የአየር መንገዱ የከፍታ በላይ ከፍታ!

 የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ የመጀመሪያው የተባለለትን የቦይንግ አውሮፕላኖች የግዥ ስምምነት ሰሞኑን በዱባይ ከአውሮፕላኖቹ አምራች ቦይንግ ኩባንያ ጋር ተፈራርሟል። በስምምነቱ መሰረትም አየር መንገዱ 67 ቦይንግ ጀት አውሮፕላኖችን ከኩባንያው ይገዛል። ስምምነቱ 11 አዲስ 787 ድሪምላይነር አውሮፕላኖችን እንዲሁም 20 አዳዲስ 738 ማክስ አውሮፕላኖችን ኩባንያውን ለማዘዝ ያስችለዋል።

ስምምነቱ ተጨማሪ ማክስ 15 ድሪምላይነሮችንና 21 ተጨማሪ ማክስ አውሮፕላኖችንም እንዲሁ የማዘዝ እድል እንዲኖረው የሚያስችል ስለመሆኑ ከአየር መንገዱ የተገኘ መረጃ አመልክቷል። በአየር መንገዱ ታሪክ ትልቅ የግዢ ስምምነት የተፈጸመበት ስምምነት ከመሆኑ በተጨማሪም በአፍሪካ ታሪክም ትልቁና የመጀመሪያው የግዥ ስምምነት መሆኑን አየር መንገዱ አስታውቋል። አየር መንገዱ ራሱን ለማሳደግና ለማዘመን የያዘውን የ2035 ስትራቴጂክ እቅድ ራእይ እውን ለማድረግ ፋይዳው ከፍተኛ መሆኑም በአየር መንገዱ በኩል ታምኖበታል።

የአየር መንገዱ አየር ባስ ከተሰኘ ሌላ ኩባንያ ጋርም እንዲሁ 11 ኤየር ባስ ኤ 350 የተሰኙ አውሮፕላኖችን ለማዘዝ የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ከኤየር ባስ ኩባንያ ጋር በዱባይ ፈጽሟል። ይህም ስምምነት ተጨማሪ ስድስት ተመሳሳይ አውሮፕላኖችን ማዘዝ የሚያስችለው መሆኑንም የአየር መንገዱ መረጃዎች አመልክተዋል።

ስምምነቶቹ የአየር መንገዱን የከፍታውን የላቀ ከፍታ የሚያሳዩ፣ ለስትራቴጂክ እቅዱ ራእይ መሳካት የያዘውን ቁርጠኝነት በሚገባ ያመላክታሉ። እንደ ሀገር ብቻ ሳይሆን እንደ አህጉርም እንደ በርካታ ሀገሮች ታዋቂ አየር መንገዶች ሲታይ፣ ይህ ስምምነት አየር መንገዱ የደረሰበትን የስኬት ማማ ያመለክታል።

የሚገዛቸው አውሮፕላኖች ብዛት፣ የአውሮፕላኖቹ ቴክኖሎጂ የላቀ መሆን፣ ገዥው የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ሻጮቹም ዓለም አቀፍ የአውሮፕላን አምራች ኩባንያዎች መሆናቸው ሲታሰብ፣ ሌላ ነጋሪ ሳያስፈልግ ስምምነቱ ብቻውን የአየር መንገዱን ከፍታ በሚገባ ያረጋግጣል። የአየር መንገዱን ከፍታ ብቻም ሳይሆን፣ የኢትዮጵያንና የአፍሪካንም የዘርፉን ከፍታ በእጅጉ ያሳያል።

አየር መንገዱ በትልቅ እድገት ላይ እንደሚገኝ ይጠቁማል። በአየር መንገዱ ዕድገት ተቋሙ ብቻ አይደለም የሚኮራው፣ የአየር መንገዱ ባለቤት ኢትዮጵያም፣ የአየር መንገዱ ተገልጋይ አፍሪካም ጭምር በእጅጉ ይኮራሉ።

እንደሚታወቀው ፤ አየር መንገዱ በአፍሪካ መሪ አየር መንገድ ለመባል በቅቷል፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ አንቱ ለመባል ከበቁት አየር መንገዶች መካከል ነው። በሚጠቀማቸው ዘመናዊ አውሮፕላኖችና ቴክኖሎጂዎች፣ ለደንበኞቹ በሚሰጣቸው የተቀላጠፈና ፈጣንና ደህንነታቸው የተረጋገጠ አገልግሎቶቹ በአጠቃላይ በሚያከናውናቸው ተግባሮቹ በየጊዜው ሽልማቶችና ዓለም አቀፍ እውቅናዎች ሲሰጡት ዘመናትን ተሻግሯል።

ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን አፍሪካን ከመላ ዓለም ጋር በማገናኘቱ በእጅጉ የሚጠቀሰው ተቋሙ፣ በዓለም አስቸጋሪ ሁኔታዎች በገጠሙ ጊዜም እንደ ሌሎች አየር መንገዶች ሸብረክ አላለም። በወረርሽኙ ምክንያት በመላ ዓለም እንቅስቃሴዎች ቀጥ ባሉበት እና ዓለምን በእጅጉ በተፈተነችበት ወቅት መድኃኒቶችንና የተለያዩ ሸቀጦችን በማጓጓዝ መላ ዓለምን የታደገ የክፉ ቀን ባለውለታም ነው።

በዘርፉ የሰው ኃይል ልማቱም በእጅጉ ይታወቃል። በአህጉር ደረጃም የአፍሪካ አየር መንገዶች የልህቀት ማእክል ተደርጎ ይታያል። አየር መንገዱ ያፈራቸው እንዲሁም በአየር መንገዱ ልምድ ያካበቱ የአየር መንገዱ ልጆች በመላ ዓለም በሚገኙ ታዋቂ አየር መንገዶች በብቃታቸው በባትሪ የሚፈለጉ ናቸው።

አየር መንገዱ አሁን የደረሰባቸው ታላላቅ ስምምነቶች የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካም የዓለምም ትልቅ ስኬት በመሆን በየጊዜው ዘመኑን የዋጁ ቴክኖሎጂዎችንና አገልግሎቶችን በመጠቀም ሲሰጥ የቆየውን አገልግሎት የላቀ ደረጃ ለማድረስ ያስችሉታል።

ተቋሙ ውድድሩን ሁሌም የሚያደርገው ከአህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ አቻ አየር መንገዶች ጋር መሆኑ ይታወቃል። ውድድሩ ጠንካራ ውድድር እንደሚሆን ይጠበቃል። ይህን ውድድር ግን በስኬት እየተወጣ እዚህ ደርሷል።

በሀገር ቤት ውድድር ባይኖርበትም ተወዳዳሪ ያለበት ያህል ሰፊ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑ ይታወቃል። በዓለም አቀፍ ደረጃ እያገኘ ያለው ክብርና አሁን የደረሰባቸው ስምምነቶች ይህን የሀገር ቤት በረራውንም የበለጠ እንዲያስፋፋና እንዲያዘምን ዕድል ሊፈጥሩሉት ይችላሉ።

እንደ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ትንበያ፤ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ቀጣይነት ባለው መልኩ እንደሚያድግ ይጠበቃል። ይህ ዕድገት ደግሞ ብዙ ፍላጎቶችን ይዞ ይመጣል። ከእነዚህም መካከል አንዱ ምቹና ፈጣንና አስተማማኝ የትራንስፖርት አገልግሎት ማግኘት ነው። ለእዚህ ደግሞ የአየር ትራንስፖርት ተመራጩ ነው፤ አየር መንገዱ ይህን የኢትዮጵያን ዕድገት የሚመጥን አገልግሎት በሀገር ውስጥ ለመስጠት አሁን ያደረጋቸው ስምምነቶች ሚናም ከፍተኛ እንደሚሆን ይታመናል።

ሀገሪቱ ብልጽግናን ለማረጋገጥ በተለያዩ ዘርፎች እየታተረች ባለችበት በዚህ ወቅት ከአየር መንገዱ የተሰማውን ይህ ታላቅ ዜና አርአያነት ያለውና ሌሎች የልማት ዘርፎችም ትምህርት ሊቀስሙበት የሚገባ ነው። ሁሉም በየዘርፋቸው ለተቀመጡ ራዕዮች ስኬት ርብርባቸውን ማጠናከር ያለባቸው ስለመሆኑ የአየር መንገዱ ስኬታማ ጉዞ ትልቅ ትምህርት ይሆናል!

አዲስ ዘመን ኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You