
“ዋና ዓላማችን ደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያን ብቻ የሚጎበኝ ቱሪስት መሳብ ሳይሆን የቱሪስት መዳረሻዎቹን በኔትወርክ ማያያዝ ነው” የሚሉት አቶ ወንድሙ፤ አንዱ ጋ ጀምረው ሌላውን እየጎበኙ ቀለበት ሰርተው ወደ መጡበት እንዲመለሱና በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች ያሉ መስህቦችን ጎብኝተው ለየክልሎቹ የገቢ ምንጭ ፈጥረው እንዲመለሱ ለማድረግ መሆኑን ይገልፃሉ።
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ህዳር 9/2016