የአንጋፋው አርቲስት የ50 ዓመታት ጉዞ

ገጣሚ ተዋናይና የቲአትር አዘጋጅ ነው። ከ1960ዎቹ ዓ.ም ጀምሮ በጥበብ ስራ ውስጥ በመግባት እጅግ በጣም ብዙ ማህበራዊና ሎሎች ይዘት ያላቸውን የጥበብ ስራዎች ለህዝብ በማቅረብ አንቱታን አትርፏል። ከልጅነቱ ጀምሮ በውስጡ በዘለቀው የጥበብ ጥማት በርካታ ቦታዎች ላይ በመገኘት ገና በወጣትነቱ ጥበብን ተጠብቦባታል። የአዲስ አበባ ቲአትርና ባህል አዳራሽ (ማዘጋጃቤት) ቲአትር ቤት ሆኖ እንዲቆም ከፍ ያለ ሚናም ተጫውቷል።

በቲአትር ጽሁፍ ከሠራቸው ሥራዎች መካከል ሀሙስ፣ ዱላው፣ ቤቱ ተጠቃሽ ናቸው። በአዘጋጅነት ደግሞ ሮሚዮና ዡሌት፣ የክፉ ቀን ደራሽ፣ ጤና ያጣ ፍቅር፣ ፍቅር የተራበና ሌሎችንም ማንሳት ይቻላል። አሁን ላይ በብዙዎች ዘንድ እጅግ ተዋዳጅነትን ባገኘው ሲትኮም (በስንቱ ) ድራማ አድናቆትን ከማግኘቱም በላይ በህዝብ ልብ ውስጥ ይበልጥ አይረሴ ሆኖ እንዲቀመጥ እያደረገው ነው፤ የዛሬ የህይወት ገጽታ አምድ እንግዳችን አርቲስት ስዩም ተፈራ ።

አርቲስት ስዩም ተፈራ ተወልዶ ያደገው ቅልጥ ካለው የአራት ኪሎ መንደር በተቃራኒው በሚገኘው ባለወልድ ወይም ካህን ሰፈር በሚባለው አካባቢ ነው። ለአባቱ ብቸኛ ልጅ ሲሆን፤ ለእናቱ ግን ከአስር እህትና ወንድሞቹ መካከል የሚገኝ ልጅ ነበር።

“……እኔ ተወልጄ ያደኩት አራት ኪሎ ባለወልድ ካህን ሰፈር ነው። በሚገርም ሁኔታ ይህ ሰፈር የዋናው አራት ኪሎ የሁካታው የግርግሩ የመጠጥ ቤቱ ብቻ የብዙ ነገር መገኛ ከሆነው በተቃራኒ ያለና በሰፈሩ ከአንድ ግሮሰሪ በስተቀር ምንም የማይታይበት ነበር፤ እኔም ያደኩት በዚህ ሰፈር ነው”ይላል።

አርቲስት ስዩም የአራት ኪሎ ልጅ ነውና የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱንም ሀ ብሎ የጀመረው በዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት ነበር። የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን ካጠናቀቀ በኋላም የሁለተኛ ደረጃውን ትምህርት የቀጠለው በዛው ትምህርት ቤት ነው።

አርቲስት ስዩም፤ መካከለኛ ተማሪ በመሆን ትምህርቱን ይማር እንደነበር ያስታውሳል። ነገር ግን ከትምህርቱ ጎን ለጎን አንዳንዴም ከትምህርቱ በላይ ለጥበብ ሥራ ልዩ ፍቅር እንደነበረው ያስታውሳል። አርቲስት ስዩም የዛሬው እንጀራው የሆነውን የጥበብ ስራ በየሲኒማ ቤቱ በመሄድ ማየትም የጀመረው በለጋነት እድሜው ነበር። በዛ እድሜው ትምህርቱን ትቶ ሲኒማ ቤት ሲገባ አባትና እናቱ ተቃውሞ ባይኖራቸውም ‹‹ ጊዜ ይለይለት›› የሚል ምክራቸው ግን አይለየውም ነበር። እሱ ግን የሚወደው ፊልም መታየቱን ከሰማ ሲኒማ ቤት መሄድ አለብኝ ብሎ ካሰበ የሚያቆመው ሀይል እንዳልነበር ያስታውሳል። በኋላ ግን አባቱ በጊዜ በሞት ስለተለዩት የሚወደውን የሲኒማ ቤት ውሎ አጠናክሮ ለመቀጠል እድል አገኘ።

“…….በትምህርቴ ሰነፍ አልነበርኩም እጅግ ጎበዝ ነኝ እንዳልል ደግሞ አንደኛ ወጥቼ አላውቅም ፤ ግን ጎበዝ እንደሆንኩኝ አውቃለሁ፤ ግን ደግሞ ሲኒማ ቤት መግባት ከትምህርቴ ጎን ለጎን የምሰራው ስራ ነበር። ክፍል ገብቼ ከተማርኩ አብዛኛውን የትምህርት አይነቶች እወዳቸዋለሁ ፤በአግባቡ እረዳቸዋለሁ። ነገር ግን ከማያቸው የሲኒማ ቤት ፊልሞች ጋር እያጣመርኩ ስማረው ደስ የሚለኝ ጂኦግራፊና ታሪክ ነበር። የሚገርመው ነገር ግን ከሲኒማ ፍቅሬ የተነሳ ፈተና እንኳን ቢኖር ፈተናው ይቀራል እንጂ ከሲኒማ ቤት የሚያስቀረኝ ሀይል አልነበረም”ይላል።

እንዲህ እንዲህ እያለ የቀጠለው የሲኒማ ፍቅር ደግሞ ዋል አደር ሲል በትምህርቱ ላይ ተጽዕኖ ማድረሱ አልቀረም። ሚዛኑን ጠብቆ መሄድ ያልቻለው ፍላጎትና ትምህርት አርቲስት ስዩም ላይ ጫና አሳደረ፤ ይህ ደግሞ በትምህርቱ እንዲሰላች ጭርሶውንም እንዳይፈልገው መንገድ ከፈተ ፤ በዚህ የተነሳ አርቲስት ስዩም ከ11ኛ ክፍል በላይ በትምህርቱ መዝለቅ ሳይችል ቀረ። የ11ኛ ክፍል የሁለተኛ መንፈቅ አመት ማጠቃለያ ፈተናን እንኳን ሳይወስድ ትምህርቱን አቋረጠው።

ከዚህ በኋላ ልዩ ፍቅርና ስሜት ወደነበረው የጥበብ ሥራ ዞረ፤ ሲኒማ ቤት መሄዱንም አጠናክሮ ቀጠለ። ከዛም ሲኒማ ቤት ያየውን ፊልም የተዋናዩን ገጸባህርይ በመላበስ እንደገና አብረውት ላዩትና ላላዩት ጓደኞቹ በጥሩ ሁኔታ መተወን ጀመረ። በዚህ ሁኔታም በጣም ብዙ ተመልካች አገኘ።

ይህ ሁኔታው ግን የእንጀራ ገመዱን ከፈተለት ማለት ይቻላል። በሲኒማ ቤት ያየውን ፊልም ዳግም ሲተውን ያየው አንድ ሰውም አንተ የጥበብ ሰው መሆን የምትችል ልዩ ችሎታ ያለህ ነህና ለምን በየሜዳው ታባክነዋለህ ወደ ጥበብ ስራው መግባት አለብህ አለው። ይህ በጣም የልብ ልብ የሆነው አርቲስት ስዩም በጣም በመደሰት ሊሰራ የሚችለውን ቲአትር ማፈላለግ ጀመረ። ለመጀመሪያ ጊዜው “የጥበብ ሰው መሆን የምትችል ነህ ” ያለውን ሰው ቲአትር በመጫወት እጁን አሟሸ።

” … ለጥበብ ስራ ልዩ ፍቅር ያለኝ ከመሆኔ የተነሳ በሲኒማ ቤቶች አካባቢ አልጠፋም፤ ትምህርቴን ካቋረጥኩ በኋላ ደግሞ በሙሉ ጊዜዬ የማየው ነገር ቢኖር ፊልም ብቻ ሆነ። ፊልሙን ማየት ብቻ ሳይሆን ደግሞ ልክ እንደተዋናዮቹ አድርጌ ዳግም በመጫወትም የሚችለኝ ጠፋ። ይህንን ብቃቴን የተመለከተ አንድ ሰው ደግሞ የራሱ የሆነውን የቲአትር ስራ እንድጫወትለት ሰጠኝ። ሥራውን በሚገባ ሠራሁ እኔም በጣም ተበረታታሁ ” በማለት ሁኔታውን ያስታውሳል።

የመጀመሪያ ሙያውን በዚህ ሁኔታ የፈተሸው አርቲስት ስዩም፤ ከዚያ በኋላ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኪነጥበባትና ቲያትር ቤት (አምስት ኪሎ) የጥበብ ስራውን በማሳየት ጅማሬውን አጠናክሮ ቀጠለበት ።

“…….እንዲህ እንዲህ እያልኩ የጀመርኩት የጥበብ ስራ ተፈሪ ብዙአየሁ የሚባል ሰው ከውጭ ሀገር መጥቶ በቲአትር ጥበብ ወጣቶችን ማሰልጠን እፈልጋለሁ በማለት ወወክማ ስልጠና ሲጀምር፤ እኔን የሚያውቀኝ ሰው እዛ ሄደህ ሰልጥን ብሎ በጠቆመኝ መሰረት እዛ ሄጄ ተፈትኜ በማለፌ ተፈሪ ብዙአየሁ “ባለካባ ባለዳባ” የተሰኘውን ስክሪፕት ሰጠኝ አጠናሁና ለመተወን በቃሁ። ይህንን ቲአትር ይዘንም ለመጀመሪያ ጊዜ ሀገር ፍቅር ቲአትር ቤት ለማሳየት ገባን። በዛም ትልቅ ተቀባይነት በማግኘት ሌሎች እንደ እሳት ሲነድ፤ ቤቱ የሚባሉና ሌሎችም ቲአትሮች መጡ። እነሱን እየሰራን ታዋቂነትን አግኝተን ቀጠልን ” በማለት ሁኔታውን ያስታውሳል።

ከዛም እዚሁ ቲአትር ቤት እነጋሽ ጸጋዬ መጥተው ታዋቂ ሲሆኑም እንደ አቦጊዳ፤ መልዕክተ መቅድም ፤ኦቴሎና ሌሎችም ላይ ፍጹም ደስተኛና የሙያው ሰው በመሆን ድንቅ ብቃቱን አሳየ። ይህ ሁኔታ ደግሞ በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነትን አስገኘለት፤ ለእስከዛሬም እሱነቱም መሰረት ጣለበት።

አዲስ አበባ ቲአትርና ባህል አዳራሽ (ማዘጋጃ ቤት ) በ 1968 ዓ.ም በ100 ብር ደመወዝ ተቀጥሮ የቲአትሩን አለም ተቀላቀለ። በወቅቱ እነ ፍቃዱ ተክለማርያም፣ አላዛር ሳሙኤል፣ ከበደ ደገፉ፣ ፍቅርተ ጌታሁን፣ ወለላ አሰፋ እና ሱራፌል ሁሉም አንድ ላይ ወደ ቲአትር ቤቱ ሄደው ሥራቸውን መጀመራቸውን የሚናገረው አርቲስት ስዩም ከስራው ባሻገር የነበረውን ጉጉት ሲያስታውስ ግርም ይለዋል።

“…….በነገራችን ላይ ቲአተር ቤቱ ገና መጀመሩ ከመሆኑ የተነሳ ቀደም ብለው ስራውን የተቀላቀሉት ለእኛ ከፍ ያለ ንቀትን እያሳዩ ነበር፤ እኛ ደግሞ ያ ነገር ከፍ ያለ እልህ ስለጫረብን እንኳን የሚመለከተንን የቲአትር ስራ ቀርቶ የማይመለከተንን የመድረክ ዝግጅት አናጺና ቀለም ቀቢ በመሆን እንሰራ ነበር ፤ በዚህም ቲአተር ቤቱን በአጭር ጊዜ ውስጥ ታዋቂና ዝነኛ አደረግነው”በማለት ይገልጻል።

እነ ስዩም ወደቲአትር ቤቱ ከመምጣታቸው በፊት የባህል አዳራሹ ለፊልም ማሳያነት ነበር አገልግሎት የሚሰጠው። እነሱ ደግሞ ወደቲአትር ቤትነት በመቀየር የመስራችነት ሚናቸውን በከፍተኛ ሁኔታ ተወጥተዋል። በሌላ በኩል በአጭር ዓመታት ወስጥ ከነባሮቹ ቲአትር ቤቶች ጋር ተፎካካሪ አለፍ ሲልም በጣም ተደናቂ ለመሆን መቻሉም ሌላው የእነ ስዩም ጥረት በመሆኑ፤ በዚህም ዛሬም ድረስ ኩራት እንደሚሰማው ያብራራል።

ሌላውና ትልቁ ነገር ደግሞ እነ አርቲስት ስዩም የቲአትር ስራ ውስጥ ሲገቡ ህዝቡ ቲአትር የሚያየው ከፍ ያለ የሙዚቃ ድግስ ተዘጋጅቶ እሱ ለማሳረፍ የሚቀርብን ቲአትር ብቻ ነበር። ነገር ግን እነ ስዩምና ጓደኞቹ ቲአትር ቤቱን ለቲአትር መስሪያ በሚያመች መልኩ በራሳቸው ወጪና ጉልበት አዘጋጅተው፤ የሰሩትን ቲያትር ያለምንም የሙዚቃ ጉቦ ህዝቡ ከፍሎ ገብቶ እንዲያይ ያደረጉ መሆናቸውም እስከ አሁን ድረስ የሚያውቁት ሰዎች እየተደነቁባቸው እነሱም ላቅ ያለ ኩራት እየተሰማቸው እዚህ ደርሰዋል።

አርቲስት ስዩም ዘመን መለወጫ በዓል ሲሆን ሌሊቱን ሙሉ የሙዚቃ ዝግጅቶች በየቲአትር ቤቱ ይቀርባሉ። ህዝቡም ሙዚቃን ለማየት ይገባል፤ ነገር ግን የእሱን “ፍቅር የተራበ ” ቲአትር በሙዚቃው ፋንታ ሌሊቱን ሙሉ ሰው ገብቶ አይቶታል፤ ይህ

 ለእርሱ በጣም ትልቅ ታሪኩ መሆኑን ይናገራል።

ሌላው የማዘጋጃ ቤት ቲአትር ቤቱ ሲመሰረት የመጡት አራት ሰዎች ብቻ ነበሩ። ሲመጡም በቲአትር ቤቱ ተላላኪ የለም፤ ዘበኛ የለውም፤ የሂሳብ ሹም አልነበረም፤ ሁሉንም ስራ እንችላለን ብለው ሰርተዋል።

“……እኛ ቲአትር ቤቱን ስንቀላቀል ከላይ የጠቀስኳቸው ባለሙያዎች ሁሉ አልነበሩም። በዚህም ምክንያት ጽዳት ተላላኪ ሂሳብ ሹም ጥበቃ ቀለም ቀቢ አናጺ ሆነን የምንሰራው እኛው ነበርን። ይህ የእኔ ስራ አይደለም ብሎ የሚል አልነበረም ፤ ብቻ እኛ በወኔ የምንሰራው እንድንታወቅ ነበር ፤ በተለይም ታላላቆቻችን ያሳዩን ንቀት ከፍ ያለ ሀይልና ጉልበት ሆኖን ነበር” በማለት ስለነበረው ሁኔታ ያስረዳል።

በርካታ ዓመታትን ከፍ ባለ የሙያ ፍቅር የጓደኝነት መተሳሰብ በርካታ ቲያትሮችን ሰርተዋል። በዚህ መካከልም ከጓደኞቹ ጋር የማይረሱ መልካም አጋጣሚዎችን ብሎም ክፉ ጊዜያትንም አሳልፈዋል። እስከ አሁን ድረስ በህዝብ ውስጥ ያስገቡትን አይረሴ ስራዎችንም አበርክቷል። ከምንም በላይ ደግሞ ከፍ ያለ የህዝብ ፍቅርና አክብሮት አልተለዩትም፤ በዚህም እጅግ በጣም ደስተኛ ነው።

ከዚህ ሁሉ የስራ ቆይታ በኋላ ግን በአዲስ አበባ ባህል አዳራሽ (ማዘጋጃ ቤት ) የመስራት ሁኔታው አከተመ ፤ ምክንያቱ ይላል አርቲስት ስዩም “…….ካቋቋምኩት ቤት ወደሌላ ቲያትር ቤት ለመዘዋወሬ ዋናው ምክንያት ባህርዬ ለአለቆች ምቹ አልሆን ብሏቸው ይመስለኛል። እኔ ላይ የደረሰውን በምሳሌ ባስረዳ “ቃሪያ መፋጀቱን ትቶ ቲማቲም ልሁን” ቢል ይሆናል? አይሆንም ቃሪያም እንዳለ ነው የሚያምረው እኔም ከአቋሜ ጋር አብሬ ልኑር በማለት ዝውውሬን ተቀብዬ ወደ ራስ ቲያትር ቤት ሄድኩ” ይላል ።

የራስ ቲያትር ቤት ቆይታ

ራስ ቲያትር ከእነ ደበሽ ጋር ጥሩ የስራ ጥምረት ፈጥረው ይሰሩ እንደነበር ያስታውሳል። እንደ ዛሬ ጊዜ ትንሽ ሰርቶ ብዙ ማግኘት የሚባለው ነገር ባይኖረም፤ ብዙ ለፍተው በሚያገኟት አነስተኛ ገቢ ግን ተሳስቦና ተፋቅሮ በመኖሩ በኩል የነበረውን ነገር ሲያስታውስ ደስታ ይሰማዋል።

ሁሌም ጠዋት ወደቲያትር ቤቱ ሲሄዱ ምን አዲስ ነገር እንስራ ለሚቀጥለውስ ምን ሰርተን ህዝባችንን እናዝናና እናስተምር? የሚለውን በሚገባ አስበውበት ብዙ ተወያይተውበት ፤ተጣልተውበት ከዛ ወደስራ ቀይረው ህዝቡ አይቶት በሚሰጠው አስተያየት ተደስተው ያሳልፉ ነበር። ‹‹ ብቻ በጣም መልካም የሚባሉ ጊዜያትን አሳልፈናል፤ በዚህም በጣም ደስተኛ ነኝ።›› በማለት ይናገራል።

አርቲስት ስዩም ከቲያትር ስራው ባሻገር የራሱን ፊልም ለመስራት ከፍ ያለ ጥረትንና ሙከራዎችን አድርጎ ነበር፤ ነገር ግን በተለያዩ ምክንያቶች ፍጻሜው ላይ ለማድረስ አልቻለም። ሁለገብ የሆነው አርቲስት ስዩም ከልጅነቱ ጀምሮ በርካታ ፊልሞችን ከማየቱ የተነሳ የራሱን ፈጠራ እያደረገ ወጣቶችን ለማዝናናት በማሰብ በ1962 ዓ.ም በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የወጣቶች ፕሮግራም ላይ ወጣቶችን ሊያዝናና ይችላል ያለውን “አስማት” የማሳየት ትርኢት ለማቅረብ ተስማማ ፤በዚህም ወጣቶችን ሰብስቦ አስማት ለማቅረብ ሞከረ፤ ስራው በካሜራ ጥበብ የሚሰራ ከመሆኑና እሱም በደንብ የተረዳው ስለነበር ጥሩና የተሳካ ሆነ። ነገር ግን ወቅቱ የፖለቲካ ትኩሳቱ የጋለበት ስለነበር ለወጣቱ ምን ያስተምራል ትርጉሙስ ምንድን ነው? በሚል ስለመከልከሉ ይናገራል።

በወቅቱ ከፍተኛ የሆነ ሀዘንና ቁጭት ተሰምቶት ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በር ላይ ቁጭ ብሎ ያለቀሰውን እንባ አይረሳውም፤ አርቲስት ስዩም በለቅሶው ላይ እያለም ግርማ ቸሩ የሚባል የስፖርት አሰልጣኝ አግኝቶት ” አይዞህ ወጣት ነህ አትዘን እኔም ዛሬ ላይ የደረስኩት እንደ አንተ ብዙ መጥፎ አጋጣሚዎችን አሳልፌ ነው፤ በርታ ሞራልህን ሰው እንዳይነካብህ” በማለት ያጽናናውና የመከረው ምክር ዳግም በሁለት እግሩ እንዲቆም አቅም ሆነው። ሌሎች ስራዎችንም በአግባቡ መስራት እችላለሁ ብሎ እንዲያስብ እንዳገዘውም ያብራራል።

ከዛም በኋላ ዳግም ወደቴሌቪዥን በመሄድ ትንሽ ይሳቁ፣ ስጥ እንግዲህ የሚሉ ቋሚ ፕሮግራሞችን በማዘጋጀት እነ አለባቸውና ልመንህ ተቋሙን እስከሚቀላቀሉ ድረስ ህዝቡን በማዝናናት እንደሰራም ይናገራል።

አርቲስት ስዩም ተለማማጭ እንዲሁም ተለዋዋጭ ያልሆነው ባህርይው ብዙ እንዳሳጣው ያውቃል፡ ይህንንም ይናገራል። ነገር ግን እሱ የሚያምነው ተለማምጦ በማደር ሳይሆን አቅምን ተጠቅሞ ሰርቶ ህዝብንም አሰሪንም በማስደሰት ነው። የጥበብ ስራን ከጀመረበት የጊዜ ርዝመት አንጻር ምንም ያልተጠቀመ ባለሙያ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም።

ነገር ግን ዛሬም ድረስ አምነውበት ቀጥተኛ አቋሙን ተቀብለው አብረን እንስራ የሚሉትን ሲያገኝ እጅግ በጣም በመደሰት እምቅ የፈጠራ ችሎታውን እንዲሁም የህይወት ዘመን ልምዱን በማቀናጀት ፍሬ ያለው ስራ ሰርቶ መውጣትን ይፈልጋል።

“….እኔ ተወልጄ እዚህ እስከምደርስ ድረስ ስራ ለነገዬ የሚባለውን ነገር አላውቀውም ፤ እጠላዋለሁ። አንድ ሰው መጥቶ ይህንን ብንሰራ እንዲህ ብናደርገው ካለኝ ወዲያው ወደተግባር መግባት እፈልጋለሁ። ነፍሴም የምትፈቅደው እንደዛ ነው ፤ በነገራችን ላይ ተንጠልጥሎ የሚቆይ ስራም ሆነ ሀሳብ መጥፎ ነው። የሚገባበት ነገር አይታወቅም። በመሆኑም አሁንም ቢሆን እንስራ የሚሉ ሰዎች ወደእኔ ከመጡ ንቁ ፈጣሪ ሆኜ አብሬያቸው መስራት የምችልበት ሁኔታ ላይ ነኝ ብዬ አምናለሁ” በማለት ይናገራል።

አርቲስት ስዩምና ህመሙ

አርቲስት ስዩም ለጥበቡ ብዙ ለፍቷል በራሱም እንዲሁም ውጫዊ በሆኑ ምክንይቶች ያን ያህል የተጠቀመ ሰው አለመሆኑ ይነበብበታል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ያጋጠመው ህመም ትንሽ የጎዳው ይመስላል። ነገር ግን ዛሬም ስራ ካሉት የትም ሄዶ መስራት የሚችል የመንፈስ ጥንካሬ ደግሞ ፊቱ ላይ ቁልጭ ብሎ ይነበብበታል።

አርቲስት ስዩም የዛሬ 7 ዓመት ገደማ በቀኝ እጁና እግሩ አካባቢ ህመም ተሰምቶት ህክምና ሲያደርግ የነርቭ ህመም እንደሆነ ተነግሮታል። በወቅቱም አጥንቶችህ አርጅተው ነርቭህን እየተጫኑት ስለሆነ በሀገር ውስጥ አልያም በውጭ ሀገር ሄደህ ጥሩ ህክምናን ማግኘት አለብህ የሚልም ምክር ተሰጥቶት ነበር።

ህክምናው በሀገር ውስጥ የማይሆን ሲሆንበት የውጭው ሀገር ምን ይመስላል ብሎ ሲጠይቅ አራት መቶ ሺ ብር እንደተጠየቀም ያስታውሳል። ይህንን ገንዘብ ከፍሎ የመታከም አቅሙ ስለሌለው እምነቱን በአምላኩ ላይ አድርጎ ጊዜያዊ ማስታገሻዎችን እየወሰደ ለመቆየት ተገዷል።

ከዛ ግን በጓደኞቹ በደጋግ ኢትዮጵያውያን አማካይነት ወደህንድ ሀገር ሄዶ 8 ሰዓት የፈጀ ቀዶ ህክምናን አድርጎ የዛሬ 5 ወር ገደማ ወደ ሀገሩ ተመልሶ አሁን ላይ በጥሩ ጤንነት ስራውን እየሰራ ያለ አርቲስት ነው።

“…….ህመሜ ብዙ ነገሮችን ያስተማረኝ ነው ። በተለይም ህዝብ ስለእኔ ምን ያህል እንደሚያስብና እንደሚጨነቅም ያየሁበት ጊዜ ነው። ህዝብ ሳልጠብቀው በየቤቱ የራሱን መለኪያ ይዞ እንደሚወደኝና እንደሚያከብረኝም ተረድቻለሁ። ፍቅሩን ሳየው ግን በእኔ በኩል የተሰማኝ ለዚህ ህዝብ በቂ ግልጋሎትን እንዳልሰጠሁት ነው” በማለት ይናገራል።

በስንቱ ድራማ

አርቲስት ስዩም አሁን ላይ እየሰራ ያለው በስንቱ አስቂኝ የቤተሰብ ድራማ ይበልጥ ከህዝቡ ጋር እንዳቀራረበው ይገልጻል። ድራማውም በርካታ ማህበራዊ ህጸጾችን በሳቅ አዋዝቶ የሚያስረዳ ከመሆኑ አንጻር ቁምነገረኛ አስቂኝ ድራማ ሊባል እንደሚችልም ያብራራል።

ዘንድሮ አርትን ለመስራት ለሚያስብ ሰው በሩ በጣም ሰፊ መንገዱም ምቹ ነው። ነገር ግን የመንገዱ መስፋት ስራዎች እንዲሳሱም መንገድ እየከፈተ ነው። የጥበብ ስራ ደግሞ ጠንካራ ልብን የሚፈልግ በመሆኑ ሊታሰብበት ይገባል ይላል።

መልዕክት

በሀገራችን ገንዘብ ያላቸው ሰዎች ለንግድ ስራዎች የሚሰጡትን ትኩረት ያህል ጥበቡን ለማደሳደግ የሚሆኑ ቲአትር ቤቶችን ለመገንባት የሚፈቅዱ ቢሆኑ ኖሮ አሁን ላይ በዘርፉ ትልቅ እድገት ይመዘገብ ነበር። በመሆኑም ጥበብን ለማስተዋወቅ ለማሳደግ ገንዘብ ወሳኝነት ያለው በመሆኑ ገንዘብ ያላቸው ሰዎች ያስፈልጋሉ። በዚህ ዘርፍም ማሰብ በጣም ያስፈልጋል። መንግስትም ቢሆን ጥበብ የፈለገውን መልዕክት ለማስተላለፍ አይነተኛ መንገድ መሆኑን በመረዳት ተገቢውን ትኩረትና እገዛ ለጥበብ ስራዎችና ለማሳያዎች መፍጠር ያስፈልጋል ይላል።

አሜሪካንን ጨምሮ እምብዛም ታሪክ የሌላቸው የዓለም ሀገራት የሚፈልጉትን ነገር የሚያደርጉት ተጽዕኖ የሚያሳድሩት በፊልማቸው ነው የሚለው አርቲስት ስዩም፤ እኛ አድዋን ያህል ታሪክ ይዘን የምንሰራው ነገር የለንም። ይህ ታሪክ የእነሱ ቢሆን ምን ሊሰሩ እንደሚችሉ ማሰብ ቀላል ነው። ነገር ግን እነሱ ታሪክ ሳይኖራቸው ታሪክ ፈጥረው አለምን እያሳመኑ ወደራሳቸው እየሳቡ መሆኑንም ይገልፃል።

የቤተሰብ ሁኔታ

አርቲስት ስዩም ባለትዳርና የአምስት ልጆች አባት ነው። አንድ ልጁ ወደእሱ ሙያ የማዘንበልና የመሳብ ሁኔታን ያሳይ የነበረ ቢሆንም፤ የራሱን መንገድ መርጦ ግን ከስራው መውጣቱን ይናገራል።

እፀገነት አክሊሉ

አዲስ ዘመን ኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You